የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

May 22, 20202 min

መጀመሪያ ይሙቀኝና ማገዶውን እጨምራለው!

በሚስጥረ አደራው

“መጀመሪያ ይሙቀኛና ማገዶውን እጨምራለው ” የአብዛኛዎቻችን ሰዎች የህይወት መርህ ነው። ማገዶ ከሌለው ጓዳችን ውስጥ ሙቀት የምንጠብቀው ምን ከምን እንደሚቀድም ስለማናውቅ ነው። ይህ አለማወቃችን ነው ያሰብናቸው ነገሮች እንዳይሳኩ፤ የጠበቅናቸው ነገሮች እውን እንዳይሆኑ የሚያደርገው። በቂ ማገዶ ሳንጨምር ሙቀት ልናገኝ አንችልም። የቀዘቀዘው ኑሮዋችን እንዲሞቅ ከፈለግን በርከት ያለ ማገዶ መማገድ አለብን። ብዙዎቻችን ግን የሚጠበቅብንን ነገር ሳናደርግ፤ ማለትም ማገዶዋችንን ሳናሰናዳ የቀዘቀዘው ቤታችን እንዲሞቅ እንጠብቃለን። ሲበዛ የዋሆች ስለሆንን።

የምንፈልገው ነገር ምንም ይሁን ምን ልንከፍለው የሚገባ ዋጋ አለ። መክፈል ያለብንን መስዋትነት ሳንከፍል ህልማችን እንደ አስማት በደቂቃ እውን እንዲሆን የምንጠብቅ ከሆነ ጊዜያችንን እያባከንን ነው። አለመታደል ሆኖ ሰዎች የስኬት ጫፍ ላይ ሲደርሱ፤ ለብቻቸው የከፈሉትን ስቃይ፤ ማንም ሳያያቸው የደከሙትን ልፋት፤ ማንም ሳያመሰግናቸው ያፈሰሱትን ላብ የሚረዳ የለም። ቶኒ ሮቢንስ የተባለ ጸሃፊ አንድ ደስ የሚል አባባል አለው “ሰዎች በአደባባይ የሚሸለሙት ለብቻቸው ለዘመናት ላፈሰሱት ጉልበት ነው” ይላል። እውነት ነው፤ እንደው በደፈናው ካየነው ከሰዎች ስኬት ጀርባ ያለውን ህይወት ስለማናውቅ፤ በቀላሉ የሚገኝ ይመስለናል። ለዚህም ነው “ስኬትን አሳየኝና ዋጋውን እከፍላለው” የሚል አመለካከት የተጠናወጠን። ልክ “መጀመሪያ ይሙቀኝና ማገዶውን እጨምራለው” እንደሚለው ሞኝ።

ምልክት ፈላጊ መሆን ለምናስበው ነገር መክፈል ያለብንን መስዋትነት ወይም ዋጋ እንዳናውቅ ያደርገናል። ለምሳሌ መልካም ቤተሰብ ስጠኝና ጥሩ ሚስት እሆናለው የምትል ሴት፤ ማገዶውን ሳትጨምር ቤቷ እንዲሞቅ የምትሻ ሞኝ ናት። መጀመሪያ የሚቀድመው መልካም ሚስት መሆን ስለሆነ። ጎበዝ ተማሪ አድርገኝና ማጥናት እጀምራለው የሚለውም ተማሪ እንደዛው፤ የጥናት ማገዶውን ሳይማግድ የትምህርትን ሙቀት የሚጠብቅ ተላላ ነው። ጥሩ ጓደኛ ስጠኝና ጥሩ ሰው እሆናለው የምንለው ስንቶቻችን ነን? ትክክለኛዋን ሴት ሳገኝ ወይም ትክክለኛውን ሰው ሳገኝ የተስተካከለ ኑሮ እጀምራለው እያልን በእድሜያችን የምንቀልድ ብዙዎቻችን ነን።መቅደም ያለበት የገዛ እራሳችን ለውጥ መሆኑን ስለማናውቅ።

ሳናውቀው በተለያየ የህይወታችን ገጽታዎች ይህንን አመለካከት ይዘን ነው የምንጓዘው። ይህች ምድር ልክ እንደ ባንክ አካውንታችን ናት፤ ያላስገባንባትን ልናውጣባት ከሞከርን የማይቻል ብቻም ሳይሆን እራሳችንንም ችግር ውስጥ እየከተትን ነው። በህይወታችን የምናገኘው ነገር አስከቀድመን የከፈልነውን ነው። 10ብር ባንካችን ውስጥ አስገብተን፤ 200ብር እናውጣ የምንል ከሆነ አይምሮዋችን በትክክል መስራቱን ማረጋገጥ አለብን። ይህ አመለካከት ለህይወታችንም የሚሰራ ነውና። ያልሰጠነውን ለመቀበል የምንሞክር ከሆነ ትርፉ መከፋት ነው።

ሁሉ ነገር ዋጋ አለው። እንደሸቀጥ ሁሉ በህይወታችን የምንፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ የሚጠይቁት የተለያየ ዋጋ አለ። ልዩነቱ የምንከፍለው በገንዘብ አለመሆኑ ነው። ለመልካም ኑሮ የሚከፈለውን ዋጋ ሳንከፍል መልካም ኑሮ እየጠበቅን ከሆነ ልክ ማገዶውን ሳያሰገባ ሙቀቱን እንደሚጠብቀው ሞኝ እየሆንን ነው። ምንም ነገር ሳናጠና ፈተናችንን በጥሩ ሁኔታ ለማለፍ እየተመኘን ከሆነ እራሳችንን እያታለልን ነው። ጥሩ ሰራ ለመያዝ ፤ጥሩ ደሞዝ ለማግኘት የሚያስችለንን ብቃት ሳናከብት ደረጃውን ለመዝለል ከሞከርን ውጤቱ ውድቀት ነው።መልካም የትዳር አጋር ሳንሆን የሞቀ ጎጆ ስጠኝ እያልን ከሆነም ተሳስተናል። ከሱስ ለመላቀቅ የሚከፈለውን ዋጋ ሳንከፍል፤ በተዓምር የተመሰቃቀለው ኑሮዋችን እንዲቀና የምንጠብቅ ከሆነ አሁንም ተሳስተናል።ባጠቃላይ በማንኛውም መስክ ላይ መክፈል ያለብንን ነገር ሳንከፍል ውጤቱን መጠበቅ አንችልም።
 
የምንመኘውን ኑሮ ለመኖር የምንከፍለው ዋጋ ምን እንደሆነ በቅድሚያ ማወቅ አለብን። ያንን ዋጋ ሳንከፍል ግን በባዶ ተስፋ ነገሮች እንዲስተካከሉ የምንሻ ከሆነ ጊዜያችንን ከማቃጠል በቀር የምንፈይደው አንድም ነገር የለም። ለራሳችን አዘውትረን መንገር ያለብን ነገር ቢኖር የምናገኘው የሰጠነውን ነው። ከኑሮዋችን ውስጥ የምንጠብቃቸው ነገሮች በቅድሚያ የህይወት ባንካችን ውስጥ መኖራቸውን ማወቅ መቻል አለብን። ያላስቀመጥነው አናገኘምና።

በህይወት ባንካችን ውስጥ ያስቀመጥነው መልካምነት ከሌለ፤ ይህች አለም እንዴት ክፉ ሆነችብኝ ብለን የማማረር ብቃቱ የለንም። ያከማቸነው ትጋት እና ስራ ከሌለ እንዴት ያሰብኩት አልተሳካም ማለት አንችልም። ከላይ እንደተገለጸው ለሁሉም ነገር ዋጋ አለው፤ ያን ዋጋ ሳንከፍል ምኞታችንን የግላችን ለማድረግ አንችልም። ከምንም በላይ ደግሞ መቅደም ያለበትን ነገር ማወቅ አለብን፤ ከስኬታችን በፊት ስራ ይቀድማል፤ ከሙቀቱ በፊት ማገዶው መማገድ እንዳለበት ሁሉ።

በሚስጥረ አደራው

    90
    0