• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ማነው ትክክል? (በሚስጥረ አደራው)


ማነው ትክክል? (በሚስጥረ አደራው)

ለትክክለኛነት እና ለስህተተኛነት ጥያቄዎቻችንን መልስ እንደመስጠት፤ ለእውነት እና ለሃሰት መለኪያችን መስፈርትን እንደማግኘት፤ ለማንነታችን  ትርጉምን እንደመፈልግ ህሊናን የሚረብሽ ምን ነገር አለ? ልብ እና አይምሮ ሲቃረኑ፤ እምነት እና ፍላጎት ሲጣሉ፤ ግለኝነትና ማህብረሰብ መስመር ሲለዩ ምን ማድረግ እንችላለን?በመንታ መንገድ ላይ ቆመው እንደመዋዥቅ ምን የሚያስጨንቅ ነገር አለ?

አንዳንዴ በውስጣችን ልክ የሚመስለንን ነገር እንዳናደርግ፤ ፍላጎታችንን እንዳንኖር፤ እውነተኛ ማንነታችንን እንዳናወጣ የሚያስፈሩን ብዙ ነገሮች አሉ። ልማድ እና የማህበረሰብ መስፈርት ዋነኞቹ ናቸው። ለምሳሌ በእውነተኛ ፍቅር ማንም ሰው ክርክር የለውም፤ ነገር ግን እውነተኛ ፍቅር በሚይዛቸው ሰዎች ላይ ግን ጥያዎች ይኖራሉ። በእድሜ የሚለያዩ ሰዎች ሲዋደዱ፤ በሃይማኖት የሚለያዩ ሰዎች ሲዋደዱ፤ በዘር የማይገናኙ ሰዎች በፍቅር ሲወድቁ፤ የእውነተኛ ፍቅር ትክክለኛነት በማህበረሰቡ ዘንድ ጥያቄ ወስጥ ይወድቃል።

ውሸትን እንውሰድ፤ የትኛውንም ሃይማኖት ብንከተል ውሸት ከሌሎች ሃጥያቶች እኩል ሃጥያት ነው። ነገር ግን ውሸት ቅዱስ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፤ ሰዎችን ከጥፋት ለማዳን ወይም ሰዎችን ለማስታረቅ እንዋሻለን። ታዲያ ትክክለኛ እና ስህተት የምንላቸው ነገሮች እንደየሁኔታው ይለያዩ ይሆን?

ይህንን እንድል ያነሳሳኝ ነገር፤ ሰው ውስጣዊ ፍላጎቱ እና ማህበረሰቡ የማይቀበለው ነገር ሳይጣጣም ሲቀር፤ የራሱ የህይወት እይታና የብዙሃኑ እይታ አልታረቅ ሲለው ምን ማድረግ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ነው። ሰው ለራሱ ያለው የማንነት ትርጉምና ማህበረሰቡ የሚሰጠውን ትርጉም እንዴት መታረቅ ይችላል? የትኛው ነው ትክክል? የትኛው ነው እውነት? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አልያም ለማስረዳት አይደለም የዚህ ጽሁፍ አላማ።

ነገር ግን በህይወታችን መሰረታዊ በምንላቸው ነገሮች ላይ የውስጣችን ሃሳብ እና የማህበረሰቡ ዳኝነት ሳይታረቅ ሲቀር የሚገጥመንን ፈተና እንዴት ማለፍ እንችላለን የሚለውን ሃሳብ ማንሳት ፈልጌ ነው። “ትክክል” አልያም “ስህተት” የሚባሉት ነገሮች እንዴት ተብለው ነው እውነተኛነታቸው የሚጣራው? የማንንስ መስፈርት ተንተርሰው ነው የሚዳኙት?

ምናልባትም በእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ እየዋዠቅን ከሆነ  የሚከተሉት ነጥቦች አይምሮዋችንን ሰፋ ያደርጉታል፦

የተለመደ ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም- ለምሳሌ እንደ ኤሮፕያውያን አቆጣጠር እስከ  1954 ዓ.ም ድረሰ ሰዎች አንድ ማይል (1.6 ኪ.ሜ) ለመሮጥ ከአራት ደቂቃዎች በላይ እንደሚወስድባቸው ይታመን ነበር። አንድም ሰው ቢሆን ከአራት ደቂቃ በታች አንድ ማይል ሮጦ ስለማያውቅ፤ለሰው ተፈጥሮ የሚከብድ ነገር እንደሆነ ይታመን ነበር። ማንም ሰው ጥያቄ ውስጥ አስገብቶትም አያውቅም። ነገር ግን በ1954 ሮጀርስ ባኒስተርስ የተባለ እንግሊዛዊ አንድ ማይልን ከ4 ደቂቃዎች በታች ሮጦ ለማሸነፍ ቻለ። ከዛ በኋላ ብዙ ሰዎች ከአራት ደቂቃ በታችን አንድ ማይልን ለመጨረስ ችለዋል። ስለዚህ የለመድነው ነገር ሁሉ ትክክል ወይም እውነት ነው ማለት አንችልም። ውስጣችን እስከነገረን ደረስ እውነታውን በራሳችን መፈለግ መቻል አለብን። (ምንጭ ከሌስ ብራውን ንግግር)

አዲስ ነገርም ሁሉ ስህተት አይደለም- አጼ ምኒሊክ በመጀመሪያ ፎቶግራፍ ማንሺያ መሳሪያን ሲያስተዋውቁ፤ የቤተመንግስቱ ሰው ሁሉ የሰይጣን ስራ እንደሆነ አድርጎ አምቷቸው ነበር፤ መኪናንም ሲያስገቡ እንደዛው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ከተለመደው ነገር ውጪ የሆነ አዲስ ነገር ሲገጥመው በቀላሉ ለመቀበል ይከብደዋል። አዲስ ሃሳብ ሲኖረን ተቃውሞ የሚገጥመን ሃሳባችን ብዙውን ጊዜ  የማይረባ ሆኖ አይደለም፤ በማህበረሰቡ ዘንድ አዲስ ነገርን መቀበል ቀላል ስላልሆነ ነው።

እውነት ስምምነት ነው፤ ከብዙሃኑ የራቀ እውነት ውሸት ይመስላል– ሶቅራጠስን እንውሰድ፤ ለሞት ያበቃው ከብዙሃኑ ተለይቶ የራሱን እውነታ በማንጸባረቁ ነው። ብዙሃኖቹ የተስማሙበትን በመቃወሙ እንደስህተት ተቆጥሮበት ለሞት ተዳርጓል። ማንም የማያነሳቸውን ጥያቄዎች በማንሳቱ፤ ሁሉም ተስማምቶባቸው የነበሩትን ሃሳቦች በመርመሩ እንደወንጀል ተቆጠረበት። እውቀትን በማስፋፋቱ፤ በማህበረሰቡ የተዳፈኑ ነገሮችን በመቆስቆሱ ወጣቶችን እንዳበላሸ ተደርጎ እንዲሞት ተደርጓል። እውነታው ግን ዛሬም ደረስ የዚህ ታላቅ ሰው ስራዎች ህያው ሆነው ይኖራሉ። ይህ ማለት ከብዙሃኑ ስነለይ ስህተተኞች ነን ማለት አይደለም።

ማህበረሰቡን ባይፈራ ሁሉም የራሱ የሆነ እውነት አለው- የራሳችን እውነት ስል፤ ለምሳሌ በገጠር ስለሚኖሩ ሰዎች የሰማሁትን ላጫውታችሁ። በአንድ አንድ የገጠር ከተማ ሴት ልጅ ምንም እንኳን መጸዳጃ ቤት መሄድ ቢያስፈልጋት በቀን እንደወንዱ በነጻነት መውጣት አትችልም። ጀንበር ሳትወጣ አልያም ጀንበር ስትጠልቅ ብቻ ነው ለሴቷ ትክክለኛው የመጻደጃ ሰዓት። ይህንን እንደ ህግ ተቀብለው የሚኖሩት ብዙዎች ናቸው፤ አንዳንዶች ግን ልክ አለመሆኑ ቢገባቸውም የብዙሃኑ ስምምነት አንቆ ይይዛቸዋል። ማህበረሰቡን ባይፈሩ እነሱም እንደወንዶቹ ነጻነታቸውን ባጣጣሙ። በተለይ ይህ ሃሳብ የሁላችንም ቤት የሚያንኳኳ ነው፤ እርግጠኛ ነኝ አካባቢያችንን ባንፈራ ልንቀይራቸው የምንሻቸው ብዙ ልማዶች አሉ። ግን እስከመቼ በዚህ ሁኔት እንዘልቃለን?

እንግዲህ ለሁሉም ነገር የማህበረሰቡን ይሁንታ መጠበቁን መተው አለብን። አንዳንዴ የውስጣችን ሹክሹክታ ከማህበረሰቡ ጩኸት በላይ እውነት ሊኖራት ይችላል።ይህንን ስል ልማድና ባህልን ገፍትረን እንጣል ማለቴ አይደለም። ወሳኝ በሆኑ የህይወታችን ጉዳዪች ላይ ግን ስለራሳችንም ሆነ ስለአመለካከታችን የራሳችን የሆነ ትርጉም ሊኖረን ይገባል። ፍላጎቶቻችን እና እምነቶቻችን ከብዙሃኑ ጋር አልተስማሙም ማለት ተሳስተናል ማለት አይደለም። ይህን ጽሁፍ በአጭሩ የምትገልጽ ግጥም ትዝ አለችኝ ፦

“Two roads diverged in a wood, and I—

I took the one less traveled by,

And that has made all the difference.”- ROBERT FROST- በአገረኛ እንዲህ ተርጉሜ አቅርቤያታለው

“በመንታ መንገድ ላይ ልቤን አገኘሁት ግራ ቀኝ አዙሬ ሁሉን አሳየሁት ሰው ሁሉ የሄደበት ኮቴ የበዛበትን ፤ አልፈልግም ብሎ ጭር ያለውን መንገድ ሄደ ተከትሎ” -ሚስጥረ አደራው

43 views0 comments