የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
"ቃል-ኪዳን ነበረን" (በወሰን ሰገድገ/ኪዳን)

በአንድነት ያቆመ - በአንድ ያስተሳሰረን፣
በፅኑ ተጋምዶ እጅግ የደደረ፣
ዘመናት ያለፈ - ዘመናት የኖረ፣ በላብ የከበረ፣
በደምና በአጥንት የተመሰጠረ፣
በእኔና አንተ መሃል - ቃል-ኪዳን ነበረ።
ከአንተ በፊት ያርገኝ
እኔን ያስቀድመኝ
አንተን ክፉ አይንካህ
እንኳን ሌላው ቀርቶ - ዕንቅፋት አይምታህ
የሚልቃል ነበረን - በእምነት የቀለመ፣
በሀገር ፍቅር ላይ -ፀንቶ የታተመ!
በየተራራው ላይ - “ላብ ደምን ይተካል” እያልን ስንሮጥ፣
ከፍባለ ሞራል - ሶምሶማ ስንረግጥ፣
አምባው ሲንቀጠቀጥ - በሕብረ ድምፃችን፣
በአንድ መቆም ነበር - ደግሞም አብሮ መሞት -የሁሌ ቃላችን!
ኮቾሮ በድንጋይ - ቀጥቅጠን አልመን፣
የቆርቆሮውን ወጥ _ በብረት ባርኔጣ - ገንፈልፈል አድርገን፣
ፍርፍር ቢጤ ሰርተን - እየተጎራረስን፣
ከአንድ ኮዳ ውሃ - ተካፍለን ጠጥተን፣
“ተመስገን” እያልን - በፍቅር ያፀናነው - ቃል-ኪዳን ነበረን!
"ፋሉል ብረት" እሣት - ከላይ ሲዘንብብን፤
አንድ ላይ ልንወድቅ - ወድቀን ልንነሳ - ቃል-ኪዳን ነበረን!
የመድፍና የታንክ ነጎድጓድ ወላፈን፣
ከፀሐይ ንዳድ ልቆ ሲያነደን ሲልፈን
አይዞን ተባብለን፤
ለአንደኛችን መኖር - ከአንዳችን ፊት ቀድመን
ሞትን እንደ ፀጋ - በእምነት ተቀብለን፣
ስለ ሀገር ክብር፣
ሕይወት ልንገብር - በአንድ ዓላማ ፀንተን፣
በደም የከተብነው - ቃል-ኪዳን ነበረን።
ቃልኪዳ ንነበረን - በደም የፀደቀ - በግብር የደመቀ፣
እንኳንስ ያገሩን - የአፍሪካን ወንበዴ - በፅናት ያረቀ፣
ቃል-ኪዳን ነበረን - የማይነቃነቅ፣
ዓለምን ያስቀና - እያደር የሚደምቅ!
በሠላሙ ጊዜ - በአንድ ጋቤጣ እየጠጣን "ስዋ"
ቃልኪዳን ነበረን - አብረን ልንሰዋ!
“አደይ ማርያም” ብለን - አብረን ተገባብዘን፣
በአንድ ትሪ በልተን - በአንድ ዋንጫ ጠጥተን፣
በሐቅ ያደመቅነው _- ቃልኪዳን ነበረን!
የክፉ ቀን ጓድህ - የክፉ ቀን ጓዴ፣
በእምነት ተቆላልፈው - ክንድህና ክንዴ፣
በፍቅር ተጋምደን - በፅናት የቆምን - አልነበርንም እንዴ!?
ምነው በለሊቱ - በድቅድቅ ጨለማ - በድንገት ከዳኸኝ፣
አንተ አለኸኝ ብዬ -የእግዜር ዕንቅልፍ ወስዶኝ፣
አድብተህ እንደአውሬ - እንደእባብ ነደፍከኝ፣
እንዳይሆን አድርገህ ልቤን ሸቀሸቅከኝ!
“አገር አማን ብዬ - ወገን አለኝ ብዬ - ሳሸልብ ጠብቀህ፣
ማተብህን ጥለህ - እምነቴን በጥሰህ፣
ስታዘንብ ጥይት በሰውነቴ ላይ፣
በስተመጨረሻ - ዐይቼህ ነበረ - በቁም ስትሰቃይ፣
ይብላኝ እንጂ ለአንተ - እኔ እንደታመንኩት
ነፍሴ ከመውጣቷ - ከማለፌ በፊት፣
እንደ ተለመደው - ቃል እንደገባሁት፣
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” - ብዬ ነው የሞትኩት!
ሀገር አልከዳሁም - ወገን አልከዳሁም
ቃል አላፈረስኩም!
ስሄድ እንኳ ከዓለም “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ማለት አልረሳሁም!
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት!!
ሕዳር 1 ቀን 2013 ተጻፈ።