top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

በራስ መተማመንን (SELF CONFIDENCE) ለማሳደግ የሚረዱ አስር ሙያዊ ምክሮች

ለራስዎ ያለዎት ከፍ ያለ ግምት ሌሎች እርስዎን የሚያዩበት መንገድ ጥሩ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና አለው። በራስ የመተማመን ስሜት ሲኖርዎትም በተሰማሩበት ሥራ ላይ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ እርዳታ አለው። ምንም እንኳን በራስ መተማመን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩት ምክንያቶች ብዙዎቹ ከእርስዎ ቁጥጥር ውጭ ቢሆኑም፣ በራስ መተማመንን ለመገንባት የሚረዱ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ። እነዚህን 10 ስትራቴጂዎች በመጠቀም ያልዎትን በራስ መተማመን ከፍ አድርገው ችሎታዎን በትክክለኛው ሁኔታ ሥራ ላይ ማዋል ይችላሉ።

1. አለባበስዎ ጥሩ ይሁን (Dress sharp)።

የእርስዎ አካላዊ ገጽታ እና አለባበስ ላይ ከማንም ሰው በላይ እርስዎ የቀረበ እይታ እና ግንዛቤ አለዎት። ስለሆነም፣ ጥሩ ሆነው እንደማይታዩ በሚሰማዎት ጊዜ፣ ከሌሎች ጋር የሚያደርጉት የሃሳብ ልውውጥ ሂደት ውስጥ ምቾት እንዳይሰማዎት ያደርጋል። ስለራስዎ ገፅታ ግን መልካም አመለካከት ሲኖርዎ ምቾትዎ ይጠበቅና ከሰዎች ጋር የሚያደርጉዋቸው ግንኙነቶች ላይ ልበ ሙል ይሆናል። የራስ ገፅታን ጥሩ ለማድረግ የሰውነትን እና የገላን ንፅህና መጠበቅ፣ ፀጉርን እና ፂምን በቅጡ መከርከም እንዲሁም በወቅቱ ተቀባይ የሆኑ ፋሺኖችን በማዎቅ እና አቅም በፈቀደ መልኩ መከተል ይረዳል። ይህ ማለት በልብስ ላይ ብዙ ገንዘብ ማውጣት አለብዎት ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ ብዙ ርካሽ ልብሶችን ከመግዛት ይልቅ፣ ጥቂት የተመረጡ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች መግዛት አለባበስን ጥሩ ለማድረግ ከመርዳታቸውም በላይ ለረጅም ጊዜ ዘመናዊ ሆነው እንዲቆዩ ስለሚያደርጉ ረዘም ላለ ጊዜ ወጪን ይቀንሳሉ።


2. ሲራመዱ ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ ይራመዱ (Walk faster)።

አንድ ሰው ስለ ራሱ ያለውን ስሜት ለማወቅ ብዙዎች ከሚጠቀሙባቸው ቀላል መንገዶች ውስጥ አንዱ አረማመዱን መመርመር ነው። ዝግ ብሎ የሚራመድ ነው? ሲራመድ ድካም ይታይበታል? ወይስ ሃይል የተሞላ እና አላማ ያለው አካሄድ አለው? በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች በፍጥነት ይራመዳሉ። አፋጣኝ የሆነ ጉዳይ ባይኖርብዎትም እንኳ ፈጠን ብለው በመራመድ የራስዎን መተማመን ከፍ ማድረግ ይችላሉ።


3. ሁሌም ጥሩ የሰውነት አቋም ያሳዩ (Have a good posture)።

በተመሳሳይ መንገድ፣ አንድ ሰው ሰውነቱን የተሸከመበት መንገድ ሰውየው ስላለው የራስ መተማመን ብዙ ይናግራል። የተጣበቁ ትከሻዎች እና የተልፈሰፈሰ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ሰዎች የራስ መተማመን ማጣትን ያሳያሉ። እራሳቸውን ከፍ አድርገው አይመለከቱትም። ጥሩ አቋም በማሳየት ግን በራስ መተማመን ይሰማዎታል። ቀጥ ያለ ሰውነት ይኑርዎ፣ ጭንቅላትዎን ወደላይ ከፍ ያርጉ፣ ከሌሎች ጋር ሲነጋገሩ የዓይን ለአይን ግንኙነት ያድርጉ። ይህንም ሲያደርጉ ሌሎች ላይ አዎንታዊ ስሜት ያሳድራሉ፣ እናም በፍጥነት የበለጠ ንቃት እና ኃይል ያሰማዎታል።


4. ለራስዎ ስለ ራስዎ ማስታዎቂያ ይስሩ (Do personal commercial)

ጠንካራ ጎኖችዎን እና ግቦችዎን የሚያጎሉ ከ 30-60 ሰከንድ የሚዎስዱ ንግግር ይጻፉ። ከዚያም በራስ የመተማመን ስሜት በሚፈልጉበት ጊዜ በመስታወት ፊት ለፊት በመቆም (ወይም ጭንቅላትዎ ውስጥ በማነብነብ) ለራስዎ ይንገሩ።


5. በምስጋና የተሞሉ ይሁኑ (Have gratitude)

ምስጋና ሊሰማዎት የሚያነሳሳዎትን ነገሮች ሁሉ በአዕምሮዎ ውስጥ በመዘርዘር የሚያስቡበት ጊዜ በየዕለቱ ይመድቡ። ያለፉትን ስኬቶችዎን፣ ልዩ ችሎታዎችዎን፣ ወዳጆችዎን እና አዎንታዊ እንቅስቃሴዎን ያስታውሱ። ምን ያህል እርቀት እንደመጡም ለመገንዘብ ይረዳዎታል፣ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ወደ ስኬት ለመሄድም በእጅጉ ያነሳሳዎታል።


6. ለሌሎች ሰዎች ስለ ጥሩ ስራቸው አድናቆትን ይለግሱ (Complement others)።

ስለራሳችን አሉታዊ በሆነ መልኩ ስናስብ፣ ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ማጣጣል እና በጀርባቸው ላይ መጥፎ ነገር መሸረብ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ይህንን የኑሮ ዘይቤ ለማቋረጥ ሌሎች ሰዎችን የማመስገን ልማድ ይኑርዎት። ከሰዎች ጀርባ መጥፎ ነገር መመኘት ወይም መጠንሰስን አስወግደው በሰሯቸው ጥሩ ስራዎች አድናቆትን ለመግለፅ ይሞክሩ። በሂደቱ ውስጥም በጣም ይወደዳሉ፣ በዚህም በራስ መተማመን ይገነባሉ ። በሌሎች ውስጥ ምርጡን በመፈለግና በመመስከር በተዘዋዋሪ ምርጡን ወደ ራስዎ ዘንድም ያመጣሉ።


7. ከፊት ረድፍ ይቀመጡ (Sit in the front row)

ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ ጽ / ቤቶች እና ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ሰዎች መጨረሻ ለመቀመጥ ይጥራሉ። ምክንያቱም በቀላሉ መታየቱ ያስፈራቸዋል። ይህም በራስ መተማመን ማጣትን ያሳያል። በፊተኛው ረድፍ ላይ ለመቀመጥ ሲዎስኑ ይህንን ያለፈቃድ የሚመጣ ፍርሃት አሸንፈው በራስ መተማመንዎን መገንባት ይችላሉ። በተጨማሪም ከዋናው ፊት ለፊት ለሚነጋገሩ ሰዎች በይበልጥ ግልጽ ይሆናሉ።


8. ሃሳብዎን ይግለፁ (Speak up)

በቡድን ውይይቶች ወይም ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ሁኔታ ውስጥ ብዙ ሰዎች ሃሳባቸውን ከመግለፅ ይቆጠባሉ። ምክንያቱም ሰዎች ከንግግራቸው ተነስተው እንዳይገምቷቸው ስለሚፈሩ ነው። ይህ ፍርሃት ትክክል አይደለም። ብዙ ጊዜ ሰዎች ከምናስበው ይልቅ የሰውን ሃሳብ የመቀበል ፍላጎት አላቸው። በእርግጥ ብዙ ሰዎች በተመሳሳይ ፍራቻ የተጠቁ ናቸው። በእያንዳንዱ የቡድን ውይይት ቢያንስ አንድ ጊዜ ለመናገር ጥረት በማድረግ የተሻለ የህዝብ ንግግር ክህሎት እንዲያዳብሩ ፣ ይበልጥ በራስ መተማመን እንዲኖርዎት እና በእኩዮችዎ ዘንድ መሪነትን እና ተቀባይነትን እንዲያገኙ ያደርግዎታል።


9. ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ልምድዎ ይሁን (Work out)

ልክ እንደ አለባበስ አይነት፣ አካላዊ ብቃት በራስ መተማመን ዘንድ ከፍተኛ ሚና አለው። ቅርጽዎ እንደተበላሸ ከተሰማዎት በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርጎ የመታየት እና ሌሎችን መማረክ አለመቻል ስሜት ይሰማዎታል። አካላዊ እንቅስቃሴን በማድረግ አካላዊ ገጽታዎን ያሻሽላሉ፣ ኃይልን ያገኛሉ፣ ለአዎንታዊ ስራም ይነሳሳሉ።


10. የሚያደርጉት አስተዋፅዎ ላይ ያተኩሩ (Focus on contribution)

ብዙውን ጊዜ እኛ ስለምንፈልጋቸው ነገሮች እንጂ የሌሎች ሰዎች ፍላጎቶች እና በሌሎች ላይ ስለሚመጣው ጥሩ ለውጥ አናስብም። ስለራስዎ ማሰብ ካቆሙ እና ለተቀረው ዓለም ላይ ለውጥ እንዲመጣ በሚያደርጉት አስተዋፅኦ (መዋጮ) ላይ ካተኮሩ፣ ያሉብዎት ጉድለቶች አያስጨንቁዎትም። ይህ በራስ መተማመንን ይጨምራል እናም በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ውጤታማነት እንዲሳተፉ ያስችልዎታል። ለዓለም ጥሩ እያደረጉ በሄዱ መጠን የግል ስኬት እና እውቅናንም እየተጎናፀፉ ይሄዳሉ።


52 views0 comments

Comentarios


bottom of page