top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

በሪያድ የ14ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል እድምታ


የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በሪያድ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በጋራ በመሆን ለአመታት በዓሉን አክብርዋል። ለኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ቆይታቸው ከአጓጊ ሃገር አቀፍ በዓላት መካከል ይኸው በዓል በትልቁ የሚጠቀስ ሲሆን ኢትዮጵያውያን የዘር፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ አቋም ሳይለያቸው አንድ አዳራሽ ውስጥ ወይም የመሰባሰቢያ ቦታ ላይ ሆነው በየቋንቋቸው እና ፍላጎታቸው በዓሉን ያከብራሉ።


ሐሙስ December 19 2019 እንደ መስቃን ሚድያ ኔትወርክ እና እንደ የመስቃን ማህበረሰብ አካል ዘግይተን ነበር ወደ በአሉ ቦታ ጉዞ የጀመርነው። ኤምባሲው ከምንኖርበት ክፍለ ከተማ 16 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ቁሶች ከሸከፍና የመኪናችንን ሞተር ከቀሰቀስን በዃላ ፊታችንን ወደ ኤምሲው በሚወስደው አቅጣጫ በማዞር አቀናን። በንጉስ ፋሃድ ስም የተሰየመው ፈጣን ጎዳና (highway) ለመሃል ከተማው (city center) ቅርብ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ሰሜን ሪያድ ለመሄድ የመጀመሪያ አማራጭ ጭምር ስለነበር በዚሁ ጎዳና ወደ አለምንበት አቀናን። ይህ… ንጉስ ፋሃድ ጎዳና (king fahad road) ዘውትር ጠዋትና ከስራ መመለሻ ሰዓት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ስለሚኖረው አማራጭ ካልታጣና ከስራ ቀናት ውጪ ከሆኑ ቀናት ውጪ ብዙም ተመራጭነት አልነበረው። እንሞክረው… ብለን ከፈጣኑ ከዳና ተዶልን:: ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዝን በዃላ ከገጠመን የትራፊክ መጨናነቅ በቀር ጎዞው ብዙም አስቸጋሪነት አልነበረው። አንዳንድ ጊዜ ከትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ ለመውጣት የመውጫ መንገዶች ጭምር ስለሚዘጋጉ ከ30 ደቂቃ እስከ 60 ደቂቃ ያህል ይፈጃል።


የዲፕሎማቲክ መንደር መግቢያዎች ጥብቅ የሆነ ፍተሻ የሚደረግባቸው ቦታዎች ናቸው። በስራ ቀናቶችና በስራ ሰአት ፍተሻው የሚቀል ሲሆን በምሽት ግን ወደ መንደሩ ለመግባት በቂ ምክንያት ከሌለና ከመንደሩ ተያያዥ የሆነ ስራ ከሌለ በጣም አስቸጋሪ ነው። የመኖሪያ ፍቃድ ከሌለ ደግሞ ለእስር መዳረግና ወደ ሃገር መባረር ጭምር ያስከትላል። ኤምባሲው ውስጥ የሚከበር በዓልም ሆነ ስብሰባ ሲኖር ግን የመንደሩ የደህንነት አካላት መረጃው ስለሚኖራቸው ወይም ኤምባሲው ሰለሚያሳውቅ ወደ ተጠቀሰው ኤምባሲ ለሚሄድ የሚመለከተው ሃገር ዜጋ ፍተሻው የቀለለ ነው የሚሆነው።


የዲፕሎማቲክ መንደር የደቡብ መግቢያን በመጠቀም ከትራፊክ መብራቱ በፊት ወደ ቀኝ እንደታጠፍን ብረት ለበስ መኪናዎች እና በተጠንቀቅ መሳሪያቸውን ወድረው የቆሙ ወታደሮች አለፍን። የመጀመሪያ ፍተሻ መሆኑ ነው። ወደ ሁለተኛው ፍተሻ ስንቃረብ ታፋው ላይ የታሰረው ሽጉጥ ላይ እጁን በማሳራፍ “ወደ የት ናቸሁ” በማለት በትህና ጠየቀን። ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ እየሄድን እንደሆነ ስንጠቅስለት ሳያንገራግር በትህትና እንድንገባ ፈቀደልን።


ገና… ከኤምባሲው ግቢ ሲገባ በባህል ልብስ እና በክት ልብስ ያሸበረቁት ኢትዮጵያውያን ውበት ከቡናው መአዛ ጋር ተደማምሮ በእጅጉ ያውዳል። የዛሬ የተለየ… ቀን ነው። በስደት በምንኖርባት የሪያድ ከተማ የሚገኘው ኤምባሲያችን ትንሿ ኢትዮጵያ አይነት አብዛኛው ታዳሚ በባህላዊ አለባበስ ከማሸብረቁ ባሻገር ለአፍታ እንኳን ቢሆን የሳዑዲ አረቢያ የኑሮ ውድነት እና የቤተሰብ ክፍያውን የዘነጋ ይመስላል። ይገርማል… እንደዚህ ባለ ልዩነታችን ውስጥ አንድነታችን ጉልህ ሆኖ ይታያል። ሁሉም እንደየባህሉ ያዘጋጀውን ምግብና የባህል እቃዎች መመልከት ምንኛ ያስደስታል። ሁሉም የባህሉን ጭፈራ በየፈርጁ ያስነካዋል። በተመስጦ ለተመለከተው ትንሿን ኢትዮጵያን ያየ… ያህል ቀልቡ በናፍቆት ይናወጣል። ታዳሚው… ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ዝግጅት ያደረገ ይመስላል። ሽር… ጉድ… ይላል። ቤተ መስቃኑ ከሰባት ቤት ጉራጌ ጎን ወይም ሁለቱ ማህበረሰቦች ኩታ ገጠም ሆነን በዓሉን እናሳልፍ በሚል ተስማምተው ስለነበር የእነዚሁ ጉራጌውያን ኩታ ገጥሞ በዓሉን መካፈል የእነርሱ ለሆነው ታዳሚ ሁሉ ትልቅ የሆነ ድምቀት ፈጥሮበት ነበር። የመልካም ግኑኝነት ድልድይ መዘርጋቱ መልካም ጅማሮ ቢሆንም መፈላለጉ ወይም አንድ ሆኖ መታየቱ ለበዓላት ማድመቂያ እና ለሶሻል ሚድያ ወይም ለፖለቲካ ግብዓት ብቻ ባይሆን ይመረጣል።


ታዲያ… እነዚሁ ጉራጌውያን በስምምነቱ መሰረት መደዳውን ተስተካክሎ በተቀመጠ ጠረጴዛ የባሀል ምግባቸውን ደርድረው ስለነበር ክትፎ፣ አይቡ እና ጎመኑ ተደበላልቆ የትኛው የባህል ምግብ የየትኛው እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች ነበር። የባህል ጭፈራውም እንደዚሁ ከጉራጌው በቀር ሌላው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ልዩነነቶቹን ለማወቅ አዳጋች ሆኖበት አምሽቷል። የጉራጌው ወጣት ሁለቱ ጉራጌዎች የባህል እቃዎችን ምግብ የደረደሩበት ቦታ ፊትለፊት በመሰባሰብ የባህሉን ጭፈራ ተያይዞታል። አባቶች በአንድ ጥግ በኩል መደዳውን ተቀምጠው በደስታ የሚራኮተውን ህዝበ ጉራጌ እና ህዝበ ኢትዮጵያን በአድናቆት እና በአግራሞት ያስተውላሉ። እነዚህ አባቶች የበአሉ ድምቀት ከመሆናቸው ባሻገር ባህል እና በዓል ያለ እነርሱ የሚታሰብ አይደለም።

የጉራጌ ሴቶች በባህላዊ ልብስና የሻሽ አስተሳሰር ተውበው ለበአሉ ልዩ ድምቀት አጎናጽፈውታል። ብቻ… ሁሉም የባህል ጭፈራውን በቋንቃው ተያይዞታል። ታዳሚው ከባለፉት አመታት ዝግጅቶች በተሻለ በሚያስብል ሁኔታ በዓሉን እየኮመከመ የአንባሳደረሩን መምጣት ይጠባበቃል። በብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በአል ዝግጅት አምባሳደርና ተጋባዥ እንግዶች የየብሄሩን ዝግጅት ለመቃኘት እነዚያ… ብሄረሰቦች የባህል ምግባቸውንና እቃዎች ለታዳሚው ለማሳየት ያዘጋጁት ጊዜያዊ ቦታ ወይም መድረክ ድረስ መጥቶ መጎብኘቱ እንዲሁም ከተዘጋጀው የባህል ማዕድ መቋደሱ የተለመደና ከበአሉ ድምቀት አንዱ ነው። በበዓሉ ዝግጅት የሚካፈሉት የሁሉም ብሄረሰብ ተወካዮች እንግዶቹ ወደ ማሳያው ቦታው ካልመጡ ከተዘጋጀው የባህል ማዕዱ የማያቋድሱ ሲሆን ከሰዓታት ቆይታ በዃላ አምባሳደሩ ከታዳሚዎች ጋር ያደርጉት የነበረውን ውይይት ጨርሰው በበዓል አዘጋጅ ኮሚቴዎችና በሃገር ሽማግሌዎች ታጅበው በመምጣት ለየብሄሩ ተወካዮች እና አዘጋጆች በደማቅ ፈገግታ ምስጋናቸውን እያቀረቡ በዓልና ባህል ነውና ከተዘጋጀው ማእድ ያዘጋጀውን ማህበረሰቡ ላለማስከፋት ጭምር በትሽ… በትንሹ ወይም ለቅምሻ ያህል ከማዕዱ በማንሳት ወደ ቦታቸው ተመለሱ። የባህል ምግቦች በመስቃን፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በቀቤና፣ በሶማሌ እና በሐረሪ ማህበረሰብ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን ለአንድ ተጋባዥ እንግዳ ከሁሉም ተዘጋጅተው ከነበሩት የባህል ምግቦች ከብዛታቸው አንፃር መቋደሱ የሚከብድ ቢሆንም የጉራጌ የባህል ምግቦች በሪያድ ለአመታት በተደረገው የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ለታዳሚው ተቀዳሚ እና ተመራጭ የባህል ምግቦች ነበሩ። ለእዚያም… እኮ ነው ኢትዮጵያ ተብሎ ሲጠራ የጉረጌ ሰላም ፈላጊነት፣ ጨዋነት፣ ታታሪነት እና የባህል ምግቦች አብረው የሚታወሱት። የበዓል ዝግጁቱና ጭፈራው እስከ ለሊቱ 6፡30 ሰዓት ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም ከበአል አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሮግራሙ ከለሊቱ 7፡00 ሰዓት እብደሚያበቃ ማሳሰቢያ በመሰጠቱ ለበአል ድምቀት ያዘጋጀነቸውን እቃዎችን መሸከፉን ተያያዝነው። በዛሬው ዝግጅት በባህላዊ አብሮነታችን የመጣውን ሁሉ በፍቅርና በክበር ብሉልን ጠጡልን እያለ ሲያስተናግድ የነበረው የየብሄሩ ተወካይ የበጎነቱ ጥግ እጅግ በጣም ያስደምም ነበር።


ውድ ወገኖች አብሮነታችን እና እርስ በራስ መከባበራችን ይቀጥል ዘንድ ምኞታችን የገዘፈ ነው። ያ…አብሮነታችን በታሪክ የሁላችንም የበጎነታችን ወጤት ቢሆን እንጂ የአንዱ ብቻ አልነበረም።


ሰላም ለሁሉም!

ቸር… እንሰንበት!


መስቃን ሚድያ ኔትዎርክ

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

60 views0 comments

Comments


bottom of page