የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

Apr 25, 20212 min

በጀንበር አይከበርም በጀንበር አይወደቅም! (ሚስጥረ አደራው)

“Failure is not a single, cataclysmic event. You don’t fail overnight. Instead, failure is a few errors in judgement, repeated every day. Success is nothing more than a few simple disciplines, practiced every day.” Jim Rohn

በአንድ ጀንበር የሚወድቅም ሆነ በአንድ ጀምበር የሚከብር የለም። ሁሌም ስለ ስኬትና ስለውድቀት ልዩነት ስናስብ የምንዘነጋው አንድ ነጥብ አለ። በህይወቱ የተሳካለትም ሆነ ያልተሳካለት ሰው ሁለቱም መስዋትነትን ከፈልዋል። አንደኛው ለስኬቱ ሌላኛው ለውድቀቱ ጊዜያቸውን መስዋት አድርገዋል። እዚህ ላይ ታዲያ ሰው ለውድቀቱ እንዴት ይለፋል? እንል ይሆናል። ነገር ግን እውነቱ ይህ ነው። በእለት ተእለት ኑሮዋችን የምናደርጋቸው ጥቃቅን ውሳኔዎች ናቸው በስተመጨረሻ የምንቆምበትን ማማ አልያም የምንወድቅበት ገደል የሚወስኑት።

የስኬታማ ሰዎችን ህይወት ስንቃኝ የሚታየን አሁን የቆሙበት ማማ እንጂ ማማው ላይ ለመደረስ የከፈሉት መስዋትነት አይደለም። ህይወታቸው እንዳሰቡት ያልሆነላቸውንም ሰዎች ሰው ስናይ የመጡበት እረጅም የስህተት ጎድና አይታየንም። ከላይ የሰፈረው የጂም ሮን ንግግር የስኬትንን እና የውድቀት ልዩነት በሚገባን መልኩ የሚያስረዳ ድንቅ ንግግር ነው።

“ውድቀት በአንዴ እንደ ዱብ እዳ የሚወርድ መዓት አይደለም፤ ሰው በጀንበር አይወድቅም። ውድቀት ትናንሽ ስህተቶች በቀን በቀን ሲደጋገሙ ማለት ሲሆን ስኬት ደግሞ ትናንሽ ቁም ነገሮች በእየለቱ ሲከወኑ ማለት ነው።”

ስለ መልካም ህይወት ስናስብ አልያም ስኬታማ ለመሆን ስንመኝ ስኬት እሩቅ እየመሰለን የምንታለለው አብዛኛዎቻችን ነን። ስኬታችንም ሆነ ውድቀታችን የባህሪዎቻችን ውጤቶች መሆናቸውን መገንዘብ ያቅተናል። በቀን በቀን የምናደርጋቸው ነገሮችና የምወስናቸው ውሳኔዎች የነገውን ማንነታችንን የምናንጽባቸው መሳሪያዎቻችን ናቸው። ዛሬ ላይ ላይ ያለን ማንነት እና ህይወት፤ ነፍስ ካወቅንበት ጊዜ ጀምሮ የወሰንናቸው ውሳኔዎች ውጤቶች ናቸው። እርግጥ ነው ይህንን አሜን ብሎ መቀበሉ ይከብደናል። ለስህተቶቻችን ሌሎችን መውቀስ፤ ለውድቀታችን ምክንያቶችን መደርደር እራሳችንን ከጥፋተኝነት ለማዳን የምንጠቀምባቸው ማምለጫዎቻችን ስለሆኑ።

“consistency” ማለትም ነገሮችን በቁርጠኝነት ያለማቋረጥ መከወን የስኬት ወሳኙ ንጥረ ነገር ነው። አብዛኛዎቻችን ግን ዛሬ የወሰንነውን ወሳኔ ከቀናቶች በላይ ማዝለቁ ይከብደናል። በስሜታዊነት የምንወስናቸው ውሳኔዎች ውጤት የማያመጡት ውሳኔዎቻችን ደካማዎች ሆነው ሳይሆን ቁርጠኝነት ስለሚጎድለን ነው። ለምሳሌ ውፍረትን ለመቀነስ የሚጥር ሰው፤ በየቀኑ የሚበላውን ምግብ ካልተቆጣጠረ በቀር አንድ ቀን እየጾመ ሌላ ጊዜ ከልክ በላይ እየበላ ያሰበውን የክብደት መጠን ሊያሳካ አይችልም። ማንም ሯጭ ዛሬ ሮጦ ወር አያርፍም፤ ህይወትም እንደዛው ናት መሆን የምንፈልገውን ነገር እለት በእለት ልንኖረው ይገባናል።

የትኛውም አይነት ስኬት የሚመነጨው ከቁርጠኝነት ነው። በእለት ተእለት ኑሮዋችን አላማችንን የሚያንጸባርቁ ነገሮችን መከወንን ካላቻልን አላማችንን እውን ለማድረግ ይከብደናል። ጊዜ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው። “ህይወትን እወዳለው የሚል ሰው፤ ጊዜውን በከንቱ አያጠፋም” የሚባለው አባባል፤ ኑሮዋችን ብለን የምጠራው የኛ ገጽታ ጊዜያችንን የምናጠፋበት ነገር መሆኑ ለማስረዳት ነው።

ማንነታችን ጊዜያችንን የምናጠፋባቸውን ነገሮችን የሚያንጸባርቅ መስታወት ነው። ይህ ነጥብ ከላይ ወደሰፈረው አባባል መልሶ ያመጣናል። ሰው በጀንበር አይከብርም በጀንበርም አይወድቅም። ዛሬ ያለንበት ማማ ወይም የወደቅንበት ገደል እስካሁን ጊዜያችንን መስዋት ያደረግንባቸው ውሳኔዎች ድምር ነው። ስኬት እሩቅ አይደለም ይልቁንም እየረገጥነው የምንጓዘው ጎዳና እንጂ።

በቀን በቀን የምናደርጋቸው ነገሮች መሆን የምንፈልገውን ማንነት ያንጸባርቃሉ? ይህንን መመለስ ከቻልን በእርግጠኝነት ወደፈልገንው ጎዳና እራሳችንን መምራት እንችላለን።

    300
    1