የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ለጎንደር እና ለደባርቅ ሙስሊሞች ፍትህ መጠይቅ ጥላቻ መንዛት አይደለም! (በአቡ ዳውድ ኡስማን)

በጎንደር እና በደባርቅ በፅንፈኞች አማካኝነት በሙስሊሞች እና በመስጂዶች ላይ የተፈፀመው የተቀናጀ ጥቃትን አስመልክቶ በመላው አለም የሚገኙ ሙስሊም ኢትዬጵያውያን እና ስለእውነት የቆሙ ሰዎች ሁሉ እያወገዙት እና ፍትህ እንዲሰፍንም እየጠየቁ ይገኛሉ።
ሆኖም አንዳንዶች ፍትህ ለጎንደር ሙስሊሞች እየተባለ በጋራ ሲጠየቅ ሲመለከቱ አላማው ለጎንደር ተጎጁ ሙስሊሞች ፍትህ እንዲያገኙ ሳይሆን የጎንደር ከተማን ስም ለማጥፋት ነው፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ነው፣ በሙስሊሙ እና በክርስቲያኑ መካከል ግጭት ለማቀጣጠል ነው፣ የደም ነጋዴዎች ሆናችሁ ነው፣ የተከሰተውን ችግርም ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲስፋፋ በማሰብ ነው ይህን የምታደርጉት በማለት ሲወነጅሉን ይስተዋላል::
ለነዚህ ወገኖች ስለዘመቻው እውነታ አጭር ነጥብ እናስታውሳቸው:-
በቅድሚያ ሃገር ማለት በዋናነት ድንጋይ እና ተራራው ብቻ ማለት ሳይሆን በውስጧ ያሉት ህዝቦችም ናቸው:: ሀገሪቷ የጋራችን እና የሁላችንም እስከ ሆነች ድረስ አንዱ ሃገር አፍራሽ ሌላው ደግሞ ሃገሩን ጠባቂ በሚል ስላቅ ህዝቡን መከፋፈል ስህተት ነው::
በጎንደር እና በደባርቅ በፅንፈኞች የተፈፀመው ጭፍጨፋ እና ጥቃት በድንገት የተፈፀመ ጊዜያዊ ግጭት የፈጠረው ሳይሆን ታስቦበት እና ታቅዶበት፣ ጊዜ ተጠብቆለት፣ በሙስሊሙ ላይ የጥላቻ ሰበካ እስከ ጥግ ድረስ ተሰብኮበት ፣በከተማው አንዳንድ አመራሮች እና የፀጥታው ክፍል ጭምር መዋቅራዊ ድጋፍ የነበረው ጥቃት ነው::(ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ሃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ለእስር የተዳረጉ አመራሮች ማሳያ ናቸው)::
ይህ የተደራጀ ጥቃት ከተፈፀመ በኃላም ጥቃቱን በግልፅ ከማውገዝ ይልቅ አነስተኛ ግጭት በማለት ጉዳቱን በማሳነስ ለመሸፋፈን እና ከዛ ከፍ ሲልም ጥቃቱ የተፈፀመው በተጎጂው ሙስሊም ማህበረሰብ እንደተደረገ ተደርጎ ሲገለፅ ሰንብቷል::
የዚህ መሰሉ አደገኛ አካሄድ የጎንደር እና የደባርቅ ሙስሊሞች ፍትህ እንዳያገኙ ለማፈን በመሆኑ እውነታው ታውቆ ያለምንም መሸፋፈን ሁሉም ወንጀለኛ ለህግ እንዲቀርብ ሁላችንም ድምፃችንን እያሰማን እንገኛለን::
ይህን ያህል ከባድ ጥቃት በሙስሊሞች ላይ ተፈፅሞም በጥቃቱ ላይ የሌሉ ክርስቲያኖችን አጥቁ፣ እርምጃ ውሰዱ፣ሌላ አካባቢዎች ላይም መስል የበቀል እርምጃ ውሰዱ እየተባለ በሙስሊሙ መሪዎች እና አንቂዎች በኩል ቅስቀሳ አልተደረገም:: ሌላው ቀርቶ የጎንደር ሙስሊሞችን እንኳን ያጠቋቹን የበቀል እርምጃ ውሰዱባቸው የሚል ቅስቀሳ አልተደረገም:: ይልቁንም ሁሉም ንዴቱን እና ቁጣውን በመቆጣጠር መሰል ጥቃቶች ሌላ ቦታዎች እንዳይፈፀሙ ጥንቃቄ እንዲደረግ ነው ማሳሰቢያ ሲሰጥ የነበረው::
ሌላው መዘንጋት የሌለበት ነጥብ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጎንደሩን ጥቃት ተከትሎ በስልጤ ዞን በወራቤ የተፈፀመው ጥቃትም ለአንዱ ወንጀል ሌላው ተጠያቂ ማድረግ ኢስላማዊ መርህ ባለመሆኑ በተመሳሳይ ጥቃቱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ በግልፅ ተነግሯል::
የዞኑ አስተዳደር እና ህዝቡም ጥቃቱን ሳያድበሰብስ በማመን፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተ እምነቶች መልሶ በመገንባት እና ይህን የፈፀሙ ጥፋተኞችን ለህግ ለማቅረብ በተጨባጭ እርምጃ እየወሰደ እንደውም ድንበር ያለፈ እስር እየፈፀመ ይገኛል:: በጎንደርም የዚህ መሰሉ ተጠያቂነት እንዲኖር ነው ትግላችን!
አሁን ላይ በጎንደር ፍትህ ካልሰፈነ ፅንፈኞችም የልብ ልብ ይሰማቸዋል:: ብዝሃነትን በመቃወም ነገም ሌላ ጥፋት ማጥፋታቸው አይቀርም:: መንግስት ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ለማንም ያላዳላ፣ ማንንም ከተጠያቂነት የማያሳልፍ የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን አለበት::
ተጎጂዎች ፍትህን ይሻሉ! ገዳዮች በከተማው ላይ እየተጎማለሉ ሟቾች አፈር ለብሰው ተረስተው ሊቀሩ አይገባም! በመሆኑም ለጎንደር እና ለደባርቅ ሙስሊሞች የፍትህ ጥየቃው ዋና ማሳካት የሚፈልገው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው:-
በጎንደር እና በደባርቅ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት እውነታውን ማመን፣ ጥቃቱ በሁለቱ እምነት ተከታዮች መካከል የተከሰተ ተራ ግጭት ሳይሆን ጥፋቱ በሙስሊሞች ላይ በፅንፈኞች የተፈፀመ ፀረ ህዝብ ፍጅት መሆኑ እውቅና እንዲሰጠው ማድረግ
ለተፈፀመው የሽብር ጥቃት እና ጭፍጨፋ የከተማው አስተዳደር ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ ተጎጁውን ህዝበ ሙስሊሙን በግላጭ ይቅርታ መጠየቅ
በሽብር ጥቃቱ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች እና መሳጂዶች ፍትህ በማስፈን ካሳ እንዲከፈላቸው ማድረግ
በዚህ ፀረ ሙስሊም በሆነ የሽብር ጥቃት የተሳተፉ፣ ያስተባበሩ፣ ቀድሞውንም በስብከት ፀረ ሙስሊሞች ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ ሰባኪያን፣ ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፀጥታ እና የሲቪል አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም በከተማው ይህን ወንጀል በስፋት የፈፀሙ ፅንፈኛ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ
በጎንደርም ሆነ በሌላ ቦታዎች የሙስሊም ጥላቻን የሚሰብኩ፣ በሰላም ከሌላ እምነት ጋር መኖርን የማይቀበሉ ሰባካዎች እንዲቆሙ ማስደረግ ናቸው።
ከዚህ ውጭ ሌላ ምንም አጀንዳ የለንም! እነዚህ እንዲሳኩ መጠየቅ ግጭቱ ማባባስ ሳይሆን ዘላቂ ፍትህ እና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነው:: ይህን የፍትህ ጥያቄ በተቋም ደረጃ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ምክርቤት ፕሬዝደንት ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስን ጨምሮ የአማራ ክልል መጅሊስ ፣የጎንደር ከተማ መጅሊስ እና በመላው አለም የሚገኙ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ኮሚውኒቲዎች በይፋ በመግለጫ የጠየቁት ነው።
አቡ ዳውድ ኡስማን