top of page

 መሃመድ ጁሃር

ስለ አርበኛነት ሲነሳ ስለ ጀግኖችና ጀግንነት ተያይዞ ይነሳል ከጀግና ህዝብ መሃልም ጀግኖች ይፈጠራሉ ጀግንነት የእናት አባት ውርስ ባይሆንም ፈጣሪ መሪን ይቀባዋል እንዲሉ ተቀብተው ይወለዱታል፡፡ የጀግንነት መገለጫው በርካታ ቢሆንም አንዳንዶች ከአስቸጋሪ አውሬ ጋር ግብግብ በመግጠም ማለትም ከአንበሳ ፣ ከዝሆን፣ ከነብር ፣ወዘተ ታግሎ ማሸነፍ እንደ ጀግንነት  ሲቆጥሩት ሌሎች ደግሞ በጨበጣ ውጊያ አንገት ለአንገት መቀነጣጠስና በጥይት ተኩሶ አልሞ መግደል አልያም ምንም አይነት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በሌለበት በፈረስና በጦር ተዋግቶ ድል መቀዳጀት የጀግንነት ዘርፍ ነው በማለት ያምናሉ በሌለ በኩልም ድህነት  በልማት ድል መንሳትም የጀግንነት አካል ነው በማለት የሚከራከሩም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

 

 በመሆኑም በዚህ ጽኁፍ ታሪኩ የምንዘክርለት ጀግና ምንም አይነት የጦር መሳሪያና የተማረ ህዝብ በሌለበት ብቅ ብሎ የመስቃን ቤተ ጉራጌ ህዝብ አንድነትና ክብር ለማስጠበቅ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል ተብሎ የሚነገርለት በመጨረሻ የህይወቱ ፍጻሜ ላይ ግን ህዝቡን ተራግሞ መሞቱ ስለሚወራለት የጦር አበጋዝ ገድል ይሆናል ፡፡ መሀመድ ጁሀር ይባላል ፡፡ መሀመድ ጁሀር ቁመቱ ረጅምና ለግላጋ ስለነበረ ተፈጥሮው የማንንም ሰው ቀልብ የሚያማልል ውበትና ደም ግባት የነበረው ጎልማሳ ሲሆን ፈረስ ግልቢያ ሲነሳ መሀመድ ጁሀር ፣ መሀመድ ጁሀር ሲነሳም የፈርስ ላይ ውጊያና የፈረስ ጉግስ ተያይዞ ይነሳል፡፡ በአጠቃላይ ፈረስና መሀመድ ጁሀር የአንድ ሳንቲም  ሁለት ገጽታ መሆናቸው የሚያሳይ ስንኝ ተቋጥሮም እንዲህ ተብሏል።

 

ባትሸጌ ደረቦ

መሌ ሰር ኤነቦ

ጁሃር በኬሬቦ

ደጎ በመጬቦ

ኬረሶ ቢዛቦ

ደልባር በገነሞ

ሽፋ በሲርበሞ

ጃቢር በሶሰሞ

በፈረዝ ቲያስሮ

ዋይም ደስ የበሮ

 

  ተብሎላቸዋል፡፡ ትረጉም:- ይህም ማለት እነዚህ ባንድ ወቅት የነበሩ የጦር አበጋዞች ፍርሃት የማይሰማቸውና ፈረስ ላይ ሲወጡም ግርማ ሞገሳቸው አስፈሪና ውብ እንደነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር መሀመድ በተሳተፈበት የጦር ግንባር አሸንፋለሁ ብሎ መገመት የማይታሰብ ከመሆኑም በላይ  መሀመድ ጁሃር  ፈረስ ላይ ሆኖ ጦሩ ሲመዝ መላዕክት እንጂ የሰው ፍጡርነቱ  ያጠራጥር እንደነበር አባቶች ይናገራሉ ይህንንም አስመልክቶ  የሚከተለው ስንኝ ተቋጥሮለታል፡፡  

  

ዲና ፈረዝ ቲጨን ሻዶ የወቅጥር

እም መስቃን እንቧር ምኬሎ ጠቀር

ውሪበ አቦራት የተቦን ታትበር

ዶቢም ኸነ ጎይባን ውጣ በሠበር

የውራግ ነኖክ ጁሃር ተደልባር !!

 

 ትርጉሙም ፡- ጠላት ፈረስ ጭኖ ሻዶ / አያቶቻችን / ለመግደል ሲመጣ በቀበሌ ሳትከፋፈል ሁልህም ውጣ መሀመድ ጁሃርና የለንቴ ደልባር የመሳሰሉ ሰኬታማ የጦር መሪዎች ከጎንህ አሉልህና ለድል አታስብ የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ይህ አባባል የመስቃን ህዝብ በእነሱ ላይ የነበረው እምነትና እነሱም ለጠላት ፍጹም የማይንበረከኩ እንደነበሩ የሚያሳይ አባባል ነው፡፡የመሀመድ ጁሀር ጀግንነትና  የጦር ስልት አዋቂነት አንድአንድ በአረብኛ የተጻፉ መጽሀፍቶች ሳይቀሩ አሞካሽተውታል፡፡በተለይም ሼክ ዑመር ሼክ በሽር የሚባሉ የወሌኔ ሼክ “ጥሮኒ” የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ በሚለው መጽሀፍ ላይ እንዳስቀመጡት “ከባለታሪካችን ውስጥ መሀመድ ጁሀር የመስቃኑ ሰው ተጠቃሽ ነው ፡፡

 

 ጀግና ነበር፡፡ ለጀግንነቱ  ወደር የሌለው ሆኖ የታየ በመሪነቱም ጊዜ ፍትሃዊ የነበረ አልቃሻና ሆደ ባሻ  ነበር፡፡ መሪ ሆኖ  ባገለገለ ጊዜም ፍጹም ቀልድና ጨዋታ በመተው በጥንቃቄ ለአሄራ ጉዳይ ብቻ ታጥቆ የተሰማራ ከአዱንያ ጣፋጭ ነገሮች ሁሉ ለአሄራው ያስተላለፈ ሰው ሆነዋል፡፡ ራሡም  ከአላህ ጋር በመተሳሰብ የሚያለቅሥና በዚህም ሁኔታው እስከ መጨረሻው ድረስ እራሡን አጥርቶ  ለቆመለት አላማ በጅሀድ ከተሰውት ጋር ሆኖ አልፏል ፡፡ አላህ ይማረውና ” በማለት ተናግረዋል፡፡ በአጼ ሚኒሊክ የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ ወቅት የጦር ሀይላቸው አሰልፈው ጉራጌ በተለይም የመስቃን ምድር ሲገቡ ለአጼ ሚኒሊክ  የገጠማቸው ፈተና ቀላል እንዳልነበር አበው ይናራሉ፡፡ የመስቃን ቤተ-ጉራጌ ህዝብ በመሀመድ ጁሀር የጦር መሪነት በጦርና በጎራዴ ብቻ የሚኒሊክ ሰራዊት በመመከት  ሁለት ሶስት ጊዜ አንቀጥቅጠው መመለሳቸው ይነገራል፡፡ በተለይም ጎጌቲ ቀበሌ ሻቤ በሚባለው ስፍራ ላይ የሚኒሊክ ጦር በደረሰበት ሸንፈት በእጅጉ ማፈሩና የጦርነቱ ሂደት በቅርብ ርቀት ይከታተሉ የነበሩ ሌሎች ታዛቢዎች በተለይም እንቦር ላይ አጋላ በሚባለው ቦታ  የመሀመድ ጁሀር ቀኝ እጅ ስለነበረው የእንቦሩ ዓሊ ፎርገቶ በሚኒሊክ ጦር ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጀብድ ስንኝ ቋጥረው እንዲህ  ብለውለታል፡፡  

 

የፎርጌ ፋፍነት ምናህረው ናውድሁ

ኤታሁታን ንግፍርም ኤተሁ ናተዥሁ

ባጋላ ተት አዘር አርብ ቁም ቢቡሪ

እንኳ ይድነብጤ ኤሰበ ይቀጥሬ

አቅም አማራሺ ኧጅላጅም ቋጠሪ

ሹም ልማድመውታን የፎርጌ አቀቦሪ  !!!

 

ትርጉሙም፤- የአሊ ፎርገቶ ጀግንነት ስንቱ ልንገራችሁ የትኛውን ትቼ የቱን ላውራላችሁ አጋላ በሚባል ቦታ ጦርነት ተነሳ ሲባል እንኳን ሊደነግጥ የሚገድለውና የሚማርካቸው ሰዎች ቁጥር ማሰላሰል ጀመረ በማለት በሚኒሊክ  ሰራዊት ላይ የተጎናጸፉት አንጸባራቂ ድል አወድሰውለታል  በመስቃን  ህዝብና በሚኒሊክ ሰራዊት መካከል በተለያዩ አውደ ግንባሮች ፍልሚያ መደረጉ የተለያዩ ታሪክ ድርሳናትና በተለይም ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በጻፉት የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ በሚለው መጽኀፋቸው ላይ የሰፈረ ቢሆንም የመስቃን ሽማግሌዎች በአፈ ታሪክ ደረጃ ከሚነገረው በስተቀር እስከዛሬም በእለት እሮብ ስለተደረገው ውጊያና ስለተጎናጸፉት ድል ምንም አለመባሉ ግን ያስገርማል፡፡

የመስቃን ህዝብ እስከ ዛሬም የሮብ  ወታደር ኸማ ጥፎ እያለ / በእለት ረቡዕ  እንዳለቁት እንደ ሚኒሊክ ወታደሮች ጥፋ/ እያለ የእለቱን ድል በሁሉም አዕምሮ እንዳይረሳ አድርጎታል፡፡ አንዳንድ የጎረቤት ሴቶችም ስለዚህ ቀን ስንኝ ቋጥረው እንዲህ በማለት ፍልሚያውን ይዘክሩታል ፣፣ 

 

ቶሪ ፈያ ሰንብት ወገሬት ኧደር

ቀልበኛ ኤላቢም ተመስቃን ወንበር

ተመሀመድ ጁሀር ተለምቴ ደልባር   !!!

 

ትርጉም፡- ቶራ የምትባል መንደሬ ደህና ሁኝ ልቤ ከነ መሀመድ ጁሃር ከጀግኖቹ ጋር መኖር ፈልጋለች በማለት  እንጎራጉረዋል፡፡ ሴቶች ይህን ያሉት የመስቃን የጦር አበጋዞች እነ መሃመድ ጁሃር ለሚኒሊክ አንገብርም በማለት በከፈቱት የመጀመሪያ  ፍልሚያ ድል ሲያደርጉ በማየታቸው ተደስተው እንደነበርና ሁሉም ሰው ልክ እንደ መስቃን ጦር አበጋዞች ተዋግተው ክብራቸው እንዲያስጠብቁ ለማነሳሳት የቋጠሩት ስንኝ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ የመሀመድ ጁሃር የታሪክ ገድልም የሚጀመረው ከዚህ ሲሆን አጼ ሚኒሊክ የኢትዮጵያ አንድነት ለማስጠበቅ አልያም ኢትዮጵያ በአንድ ማዕከላዊ መንግስት እንድትመራ ለማድረግ አልመው በተለያየ የሀገራችን አካባቢዎች የጦር ዘመቻ ከፍተው በድል ቢመለሱም የጉራጌ ህዝብ ለማስገበር  ያደረጉት ዘመቻ ግን እንደ ሌሎች አካባቢዎች  ቀላል እንዳልነበረና በተለይም በመጀመሪያዎቹ ዙሮች የአጼ ሚኒሊክ ወታደሮች የከፈሉት ዋጋ ከባድ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ በዚህም መሰረት የአጼ ሚኒሊክ ሰራዊት  የመስቃን ህዝብ ለማስገበር በከፈቱት የመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሶስት ውጊያዎች ሽንፈት ስለገጠማቸው የተለየ ስልት መቀየስ ያስፈልግ ስለነበር አጼ ሚኒሊክ ከጦር አበጋዞቻቸውና አማካሪዎቻቸው ጋር በመምከር በአቶ ገሌ የሚመራ ቡድን ለድርድር ወደ መስቃን ምድር ይልካሉ፡፡ መልዕክተኞች መስቃን ምድር እንደደረሱ  ለህዝቡ ያቀረቡት ጥያቄ መሪያችሁ ወይም የጦር አበጋዛችሁ ማን ነው ? የሚል ነበር፡፡ ህዝቡም እነሱን ከቁብ ሳይቆጥር በልበ ሙሉነትና በኩራት መሪያችን መሀመድ ጁሃር ነው በማለት ወደ እሱ ይጠቁማሉ ፡፡ መልዕክተኞችም በመሀመድ ጁሀር ለግላጋ ቁመናና ወንዳወንድነት  ተገርመው እስቲ ጀግንነትህን አሳይ ይሉታል፡፡

 

ምንጭ  -  ጋዜጠኛ ሪድዋን ከድር

bottom of page