top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“መማር ያስከብራል”ን ከዙፋኑ ማን አወረደው?


“መማር ያስከብራል”ን ከዙፋኑ ማን አወረደው?
“መማር ያስከብራል”ን ከዙፋኑ ማን አወረደው?

በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ፣ መስከረም 12 አብዛኛው የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፣ በወሩ የመጨረሻ ሳምንታት አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአዲሱን ትምህርት ዘመን መጀመር እንዲሁም በቅርቡ ይፋ የተደረገውን የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መነሻ በማድረግ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ መማር ያስከብራል?” ብላ በመጠየቅ ምላሹን ለማግኘት መጻሕፍትን በማገላበጥ፣ ምኁራንና ይመለከታቸዋል የተባሉ ኀላፊዎችንም በማነጋገር ርዕሱን የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጋዋለች።

የዘመናዊ ትምህርት ታሪካዊ ዳራ፣ የቀደመ የማኅበረሰባችን የትምህርት አመለካከት በጊዜ ሒደት ያሽቆለቆለበት አንድምታ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በትምህርት ስርዓቱ ላይ፣ የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው ምን ይዞ መጣ የሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮችም ተዳስሰዋል።

ለወራት ከዐይናችን የተሰወሩና እንደየትምህርት ቤታቸው ስርዓት ተመሳሳይ የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎች ከመስከረም 12 ጀምሮ መታየት ይጀምራሉ። በአዲስ ቦርሳ፣ የባዶ ገጾች ስብስብ የሆኑ ብዕር ያላረፈባቸውን ደብተሮች ሸክፈው፤ ለቀለም ትምህርት እንደ ባዶ ወረቀት ንጹሕ የሆነ አእምሯቸውን ይዘው የሚሔዱ አዳዲስ ተማሪ የሆኑ ሕፃናትም አዲስ የሚሆንባቸውን ዓለም የሚቀላቀሉት ከሰሞኑ ነው፤ ትምህርት ሊቀስሙ፣ ሊማሩ። ወላጅና አሳዳጊም ሳይታክት ባለው አቅም ሁሉ ልጁን ተማሪ ቤት ይልካል።

እርግጥ ነው! “ተማር ልጄ…ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው” የሚለው የአባት ምክር ከቃል አልፎ በሙዚቃ ተከሽኖ ትውልድ የተሻገረባት፣ “መማር ያስከብራል አገርን ያኮራል!” የሚለው ቃልም በዜማ ታጅቦ በዝማሬ ሲሰማ የቆየባት አገር ናት፤ ኢትዮጵያ። “የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም” ይሉት ብሂልም ከዚህ ዘርፍ ይካተታል። ትውልድ በተሻገሩ እነዚህ ምክር አዘል ሐሳቦች መካከል የተለየ ሐሳብ ይዞ የወጣ ትውልድ ደግሞ ተገኝቷል፤ “እውነት መማር ያስከብራል ወይ?” ብሎ የሚጠይቅ።

መማር ያስከብራል?

የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን ከአዲስ አበባ ርቆ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ነው የተማረው። ከሦስት ዓመታት የትምህርት ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2010 መጨረሻ ተቀብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አዲስ አበባ ሲመጣ ሁሉም በደስታ ተቀብለውታል። ከአንድ ወር በኋላ ግን ጥያቄዎች ጀመሩ፤ “ሥራ አላገኘህም?” ባዩ በዛ። ይህ ጥያቄ ወራትን ቆጥሮ ለዓመት ዘለቀ፤ አበራ ባዩ 3.4 ነጥብ በማምጣት በጥሩ ውጤት ትምህርቱን ያጠናቀቀ ቢሆንም ሥራ ለማግኘት ግን አንድ ዓመት ወስዶበታል፤ ሥራውም ቋሚ ሳይሆን የተለማማጅነት ዕድል ነው። “ለምን ተማርኩ ብዬ አማርሬ አውቃለሁ፤ በዩኒቨርስቲ ሳለን ከተመረቅኩ በኋላ ሥራ እንደማገኝ ነበር የማስበው።” ያለው አበራ፤ በአንድ ጎን ተምሮ የተመረቀበትን የትምህርት ዘርፍ መምረጡ በሌላ በኩል ‘ትምህርቱን ትቼ ነጋዴ በሆንኩ ኖሮ’ በሚል ቁጭት ብዙ ጊዜውን አሳልፏል። አበራ ጨምሮ እንዲህ አለ፤ “ሁሉም ሰው በመማር ሊፈታው የሚፈልገው የራሱ ችግር ይኖራል፤ ያንን ማድረግ አለመቻል ተስፋ ያስቆርጣል፤ ግዴለሽም ያደርጋል” ሲል በጊዜው ተሰምቶት የነበረውን ስሜት ይገልጻል። “ተምሮ ምን አመጣ? ከእርሱ እኔ ያልተማርኩት እሻላለሁ” የሚለው መብዛቱም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር አያይዞ ይጠቅሳል።

እንደ አበራ ያሉ እልፍ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሉ፣ “ትምህርት ምን ይሠራል? ድሮ እንጂ አሁን መማር ያስከብራል ብሎ ነገር የለም” ብለው ከማመን አልፎ ለማሳመን የሚከራከሩ። ይህ ሁሉ ግን መማር ምን ማለት እንደሆነ ካለመረዳት የመነጨ፤ በተዘዋዋሪም የትምህርት ሥርዓቱ ግድፈት እንደሆነ የሚናገሩት መሠረት አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥርዓተ ትምህርትና ኢንስትራክሽን ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የሚያገለግሉት መሠረት፤ “ትምህርት ማለት ቀጣይነት ባለው የሕይወት ዘመን የሚቀሰም እውቀት ነው። ደግሞም እውቀት፣ ክህሎትና እሴትን ያካትታል። ሦስቱ ነገሮች በማንኛውም የትምህርት ሒደት ውስጥ መካተት አለባቸው።” ሲሉ ያብራራሉ።

ምንም እንኳ ብዙ ሰው መማርን አብዝቶ የሚሻ ቢሆንም እሴትና ክህሎትን ሳይሆን ማወቅ ላይ ብቻ ያተከራሉ። ይህም ትምህርትን ከምሉዕነቱ የሚያጎድል ከመሆኑ ባሻገር ዲግሪ መጫን ወይም ዲፕሎማ ማግኘት የመማር አቻ ትርጓሜ ሆኖ እንዲቆጠር አድርጓል። መሰረት እንደሚሉት፤ የትምህርት ዓላማ በእውቀት ማበልጸግ ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባር ማነጽን፣ በክህሎት ማዳበር እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ማንነት ጋር ማተሳሰርን ይጨማራል። ይህ ሲሆን የትምህርት ምንነትና ጠቀሜታን መረዳት ይቻላል።“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሠራርን በተመለከተ ከሕንድ አገር የአመራር ባለሙያዎች መጥተው ነው ሥልጠና የሰጡት” ሲሉ ለምሳሌ የጠቀሱት መሠረት፤ በአገራችን በ52ቱም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማኔጅመንት (አመራርነት) እንደሚሰጥ ግን አያዘው አስታውሰዋል። ይህም የሚያሳየው ምንም እንኳን ትምህርቱ እየተሰጠ ቢሆንም ተገቢውን ያሟላ ባለመሆኑ አገልግሎት እየተሰጠበት እንዳልሆነ ነው።

ይሁንና ትምህርት በአግባቡ ሲተገበር መልካሙን ነገር ጥሩ አድርጎ ሊያስቀጥል፤ በአግባቡ ላልተጠቀሙበት ግን መጥፎውን የባሰ የሚያከፋ ይሆናል ብለዋል። የከፋ ጊዜ አጥፊ፣ ሙስና የተወዳጀውና ለአገሩ የማያስብ ዜጋን ይፈጥራል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚል ርዕስ እጓለ ገብረ ዮሐንስ በ1956 ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይ “ስለትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከሆነ ማናቸውም የሕይወት ችግር ሊፈታ ይችላል። ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። እንዲሁም ስለ ትምህርት የሚናገር ሰው ሦስት ጥያቄዎችን ለመመለስ መዘጋጀት አለበትም ይላሉ። እነዚህም ትምህርት ሲባል ምንድን ነው፤ ለምን ወይስ ምን ዓላማ ማገልገል ይገባዋል፤ በምን ዓይነት ዘዴ ሊከናወን ይችላል የሚሉ ናቸው። እጓለ፤ “የመጀመሪያዎቹ ኹለት ጥያቄዎች ሰው ምን መሆን እንደሚገባው እንመረምር ዘንድ ስለሚያሳስቡን በቀጥታ ወደ ሥነ ምግባር ፍልስፍና ሰፈር ይመሩናል።…በምን ዓይነት ዘዴ ሊከናወን ይችላል የሚለውን ጥያቄ በደንብ ለመመለስ ደግሞ ነገረ ነፍስ ወይም ሳይኮሎጂ የሚባለው የእውቀት ቅርንጫፍ ያስፈልጋል” ይላሉ። በአንጻሩ ይህን ሥርዓተ ትምህርቱም ሆነ ማኅበረሰቡ የተረዱት አይመስልም። መሠረት በበኩላቸውም ማኅበረሰቡ “የዲፕሎማ በሽታ” አለበት ባይ ናቸው። ቤተሰብ ልጄ ተመረቀ ይላል፤ ተማሪዎችም መመረቁ ላይ የሚያተኩሩትን ያህል ትምህርቱ ላይ አያተኩሩም። ሲማሩም ገና ለገና ስለሚያገኙት ደሞዝ በማሰብ ነው። “[በተመረቅሁበት ሙያ] ሠርቼ አገሬን አገለግላለሁ ከሚለው ይልቅ ቤትና መኪና እገዛለሁ የሚል አስተሳሰብ

ካለ ለትምህርት የሚሰጠው ግምትና አመለካከት የወደቀ ነው።” ሲሉም ገልጸውታል።

መሠረት ትምህርትን ከሀብትና ንግድ ጋር ማገናኘት ስህተት መሆኑን ነው የሚናገሩት። ትምህርት በራሱ ዋና እና መብራት ነው፤ ነጋዴውም ሆነ የተማረው በየሙያው ለአገራቸው ያበረክታሉ። እንደውም ትምህርት ነጋዴን ጥሩ የሚያደርግ ነው ይላሉ። ባይሆን “ሀብት ያለውና የተማረው ሰው በአንድ ተባብሮ ነው አገር የሚገነባው እንጂ ነጣጥሎ አይቻልም።” ብለዋል። ቀደም ብለን ከጠቀስነው መጽሐፍ ላይ እጓለ ዮሐንስ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥቱን ለትምህርት ቤትነት መስጠታቸውን በጠቀሱበት ምዕራፍ እንዲህ አሉ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታሪካዊ ዕድሉ ለመድረስ ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ትልቅነት በእጁ ለማድረግ በትምህርት እየተመራ ወደፊት ይጓዛል። ከዚህ ዓላማው ከሚያደርሱት መሣሪያዎች አንደኛው ትምህርት ነው። ኹለተኛው ትምህርት ነው ሦስተኛውም ትምህርት ነው።” እንዲህ ያለ እሳቤ ይነገር በነበረባት አገር ላይ በጊዜ ሒደት በተሸረሸረ ትኩረት ምክንያት ግን መማርና ትምህርት በሚዛኑ ክብደታቸው ቀንሶ ታይቷል።

ኢትዮጵያ እና ትምህርት

ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1874 እስከ 1983” በሚለው መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፤ የዘመናዊ ትምህርት ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዓመት ነው። በአንድ ጎን ሚስዮናውያን ሲጠቀሱ በተጓዳኝ አጼ ቴዎድሮስ በአውሮፓ ቴክኖሎጂ በተለይም በዚህ ቴክኖሎጂ ወታደራዊ ጥቅም ተማርከው ወጣት ኢትዮጵያውያን በእጅ ሙያ የሚሰለጥኑበትን ትምህርት ጋፋት ላይ ማቋቋማቸው ተጠቅሷል።

ይሁንና ዘመናዊ ትምህርት ለመስፋፋት የበለጠ አመቺ ሁኔታ የተፈጠረለት ከዐድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሔድ ነው። ከዚህ በኋላም መደበኛ ትምህርትን የተመለከተ ቀጣይ ወሳኝ የሚባል ድርጊት የነበረው በ1900 በንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ሥም ትምህርት ቤት መከፈቱ ነው። ባህሩ ዘውዴ በመጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፤ በጊዜው ተፈልጎ የነበረው ባሕላዊና ፈር ያልለቀቀ ሥልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ነበር።

የትምህርት ጉዳይ በሚመለከት ታድያ የአውሮፓውያኑ እጅ በብዛት የነበረ ቢሆንም ከኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ለማረጋገጥ የተለያዩ አስተዳደራዊ አካሔዶች ተደርገዋል። ይህም በሒደት በ1923 የትምህርት ሚኒስቴር ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት ሆኖ እንዲቋቋም አስችሏል። በተጨማሪ ሌሎች መዛግብት እንደሚያስረዱት፣ ትምህርትን የተመለከቱ መመሪያና አዋጆች በተለያየ ጊዜ ወጥተዋል። ከዚህም መካከል የመጀመሪያው የትምህርት አዋጅ በአፄ ምኒልክ በ1898 የወጣ ሲሆን፤ ንግሥት ዘውዲቱ በ1921 ያወጡት ዘመናዊ ትምህርት ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ተጣጥሞ እንዲሰጥና ልጅ ያለው ሁሉ ልጁን እንዲያስተምር የሚያስገድደው አዋጅ እዚሁ ላይ ተጠቃሽ ናቸው። በጊዜው በተለይም የአፄ ምኒልክን አዋጅ ጥቂት ዓመታት ተሻግሮ በ1912 ኧርነስት ወርክ የተባሉ ጥቁር አሜሪካዊ ፕሮፌሰር የአገር ውስጥ ሁኔታና ፍላጎትን እንዲሁም ለሙያ ሥልጠና ግምት የሰጠ የትምህርት ስርዓት ያስፈልጋል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተው እንደ ነበር አሁንም ታሪክ ያስረዳናል። ይሁንና በአፄ ምኒልክም ሆነ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተለያየ ምክንያት ሐሳባቸው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። በመካከል የተፈጠረው የጣልያን ወረራ እና የአምስት ዓመቱ ጦርነት ቀድሞ የተሔደውን እርምጃ ሁሉ እጥፍ ወደ ኋላ የመለሰ ነበር። እናም አፄ ኃይለ ሥላሴ ንግሥና ዘመን ይልቁንም ከድል በኋላ በ1934 ትምህርት ሚኒስቴር እንደገና ተቋቁሞ ከብሪታንያ በመጡ የትምህርት ባለሙያዎች የሚመራ ትምህርት በብሪታንያ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት መሰጠት ተጀምሯል። በ1945 ደግሞ የትምህርት አቅጣጫው ሙሉ በሙሉ በአሜሪካ የትምህርት ሥርዓት ተቀየረ። ይህም ስርዓት እንደጠለ በደርግ አስተዳደር በትምህርት ቤቶች የሶሻሊስት ፍልስፍና በማስተማር ተማሪው የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለምን እንዲቀበል የሚያስችል ትምህርት በቀጥታ ኮሶሻሊስት አገሮች ተቀዳ።

በኋላ አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጠው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በ1986 ወጣ። ይህ በኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወጣ ሊባል የሚችለው ፖሊሲ ከቀደሙት ተጽዕኖች ሙሉ ለሙሉ ነጻ እንዳልሆነ አገር በቀለ እውቀት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ምሁራን የሚናገሩት ነው። ቢሆንም ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደሆነም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ እንሰማለን።

ትምህርትና ፖለቲካ

ታሪክ ከሚነግረን ከዚህ እውነት በተጓዳኝ እንደ አገር ለቅኝ ገዢ የማትመቸው አገር ኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓትን ከተዋወቀችበት ጊዜ ጀምሮ ግን ትምህርት ስርዓቷን ነጻ ሳታደርገው ቆይታለች። ከዛም ሲሻገር ሥርዓተ ትምህርቷ ከውጪ አገራት ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውስጥ ፖለቲካ ጫናም ጸድቶ ያውቃል ብሎ ደፍሮ የሚናገር የለም። ባህሩ ዘውዴ በመጽሐፋቸው እንዳተቱት፤ ሥርዓተ ትምህርቱ መጀመሪያ ላይ በጣም የሚያስፈልጉት አስተርጓሚዎች ናቸው በሚል እሳቤ

ምክንያት የሚያደላው ወደ ቋንቋ ትምህርት ነበር። መጀመሪያ ፈረንሳይኛ፣ በኋላም እንግሊዘኛ ቋንቋዎች በጊዜው ሲያገለግሉ እንደነበርም በዚሁ መጽሐፍ ተገልጾ ይገኛል።

የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አንዷለም አድማሴ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ ቆይታ የትምህርት ስርዓት ከመንግሥት መለዋወጥ ጋር መገናኘት እንደሌለበት ተናግረዋል። መንግሥት ቢቀያየር እንኳን ዜጋንና ማኅበረሰቡን በአግባቡ ማገልገል የሚችልና የሚቀጥል የትምህርት ሥርዓት መኖር አለበት ይላሉ። የትምህርት ሥርዓት የፖለቲካ መሣሪያ መሆን የለበትም ሲሉ “በእገሌ ዘመን ወይም በእገሌ ስርዓት የተማሩ” የሚለውን በትምህርት መከፋፈልን አጥብቀው ይቃወማሉ። ይህን ሐሳብ ብዙዎች የሚስማማ ሆኖ ጣልቃ ገብነቱ እስከ ምን ድረስ ነው የሚለው ግን ሊነሳ ይችላል። የትኛውም መንግሥት ለአገርና ለሕዝብ የሚበጀውን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጉ አይቀርምና። ነገር ግን ያም ቢሆን የማኅበረሰቡን ፍላጎት እንዲሁም ማንነት መሠረት እንዲያደርግ ይጠበቅበታል። ከራሱ ድምጽ ይልቅ ከማኅበረሰቡን ድምጽ ማድመቅ ይኖርበታል። እዚህ ላይ ግን ቀድሞውንም ክፍተት እንደነበር እጓለ ዮሐንስ በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፤

“ሕዝባችን ምኞቱን፣ ተስፋውንና ናፍቆቱን መጓጓቱንም በጠቅላላው ከማናቸውም የምኞቱ አንቀጽ የሚደርስበት በትምህርት መሆኑን በመረዳት ልጆቹን፣ የልጅ ልጆቹን ለትምህርት አሰልፎአል። በዚህ በኩል የሚታየው የአገራችን ጥረት መጠን የለውም። እዚህ ላይ በተለይ ሕዝብ ከመንግሥት፣ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በአንድ ሊቀ መዘምራን እንደሚመራ የክላሲክ ሙዚቃ ኦርኬስትራ አባሎች የድምፃቸው መጠን ተባብሮ ተስማምቶ ይሰማል፤ ምንም እንኳን ለጊዜው የአንደኛው ድምጽ ማለትም የመንግሥት በጣም ጎልቶ ስለሚሰማ ጣዕመ ዜማውን ቢያዳክመውም።” ይህን ሁሉ ካነሳን ታድያ አሁንስ? ለትምህርት ያለው አመለካከት እንዲሻለው፣ በትምህርት ለውጥ እንዲመጣና መማር ያስከብራል ዳግም እንዲዘመር ምን ተደረገ? አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታስ ምን ይዟል? ከፖለቲካስ ነጻ ነው ወይ?

ስለ ትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው

የትምህርት ፍኖተ ካርታ በጥቅሉ የትምህርት ስርዓትን አቅጣጫ የሚያሳይ ጠቋሚ ነው። ዓላማውም በተሰጠው ጊዜ የሚፈለገው የሰው ኀይል በምን መልክ ተቀርጾ መውጣት አለበት የሚለውን እና ከኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ጋር የትምህርት ሥርዓቱን ማቀናጀት ነው። ይህን የነገሩን የትምህርት ፍኖተ ካርታው ዝግጅት ላይ በማስተባበር ከፍተኛ ድርሻን የተወጡት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ኀላፊ የዓለም ሎሬት ጥሩሰው ተፈራ (ፕሮፌሰር) ናቸው። “አሁን ያለው የትምህርት ሥርዓት ጊዜው ከሚጠብቀው ጋር አብሮ መቀየር ያለበት ነው፤ አግባብነትና ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግም ዝግጅቱ ተጀምሯል” ያሉት ጥሩሰው፤ ኢትዮጵያ ስትገለገልበት የቆየችው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ምክንያት ሆኖ ያስገኛቸው ብዙ ውጤቶች እንዳሉ ግን አንስተዋል። በተለይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በየአካባቢው በመክፈት እና መሰል ጉዳዮች ላይ የተሠሩትን ሥራዎች ጠቅሰው፤ ያም ሆኖ ትምህርቱ አግባብነት እና ጥራት አጠያያቂ ሆኖ ሰንብቷል ብለዋል። በተለይም የተማሪዎች ትምህርት መልቀቅ ያለበት ደረጃ ከፍተኛ መሆን፣ አራተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብ የማይችሉ ልጆች መኖራቸው፤ ብቃት ያላቸው ምሩቃን ቁጥር ማሽቆልቆልም ስርዓቱ እንዲለወጥ የሚጠይቁ ምክንያቶች ሆነዋል።

አንዷለም በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፉ ሲመራበት የቆየው ስርዓትና ፖሊሲ ያመጡት ውጤት እንዳለ ጠቅሰዋል። በተለይም በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ጥሩ የሚባል ቢሆንም አፈጻጸሙ ላይ ካልሰመረ ዋጋ እንደማይኖረው ተናግረው፤ የአፈጻጸም ችግርን ጨምሮ ከጊዜው ጋር አለመሔድ ሥራ ላይ የቆየው የትምህርት ሥርዓት እንከኖች ናቸው ብለዋል።

ጥሩሰው እንዳነሱት በተለይም አሁን የሚነሳውን የሥነ ምግባር ችግርም ታሳቢ ያደረገ ነው። ከጽንሰ ሐሳብ ተሻግሮ ተግባራዊ ትምህርት ላይ ያተኮረ፣ መዋዕለ ሕፃናትን እንደ አንደኛ ደረጃ ሁሉ በትኩረት ውስጥ የሚያስገባ ስርዓት በዚህ ፍኖተ ካርታ ታሳቢ ተደርጓል። “የፈለገው ግንባታ ቢሟላ፣ ቤተ ሙከራ እና ቤተ መጻሕፍት ቢገነባ መምህሩ ብቃትና ፍላጎት ያለው ካልሆነ ዋጋ የለውም፤ የሚያንቀሳቅሰው እሱ ነውና” ያሉት ጥሩሰው፤ ፍኖተ ካርታው የመምህርነት ሙያ ተፈላጊ እንዲሆን ማድረግንም ከግምት አስገብቷል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር ከቀደሙትና የውጪ አገራት ተጽዕኖ ከነበረባቸው የትምህርት ሥርዓቶች በተለየ አገር በቀል እውቀትን ለመጠቀምም የሚያስችል ነው። “በእደ ጥበብ፣ በሕግ፣ በጤና እና መሰል ጉዳዮች አገር በቀል እውቀት አለን። እነዚህ እውቀቶች በቅጡ ተጠንተው ወደ ስርዓተ ትምህርት የሚገቡበት መንገድ መፈለግ አለበት፤ ያ ሲሆን ከታች ጀምሮ መሰጠት ይችላል፤ ይህም በፍኖተ ካርታው ተካትቷል” ብለዋል፤ ጥሩሰው። ይህም አገርዊና ዓለማቀፋዊ እውቀት ያለው ሁለገብ ዜጋን ማፍራት የሚያስችል ነው።

በፍኖተ ካርታው ዙሪያ በነበሩ እንቅስቃሴዎች በአገር ዐቀፍ ኮሚቴ አባልነት ተሳትፎ ያደረጉት አንዷለም በበኩላቸው፤ ፍኖተ ካርታው ዘመን ተሻጋሪ ለውጥ ማሳየቱ አይቀሬ ነው ይላሉ። የትምህርት ሥርዓት አገር የመገንባትና የማፍረስ ያህል ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል።

“ስርዓተ ትምህርት ሲቀረጽ ዓላማው ምንድን ነው የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው፣ ይህም አግባብነት ይባላል። ዓላማው ከታወቀ ያንን መደገፍ የሚችል የትምህርት ሥርዓት ማዘጋጀትና አስፈጻሚ ተቋማትንም መለየት አያስቸግርም” የሚሉት አንዷለም፤ እውቀትን ከልምድ ያስተባበሩ ምሁራንና ሊቃውንት በዘርፉ በብዛት ስለሚገኙ ፖሊሲውን በአግባቡና በበቂ ሁኔታ ለመከለስ ያስችላል ብለዋል። በዚህ መሠረት 36 አጥኚ ምሁራን፣ 73 ረዳት አጥኚዎችና 15 ሺሕ ሰዎች የተሳተፉበት ቅድመ ጥናት ውጤትን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ሲሆን፣ ልጆች በሰባት ዓመታቸው ትምህርት ጀምረው በ18 ዓመታቸው ያጠናቅቃሉ። ቅድመ መደበኛ ለኹለት ዓመታት፣ አንደኛ ደረጃ ለስድስት ዓመታት፣ መለስተኛ ኹለተኛ ደረጃ ኹለት ዓመታት፣ እንዲሁም ከፍተኛ ኹለተኛ ደረጃ የአራት ዓመታት ቆይታ ይኖራቸዋል ተብሏል። የስድስተኛ ክፍል ክልል ዐቀፍ ፈተና፣ ስምንተኛ ብሔራዊ ፈተና እንዲሁም የዐሥረኛ ክፍል ፈተና ደግሞ እንዲቀር ይሆናል። በተመሳሳይም በፍኖተ ካርታው መሠረት ከቀረቡ 36 የሚደርሱ ነጥቦች መካከል በትምህርቱ ላይ ብቻ ሳይሆን አቅም ላይ መሠረት ያደረጉና የምገባ እንዲሁም ነጻ ትምህርትና መሰል ጉዳዮችም ተጠቅሰዋል። ፍኖተ ካርታው በውዝግቦች መካከል አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በተለያየ አቅጣጫ አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቷል። በጥቅሉ ለትምህርት ሥርዓቱም ሊያመጣ የሚችለውን በጎ ተጽዕኖ እንዲሁም እንደ አደራ እቃ ሳይነካ የቆየውን የትምህርት ፖሊሲ ለመለወጥ ቀዳሚው እርምጃ መሆኑን የሚናገሩም ጥቂቶቸ አይደሉም።

“የመምህር ልጅ ነኝ፤ ወላጅ አባቴ ከሠላሳ ዓመታት በላይ በመምህርነት አገልግሏል፣ እኔም በተመሳሳይ መምህር ነበርኩ” ያሉት አንዷለም ደግሞ በበኩላቸውም በእርሳቸው ጊዜ ላሉም ሆነ ለቀደሙት ለውጡ በእጅጉ የሚያስደስት እንደሆነ ነው ያስረዱት። በአንጻሩ ነጥቦችን እያነሱ ተቃውሞ ያሰሙ አልጠፉም። ለዚህም የቋንቋ ነገር በዋናነት የሚነሳ ሲሆን ሌሎች ነጥቦችም እንደየመስኩ መጠቀሳቸው አልቀረም።

መሠረት ፍኖተ ካርታው ጎላ ያለና ከቀደመው የተለየ የሚቀይረው ነገር አለ ብዬ አላምንም ብለዋል። ይህንንም ያሉት ፍኖተ ካርታው አቅጣጫ ማሳየቱ ብቻ ሳይሆን ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ጋር መቆራኘት ያለበት በመሆኑና ወሳኙ ሥራ የመምህር በመሆኑ ነው። በበኩላቸው ፍኖተ ካርታው ብዙ አቅጣጫ ይጠቁም እንጂ መምህራን ይህን ለመተግባር በሚያስችል አቋም ላይ ስለመሆናቸውና በመምህራንም የአመለካከት ለውጥ ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ። በንግግራቸውም “ከተማሪው ጋር የማይስተካከል መምህር በፍኖተ ካርታው የሚሰጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ ሊያደርገው ይችላል ብዬ አላምንም። ተርጓሚው መምህር ነውና የእነርሱ ነገር ተጨባጭ አይደለም፤ ወዴት እንደሚሔድና ምን እንደሆነ አያውቁትም። ይህም መሆኑ

ውጤታማ አያደርግም።” ሲሉ ነው የገለጹት። አያይዘውም ትምህርት ቤቶች ከአጥራቸው ወላጅም ሆነ ማኅበረሰቡ አልፎ እንዲገባ እንደማይፈቅዱት ሳይሆን ይህኛው ላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍና እንዲያውቀው መደረግ አለበት፣ ሁሉም “የእኔ ነው” የሚለው ሥርዓት ሲኖር፤ ለትምህርት ያለው አመለካከት እንዲታረም፣ በፍኖተ ካርታውም ለውጥ እንዲመጣ ያግዛል ባይ ናቸው። ሌላውና በፍኖተ ካርታው ተነስተዋል ከተባሉ ውዝግቦች መካከል ቋንቋን የተመለከተ አንዱ ነጥብ ነው። በዚህም የፌዴራል የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጥ የሚለው ሐሳብ ብዙ አጨቃጭቋል። በተለይ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት ተቃውሞው ላቅ ያለ ነበር። ይህንንም በተለያዩ ጋዜጣዊ መግለጫዎች አንጸባርቀዋል። ይህንንም ተከትሎ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ቋንቋን በተመለከተ ክልሎች የራሳቸውን ቋንቋ በአፍ መፍቻነት፤ የፈለጉትን አንድ ተጨማሪ ቋንቋ ደግሞ ጨምረው እንዲያስተማሩ ፍኖተ ካርታው እንደሚፈቅድ ጠቅሰዋል። ምንም እንኳ ይህ አስተያየት ከአንዱ መግለጫ ወደ ሌላው መግለጫ ልዩነት የታየበት ቢሆንም፤ የፌድራል የሥራ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጥ የሚለው የፍኖተ ካርታው ምክረ ሐሳብ ነው የሚለው በትክክል ጎልቶ መሰማት ችሏል። መፍትሔ ይህም ሁሉ ሆኖ እስካሁን አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የተቃወመ አልተሰማም። እንደውም የትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርጓል የተባለው የቀደመው አሠራር መቀየሩን እየተቃወሙ አዲሱን የተቀበሉት አሉ። ይሁንና ምንም እንኳ ፍኖተ ካርታው ሙያው ላይ ባሉ ምሁራን የተዘጋጀ፣ ለበርካታ ዓመታት የተደረገን ጥናት መሠረት ያደረገ ቢሆንም አሁንም ፖለቲካ የሙጥኝ ያለው ይመስላል። ወይም ብዙዎች ከወቅታዊ ፖለቲካ ጋር እያስተሳሰሩት ይመስላል። ለዚህ ማሳያው አንድም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “የትምህርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታው ኢትዮጵያ የምትመራበትን የፌደራሊዝም ሥርዓት በምንም መንገድ አያፈርስም፤ ይህንን የማድረግ አቅም የለውም” ብሎ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ጥያቄ መነሳቱ ነው። ይህንን እና ፍኖተ ካርታው ወደ ታች በማውረድ በኩል የታሰቡ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ከተቃውሞዎች ጀምሮ ፈታኝ ጉዳዮች እንደሚኖሩ ሎሬት ጥሩሰው እንዲሁም አንዷለም በተመሳሳይ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ጥሩሰው በበኩላቸው ከመንግሥት መዋቅር መስተካከል ጀምሮ አቅም ግንባታም ያስፈልጋል ብለዋል። የፖለቲካ አመራር ቅንነትና የትምህርት አቅጣጫውን ተግባራዊ የሚያደርግ አቅም ያለው አካል መመደብ እንደሚስፈልግም አሳስበዋል። በየደረጃው ያሉ ሰዎችን ካድሬ ሳይሆን ባለሙያዎች እንዲሆኑ በማድረግም የመንግሥት ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከዚህ በተረፈ የገንዘብ አቅም ጥያቄ እንዳለ አውስተው አሁን ለትምህርት ወጪ ከሚደረገው 23 በመቶ በጀት በተጨማሪ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ገቢዎችን ማግኘት አስፈላጊ እንደሚሆንና ከመንግሥት ቋት ብቻ መፈለግ የለበትም ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። አንዷለም በተመሳሳይ ይኖራሉ የሚባሉ ተግዳሮቶችን የጠቀሱ ሲሆን፤ ሁሉም ግን በቁርጠኝነትና ኀላፊነትን በመውሰድ ከሠራ ሁሉም ቀላል እንደሚሆን ጠቅሰዋል። የፋይናንስ ችግሩን በተመለከተ ከትምህርት ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ተቋማትን የልማት ድርጅት እንዲሆኑ በማድረግ፤ ዘርፉን ከበጀት ማላቀቅም የሚቻልበት መንገድ አለ ሲሉ ሐሳብ አቅርበዋል።

በ2013 ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው አዲሱ ፍኖተ ካርታ በአገር ህልውና፣ በተማሪዎች የነገ ማንነትና በብዙዎች የዛሬ ሕይወት ላይ የሚወስነው ትምህርት፣ ዳግም ያስከብራል እንዲባል አሁንም ብዙ መሠራት ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ ግን ሳይታለም የተፈታ ነው። “እንደተባለው ይህ ተግባራዊ ከሆነ…” አለ አበራ፤ “አዲስ ለሚገቡት ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ የተሻለ ነገር ይዘው እንዲወጡም ያስችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔ በበኩሌ ግን በዚህ ቀጥሎ መማር ይቆየኝ ብያለሁ”

ምንጭ - አዲስ ማለዳ

23 views0 comments

Comments


bottom of page