የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

Sep 2, 20183 min

‘‘የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’ ሙስሊም የባረከውን ክርስቲያን ያቃርጣል

ጁሀ ስለሚባለው የዓረቡ ዓለም ሰው ትንሽ ነገር አጫውቻችሁ ነበር። ዛሬ ደግሞ የሱን አንድ ታሪክ ልጨምርላችሁ፡-

ጁሀ ድሀ ሰው ነው ። ድህነት አንድ ጊዜ ጭራሽ ፎቅ ሰራበት ። በፊት ከነበረው እጅግ ባሰበት ፡፡ በዚህ ምክንያት መኖሪያ መንደሩን ትቶ ስራ ፍለጋ ተሰደደ፡፡ ርቆ ከተሰደደ በኋላ አንድ አካባቢ ደረሰ፡፡

አካባቢው ላይ መስጂድ ነበር ፡፡ ቤሳቢስቲን የሌለው ሰው ፣ የሚበላው ያጣ ፣ የሚጠለልበትም ግራ የገባው ሰው፣ ቤተ አምልኮዎች ምርኩዞቹ ናቸው ፡፡

ጁሃ መስጂዱ ውስጥ ተጠለለ-በእንግድነት ፡፡ ያካባቢው ሰዎች ችግሩን ቀረብ ብለው ጠየቁት ፡፡ ስራ ፈላጊ ሰው ስለመሆኑ ገለፀላቸው ፡፡

ከጠየቁት ሰዎች አንደኛው ፣ ‘‘ ስናይህ እስልምናን በደንብ የምታውቅ ሰው ትመስላልህ ፡፡ መስጂዳችን አሁን ኢማም የለውም ፡፡ ስለዚህ ለምን የመሰጂዳችን ኢማም አትሆንም? ’’ ፣ ጠየቀው፡፡

ጁሃ የመስጂዱ ኢማም ለመሆን ተስማማ፡፡ ነገር ግንኮ ያን ያህል ዕውቀት የለውም፡፡

የጁማ ዕለት ደረሰ፡፡ ያካባቢው ሰው ስለአዲሱ ኢማም ሰምቷል ፡፡ መስማት ብቻ ሳይሆን አዲሱ ኢማም ከሶላት በኋላ የሚናገሩትን ነገር ለመስማት በጅጉ ጓጉቷል፡፡

ዕለተ አርብ ደርሶ ከሶላት በኋላ ፣ መስጂዱ ውስጥ ለተሰበሰቡት ሰዎች ፣‘‘ ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ፣ በዚህች የተቀደሰች ዕለት አዚህ የተሰበሰብንበት ምክንያት ታውቃላችሁ?’’ ፣ ጠየቃቸው ፡፡

ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ ‘‘ አናውቅም!!’’ ፣ መለሱለት፡፡

‘‘ ካላወቃችሁ ለምን ትመጣላችሁ? ሰላም አሌኩም ’’ ፣ አላቸው፡፡

ቀጣዩ የጁማ እለት ደረሰ፡፡ ከሶላት በኋላ ጁሃ፣ ፣‘‘ ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ፣ በዚህች የተቀደሰች ዕለት አዚህ የተሰበሰብንበት ምክንያት ታውቃላችሁ?’’ ፣ያንኑ ጥያቄ መልሶ ጠየቃቸው ፡፡

‘‘ አዎ!! እናውቃለን!!’’ ፣ሲሉ መለሱለት፡፡

‘‘ እህ! ካወቃችሁ ለምን ትመጣላችሁ? ሰላም አሌኩም !’’ ፣መለሰላቸው ፡፡

ሶስተኛው የጁማ ቀን መጣ፡፡ በዚሁ ዕለትም ከሶላት በኋላ ጁሃ፣ ፣‘‘ ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ፣ በዚህች የተቀደሰች ዕለት አዚህ የተሰበሰብንበት ምክንያት ታውቃላችሁ?’’ ፣ያንኑ ጥያቄ መልሶ ጠየቃቸው ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ፡፡

ገሚሱ ፣‘‘ እናውቃለን!! ’’ ፣ አለ፡፡ ገሚሱ ደግሞ ‘‘ አናውቅም!!’’ ፣ ሲል መለሰ፡፡

ጁሃ ከመልሶቹ በኋላ ፣ ‘‘በሉ የምታውቁት ለማያውቁት አሳውቋቸው፡፡ ዋአሰላም አሌኩም!’’ ፣ አለ፡፡

ጁሃ ችግሩን ለመወጣት የተጠቀመበት ብልጠት ይገርመኛል፡፡ ግንኮ ወደቁምነገሩ ስመለሰ እጅግ የማይመቸኝ ነገር አለው ፡፡ እኛምጋ የማይመች ነገር አለ፡፡ ስራም ይሁን አባትነት በዕውቀት ላይ ሳይሆን በሸሪክነትና በማሻረክ እየሆነ ዛሬ ላይ የደረስንበት መንገድ ይቆጠቁጠኛል ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ግን ፈጣሪ ያውቃል፡፡

የሀይማኖት አባትነት በዕውቀት ላይ ሲመሰረት ግን ደስታዬ ብዙ ነው፡፡ በመከባበርና በፍቅር ላይ ሲያርፍም፡፡

ያገራችን ሰዎችም ፣ ‘‘ ከመጠምጠም ዕውቀት ይቅደም!’’ ፣ ይላሉ፡፡

እኚህ ሰሞኑን የዓረፋን በዓል ምክንያት አድርገው በኢቲቪ መግለጫ የሰጡት አባት ፣ አስተምሯቸው ደስ ይላል፡፡ ትልቅ የሀይማኖት አባት!! እጅግ ትልቅ ሰው!!

ዛሬ አረፋም አይደል፡፡ ጉራጌ ዞን ሙህርና አክሊል ወረዳ ውቅየ ቀበሌ ልውሰዳችሁ፡፡ ውቅየ ቀበሌ ውስጥ ማርያም ቤተ ክርስቲያንና የውቅየ መስጂድን የሚለያቸው አጥር ነው ፡፡ እንደ ራጉዔልና አንዋር፡፡

በነገጋራችን ላይ የስራ አጋጣሚ ከመምሬ ‘‘ድቡር’’ ጋር አገናኝቶኛል፡፡ ምኑን ከምን አገናኝተው ጫወታውን እንዳመጡት ባላውቅም ‘‘ ሽጉጤ ’’ ፣ የሚል ስም ደስ ይለኛል ብለው አረፉት፡፡

እኔ እምለው ከረሪማ ራስን በሽጉጣቸው ያፈረሱት መምሬ ‘‘ድቡር ’’ ናቸው እየተባለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ነገር ዕውነት ነው እንዴ?

ባለፈው ሰሞን ደግሞ መለስ ዜናዊን ከመቃብር አስነሳለሁ እያለ ነበር አሉ- አንዱ ሀይማኖተኛ፡፡

ኧረ በፈጠረህ በሉት! የሞተ ሰው ተነስቶ ካየሁ? እኔ ችግር አለብኝ ፡፡ በድንጋጤ እዛው ነው ፍግም የምለው ፡፡ እና እኔ ለምን ልሙትብህ! ይልቅ እኛ መንደር ቆሻሻ ተከምሮ አስቸግሮናል ፡፡ በተአምራትህ ይህንን ቆሻሻ አስነሳልን!

አሁን የፍልሰታ ፆም አይደል፡፡ ትናንት ሊነጋጋ ሲል የሱቢ ሶላትስ ነበረ አይደል፡፡ እንግዲህ ማርያም ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ፀሎት አለ፡፡ መስጂዱም ውስጥ ፀሎት አለ፡፡ የማርያም መምሬ ፣ መምሬ ዘርጋ፣ መስጂዱ ‘‘ አዛን’’ ሲያሰማ፣ አዛኑ እንዲሰማ ሶላቱም እንዳይረበሽ አስበው ከቤተክርስቲያኑ የሚወጣውን ድምፅ ከድምጽ ማጉያው ይቀንሳሉ፡፡

ትልቅ ሰው መምሬ ዘርጋ!!

ዛሬ አረፋም አይደል፡፡ ውቅየም ይሁን አካባቢው ላይ ፣ ያሉ ሙስሊሞች ይባርካሉ እንጂ መግፈፉና ማቃረጡ የክርስቲያን ወንድሞቻቸው ስራ ነው፡፡ ተግባሩን የሚፈጽሙት ስለሙስሊም ወንድሞቻቸው ክብርና ፍቅር ነው፡፡

ትልቅ ሰዎች!!

መስቀል ሲመጣም ክርስቲያኖች ይባርካሉ፡፡ ሙስሊሞች ይገፋሉ፤ያቃርጣሉ፡፡ ስለፍቅር ፣ስለመከባበር ይደረጋል፡፡

ትልቅ ሰዎች!!

በዕምነት ብንለያይም በፍቅርና በመከባበር ሰልፍ እንዲህ በዓላትን አብረን ስናሳልፍ ኖረናልኮ፡፡

እቃወማለሁ- አንዳንድ አላዋቂዎችን ፡፡ በስላም ልኳንዳ አጠገብ ሲያልፉ ፣ በክርስቲያን ልኳንዳ አጠገብ ሲያገድሙ በነርሱ ሀይማኖት ያልተባረከ ስጋ ሸተተኝ በሚል ምክንያት የጥዩፍነት ተግባር የሚፈፅሙ ፅንፈኞችን-እቃወማለሁ!!

‘‘ የሰው ዓመል ዘጠኝ ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ’’

#የሰውዓመልዘጠኝአንዱንለኔስጠኝሙስሊምየባረከውንክርስቲያንያ

    360
    0