top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ለሌሎች “ጥሩ” የሆነው ላንተ “መጥፎ” ሊሆን ይችላል !


ዓለማችን በበርካታ ተቃራኒ ነገሮች የተሞላች ናት የተቃራኒዎች መኖር ደግሞ ለዓለም መገኛ ምንጭና የህልውና እስትንፋስ መሆናቸውን ይናገራሉ፤ ሄራክሊተስና ተከታዮቹ፡፡ ጨለማና ብርሃን ፣ጥላቻና ፍቅር ፣ግራና ቀኝ፣ ውሸትና እውነት፣ መሃይምና ምሁር፣ ድህነትና ሃብት፣ ረሃብና ጥጋብ፣ ንፉግነትና ቸርነት፣ ጭካኔና ርህራሄ፣ ፍርሃትና ድፍረት የመሳሰሉት ጥንድ ቃላት በተቃራኒነት ይታወቃሉ፡፡ ምንም እንኳን የአንዱ ጥንድ ቃል የተቃርኖ ሁኔታ ከሌላው በእጅጉ የሚለያይ ቢሆንም ከጥንዶቹ አንዱ ሁልጊዜ በክፉ ሌላው ደግሞ በበጎ ክፍል መመደባቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ጨለማ፣ ግራ፣ ጥላቻ፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ ፍርሃት፣ ንፉግነትና ጭካኔ በመጥፎ እንዲሁም ብርሃን፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ሃብት፣ ቀኝ፣ ድፍረት፣ ቸርነትና ርህራሄ ደግሞ በጥሩ ምድብ መካተታቸው ነው፡፡

ነገር ግን ጥላቻ፣ ውሸት፣ ፍርሃት፣ ንፉግነትና ጭካኔ “ሁልጊዜ መጥፎ ናቸው” ብሎ በርግጠኝነት መናገር ይቻል ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ ብርሃን፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ድፍረት፣ ቸርነትና ርህራሄ ሁልጊዜ ጥሩ ድርጊቶች ናቸው ብሎ ለመናገርስ የሚደፍር ይኖር ይሆን? በርግጥ ፍጹማውያን (objectivist) ፈላስፎች ይህን በርግጠኝነት ለማለት ይደፍራሉ፤ ምክንያቱም በእነርሱ እምነት አንድ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ወይም ድርጊት ጥሩ ከተባለ በየትኛውም ዘመን በማንኛውም ቦታ ጥሩ ነው፤ እንዲሁም መጥፎ ከተባለ ምንም ጊዜ የትም ቦታ መጥፎ ነውና፡፡ ለምሳሌ የውሻና የአሳማ ሥጋ መመገብ ነውር ከሆነ በማንኛውም ዘመን በየትኛውም ሀገር ባህል ነውር ነው ማለት ነው፡፡

ይሁንና በሌላ ጎራ የሚገኙ አንጻራውያን (relativist) ፈላስፎች ደግሞ አንድ ድርጊት በተመሳሳይ ጊዜ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል፤ ስለሆነም አንድን የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ ወይም ድርጊት አብነት አንስቶ ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ ከመበየን በፊት ደርጊቱ በየትኛው ዘመን፣ በማን ባህል፣ በማን ሃይማኖት በአጠቃላይ ከምን አንጻር የሚለውን ነገር ማጥናት ያስፈልጋል ሲሉ ማሳመኛ ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ “አንድ ወንድ ባል ለአንድ ሴት ሚስት ወይም አንድ ሴት ሚስት ለአንድ ወንድ ባል” (monogamy) ብቻ ትክክለኛ የጋብቻ ፍልስፍና እንደሆነ በርካቶች የሚግባቡበት ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡

በተቃራኒው አንድ ወንድ ባል ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሴት ሚስቶች (polygamy) የጋብቻ ፍልስፍና የሚፈቅዱና የሚያራምዱ በርካታ ባህሎችና ሃይማኖቶችም መኖራቸውም እሙን ነው፡፡ ታዲያ ትክክለኛው የጋብቻ ስነ ምግባር የትኛው ነው? ለምን? ከማን አንጻር? ከዚህም ባሻገር ለብርሃን መኖር ጨለማ፣ ለእውነት መኖር ውሸት መኖራቸው የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ በተቃራኒዎች ውስጥ የሚገኙ የመጥፎ ነገሮች መኖርም በራሱ አስፈላጊ መጥፎነት (necessary evil) ነው በሚል የሚከራከሩም አሉ፡፡ ለምሳሌ “ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል” እና “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚሉት የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የክፉ ሰዎች በእኛ ዙሪያ መኖር ምን ያህል አስፈላጊና ለትጋታችን መነሻ መሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡

ፍልስፍና በፍጹማውያንንና በአንጻራውያን እይታ ዘርፈ ብዙ ሃሳቦችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ መጠን ውስብስብ ከሆኑ የስነ ምግባር ፍልስፍና ንድፈ ሃሳቦች (moral theories) ጀምሮ በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ፣ በሳይንስና በአካባቢያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚነሱ አወዛጋቢ የስነ ምግባር አጀንዳዎችን (controversial moral issues) በጥልቀት መርምሮ አንድ አመክኗዊ አቋም ላይ እስከ መድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህ የስነ ምግባር አቀራረብ ተግባራዊ ስነ ምግባር (applied ethics) ይባላል፡፡ ተግባራዊ ስነ ምግባር ለሙያዊ የስነ ምግባር (professional ethics) ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚወጡ ህጎችና ደንቦች (legal codes) መንገድ ቀዳጅ ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያገኙና ትክክለኛ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የተግባራዊና የሙያዊ ስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ነገር ግን ጥልቅ ምርምርን የሚሹ አስተሳሰቦች በፍልስፍና መነጽር ሲቃኙ ምን አይነት ስህተት እንዳለባቸው ማሳየት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የምናነሳው የሰው ልጅ በእንስሳት፣ በእጽዋት፣ በመሬት፣ በከባቢ አየርና በሌሎች ረቂቅና ግዙፍ ፍጥረታት ላይ ስለሚፈጽመው የስነምግባራዊ ግድፈት የሚያትተውን አካባቢያዊ ስነ ምግባር (environmental ethics) ነው፡፡

በነባሩ የሃይማኖትና የፍልስፍና የሥነ ምግባር አስተምህሮ ስነ ምግባር በዋነኝነት የሰው ልጆች ብቻ መገለጫ ነው፡፡ ይህም ማለት አንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን ለመገምገም የምንችለው ድርጊቱ በሰው ልጆች፣ ለሰው ልጆች ወይም የሰው ልጆች ላይ ብቻ የሚፈጸም ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላን ሰው በጭካኔ ሲደበድብ ብንመለከት ደብዳቢው ግለሰብ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነው እንላለን፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው አንድ ውሻን ደብድቦ ሲገድለው ብንመለከት ገዳዩ ስነ ምግባር የጎደለው ሰው ተብሎ አይታሰብም፤ ምክንያቱም እንስሳት እንደ ሰው ልጆች የሞራል አቋም የላቸውምና፡፡ ነገር ግን በዘመናችን የተነሱ የአካባቢ ፍልስፍና ሊቃውንት (environmental philosophers) ስነ ምግባር ለሰው ልጆች ብቻ የሚሰጥ ጽንሰ ሃሳብ ሳይሆን በአጠቃላይ ለፕላኔታችን ለመሬት፣ ለእንስሳት፣ ለእጽዋት እንዲሁም በምድራችን ላይ ለሚገኙ ሌሎች ህይወት ያላቸውና ህይወት ለሌላቸው ነገሮች ሁሉ የሚተገበር ሃሳብ መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

ነባሮቹ የሃይማኖትና የፍልስፍና የሥነ ምግባር ሊቃውንት (ethicists) “ስነ ምግባር የሰው ልጆች ብቻ መገለጫ ነው” የሚል ስህተት የፈጸሙት ስለ ተፈጥሮ የነበራቸው አመለካከት ጠባብና የተሳሳተ ስለነበረ ነው ይለናል፤ ኖርዌጅያኑ የአካባቢ ፈላስፋ አረን ኒአስ፡፡ ኒአስ በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ “ተፈጥሮ ለራሷ” (Deep ecology) በመባል የሚታወቀውን የአካባቢ እንክብካቤ ንቅናቄን ሲመሰርት በተፈጥሮ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት ዓላማ የሰውን ልጅ ፍላጎት ለማርካት ነው በሚል እምነት ላይ የተመሰረተውን የ“ተፈጥሮን ለሰው ልጅ” (Shallow ecology) አስተምህሮ ይቃወማል፡፡ የ “ተፈጥሮን ለሰው ልጅ” አስተምህሮ ከአንድ አምላክ አማኞች ማለትም ከአይሁድ፣ ከክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖት የስነ-ፍጥረት አስተምህሮት ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ይህም ሰው ፍላጎቱን ለማርካት ደን ቢመነጥር፣ እንስሳትን አርዶ ቢመገብ ወይም አካባቢን ቢበክል ከስነ ምግባር ውጪ እንደሆነ አይቆጠርም የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡

የ“ተፈጥሮ ለራሷ” ፍልስፍና በዓለማችን ላይ የሚገኙ ህይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው እንጂ የሰው ልጅ ፍላጎትን ለማሟላት አይደለም፤ ስለሆነም ለሰው ልጅ ፍላጎት በሚል በተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ዓይነት ብዝበዛ ከተሳሳተ “ሰው ተኮር” (anthropocentric) ምልከታ የመነጨና ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ይላሉ፤ ኒአስና ተከታዮቹ፡፡ “ሰው ተኮር ያልሆነ” (non-anthropocentric) የአካባቢ ስነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች የአካባቢ ተቆርቋሪዎች፣ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች እና የመሳሰሉትን መለያዎችን አንግበው መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራትን በመመስረት ለአካባቢ ስነ ምግባር መጠበቅ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ ክልሎች በአህዮች ደህንነት ዙሪያ በመስራት ላይ የሚገኘው “The Donkey Sanctuary” የተባለውና መቀመጫውን በእንግሊዝ ሃገር ያደረገው ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሀገራችን የእንስሳት መብት ተሟጋችነት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በእንስሳት መብት ተሟጋቾች እምነት እንስሳት እንደ ሰው የደስታ፣ የሃዘንና የስቃይ ስሜት እንዲሁም የራሳቸው የተፈጠሩበት ዓላማ ያላቸው በመሆኑ ሰው እንደ እቃ ሊቆጥራቸውና ያለአግባቡ ተገልግሎ ሊጥላቸው አይገባም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ በአህዮችና ጋሪ ፈረሶች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ስነምግባራዊ ብዝበዛ ለማስቆም በጎ ፈቃደኞቹ እንስሳቱ በጉብዝናቸው ወቅት ካቅማቸው በላይ እንዳይሰሩ፣ በህመማቸው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ጥረት መደረግ አለበት ይላሉ፡፡

ከእንስሳት መብት ባሻገር ስለ ተፈጥሯዊ አካባቢ ብክለትና መቆርቆዝ፣ እንዲሁም በዚህም ሳቢያ በሰው ልጆችና በሌሎች ፍጥረታት ላይ እየደረሰ ስለሚገኘው ጉዳት የስነምግባር ተጠያቂነትም ድምጻቸውን ያሰማሉ፤ የአካባቢ ስነምግባር ፈላስፎች፡፡ በሉላዊ የካርቦን-ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠን ማሻቀብ ሳቢያ በፕላኔታችን በምድርና በከባቢ አየሯ ላይ እየተፈጠረ ላለው የሙቀት መጨመር፣ የበረዶ መቅለጥ፣ የአካባቢ ብክለት፣ የመሬት መራቆትና ድርቅ የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ቀውሶች ሰለባ እየሆነ ያለው በጠቅላላው የዓለም ህዝብ ነው፡፡ በርግጥ የቀውሱ ምክንያት የሆኑት አካላት በሰው ተኮር አካባቢያዊ ፍልስፍና ተገፍተው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ዓለምን እየመሩ ያሉት ጥቂት የዓለማችን ሃገራት ናቸው፡፡ ይሁንና የችግሩ ሰለባዎች በኢንዱስትሪው ዓለምን እየመሩ የሚገኙ ሃገሮች ብቻ ሳይሆኑ ምንም ያላጠፉ በማደግ ላይ ያሉት ሀገሮችም ጭምር ናቸው፡፡ ይህም ከስነ ምግባር መርሆዎች አንጻር ኢፍትሃዊ ነው፡፡

በመሆኑም ለካርቦን-ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠንም ለየሃገሮቹ ውሱን ኮታ ሊሰጥና የበለጸጉት በካይ ሃገሮች ያለኃጢአታቸው የቀውሱ ሰለባ ለሆኑ ደሃ ሃገሮች ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚል አቋም ይዘውም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጉባዔዎችና አህጉራዊ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረው ቀጣይነት ያለው ልማት (sustainable Development) ስትራተጂና አፍሪካውያንን ወክለው ያቀረቡት የአየር ብክለት ካሳ ጥያቄ በዚህ የስነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች ጎራ ሊያስመድባቸው እንደሚችል የአረንጓዴው ኢኮኖሚ ሊቅ ሚካኤል ስትሬት (Michael Street) በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ ስነ ምግባር የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት ተግባቦታዊ ምልልስ ስኬታማ ከማድረግ ጀምሮ ወንጀል እንዳይስፋፋ፣ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ፣ ሀገር እንደ ሀገር እንዲቀጥል፣ ከዚህም አልፎ የአንድ ሃገር ህዝቦች ከሌላው ጋር መግባባት እንዲችሉና በአጠቃላይ በዓለም ህዝብ ዘንድ መከባበር፣ ሰላምና ፍቅር እንዲኖር የማድረግ አቅም ያለው የፍልስፍና ጥናት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ሀገር ልማት ላይ ስነ ምግባር ስለሚኖረው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ የልማት ስነ ምግባር (Developmental Ethics) ባለሙያዎች ያስተምራሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ራሞሴ ያሉ የድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካውያን ፈላስፎች፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ያደጉት ወይም የልዕለ ኃያላን ሀገሮች መንግስታት በስነ ምግባር መዝቀጥ በማደግ ላይ ለሚገኙት ሀገሮች የእድገት እንቅፋት መሆናቸውን አበክረው ይናገራሉ፡፡ ይህም በጦር መሳሪያ ሽያጭ፣ በኒውክለር ኃይል አጠቃቀም፣ በዓለም አቀፍ የልማት ብድርና እርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ በልዕለ ኃያላን ሀገሮች መንግስታትና እንደ (IMF, World Bank) ባሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አማካኝነት የሚፈጸም የስነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ በሶሪያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የበሽር አላሳድ መንግስትና የተቃዋሚዎቹን የእርስ በርስ ጦርነትን ለማብቃት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አወንታዊ ጣልቃ ገብነት ሩሲያ አጥብቃ መቃወሟ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ገቢዋ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን እንደማይቀር የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል “በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና” በኢራን መንግስት መካከል የተፈጠረው ከኒውክለር ኃይል ማብላላት ጋር የተገናኘው ፖለቲካዊ ውጥረት አንዱ መነሻ የስነ ምግባር አጀንዳ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ምንም እንኳን እንደ አሜሪካና ሩሲያ ያሉ የኒውክለር ባለቤቶች ከኒውክለር የጸዳች ሰላማዊ ዓለም የመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢደመጡም ራሳቸው የኒውክለር ጦር መሳሪያዎችን ሳያስወግዱ ሌሎች የማብላላት ፕሮግራማቸውን እንዲያቋርጡ መወትወታቸው ሁኔታውን ከፖለቲካ ወደ ስነምግባር ምህዳር አምጥቶታል፡፡ በኢራንና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ የዚህ እውነታ አንዱ ነጸብራቅ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ልትሰራ ላሰበችው ግድብና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ጠይቃ መከልከሏ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስነ ምግባር መዝቀጥ በታዳጊ ሃገሮች እድገት ላይ ምን ያህል ጫና እንደሚያሳርፍ በግልጽ ማሳየት የሚችል ሌላው ሃቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ በፖለቲካ፣ በጋዜጠኝነት፣ በህክምና፣ በንግድ፣ ሌሎች ሙያዎች ውስጥ አከራካሪ የሆኑ በርካታ የስነ ምግባር አጀንዳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከአድራጊው፣ ከአስደራጊው፣ ከአደራራጊው፣ ከማህበረሰቡ ባህላዊ እሴትና ከህግ እይታ አንጻር ትክክል ወይም ስህተት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በህክምና ሙያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱ የውርጃና የምህረት ግድያን (euthanasia) የመሳሰሉ አወዛጋቢ የስነ ምግባር ጥያቄዎች ለአንዱ ትክክል ሲሆኑ ለሌላው ደግሞ ስህተት ናቸው፡፡ በመሆኑም ግለሰቦች የሰዎችን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለው ከመፈረጃቸው በፊት እንዲሁም የስነ ምግባር ደንብ አርቃቂዎችና ህግ አውጪዎች ድንጋጌዎቻቸውን ከማወጃቸው በፊት፤ ወይም ሀገሮች በሌላው ሃገር ላይ ጣታቸውን ከማንሳታቸው በፊት በሰነዱ ላይ የተፈቀዱትን ወይም የተከለከሉትን ድርጊቶች በልዩ ልዩ የስነ ምግባር ፍልስፍና መነጽሮች መቃኘታቸውንና ፍትሃዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡


ፍቃዱ ቀነኒሳ

(በአዳማ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር)

33 views0 comments

Comments


bottom of page