top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

መገን የኔ ነገር ሰሞኑን በተከታታይ በ360 የተጀመረብኝ የስም ማጥፋት ዘመቻ

Updated: Oct 10, 2020ለረጅም ጊዜ ካሰብኩበት በኋላ ከማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ ራሴን ለማቀብ እየተንደረደርኩ ባለሁበት ሳምንት እኔን አጀንዳ ያደረጉ ሰዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚፈጥሯቸውን ብዠታዎች ንቆ ማለፍና ከማህበራዊ ሚዲያ ራሴን የማቀብ ፕሮግራሜን ልቀጥል ወይስ መልስ ያስፈልጋቸዋል? እያልኩ ስወዛገብ ነበር፡፡


ለማንኛውም በአጭር በአጭሩ ራሴን ለታዳሚዎቼ ላስተዋውቅ


የትውልድ ቦታና ማንነት


የተወለድኩትም፣ እስከ 12ኛ ክፍል የተማርኩት ደቡብ ወሎ ቦረና በእነ አባባ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሸኽ ዑመር እንድሪስ አገር፣ እነ ዋለልኝ መኮነን ቀዮ፣ እነ ፕሮፌሰር አሰፋ እንደሻው መንደር –በሸኽ ደባት ቀጠና፣ አራዳ በተባለው የመካነሰላም ሰፈር ነው፡፡


የብሔር ኦሬንቴሺኔ ወሎየነት ነው፡፡ ወሎየነትን የመረጥኩት በብሔር ውህድ፣ በሃይማኖት ዋዠራ፣ ሰውነት የተባለን ማንነት በትቂቱም ቢሆን ስላሟላልኝ ነው፡፡ አማራነት፣ አረብነት፣ ኦሮሞነት…..ወዘተ በደሜ መኖራቸውን አረጋግጫለሁ (ዘር ከሆኑ?)፣ ኢትዮጵያ የዘመናት የብሄር ብሄረሰቦች ተዋስኦ ውጤት ናት የሚለውን አስረግጨ ስለማምን የበርካታ ነገዶችና ዘሮች ውጤት ነኝና ራሴን ኢትዮጵያዊ ብየ ነው የምገልጸው፡፡ የተለየ የብሄር ወገንተኝነት ተሰላቢ አይደለሁም፡፡


ለኦሮሞውና ለአማራው ያለኝ ቅርበት በተመሳሳይ ደረጃ የሆነብኝ ፣ ጋምቤላውን በርታውን ከትግሬውና አማራው አሊያም ከስልጤው የተለየ አድርጌ የማልወስድ፣ በታሪክ አጋጣሚ ባገኙት አድል ብቻ የተለያዩ አድርጌ የማምን የየትኛውም ወገንተኛ ያልሆንኩ ነኝ፡፡


ወሎን በተመለከተ ያለኝ የማይናወጥ አቋም ወሎ የወሎየዎች ስሪት ነው፣ ወሎየነት ውህድነት ነው ብየ የማምን፣ በሃይማኖት ወለተኪዳን አህመድን የያዘ፣ በብሄር ካሳ በጣሶን ያቀፈ፣ የአማራ ውጥን፣ የኦሮሞ ማማ፣ የዶባ የአርጎባ ጌጥ፣ የአፋር የሽዋ ሱልጧኔት ነጸብራቅ፣ የየአገዎቹ የስልጣኔ ማማ፣ የሮሐ ላልይበላ ተዐምር፣ የሶሎሞናውያን ሚንበር፣ የማመዶች ልዕልና፣ የየጁዎቹ ካስማ፣ የበላይ ዘለቀ የእትብት መቀበሪያ፣ የዋለልኝ መኮንን የብርሃነ መስቀል መዘውር፣ የአምስቱ ቅኝቶች ባለቤት፣ የጊሸን የተድባባ ማርያም ድንቅ ታሪክ ፤ የሾንኬ፣ የአና የዳንይ፣ የጌታው ቦረንይ ምድር፣ የ ጫሌ የደባት ጣላያን ጽዩፍነት ገድል ምድር መሆኗን የማምን ነኝና ወሎ ከቻለ ራሱን ችሎ ክልል ቢሆን የምመኝ ካልቻለ ደግሞ የአማራም ሆነ የኦሮሞ ተለጣፊና ተቀጥላ ወይም የቅርምት የውጊያ ምድር ፈጽሞ መሆን እንደሌለበት የማምንና የምገልጽ ወሎየ ነኝ፡፡ እርግጥነው የአጼ ፋሲል ስምንተኛ ትውልድ፣ የወሎ አሊቤት፣ የቦረና ቱለማዎችና የአማራ ሳይንት ውላጅ ነኝ፣ አለፍ ብየ ከቆጠርኩም የነቢዩ ሙሐመድ 52ኛ ትውልድ ነህ ተብያለሁ(በመወለድ መዳንና ትልቅነት የለምንጅ!)።


በሃይማኖቴ ሙስሊም ብቻ ነኝ፡፡ እርግጥነው ለቁጥር የሚያታክቱ መሻኢኾች ትውልድ በመሆኔ እውቀታቸውን ባይሆንም አሻራቸውን በውስጤ አየዋለሁ፡፡ በሱፊያው ትራድሽን ውሥጥ ያደግኩ ነኝ። አባቴ በሱፍያ የቃድሪያ ጦሪቃን በኋላም የሰለፊያ አስተምህሮን አዋህደው የዘለቁ በመሆናቸው እኔንም የቀረጹኝ በዚያው አውድ ነው፡፡ በደሴ የጦልሃ መርከዝ፣ በመካነሰላም መርከዘ ሱና እና በዋነነትም በሸኽ ዙበይር አብዱልመጅድና በኋላም በራሴ ንባብና ተሞክሮ ልክ ለየትኛውም የእስልምና ሴክት ጭፍን ተከታይ ያልሆንኩ ከሁሉም ይመቸኛል፣ ያዋጣኛል፣ ይጠቅመኛል ብየ ያሰብኩትን የምወስድ በመሆኔ የዚህ መስመር ተከታይ ነኝ ብየ ራሴን ለመግለጽ ይቸግረኛል ይልቁንም ሙስሊም ብቻ በሚለው ላይ መገኘት የምሻ አንድ ሰው ነኝ፡፡


እንደኔ ላለው ተራ ሙስሊም የሱፊ፣ ሰለፊ፣ ኢኽዋን፣ ጂኒ ቁልቋል ክርክር፣ ፍልስፍና፣ አሰላለፍ ፈጽሞ የማይጠቅምና (irrelevant and rubbish) ነው ብየ ስለማምን በነዚህ ቡድኖች ታቅፈው ያልበላኝ ሊያኩልኝ ከሚሞክሩ ወገኖች ጋር ጠብም ሆነ የተለየ ፍቅር የለኝም፡፡ ለኢትዮጵያ ሙስሊም አንድነት የማይጠቅም የትቂት ምሁራኖች የቅንጦት መድረክ ሁሉ ነው የሚመስሉኝ፡፡


ስለዚህ ማንነቴ ሲጠቃለል ወሎዮ፣ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የሆንኩ ሰው ነኝ፡፡


የትምህርት ደረጃ


ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪ በኢኮኖሚክስ (በማእረግ)፣ ማስተርስ ድግሪ በዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ (በከፍተኛ ማእረግ)፣ ማስተርስ ድግሪ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ በጣልያን አገር ብሬሽያ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄያለሁ።


የማህበራትና ፓርቲ አባልነት


በግል ሥራ የምተዳደር ስሆን ቀድሞ በመንግሥት ቢሮክራሲው በቂ ልምድ ያለኝ፣ እድል ሆኖ የፌደራል ተቋማትን፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጭብጥ በቅርበት መረዳት የቻልኩ፣ በትምህርት ዝግጅቴም የምኮራበት ውጤት የነበረኝ (ሁለት ማስተርስ ድግሪ የተቀበልኩ)፣ ባነበብኩትና ባወቅኩት ልክ ለአገር ለወገን ይጠቅማል ያልኩትን በተለያዩ ሚዲያዎች፣ በመጽሀፍት ያለችን ለመሰንዘር ችግር የለብኝም፡፡


ቀድሞ ለተወሰነ ጊዜ ከ(2001-2004) የኢህአዴግ ተራ በመስሪያ ቤት ደረጃ አባል የነበርኩ ግና ኢህአዴግን በብዙ ጉዳዮች ጠንቅቄ ሳውቀውና ከህሌናዮ ጋር እንደማይስማማኝ ወይም እኔና ኢህአዴግ አልተገናኝቶ ሲሆንብኝ በፈቃዴ ድርጅቱን በ2004 የለቀቅኩ ሲሆን በአሁኑ ስዓት የየትኛውም ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ የየትኛውም ማህበር (የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ግልጋሎት) አባል ያልሆንኩ ነኝ፡፡


በህዝበ ሙስሊሙ ማህበራት፣ የመጅሊስ አደረጃጀትና ኮሚቴዎች ወዘተ የየትኛውም ማህበርና ኮሚቴ አባል አይደለሁም፡፡


ግለሰባዊ አቋም


ፖለቲካ፡- ኢትዮጵያ በድንበሯና በወሰኗ የተካለሉ ህዝቦች፣ ነገዶች፣ ብሄሮች ሁሉ እኩል አገር ናት ፣ መሆን አለባትም ብየ የማምን፣ ኢትዮጵያ የተባለች አገረ መንግሥትን በመገንባት ሂደት ሁሉም ህዝቦች ድርሻ አላቸው ብየ የማምን፣ ኢማም አህመድ የወከለው የሙስሊም ሱልጧኔትና አጼ ምኒሊክ የሚወክሉት ክርስቲያናዊ የሶሎሞናዊ ስርዎ መንግሥት ኢትዮጵያ ወይም ሀበሻ የተባለች አገርን በመገንባት ትልቅ ሚናና ገድል የሰሩ ናቸው ብየ የማምን። በዋናነትም የሙስሊሙና የኦርቶዶክሱ ሚና እጅግ የላቀ ነበር ብየ የማምን።


በሀገረ መንግሥት ግንባታው የተፈጸሙ ስህተቶች መኖራቸውን (በኢማም አህመድም ሆነ በአጼ ምኒሊክ አሰላለፍ) ተቀብዮ እነዚህ ስህተቶች ዛሬና ነገ የኢትዮጵያን ኔሽን ቢልድ በማድረግ ሂደት ይታረቃሉ፣ ይስተካከላሉ ብየ የማምን፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ከመሆን ውጭ የአንድኛችን ብቻ የመሆን ፍጹም እና ኢምንታዊ እድል እንኳ የላትም ብየ የማምን፡፡ የኢትዮጵያ ታሪኳ እና መልኳ በሃይማኖትም ሆነ በጎሳ የሁሉም ህዝቦቿ ታሪክና መልክ ነው ብየ የማምን፡፡


በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ስህተቶችን ተቀብለንና አርመን በቀጣይ እንዳይደገሙ ከመስራት ያለፈ ለቂምና ካሳ መዋል የለባቸውም ብየ የማምን፣ በታሪክ አጋጣሚ የተደረጉ መልካም ስኬቶች ደግሞ ተሞክሯቸው ተቀምሮ መቀጠል አለባቸው ብየ የማምን ነኝ፡፡ በጠቅላላው ኢትዮጵያ የሁሉም፣ ስለሁሉም፣ በሁሉም፣ ከሁሉም የሆነች አገር ብቻ ናት ብየ የማምን ነኝ፡፡


ኢትዮጵያ የሶስቱ (የአማራ፣ የኦሮሞና ትግሬ) የፖለቲካ ውጊያ አውድማ ብቻ ሆና ትዘልቅ ዘንድ የማያስደስተኝ፣ የነሱ የሽኩቻ መድረክ ብቻ መበየኗም የሚያበሳጨኝ፣ የየትኛውም ጽንፍ የነካ ብሄርተኝነት እና መዘዙ የሚያሳስበኝ የሚያስቆዝመኝ፣ የየትኛውም የልሙጥ አሃዳዊነት ጽንፍ እንቅልፍ የሚያሳጣኝ፣ በዋናነት በቁጥርም የሁን በሚና የውህዳን የማይኖሪቲ ወይም የተጨፍላቂዎች ልሳን መሆን የሚዳዳኝ አይነት ሰው ነኝ፡፡


ሐይማኖት፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ማለት በኢትዮጵያ ወሰን ውሥጥ የሚኖሩ የየትኛውም የእስልምና አስተምህሮ (ሴክት) ተከታዮች የሆኑ ሁሉ ናቸው ብየ አምናለሁ፡፡


በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስም የተቋቋመ ተቋም፣ ማህበር፣ ኮሚቴ ወዘተ ሁሉ የነዚህ ሙስሊሞች ሀቅ ነው ብየ የማምን በመሆኑ በፊርቃና በዘር የተደራጀ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ስም የተመሰረተ ወይም የተደራጀ ተቋምም ሆነ ማህበር ህገ-ወጥ ነው ብየ አምናለሁ። ስለዚህም በዘርና በፊርቃ ኮታ ወይም አሰላለፍ የተደራጀ የሙስሊሞች ተቋምም ሆነ ማህበር አባልም ደጋፊም አይደለሁም።


በመጅሊሱ አደረጃጀትና አፈጻጸም ላይ ቋጥኝ የሚያካክሉ ጥያቄዎች ያሉኝ፣ በህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ እንደዚሁ ጫን ጫን የሚሉ ጥያቄዎችና ልዩነት ያሉኝ፣ በድህረ 2004 የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ እኔና አላህ ብቻ የምናውቀው ሚና ያለኝ፣ በራሱ በድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሂስና ተቃውሞ ያለኝ፣ የድምጻችን ይሰማን እንቅስቃሴ ተቃውመውም ሆነ ለእርማት በሄዱ ግለሰቦችም ሆነ በኋላ ላይ በአንጃነት በተደራጀው ቡድን ላይ ዘለግ ያለ ጥያቄዎች ያሉኝ፣ በዲያስፖራው ሙስሊም ጋር ብዙም ግንኙነትና መረጃ የሌለኝ ከሁሉም ያልተጣላሁ ከሁሉም ተለጣፊና ጭፍን ተከታይ ያልሆንኩ የማንም ያልሆንኩ የኔ ብቻ የሆነኩ አንድ ተራ ሙሰማ ሙስሊም ነኝ፡፡


የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከዘርና ከሴክት አሰላለፍ በጸዳ መልኩ ተደራጅተው፣ በተቋማት አብበው፣ በሚዲያ ተጠናክረው፣ በመንፈስ በልጽገው በሀገሪቱ የሚገባቸውን ምክንያታዊ ድርሻ (ፌይር ሸር) ለማረጋገጥ የሚጥሩ፣ ሀገሪቱ ከነሱ የምትጠብቅባቸውን ሁሉ የሚዎጡ፣ ቅሬታዎቻቸውን በሠላማዊና በሠላማዊ መንገድ ብቻ ማረጋገጥ አለባቸው ብየ የማምን ተራ አማኝ ነኝ፡፡


የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በታሪክ፣ በአኗኗር፣ በአንድት አገር ልጅነት፣ በኢኮኖሚ፣ በዴሞግራፊና ሶሺዮሎጂካል ውህደት ከሌላው የሃይማኖት ተከታይ ጋር በተለይም ከክርስቲያኑ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኘው፣ የሚያዛምደው፣ የሚያዋህደው መሰረተ ጉዳይ፣ በጥልቀትም፣ በብዛት፣ በዓይነትም እጅግ የበዛና የጠነከረ ነው ብየ የማምን።


ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የአማኞች የአጋርነት ዋልታ ያስፈልጋቸዋል ብየ የማምንና የምሰብክ፣ የአማኞች ዋልታ ስል በመወያየት፣ በሰጥቶ መቀበል፣ በዊን ዊን፣ በመከባበር፣ በመተዋወቅ፣ በመቻቻልና መገነዛዘብ አልፎም ከጣልቃ ገብነት፣ ከመናናቅ፣ መንፈሳዊነት ከራቀው ፉክክር፣ ከስነልቦናና ከሪሶርስ የበላይነት ሽሚያ፣ ከቢሮክራሲ ሞኖፖላዊ ሽኩቻ፣ ከስም መጠፋፋት፣ ከመካሰስና ከመጠቋቆም የፀዳ በመርህ ላይ ፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ፣ በጋራ ልማትና ሰላም አጀንዳዎች ላይ፣ በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ ልንሰራባቸው የሚያስቸኩሉን፣ በጋራ ልንቆም ግድ የሚለን፣ ከመበታተንና ከመኮራረፍ የሚታደገን የጋራ የትብብር የአንድነት ዋልታ ማለቴ ነው።


ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ የሁላችንም ከመሆን ውጭ አማራጭ የላትም። የአንድኛችን ብቻ ልትሆን የምትችልበት ኢምንት እድል የላትም። አገሪቱ ለሁላችንም የምትበቃ መሆኑም አያጠያይቅም። በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ያለው ዘላቂ አንድነትና ትብብር በነጠሩ መርሆዎች ላይ የቆመም ሊሆን ይገባዋል። በአገር ባለቤትነት አንዱ ባለቤት ሌላው እንግዳ፣ አንዱ ነባር ሌላው መጤ፣ አንዱ ባለ ታሪክ ሌላው ታሪክ አልባ፣ አንዱ ባለሚና ሌላው ሚና አልባ፣ አንዱ አስጠጊ ሌላው ተጠጊ፣ አንዱ ሀገር ሌላው ክፍለ–ሀገር፣ አንዱ ከአገሪቱ ከሚገባው በላይ አብዝቶ ተጠቃሚ ሌላው ምክንያታዊ ድርሻውን የሚነጠቅ፣ አንዱ አገራዊ ታማኝ ሌላው ከሀዲ፣ አንዱ አርበኛ ሌላው ባንዳ፣ አንዱ ተለማኝ ሌላው ለማኝ፣ አንዱ ተቻይ ሌላው ቻይ፣ አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ፣ አንዱ ሿሚ ሌላው አሿሚ፣ አንዱ ጨዋ ሌላው ባሪያ፣ አንዱ ህዝብ ሌላው አህዛብ ወዘተ የሚሆንበት ቅንጣትም እድል ከእንግዲህ እንደማይኖር መተማመንና በዚህ ላይ የጋራ የፀና አቋም ወስዶ ለአንዲት ሀገር እኩል ልጅነት መትጋት ያስፈልጋል። ብየ የማምን፣ የምጽፍና የምሰብክ ነኝ፡፡


እናም እኔ ይህ ነኝ፣ የራሴ ተሰላፊ፣ ያመንኩበት ዘማች! የግሌ ወታደር፣ የግሌ መልዕክተኛ!!


በአብዱልጀሊል ሸህ አሊ ካሳ

42 views0 comments

Comments


bottom of page