top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

መብለጥ ወይም መሻል በደል አይደለም! (በኢዱና አህመድ ኡስማን)

Updated: Sep 22, 2020


መብለጥ ወይም መሻል በደል አይደለም! (በኢዱና አህመድ ኡስማን)

ወዳጃችን “ዮሴፍ ገብሬ” ሆይ ዛሬ ላይ የሰውልጅ በመልካም ተጽኖ ፈጣሪ መሆን ሲጀምር የግንዛቤ እጥረት ያለባቸው እና እኩይ መንፈስ የተጠናወታቸው መታመም ይጀምራሉ። እኛ… እያለን እርሱ! ያ… ከወዲያ እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ይንፈራገጣሉ። በመልካም ተጽኖ ስር የሆኑ ሁሉ በላጩን በመልካም ከመከተል እና ከማድነቅ ውጪ አማራጭ እንደማይኖራቸው እሙን ቢሆንም እነዚያኛዎቹ… መበለጥን ሰለማይሹና ስለሚያማቸው እንዳማራጭ የሚወስዱት ላቅ ያለውን ማጥላላትና ስም ማጥፋት ብቻ ይሆናል። እባክህን ወዳጄ በላቸው… “ድመት ርቆ ተንጠልጥሎ የሚታይ ስጋን ታጥላላለች! አትደርስበትምና”

“አቅም ማወቅ በጣም ጥሩ ታላቅ ችሎታ ነው” ብሎ ነበር… ተወዳጁና አንጋፋው አርቲስት ጋሼ ማህሙድ:: የሰው ልጅን ፈጣሪ ሲፈጥረው ሁሉንም በእኩል አድርጎ ነው። ወይም ሁላችንም የአደምና የሃዋ ልጆች ነን። ቢሆንም ሰው እንደ አካባቢው፣ አስተዳደጉ እንዲሁም ፍላጎቱ አንጻር የኑሮ ደረጃው እና የማሰብ አቅሙ ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን አመለካከትና የኑሮ ደረጃ እኩል አለመሆንን አምኖ ለተቀበለው ህይወቱን በደስታ መምራት ሲቻለው መበለጥን አምኖ የማይቀበለው ደግሞ በህይወቱ ደስተኛ ካለመሆኑ ባሻገር የሌላውን ህይወት ለማጨለምና ደስታውን ለማደፍረስ ሰርክ ጉድጓድ ሲቆፍር ይኖራል።

መብለጥ ወይም መሻል በራሱ በደል አይደለም። መበለጥም እንደዚሁ! እናንተ... ዘረ አዳም-ሄዋን ሆይ... የኑሮ ደረጃችሁን አምናችሁ ተቀብላችሁ ህይወታችሁን በእርጋታና በሰከነ መንፈስ ልትመሯት ይገባል። ወደድንም ጠላንም እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ የሰው ልጅ የኑሮ ሁኔታ እና አቅም እንደተለያየ ነው የሚቆየው። ታዲያ… የእኛ እጣ ፈንታ በላቡ የሚያድር ሰራተኛ መሆን ከሆነ አሰሪን ወይም አለቃን ከመታዘዝ ውጪ አማራጭ አይኖርም። አላስተዋልነው ይሆናል እንጂ “ለበለጠው የበለጠ አለበት” ወይም ይኖርበታል። ማክበር፣ ደህናን መከተል እና መታዘዝ መሰልጠን መሆኑ ልንረዳው ይገባል። የተሻለና ደህና ካለን መልካም ነው። ከሌለን ደግሞ መበደል አይደለምና የተሻለ ያለውን መከተሉና መታዘዙ የግድ ይለናል።

ወዳጃችን “ዮሴፍ ገብሬ” ሆይ በርካታ በጎ ተግባራትን ሰለ መፈጸምህ መላው የሃገራችን ህዝቦች የሚያውቁት ጉዳይ ነው። በደል ሰለ መፈጸምህ ግን ምንም የምናውቀው ጉዳይ የለም። የአለማቱ ጌታ የሆነው ፈጣሪያችን፣ አንተ እና ተበዳይ ነኝ ባይ ብቻ የምታውቁት ጉዳይ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በድለህ ከሆነ ለተበዳይ እንድትክስ ይሁን! ተበድለህ ከሆነ ደግሞ በዳይ ይካስህ። ነገር ግን ፈጽሞውን ቢሆን የከፍታ ጉዞህን የሚገታ ሰንቃራ ሃሳብ መፈጠር የለበትም! ከፍ…ከፍ ከፍ በል! አመል ሆኖባቸው መንጫጫት ከጀመሩ “ጉራጌ ለስራ እንጂ ለአሉባልታ ጊዜና ቦታ የለውም” ብለህ ንገራቸው።

ኢዱና አህመድ ኡስማን

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

89 views0 comments

Comments


bottom of page