top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ሀገር ትሙት! – የጨካኞች መሐላ


“መሐላ” የአንድን ሥራ እውነተኛነት ለማረጋገጥ ወይንም የተነገረን አንዳች ምስክርነት ወይንም ቃል አድማጩ አምኖ እንዲቀበልና ስለ እውነተኛነቱ ጥርጥር እንዳይገባው የኪዳን ማረጋገጫ መስጠት ማለት ነው። ሰብዓዊ ፍጡር በተለያዩ አካላት መሐላውን ሊፈጽም ይችላል። በፈጣሪ፣ በመላዕክት በጻድቃንና በሰማዕታት ስሞች መማል ያለ የነበረና ወደፊትም ይቀራል ተብሎ የማይገመት የሰው ልጆች “ሃይማኖታዊ የመታመኛ መገለጫ” ነው።

አንድ ሰው የአባቱን፣ የእናቱን፣ የእህትና የወንድሙን እልፍ ሲልም የሚያከብረውን ሰው፣ አፍቃሪውን፣ በአርአያ ሰብነት የተቀበለውን ግለሰብ ወዘተ. ስም እየጠራና “ሞታቸው” እንኳን ቃሉን እንደማያስለውጠው መዳፍ እየጠበጠበ አለያም በቃሉ ጽናት እያረጋገጠ ሊምልና ሊገዘት ይችላል። (አባቴ ይሙት፣ እናቴ ትሙት ወዘተ. እንደሚባለው መሆኑን ልብ ይሏል።)

በሀገራችን ባህልና ወግ መሠረትም የነገሥታትና የመኳንንት ስም እየተጠራ መሐላ ይፈጸም እንደነበር ታሪካችን ሰንዶልናል። ሕያዋን ምስክሮችም ይህንኑ እውነት ዛሬም ድረስ ያረጋግጡልናል። “ምኒልክ ይሙት፣ ኃይለ ሥላሴ ይሙት፣ ፊታውራሪ ወይንም ደጃዝማች እከሌ ይሙት ወዘተ.” የሚሉት የመሐላ ዘይቤዎች ጊዜያቸው ቢያረጅም በትዝታ መታወሳቸው ግን አግባብ ነው፤ ታሪክም ይፈቅድልናል።

አንድ ሰው የሚምለው መሐላ ተፈጻሚነት እስከ ምን ድረስ ነው? መሐላውስ እንደሚሰጠው ተስፋ በርግጡ ኪዳን የሚጸናበት፤ ቃል የሚከበርበት፤ ድርጊት የሚታመንበት ነው ወይንስ ለይስሙላ? የሚሉት መከራከሪያዎች ሁሌም እንዳሟገቱ፣ ሁሌም ለትዝብት እንደዳረጉ ስለምናስተውል ቁርጥ ያለ “ይሆናል ወይንም የአይሆንም ውሳኔ” ለመስጠት ያዳግታል።

በተከበረው የፍርድ ወንበር ፊት ቆመውና በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ እጃቸውን አስጭነውና ጭነው “የፈጣሪን ስም” እየጠሩ የሚያስምሉትና የሚምሉትን የፍትሕ አደባባይ ተዋንያንን በማጣቀስ የመራር ትዝብቶቻችንን ገመና እንዘርዝር ቢባል እንኳን ብዙ ስለሚያስተዛዝብ በድርበቡ ማለፉ ይመረጣል። በዚሁ ደጀ ፍትሕ ገንፍሎ የሚሰነፍጠውን ሀገራዊ ጉድፍ ከመነካካት ይልቅ ለጊዜ ጊዜ ሰጥቶ በይደር ማስተላለፉ ይሻል ይመስለናል።

በተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ሸንጎ ፊት ለፊት ካባ በለበሱ ጎምቱ የፍትሕ አስፈጻሚ ሹሞች አማካይነት እጃቸውንና ልባቸውን ከፍ አድርገው በፈጣሪ፣ በሀገር፣ በሕዝብና በህሊናቸው ስም የሚዥጎደጎዱ መሐላዎችን የተግባራዊነት ጉዳይ እንመርምር ብንልም “ሺህ ምንተ ሺህ” ክሽፈቶችን ስለምንጠቃቅስ በተላመድነው አገላለጽ “ሆድ ይፍጀው” ብሎ በትዕግስት ማለፉ ብልህነት ነው።

“ማለኛ” ማለት በትልቅ በትንሹ፣ በእውነትም ይሁን በሐሰት ለመማል የሚዳፈር ሰውን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ሲሆን፤ “ማላ ፉቱ” ማለት ደግሞ መሐላን የማይፈራ፣ መሐላን እንደ ውሃ ፉት የሚል ዋሾና ሐሰተኛ ሰውን የሚወክል ሀረግ ነው። እነዚህን መሰል “መሐሊዎች” (ማለኛዎች) አድራሻቸውና መዳረሻቸው ሰፋ ብሎ የሚስተዋለው በተግባራቸው ሳይሆን በምላሳቸው ለመታወቅና ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ በሚፍገመገሙ የፖለቲካ ሠፈርተኞች ሕይወት ውስጥ ነው።

ለሀገሬ ምን በጃት፣

ያም ድንጋይ፣ ያም ኮረት ያም አፈር ጫነባት።

እንዳለው ብሶተኛ አንጎራጓሪ ዛሬ ዛሬ ሀገሬን ለማፍረስ (ቃሉ ቢቀፈኝም) የሚማማሉትና እውነትን ክደው የሀሰት ካብ የሚክቡትን የሩቅና የቅርብ ጠላቶች ብዛታቸውና ዓይነታቸው ከመትረፍረፉ የተነሳ ዘርዝረን ለመጨረስ የማንችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለናል። እኒህን መሰል ምናምንቴ ማለኛዎች ህሊናቸውን የካዱና ህሊናቸውም እነርሱን የካደ ጨካኞች ብቻም ሳይሆኑ ቃል ኪዳን ለመስበርም ፈጣኖች መሆናቸውን የዛሬው ዐውዳችን እየመሰከረልን ነው። በዚህም ምክንያት፤

ታዲያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ

እኛ ልጆችሽ ምንድን ነን?

አመንኩሽ ማለት የማንችል፤ ፍቅራችን የሚያስነውረን፣

ዕዳችን የሚያስፎክረን፤ ግፋችን የሚያስከብረን፣

ቅንነት የሚያሳፍረን፤ ቂማችን የሚያስደስተን፣

አረ ምንድን ነን? ምንድን ነን?

አሜክላ የሚያብብብን፤ ፍግ የሚለመልምብን።

ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች፤ ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር፣

ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ ከቶ ያልተበራየን መኸር፤

ምንድን ነን? ምንድነን እኮ?

እንዳለው ብዕረኛው ነፍሰ ሄር ጸጋዬ ገብረ መድኅን፤ እነሆ በዛሬዋ ጀንበራችን ፊት “የደም ዋንጫ በጨበጡ” የሟርት መሐሊዎች የግፍ ጀብድ አማካይነት ሀገርና ሕዝብ መከራ ላይ ወድቆ እያማጥን እንገኛለን።፡ ሲተበትቡ ያደጉበትን የሴራ ቡትቶ ተጎናጽፈውም በዓለም ማሕበረሰብ ፊት የትራዤዲ ተውኔታቸውን ሲተወኑ በአጫፋሪዎቻቸው ይጨበጨብላቸዋል።

ከሀዲዎቹ መድረኩን ይዘው ሲተውኑ “አይዟችሁ” ባዮቻቸው ደግሞ የእነርሱን ተውኔት እያዳመቁ “በጉሮ ወሸባዬ” ማጨብጨባቸው ለምን ዓላማ እንደሆነ አልተሰወረብንም። “ጦር ከፈታው፤ ወሬ የፈታው” በሚለው መርሐቸው፣ በቆሸሸ ህሊናቸውና በተናዳፊ ምላሳቸው እውነታችንን መበረዛቸው ከራሳቸው ጋር የገቡት የመሐላቸው ውጤት ስለመሆኑም መጠራጠር አይቻልም።

ሰሞኑን የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ የጥሞናና የማሰላሰያ ጊዜ ለመስጠትና ለዓለም አቀፍ መንግሥታትና “ጥልቅ ብዬ” ቡድኖች “የኡኡታ” ጩኸት ምላሽ ለመስጠት በመወሰን ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ፈቅ ማድረጉ ትኩስ ሀገራዊ ክስተት ነው። እንደ መከላከያችን ጀግና ጄኔራል አገላለጽ እብሪታቸው ተንፍሶ ምላሳቸው ብቻ ያልተቀበረው የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦች በጣዕረ ሞት መንፈስ አብጠው ምን እየሠሩ እንዳሉ ልብ ተቀልብ ሆነን እየተከታተልን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በ5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም “ለእንደራሴዎቹና” ለሕዝቡ ያቀረቡትን ዝርዝር ሪፖርት መለስ ብሎ ማስታወሱ ይበልጥ መነሻና መድረሻችንን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። እንዲህ ነበር ያሉት፤

“ከአሥር ሺህ በላይ እስረኛ መቀሌ ብቻ፤ እንዲሁም በድፍን ትግራይ ከሠላሣ ሺህ በላይ እስረኛ ተፈትቷል።… ሰው እንዲህ ሲታጎር አናውቅም። የተለቀቀው ይዘርፋል። የእነርሱ ርዝራዥ ይዘርፋል። … ሌሎችም ኃይሎች ተጨማምረው ሕዝቡ ጉዳት ላይ ነው። የዚህ ሁሉ ጉዳት መነሻ ኃላፊነት የማይሰማው ኃይል ቢሆንም ገፈት ቀማሹ ምስኪን ሕዝብ ነው። ለትግራይ ሕዝብ ጦርነትና ግጭት አይገባውም። የተሸከመው የጁንታ ኃይል በእጁ ላይ የነበረው ደምና ኃጢያት አስክሮት ተጨማሪ ዕዳ ሊመጣ ግድ ሆኗል።”

ይህ “ደምና ኃጢያት ያሰከረው” ኃይል የመከላከያ ሠራዊታችን ለሰላም ሲል ወደ ኋላ አፈግፍጎ ለሕዝቡ የጥሞና ጊዜ መስጠቱን እንደ ተሸናፊ በመቁጠር ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ የፈጸማቸውና እየፈጸማቸውያሉት አረመኔያዊ ድርጊቶች ለቡድኑ ማንነት ጥሩ መገለጫዎች ናቸው።

“የእኔ” እያለ የሚፎክርበት የትግራይ ሕዝብ በሙሉ የግፈኞቹ ተባባሪ ነው ማለት በፍጹም ስህተት ነው። “ስሙን ነጥቆ” የሚነግድበት ይህ የመከራ ተሸካሚ ሕዝብ ባለፉት አራት ዐሠርት ዓመታት ምን ያህሉን ልጁን ለእኩይ ዓላማቸው እንደገበረ፤ በእርግጥም የእርሱ ተቆርቋሪ ስለመሰሉት ማዕዱን አራግፎ በመመገብ፣ እንስራውን አንቅሮ በማጠጣት እንደደገፈው፤ ከሁሉም በላይ ልጁን እየመረቀ ወደ ጦርነት እቶን ሲልክ እንደነበር ታሪካችንም ሆነ ታሪካቸው ምስክር ነው።

የቃዡበትን በትረ ሥልጣን በምሉእ በኩለሄ ፈላጭ ቆራጭነት ከጨበጡ በኋላም እንደምን ለግላቸውና የራሳቸው ለሆኑ ቤተዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው መብሸንሸኛነት የሀገሪቱን የሀብት መቅኒ ሙጥጥ አድርገው እንደ መጠጡና እንደጋጡ በብዙ ማስረጃዎች ሲረጋገጥ እየሰማንና እያስተዋልን ነው። እርግጥ ነው ከሕዝቡ መሃል ተፈጥረዋል። በሕዝቡ ስምም ሲነግዱ ባጅተዋል። ይህንን እያስተዋለ ያለው የትግራይ ሕዝብ ለምን “በቃችሁ! እኛም በቃን!” ብሎ ድምፁን አጉልቶ እንደማያሰማ ግራ ቢገባን አይፈረድብንም።

ለሕዝቡ ትራስና ደጀን በመሆን አቅፎና ደግፎ ሲያገለግላቸው የኖረው ሠራዊት ተክዶ በአደባባይ ሲገደልና ሲዋረድ የትግራይ ሕዝብ አንቅሮ ለምን እንዳልተፋቸው፤ ለምንስ በሕዝብ ድምፅ እንዳልቀጣቸውና እንዳልገሰጻቸው ዛሬም ድረስ መልስ ፈልገን አላገኘንለትም። “ጠመንጃ ከያዘ ቡድን ጋር ማን ይጋፈጣል?” የሚለው ምክንያትም ከሕዝብ አቅም ጋር እየተወዳደረ ሲገለጽ ለማመን ያዳግታል። ከእነ ብሂሉስ “የሕዝብ ድምፅ የእግዜር ድምፅ” ይባል የለ? “ከልብ ቢለቀስ ኖሮ” ሕዝብ ቀጥቶ የማያሸንፈው፣ መክሮ የማይመልሰው ምን ምድራዊ ኃይል ይኖራል? የዛሬ እውነታችን የነገ ታሪካችን ስለሆነ ዘመን መሽቶ ሲጠባ ታሪክና ልጆቻችን እውነቱን ይወርሱታል።

“ጥሞና” (ጽሞና) ከህሊና ጋር የሚመካከሩበት የእርጋታና የዝግታ ጊዜ ነው። ለትግራይ ሕዝባችን የተላለፈው ቀጥተኛ መልዕክትም ይሄው ነው። በግል፣ በቡድንና እንደ ሕዝብ አንደ ሆኖ ጥሞናን (ጽሞናን) መጋራትና መግባባት ላይ ለመድረስ ዕድል ተሰጥቷል። ጥሞና (ጽሞና) ትናንትን ዞር ብሎ እንዴት ነበርነቱን ማስታወስ፣ ዛሬን ሰከን ብሎ መመርመር፣ የነገን መጻዒ ዕድል ለበጎነት መጠቀምን ስለሚያጠቃልል እርግት ብሎ ማብሰልሰልን፣ በአርምሞ መንፈስ ውስጥ በመሆን የነገሮችን አካሄድ ማውጠንጠን ግድ ይሏል።

የጥሞናውን ዕድል ለማምከንና የሕዝብን መከራ ለማራዘም በሀገር ውስጥና በዓለም ክፍሎች ሁሉ እንደ ጥንብ አንሳ ጆፌ እያንዣበቡ በሕዝብ መከራና ስቃይ ግዳዩን ለመቀራመት የሚቋምጡ የሞት ደጋሾችን “ገለል በሉልኝ” ሊላቸው የሚችለው ይሄው መከረኛ ሕዝብ ነው። የከንቱ ሰው እርግማንና የጥፋት መሐላ ዞሮ ዞሮ የሚያጠፋው ራሱን ተራጋሚውን ነው። “ተራጋሚ፤ ራሱ ተደርጋሚ” እንዲሉ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ላይ ተማምለው የዘመቱ ሁሉ ታሪካቸው በምን ዓይነት ሽንፈት እንደተደመደመ ለማወቅ የፈለገ ያውቀዋል። “ኢትዮጵያ ትሙት መሐላ” የሰነፎች ትንፋሽ እንጂ የልጆቿ ቃል ኪዳን አይደለም። ኢትዮጵያ በእሳት የተፈተነች የፍም አሎሎ ነች። እንኳን ሰነፎች ቀርተው “ብርቱ ነን!” ባዮችም ሊጨብጧት ሲሞክሩ ከስለው ማረራቸው ለዓለም የታወቀ ስለሆነ ምላሻችን “አትድከሙ!” ይሆናል። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!

(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013

25 views0 comments

Comments


bottom of page