የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ስኬት... (በሳሙኤል አሰፋ)

የሰው ልጅ የህይወት ዘመን ትልቅ ምኞት ዋነኛ ጉዳይ ነው ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፣ለመወለድ ለመኖር ፈቃድ ሳይኖረው የተወለደው የሰው ልጅ ከውልደቱ በኋላ ህይወትን ለመምራት የእርሱ ፈቃድ ምርጫና ጥረት ብቻ ስኬትን ያጎናጽፈዋል የሚለው ፍልስፍና በዚህ ጥግ ፣ አይደለም የሰው ልጅ ምንም ያክል ቢጥር ቢለፋ የፈጣሪ ፈቃድ ካልታከለበት ጥረቱ ሁሉ መና ነው የሚለው በሌላ ጥግ ተቀምጠዋል፡፡የሰው ልጅ ህይወትን እንዴትም ይኑራት መጨረሻ ሳይፈቅድ ወደዚህች ምድር እንደመጣ ሳይፈቅድ በግድ ይህችን አለም ተሰናብቶ ይሄዳል፡፡የማይቀር የህይወት እጣፈንታ የሰው ሁሉ መንገድ ነውና ይሞታል፡፡ የህይወት ኡደት ይቀጥላል፡፡ ሌላው ይወለዳል፣ ይኖራል፡፡ የውልደት የኑሮ የሞት ቅብብሉ ይቀጥላል፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያዎች የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ፈላስፋዎች ፓለቲከኞች ሁሉም ስለህይወት ስኬት ብዙ ብለዋል ብዙ ጽፈዋል፡፡ በተለይ በቅርብ ጊዜያት በሀገራችን በርካታ መጻህፍት በሀገር ውስጥ ፀሀፊዎች ተጽፈዋል ከባእድ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡በርካታ የሀይማኖት ምሁራን በሀይማኖቱ ፍልስፍና እና መርህ መሰረት ስለስኬት አስተምረዋል፡፡በርካቶች ስለ ታላላቅ የአለማችን ሰዎች የተጻፈን ግለታሪክ በማበብ የስኬታቸውን ምስጢር ለማወቅ መርምረዋል ጥረዋል፡፡ የስነልቡና ሊቃውንት ስኬትና አለመሳካት በሰው አእምሮ ውስጥ ያሉ ነገሮች እንደሆኑ፤ ሰው ለእራሱ ማንነት ለአእምሮው የነገረውንና ያሳመነውን ነገር ያንኑ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ጥረት እረፍትና የሌለው የስራ ባህል የስኬት ቁልፍ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡በተቃራኒው ደግሞ ስኬት ማለት ፈጣሪ ለሰው ያሰበውን እቅድ እርሱን መኖር ነው በማለት የስኬትን መነሻ ከሰው ወደፈጣሪ የሚወስዱም አሉ፡፡
ለመሆኑ ስኬት ማለት ምን ማለት ነው? በምድር ላይ ተሳካለት የሚባለው ሰው ምን አይነት ሰው ነው? ብዙ እድሜ የኖረ? ጥሩ ትዳር የያዘ? ብዙ ልጆች የወለደ? ብዙ ሀብትና ንብረት ያፈራ?ባለስልጣን ?በጣምየተማረ? ሁልጊዜ የሚያሸንፍ ስፖርተኛ? የታወቀ ፖለቲከኛ? የተዋጣለት ደራሲ? የፊልም ተዋናይ? ጋዜጠኛ? . . .ወይስ ሌላ?
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው መዝገበ ቃላት ስኬት የሚለውን ቃል ሲተረጉመው፤‹‹የአላማ ወይም የድርጊት ክንዋኔ በጥሩ ሁኔታ እንደታቀደው መፈጸም፡፡›› ይለዋል፡፡ እንደ አላማር ጸሀፊ ሪክ ዋረን ትርጓሜ ‹‹ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሐርና ለእግዚአብሔር ነው፡፡ ይህን እስካልተገነዘበ ይወት ትርጉም ያለው አይሆንም፡፡›› ሲሉ በአንጻሩ ደግሞ የህይወት ስኬት አስተማሪው Joseph Murphy(PHD,DD)) (የአእምሮ ብቃትን በመጠቀም መልካም ህይወትን መምራት ቁልፍ ሚስጥራት በሚል ርእስ ታትሞ በእስክንድር ስዩም በተተረጎመው የስነልቦና መጽሀፍ የህይወት ስኬትን በሰው ውስጣዊ የአእምሮ ሐይል መረዳት ጋር ያዛምደዋል፡፡ ጸሐፊው እንዲህ ይላሉ ‹‹ለአንድ ሰው የጸሎት ምላሹን የሚሰጠው ግለሰቡ የሚያምንበት ነገር አይደለም፡፡ይልቁንም ምላሹን የሚያገኘው የግለሰቡ ድብቅ የአእምሮው ክፍል ግለሰቡ ለሚያስበው ነገር ወይም አእምሮው ውስጥ ለተቀረጸው ምስል ምላሹን መስጠት ሲጀምር ነው፡፡›› በማለት ስኬት ሰው የአእምሮውን ሐይል በመረዳት በሰው ውስጣዊ ሀይል እንጂ በውስጣዊ ኃይል ላይ በመደገፍ የሚመጣ አንዳልሆነ ያስተምራሉ፡፡ አክለውም ‹‹ምንም እንኳ በእምነቶቻቸው መካከል ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩም ክርስቲያኑም፣ሙስሊሙም፣አይሁዱም፣ሆነ ቡድሀው ሁሉም ለጸሎታቸው ምላሽ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?›› በማልት ይጠይቁና ‹‹ይህ የሆነበት ምክንያት ምላሹ በኃይማኖት፣ በአንድ ተለየ እምነት፣ በባእድ አምልኮ፣በድግምት ፣በቤተክርስቲያን ስርአት፣ በቀመር፣ በወገንተኝነት፣ በመስዋእት፣ ወይም ስጦታ በመሰጠት . . ላይ ሳይሆን በሚጸልዩት ነገር ላይ ባላቸው እምነትና የመቀበል ስሜት ላይ ብቻ ተመረኮዘ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የእምነት ህግ ነው፡፡›› (ገጽ 11) በማለት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ከልክ በላይ ደክሞ እና ላብን ጠብ አድርጎ ሃብት ለማፍራት መሞከር መቃብር ስፍራ ላይ ካሉ ሃብታሞች አንዱ እንደመሆን ነው፡፡ በጣም መድከምና መልፋት የግድ ላይሆን ይችላል፡፡››(ገጽ 86) ሲሉ ስኬትን እረፍት ከሌለው የስራ ባህል እና ጥረት ጋ የሚያገናኙትን ወገኖች በተቃርኖ ይቆማሉ፡፡
አንዳንድ የmotivation አስተማሪዎች ሀብት፣ንብረት፣ትምህርት፣ውበት፣ ዝና፣ ስልጣን በአጠቃለይ ቁሳዊ ነገሮች በራሳቸው ለሰው ልጅ ደስታን አይሰጡም ይላሉ፡፡በማለት ‹‹እነዚህ ነገሮች አንተ ባለህ ነገር ውስጥ የምታገኘው እና የምትሰራው ነገር ወይንም የምንፈጥረው ነገር ነው›› በማለት ይናገራሉ፡፡በዚህ ፍልስፍና መሰረት የሰው ልጅ የሚኖረው የሚሰራው የሚሰጠው ሌሎችን የሚረዳው ለራሱ ደስታ እንጂ ከሌላው ጋር ህይወትን ለመካፈል አይደለም፡፡ይህ ደግሞ ሰው ሁሉን ነገር መተርጎም ያለበት ከራሱ የደስተኝነት እርካታ ትርፍ አንጻር ነው ወደሚል ድምዳሜ እንዳያደርስ ያሰጋል፡፡ምክንያቱም እራስን ማዕከል ወዳደረገ ጽንፍ የተጠጋ ይመስላል፡፡ መስጠቴ፣መኖሬ፣መስራቴ፣ቤተሰብ መመስረቴ፣ማገልገሌ. . . ደስተኛ ካላደረገኝ ለሌላው ምንም አላደርግም ወደሚል ድምዳሜም ሊያደርስ ይችላልና፡፡
እንደ የሃይማኖት መጽሃፍ እውነት ሰው ለተፈጠረለት የህይወት አላማ ለህይወት ጥሪው ካልኖረ ስኬታማ አይደለም የሚለው በርካቶችን ያስማማል፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፉ ውስጥ ታሪካቸው የተጻፈልን ሰዎች አንዳንዶቹ በንግስና፣ በዝና፣ በሃብት፣በጀግንነት፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ጣሪያ ላይ ኖረው ዘመናቸውን ሲጨርሱ ሌሎች ደግሞ በድህነት በስደት፣ በመገፋት፣ በመናቅ፣ በድንጋይ መወገር፣በሰይፍ ስለት መበገደል፣ በመጋዝ በመሰንጠቅ፣ በጉድጓድ እና በምድረበዳ በመንከራተት አልፈዋል፡፡ በየትኛውም የህይወት ገጽታ የፈጣሪ ፈቃድ ፈጽመው አልፈዋል ወይ የሚለው ሚዛን ላይ ተቀምጦ መመዘን አለበት፡፡ ስለዚህ የስኬት መለኪያ ምድራዊና ቁሳዊ ነው ወይንስ ሌላ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡
ሰላም ለሁሉም!
ሳሙኤል አሰፋ