የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

Sep 21, 20202 min

ማኑዋል- Life’s Instruction Manual

ብዙ እቃዎችን ስንገዛ አብሮ የሚሰጠን የመመሪያ ደብተር ወይም ማንዋል አለ። ይህ ማኑዋል የገዛነው እቃ እንዴት እንደሚሰራ፤ እንዴት እንደሚገጣጠም፤ እንዴት እንደሚለወጥ፤ ችግር ካለ ማንን እንደምናማክር፤ ሌሎች ብዙ ስለ እቃችን ጠቃሚ እውነታዎችን የሚይዝ ደብተር ነው። ብዙዎቻችን ግን ይህንን ማኑዋል ጊዜ ወስደን አናነበውም። ማኑዋሉን ሳያነብ የገዛውን እቃ ለመገጣጥም የሚሞክር ሰው ምናልባት ሊወስድበት ከሚገባው ጊዜ እጥፍና እጥፍ ይወስድበታል። በግምት ደግሞ ደጋግሞ እየሞከረ ብዙ መንገድ ከሄደ በኋላ ነው ቢሳካለት እንኳን የሚሳካለት። ከብዙ ስህተቶችና መሰላቸት በኋላ ። እንደውም አሁን ጊዜው የረቀቀ ሰልሆነ ሌሎች ሰዎች ሲያረጉ የተቀረጹትን በመመልከት እኛም እንደዛው በአቋራጭ ሲያደርጉ ያየነውን ለመድከም እንሞክራለን፤ ጉዳት ላይኖረው ይችል ይሆናል። እርግጠኛ የምንሆነው ግን የእቃው አምራች የሚሰጠን የመመሪያ ደብተር እውነተኛውና ጠቃሚውን መረጃ መያዙ ነው። እቃው እንዴት እደሚሰራ ሳያውቁ ለመስራት መሞከሩ ግን ትንሽ አይከብድም? ብዙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከደንበኞቻቸው ከሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ ብዛት ያለው ቁጥር የመመሪያ ደብተሩን ወይም Manual Instruction ካለማንበብ የመነጨም እንደሆነ ይናገራሉ።

ለነገሩ ማውራት የፈለግኩት ስለ እቃ ማኑዋል አይደለም። በህይወታችን የምንፈጽማቸው አንዳንድ ስህተቶች፤ ነገሮች እንዴት እንደሚሰሩ ከማወቃችን በፊት በድፍረት ስለምንገባባቸው ቢሆንስ? ተፈጥሮዋዊ ነገሮችም የመመሪያ ደብተር ወይም ማኑዋል ቢኖራቸውስ? በህይወታችን የሚያስፈልጉን ማኑዋሎች እንደ እቃው የመመሪያ ቅጽ በአጠረ በተመጠነ ደብተር የሰፈሩ አይደሉም፤ ግን የምር ከፈለግናቸው በዙሪያችን ግልጽ በሆነ መልኩ ይገኛሉ።

ለምሳሌ ቤተሰብ እንዴት እንደሚመሰረት ከምዋወቃችን በፊት በጭፍን የምንመሰርተው ቤተሰብ የእኛን ብቻም ሳይሆን ያለፈቃዳቸው ይህችን አለም እንዲቀላቀሉ ያመጣናቸውን ልጆች ጭምር በእጅጉ ይጎዳል። ለዚህም እኮ ነው አንዳንዶቻችን ከሁለት ሶስቴ በላይ በትዳርና በጓደኘነት ቆይተንም አልሰምር የሚለን። የትዳርና የጓደኝነትን ማኑዋል ሳናውቀው በግምት እየሞከርን ስለሆነ። እንደው ጓደኝነትና ትዳርን ለምሳሌለነት ተጠቀምኩት እንጂ፤ ብዙ በግምት የምንሞክራቸው ነገሮች አሉ። በግምት መሞከሩ ክፋት ላይኖረው ይችላል፤ ከምንፈልገው ቦታ ለመድረስ ግን እጅግ የረዘመው መንገድ ነው።

ለሁላችንም ተመሳሳይ መመሪያ ይኖረናል ብዬ አላምንም። ነገር ግን አንድን ነገር ከማድረጋችን በፊት የምንፈልገው ውጤት ምን እንደሆነና፤ ያንን ውጤት ለማምጣት ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቁ ግድ ይለናል፤ ይህ እኮ ነው የመምሪያ ቅጽ ወይም Manual Instruction የምንለው፤ ወደ ፈልገንበት መንገድ የሚያደርሰን የእውቀት መመሪያ ። የትኛውም ስኬት የራሱ የሆነ ማኑዋል አለው፤ ስኬታችን ጋር በአጭሩ ሊያደርሰን የሚችል ረቂቅ መመሪያ ። ጊዜ ወስደን ይህንን መመሪያ እና መንገድ ካላጤንነው፤ በአጭሩ ልንፈታው የምንችለውን ነገር የዘመናት ትግል እንደርገዋለን።

የምንፈልገው ምንድን ነው?

-የተሻለ ህይወት? የተሻለ ህይወት ከሆነ፤ ልንከተለው የሚገባን መመሪያ ወይም ማንዋል ምንድን ነው? የተሻለ ስንልስ በምን መልኩ?

-ሰላም ያለው ኑሮ? ሰላም ያለው ኑሮ ከሆነ፤ የሰላም ማኑዋል ምን ይላል? የእውነተኛ ሰላምን ትርጉምና ለእኛ የሚሰጠንን ግላዊ ስሜት ሳናውቅ በግምት መሞከሩ ጊዜ ማጥፋት አይሆንም?

-ፍቅር? ፍቅር ከሆነ የፍቅር ማኑዋል ምን ይላል? ለእኛ ፍቅር ማለት ምን ማለት ነው? ኤሪክ ፍሮም የተባለ ጸሃፊ “የፍቅር ጥበብ” “The art of loving” ላይ በጠቀሰው ነገር ጽሁፌን ላጠናቅቅ። “ማፍቀር ጥበብ ነው፤ እውቀትን፤ ሙከራንና ልምድን የሚጠይቅ።”

“ Loving is an Art, Loving requires Knowledge, effort and experience. The capacity to love must be developed with humility and discipline.”- Erich Fromm

ይህ እንግዲህ በጥቂቱ ጸሃፊው የፍቅርን ማኑዋል ሲያቀምሰን ነው። ለማንኛውም በህይወታችን ደግመን ደጋግመን እየሞከርነው የከሸፈብን ነገር ካለ እረፍት ወስደን ማኑዋሉን እንፈልግ። ምናልባት እጅግ አጭር የሆነ የስኬት መንገድ ሊኖረው ይችላል። እየሞከርነው ያለው በተሳሳተ መልኩ ስለሆነ ይሆናል አልሳካ የሚለን። በማወቅ የምንሰራው በግምት ከምንሰራው እጅጉን የተሻለ እና ጥራት ያለው ነው። መሞከር በህይወታችን ወሳኙ ነገር ቢሆንም፤ አውቆ መሞከሩ ግን ብልህነት ነው። ማኑዋሉን ገለብ ገለብ ማረጉ አይከፋም ለማለት ያህል ነው!!!

በሚስጥረ አደራው

    240
    0