የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ምንም አልል (ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን)

እሺ እንግዲህ በዝምታ
የልቤን ደም ስር ትርታ
የደቂቅ እድሜ ትዝታ
ትር ስትል አፍታ ለአፍታ
እያዳመጥኩ እያስታመምኩ፣ ጊዜዬን እያሰላሰልኩ
ሳልናገር ሳልጋገር፣ እደገምኩ እያሰላሰልኩ
ሳልሰለች እየመላለስኩ…
እሺ እንግዲህ በጸጥታ
የልቤን ደም ስር ትርታ
የእስትፋሴን ቃል ጉምጉምታ
ትር ስልት አፍታ ላፍታ
ሳልሰለች እየደጋገምኩ
በእግረ ህሊና እያደቀቅኩ
እየቋጠርኩ እየቆጠርኩ…
እሺ እንግዲህ አልናገርም
በአንደበቴ አልተነፍስም
በልሳኔ አልመሰክርም
አልልም ምንም አልልም
እንግዲያው ዝም እንጂ ዝም ዝም…
የልቤ ደም ስር ሲያቃጭል
ልሳኔን ሲያስነሳ ሲያስጥል
ቃላቴን ሲቃኝ ሲያጋግል
ትፋሼን ሲያን ሲያዳውል
ክል ሲል ትር ድም ሲል
ማዳመጥ ማስታመም እንጂ፣ ሌላ ምንም ምንመ አልል።