top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ሥነ – ልቦናዊ ጥንካሬ


‹በሕይወት ውስጥ መንፈሰ ጠንካራነት ፤ አልበገር ባይ ሐሞት እና ፅኑ ዓላማ ሊኖር ይገባል›› ይላሉ የሥነ ልቦና ዓዋቂዎች፡፡ ይህም ያለምክንያት አይደለም ‹‹ተፈታታኝ የመኖር ግርጦሽ፣ ጎርበጥባጣ ገጠመኝ ሲከሰት፤ ከቶም በላላ ሞራል፤ በሚልፈሰፈስ ወኔና ማንነት፤ እና በሚርድ መንፈስ፤ በአሸናፊነት ለመውጣትና ከድል አምባ ለመድረስ አይቻልምና፤ ብርቱ የሥነ ልቦናዊ (አእምሮአዊ) ማንነትና ስብዕና ባለቤት መሆን አማራጭ የለውም›› በማለትም ይገልጹታል፡፡

‹‹ባለ ድል ለመሆን እንደ ዐረብ ብረት በጠነከረ ፤ እንደ ሲባጎ በከረረ እንደ እቶን እሳት በተንቀለቀለና በጋለ ስሜት፤ በኮስታራነትና ግብግብ በመግጠም፤ የሕይወትን ውጣ ውረድ ታግሎ ለማሸነፍ ሥነልቦናዊ ጥንካሬን መላበስ ግድ ነው›› ሲሉም የሥነ - ልቦና አዋቂዎቹ ያክላሉ፡፡

እንግዲህ ይህንን የሥነልቦና አዋቂዎችን የሥነ ልቦናዊ /አእምሮአዊ ጥንካሬ አስፈላጊነትን በመሰረታዊ ሃሳብነት ይዘን በማህበረሰባዊ ሕይወት ውስጥ ስለሚታዩ አንዳንድ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬን የሚሹ ክስተቶችና ገጠመኞችን እያነሳን ጥቂት ሃሳቦችን እናያለን ፡፡

በዚህ ሃሳብ እንነሳ፤ አንድ ሰው የራሱን ኑሮ ለመምራትና ራሱንም ለማስተዳደር፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ሁነኛ ቦታ ይዞ ለመቀጠል፣ ለኑሮውም የሚያስፈልገውን መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ማግኘትና፤ የመሰረታዊ ነገሮቹ ባለቤት መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህም ይህ ሰው በመጀመሪያ ላይ የአንድ ሙያ ባለቤት ሆኖ ሥራ በመሥራት የራሱ ገቢ ሊኖረው ያሻል ማለት ነው፡፡

የአንድ ሙያ ባለቤት ለመሆን ደግሞ በመነሻ ያንን ሙያ መማር፤ በሙያው መሰልጠን ይጠበቅበታል ፡፡ በዚህ ተጠይቃዊ አካሄድ ስንሄድ ካልተማሩ ወይም በአንድ ሙያ ካልሰለጠኑ ሥራ ፤ ካለሥራ ደግሞ ገቢ ማግኘት አይቻልም፤ የሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን ማለት ነው ፡፡

ስለዚህ ሕይወትን ፊት ለፊት ለመጋጠምና ኑሮንም በአግባቡ ለመምራት መማር ወይም በአንድ ሙያ መሰልጠን አስፈላጊ ነው። ይህንንም አስፈላጊ ነገር ልንጨብጠው ግድ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሥነ- ልቦናዊ ጥንካሬ ሊኖረንና ‹‹እችለዋለሁ! አደርገዋለሁ›› የሚል ቆራጥ አቋም ልንይዝበት የግድ ይላል።

አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ‹‹እኔ አሁን በዚህ ዕድሜዬ ልማር አልችልም ...ኤጭ ! ምን አባቱ !... ሆኖ ላይሆን ነገር ...ዓለም እንደሆነ ጎዶሎ ናት... ደግሞ መቶ ዓመት ለማይሞላ ዕድሜ ... ወዘተ›› በሚል ተስፋ አስቆራጭ ሃሳብ ተሞልተው የሕይወትን ውጣ ውረድ ተቋቁመው ከጫፍ ለመዝለቅ ይቸገራሉ፡፡

ይሁንና ተስፋ ከመቁረጥ ዳርቻ ደርሰው፤ ከመሸነፍ ስርቻ ሥር ከመወሸቃቸው በፊት ቆም ብለው ሁለቴ አስበው ሥነ- ልቦናዊ ጥንካሬያቸውን በማጎልበት ብሩህ ነገርን እያለሙ ቢንቀሳቀሱ በራሳቸው ፍጥነት ተጉዘው፤ ሩቅ ከመሰላቸው የተራራው ጫፍ ላይ ሊደርሱና ድላቸውን ሊያውጁ ይችላሉ ፡፡

በእርግጥ በጠንካራ ሥነ- ልቦናዊ ማንነት፤ በጀገነ መንፈስ፤ የማይናድ የሕይወት ገጠመኝ ተራራ፤ ደልዳላ ሜዳ የማይሆን የኑሮ ኮረብታ የለም፡፡ ‹‹የምናስበው ነገር፤ አብዛኛውን ጊዜ የምንተገብረው ይሆናል›› የሚሉት እሳቤ አለ፤ ይህም ከሥነ -ልቦና ጥንካሬያችን ጋር ይያያዛል። ‹‹አንዳች ለሕይወታችን ጠቃሚ የሆነን ነገር የምንተገብረው ባለን ሥነ- ልቦናዊ ጥንካሬ መጠን ነውም›› እየተባለ ሲነገር ይደመጣል።

አንዳንድ ሰው ‹‹ጎሽ! ጎበዝ! ትችለዋለህ!›› ከተባለ ከራሱ ኪሎ በላይ የሆነን ሸክም ያነሳል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ሊያነሳው የሚችለውን ኪሎ ‹‹አትችለውም›› ከተባለና ራሱም ‹‹አልችለውም›› ብሎ በማሰብ ሥነ- ልቦናዊ ጥንካሬውን ካልፈሰፈሰው፤ በክብደት ማንሳት ውድድር ውስጥ ተሸናፊ ሆኖ ቁጭ ይላል ፡፡

ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ልዩ ልዩ ገጠመኞች ያጋጥሟቸዋል። በእነዚህ ገጠመኞች ተስፋ ቆርጠው ሁሉም ነገር የማይሳካላቸው መስሏቸው በምሬት ካቴና የፊጢኝ ተይዘው፤ ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬያቸው ከመላሸቅ፣ ሞራላቸው ከመድቀቅ ደረጃ የሚደርሱበት ጊዜ አለ፡፡

እውነት ነው ሁልጊዜ ‹‹ገንፎ በማንኪያ ዐይነት ነገር አይገጥምም» የምንኖርባት ዓለምም እንዲህ አልተሰራችም፡፡ በመሆኑም ምንም ነገር ያለውጣ ውረድ አይገኝም፤ የተለየ ችሎታና ዕውቀት ቢኖር እንኳን የሚሹትን ለመጨበጥ ጥረት ፤ልፋት ፤መውደቅ መነሳት ይጠይቃል፡፡ ቶማስ ኤድሰን ይህንን ጉዳይ እንዲህ ገልፆታል፤ በመገኛ ቋንቋ እንዳለ ላቅርበው ፡-‹‹Genius is one percent inspiration, ninety- nine percent perspiration» ስለሆነም በየዕለቱ ትንሽ ትንሽ መስዋዕትነት መክፈል ፤ ጥቂት ጥቂት መሞት የግድ ነው፡፡

አንድ ሙያ ኖሮት ሥራ ያጣ አንድ ሰው የጠንካራ ሥነ -ልቦና ባለቤት ከሆነና ብሩህ ነገርን ማሰብ ከቻለ ራሱን ሊያስተዳድርበት ወይም ሊያኖርበት የሚያስችለውን ሥራ ሊፈጥር አቅሙ አለው ተብሎ ይታሰባል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ በያዙት ሙያ አኳያ ሥራን ማግኘት ካልተቻለ የጠንካራ ሥነ -ልቦና ባለቤት ሆኖ ሥራን ሳይንቁ ዝቅ ብሎ መሥራት ከተቻለ ፤ የሥራ አጥነትን ሰንሰለት በጣጥሶ በጊዜ ሂደት ውስጥ ከከፍተኛው የኑሮ እርከን ላይ መደረሱ አይቀርም ›› የሚል አማራጭ ሃሳብና የሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ መገለጫ መንገድን የሥነ ልቦና ምሁራኑ በተጨማሪ ይጠቁማሉ፡፡ ናታን ሞሪስ የተባለ ፀሐፊም በመሰጠት ሥራን በመሥራት ስኬታማ ስለመሆን ሲፅፍ እንዲህ ብሏል «The Speed of your success is limited only by your dedication and what you’re willing Sacrifice »

ከዚህ አኳያ በአገራችን ያሉ ወጣቶቻችንን እንደ አብነት እናንሳ። የወጣቶቻችን በአንድ ሙያ መስክ መሰልጠን ወይም በአንድ የትምህርት አይነት መመረቅና የአንድ ሥራ ባለቤት መሆንን ስንፈትሽ፤ ጥቅል ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬያቸውንም ስንዳሰስ፤ ዛሬ ዛሬ በሁለቱም አቅጣጫ የሚያበረታታ ሁኔታን ማየትና መታዘብ ይቻላል ፡፡

በተለይም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ፤እንዲሁም በልዩ ልዩ የቴክኒክና የእጅ ሙያ ሰልጥነው የመንግሥት ተቀጣሪ ከመሆንም ባሻገር ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው በተገቢው ሁኔታ ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ፤ ቤተሰቦቻቸውንም ሲረዱ መታዘብ ይቻላል ፡፡

የፈጠሯቸው የሥራ ዓይነቶችና የተሰለፉባቸው የሙያ መስኮች ደግሞ በዝርዘር ሲታዩ በእውነትም ዱሮ ዱሮ ባለ ዲግሪ ወይም የከፍተኛ ዲፕሎማ ባለቤት የሆነ ወጣት ወይም የሆነች ወጣት፤ ሊሰሩት አይደለም፤ የማያስቡትን የሥራ ዓይነት ነው። ለምሳሌ የግብርና ሥራ፣ የከብትና የዶሮ ርባታ ፣ የእንጨት ሥራ፣ ግንበኛነት፣ አናፂነት፣ የኮብል የድንጋይ ንጣፍ ሥራ ወዘተ፣ ዛሬ ከልብ ተቀበሉት ሲሰሩና ተጠቃሚ ሆነው ሲታዩ ይህ እንቅስቃሴም የወጣቶቻችንን ሥነ - ልቦናዊ ጥንካሬ ወይም አእምሮአዊ ብርቱነት አንድ ማመላከቻ ነው ብዬ ለማለት እደፍራለሁ ፡፡

ከዚህ የወጣቶቻችን ሥነ- ልቦናዊ ጥንካሬ ጎን ለጎንም የአገራችን መንግሥት ለወጣቶች የሚያደርገው ያላሰለሰ ድጋፍና ያለው የወጣቶች ፖሊሲ ያበረከተው አስተዋፅኦም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ መንግሥት የሥራን ክቡርነት በማስገንዘብ ደረጃ ወጣቶች የጠነከረ ሥነ ልቦና ባለቤቶች ሆነው በማንኛውም ሥራ መስክ ተሰልፈው እንዲንቀሳቀሱ በየጊዜው የሚያደርገው የስልጠና፤ የሥራ ቦታና የፋይናንስ ብድር የማመቻቸት ተግባሩም የሚሰማራበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም ምቹ ሁኔታ መጠቀም የወጣቶቻችን ፈንታ ነው ፡፡

ታዲያ የአገራችን አንዳንድ ወጣቶች በሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ አናሳነት ወይም ደግሞ ለራሳቸው ከሚሰጡት ትልቅ ግምት የተነሳ ራስን ዝቅ አድርጎ ማንኛውንም ገቢ ሊያስገኝ የሚችልን ሥራ መሥራት ባለመፈለግ ወይም ደግሞ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ስምና ደረጃ ላይ ለመድረስ በማሰብ ወይም ደግሞ በአንዳንድ ሃሰተኛ አማላይ የደላሎች ሃሳብ በመታለል ወዘተ ያሰቡትን እንዳሰቡት «ለማግኘት ያስችላል» ብለው ወደ ገመቷቸው ባዕድ አገሮች የተወለዱበትን ቀዬ ለቀው አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ፤ ወጥተዋልም ፡፡ በእርግጥ በዚህ አይነት አካሄድ ከአገር ወጥተው ያሰቡት የተሳካላቸው ምንም ወጣቶች የሉም ባይባልም ፤ በለስ የቀናቸው በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ግን በስደት ሕይወት ክፉ ካራ ጉዳት ላይ ወድቀዋል፡፡ ዜጎችም ለአገራዊ ኀዘን ተዳርገናል፡፡

‹‹በምድራቸው፤ ባላቸው ዕወቀትና ችሎታ ተፍጨርጭረውና ሥነ - ልቦናዊ ማንነታቸውን አጠንክረው ለደላሎች የከፈሉትን ገንዘብ በአንድ የፈጠራ ሥራ ላይ ቢያውሉት ኖሮ የደረሰው ነገር፤ በየጊዜውም የሚደርሰው ጉዳትና ስብራት ባልደረሰ ነበር ›› የሚል ሆኗል፤ ክፉው የሊቢያ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ወዘተ ክስተት በተፈጠረ ጊዜ ብዙ የአገራችን ሰዎች የሰጡት አስተያየት፡፡ ይህንን አስተያየት እኔም እጋራለሁ ፡፡

በአገር በወገን መካከል ሁሉም ያምራል፤ ቢወድቁ ‹‹እኔን›› የሚል እና የሚያነሳ ፤ «ትን» ቢል ውሃ የሚያቀብል አይታጣም። ስለሆነም በሰፋና ሩቅ በሚያልም ማንነትና በደነደነ የሥነ - ልቦና ጥንካሬ አንድን ሥራ ለመሥራትና ኑሮን ለመምራት ከተሞከረ ሙከራው የማይሳካበት ምክንያት ብዙም አይሆንም፡፡

አንድ እውነት ግን እውነት ነው ፤‹‹የፈለጉት ነገር ዕለቱን ላይገኝ ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እስከ ወዲያኛው ይቀራል ማለት አይደለም ፤ በጭራሽ ፡፡ ታታሪነት፤ ፅኑ ማንነት ፤ ጠንካራ ሥነ - ልቦናዊ ስብዕና ከተላበሱ የፈለጉትን መጨበጥና ከስኬት ዳርቻ መድረስ አይቀሬ ነው ›› በማለት ስለ ሥነ – ልቦናዊ ጥንካሬ የፃፉ ምሁራን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆነ የማጠቃለያ ሃሳብ ሰንዝረዋል ፡፡ እኔም በዚህ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተስማምቼ ይህንን ጽሑፍ በዚሁ እቋጫለሁ፡፡ ተርፎ ከሚቀር ዕድሜ አይንሳንና በቀጣይ ጽሑፌ እንገናኛለን እስከዚያው ብዘ ሰላም! ለአንባቢዎቼ ተመኘሁ፤ ሰላም !!!

ፀሐፊው ሳምናስ (አምደኛ)

24 views0 comments

Comments


bottom of page