top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ላንተ ገና ሩቅ ነው" (አህመዲን ጀበል)

Updated: May 22, 2021


ለእኩልነት መታገል አጀንዳ የሚሆነው እኩል ያለመሆን ሁኔታ ስለተፈጠረ ነው። እኩል ያለመሆን ደግሞ የሆነ አካል (አካላት) ከሌሎች የበለጠ፥ከፍ ያለና የተለየ ተጠቃሚነት ወይም እድል አግኝተዋል ማለት ነው።እንዲህ ባለው ሁኔታ እኩልነትን ለማስፈን ዝቅ ያለውን ከፍ ማድረግ ወይም ከፍያለውን ዝቅ ማድረግን ይጠይቃል። ከፍ ያለው ከፍ ካለበት ደረጃ ዝቅ እንዲል ሲጠየቅ ከለመደው ከፍታ መውረድ አለመፈለግ ብዙም የሚገርም አይደለም። ሆኖም ዝቅ ያለው ወደ እኩልነት ደረጃ ከፍ ይበል ሲባል የሚቃወምና ወደ ትንኮሳ የሚያመራ ከሆነ «ትናንት ያገኘሁትን ልዩ ተጠቃሚነቴንና የበላይነቴን ላስቀጥልበት ተዉኝ» እያለ ነው ማለት ነው።ይህ አካል አቋሙን ለዉጦ ወደ እኩልነትና ፍትህ መስመር እስካልተመለሰ ድረስ የበላይነቱን እስክትተዉለትና እስክትቀበለው ድረስ አይተዉህም።


«ፍትሃዊ ያልሆነ ስርዓት ሰፍኖ በቆየበት ሀገር የሕዝቦችን ችግሮች እኩልነት መነጽር ብቻ መፍታት ስለማይቻል ፍትሃዊነትን ማስፈን የግድ ነው» በሚባልበት ዘመን «እኩል መሆን አልፈልግም። የበላይነቴ ይጠበቅልኝ» ብሎ በግልጽ መቆም የሚያሳፍር ሆኗል። በመሆኑም ከዚህ አቋም አራማጆች መካከል ብልሆቹ «ይህን ፍላጎታችንን ግልጽ ካደረግን የሚያስተች፥ የሚያሳፍርና የሚያጋልጥ ስለሚሆን» በሚል እውነተኛ ፍላጎታቸውን ደብቀው የፍትህ፣የነጻነትና የእኩልነት ጠበቃ መስለው ይቀርባሉ። ዓላማቸውን የሚያረጋግጥ ስርዓትንና ፖሊሲን ለማስፈን ተደራጅተው አካሄዳቸውን በሚያማምሩ ቃላት አስዉበው ተቀባይነትን ለማግኘት ይሰራሉ። ዘመኑ የደረሰበትን ያልተረዱ፥ ወይንም ለመቀበል የሚተናነቃቸው እብሪተኞች ደግሞ ሰሞኑን እንደሚታየው ጭምር አቋማቸውንና ፍላጎታቸውን መሸፋፈንም ሆነ መደበቅም ሳያስፈልጋቸው በይፋ እስከ መናገር ይደርሳሉ።


ፍትሃዊነት ቀርቶ እኩልነት እንኳ ከማይዋጥላቸው፥ ትናንት በነበረው ስርዓት በኢፍትሃዊነት ያገኙትን የበላይነታቸውን የማስጠበቅ ጽኑ ፍላጎት ያላቸው በተቆጣጠሩት መንግስታዊ መዋቅርና ሚዲያዎች ተጠቅመው ከጭቆናው የቻሉትን«ሀሰተኛ ትርክት» የሚል ታፔላ በመለጠፍ ክደው፣ መካድ ያልቻሉትን ደግሞ ለሀገር አንድነትና ህልዉና ሲባል የተደረገና ዘመኑ ግድ ያለው ድርጊት እንደሆነ ምክንያት በመደርደር የትናንቱን ጫቋኝ ስርዓትን «መልካምና የሚናፈቅ ስርዓት» እንደሆነ አስመስለው በማቅረብ እንድትስማማላቸው ይተጋሉ። ይህን የማትቀበል ከሆነም በሚዲያዎቻቸውና በቅጥረኞቻቸው አማካኝነት በሀሰት እየወነጀሉና እየከሰሱህ አስደንብረው አፍህን ለማዘጋት ዘመቻ ይከፍቱብሃል። ይህም ካልተሳካላቸው ሴራ ይጎበጉኑልሃል።ከእነኚህ አካላት ጋር በመሞዳሞድ፣ በማደግደግና በልመና እኩልነትንም ሆነ ፍትሃዊነትን በተግባር ማረጋገጥ አትችልም።


የእኩልትና የፍትሃዊነት ጥያቄህን አዛብተው በማቅረብ ፍላጎትህንና ዓላማህን በማጠልሸት ጫናህን ሊያበዙ ቢችሉ እንኳን በሰላምና በፍትህ አብሮ ለመኖር እኩልነትንና ፍትሃዊነትን ከሚፈልጉት ጋር በመቆም «የበላይነቴን እንዳስቀጥልበት ተዉኝ» የሚሉት አካላት ከገቡበት ጥልቅ አዘቅት አውጥቶ ዘመኑ ወደ ደረሰበት ከፍታ እነርሱን ለማድረስ ከአስተሳሰብ መሰረታቸው፣ እስከ እይታዎቻቸው፣ ከርዕዮተ ዓለም እስከ አቋሞቻቸው በእውቀትና በጥበብ ከመታገል ዉጭ አማራጭ የለህም።


ኋላቀር አስተሳሰባቸውና ፍላጎታቸውን ለመታገል ይሉኝታ የሚይዘው፥ ወይንም የሚሸማቀቅ ካለ እርሱ አንድም ጭቆናውን ወዶ እንዲቀበል አድርገው የጨቆኑት፥ አልያም «አንችላቸውም» ብሎ እጅ የሰጠ፥ ለነርሱ በማጎንበስ «ቢራሩልኝ» ብሎ ተስፋ ያደረገ፥ ያለርሱ ሚና በሌሎች ትግል ዉጤት መጎናጸፍ የሚሻ አልያም «የባሰ አታምጣ» እያለ እጁን አጣምሮ ሚናውን ሳይወጣ ያለአንዳች አስተዋጽኦ ከፈጣሪ የሚጠብቅ ሊሆን ይችላል። ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፥የሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት፥ ፖለቲካ መብቶች፥ እኩል የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና ማህበራዊ መስኮችን ጨምሮ በሁለንተናዊ መልኩ ከእኩልነት ባሻገር ፍትሃዊነት በሀገርህ በተግባር እንዲሰፍን መታገልና ማስከበር ያንተ ትውልድ ሚና ነው። ይህን ማድረግ ካልቻልክ ሕዝባዊ መጅሊስ ፥ሙሉ የእምነት ነጻነት፥በነጻ የመደራጀት መብትና እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትህ ባንተ እጅ ሳይሆን በሌሎች ኪስ ዉስጥ እንደሆነ ስለሚቀጥል ሙሉ መብትህንና ነጻነትህን በተግባር መጎናጸፍ ላንተ ገና ሩቅ ነው።

34 views0 comments

Comments


bottom of page