የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
በአንድ እጅ አይጨበጨብም - ክፍል 01 (በእሙ ኢሳን)
Updated: Sep 3, 2019

በአንድ እጅ አይጨበጨብም ሲባል ለማጨብጨብ ቢሞከርም እንኳን ሌላኛው እጅ ከሌለ ከመንቀሳቀስ በቀር የሚፈለገውን ድምጽ አያመጣም ወይም ድምጽ አልባ ነው። ድምጽ የሌለው ነገር ደግሞ ውጤት የለውም። ለማጨብጨብ ሁለት እጅ መኖር አለበት። ጉዳዩ እንዲህ እሰከ ሆነ ድረስ ደግሞ ለየትኛውም…ለሁሉም ሰው ሌላ ሰው ያስፈልገዋል። ያ… ባይሆን ደግሞ ለሁሉም ነገር ሁለት ባላስፈለገ ነበር።
ለወንድ ሴት ፣ ለጨለማ ብርሃን እያል በአለም ያሉ ነገሮች ሁሉ ግዕዙም ሆነ ህያው አንዱ ለሌላው ያስፈልገዋል ማለት ነው። አንዱ ላንዱ በሚያስፈልግበት በእዚህ የእኛው የዘቀጠ ዘመን ብቻዬን ሃገር አቀናለሁ ማለት ዘበት ነው። ሁሉም በሚችለውና በእውቀቱ ሲረባረብ የሚፈለገው ሰላምና እድገት በሚሰማ ሳይሆን በሚጨበጥ ለውጥ ነገራቶቹ ሁሉ እንደሚጠበቁት ይሆናሉ። ነገር ግን የእኔነት በሽታ በዝቶና አንዱን አስወግዶ የተደላደለ ወንበር ላይ ለመቀመጥ የሚያስቡ ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች በምንኛው የአስተሳሰብ ቀመር እንደሚያስቡ ያለተፈታ ጉዳይ ነው።
በአጼዎቼ ዘመን ከሆነ በዛ… ዘመን እርስ በእርስ መዋደድ፣ መተፋፈርና መከባበር የነበረበት ወቅት ነበር። በዘመናዊው ዘመን ከሆነ ደግሞ መተባበርና አብሮ ማደግ እየተለመደ የመጣበት ወቅት ሲሆን ይኸኛው ወይም የእኛው ዘመን ግን ከሁለቱም የወጣ ነው። ታዲያ ይህ ያለንበት የሃገራችን ሁኔታ እና ወቅት ዘምነ “ሰይጣን” እንበለው?
የዘመነ ሰይጣኑ ጥሎ ማለፍ፣ ገሎ መፎከር፣ ተችቶ መርካት፣ ንቆና አጣጥሎ መኩራራት ብቻ ነው። የዘመነ ሰይጣኑ በሰውኛ አመለካከት ሲቀየር ለመኖር ከፈለግክ እኔ በቀደድኩልህ ቦይ ፍሰስ። አልያም ደምህ ይፈሳል! የሚል አላማን አንግቦ የምትሰራው እንዳትሰራ። የምታስበውን እንዳትተገብር። የሰጠህን እንዳታመሰግን የሰራልህን ሰራ እንዳትል የሚል መመሪያ እያሰጠ ሰው በሙሉ እንዲገፋፋና እንዲጠላላ ሌተ ቀን የእኩይ ተግባራ ሃሳባቡን በማንገብ እኩይ መረቡን ይዘረጋል። እናም የሰይጣናዊ አባሎቻቸውን በመመልመል ያባላቱን ቁጥር ለማብዛት ይኳትናሉ። በምድርም ሆነ በሰማያዊው አለም ቦታ ላያገኙ በባዶ ይፍጨረጨራሉ። ታግሶ ቀን እስኪወጣ ለጠበቀ ያቺን ክፉ ቀን ከመናፍስቱ ያመልጣል። ያለበረታው ደግሞ በእነዚሁ የእርኩሳን አለቃ ይመለመልና አባል ይሆናል።
አባላቱ ሴጣናውነታቸው ሰለሚያመዝን እኛ ስሙን እንጂ እንስማችሁ አይሉም። እኛ ትክክል ነን እናንተ ግን ከጅምሩ የተሳሳታችሁ ስለሆነ አድማጭ እንጂ ተናጋሪ አትሁኑ! በተሰመረላችሁ መስመር ብቻ ሂዱ! እንጂ አትጠይቁ ይሉናል።
በመልካም ተባብሮ መተግበር እየተቻለ መጠላለፍና ገድሎ መጀገን ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? በሃገራችን የሚታየው ነባረዊ ሁኔታ ይህ ነው። ሁሉም እንደ አቅሙ እና እንደየችሎታው ቢተባበር ከድህነት አሮንቃ በወጣን ነበር።
ይቀጥላል...
በእሙ ኢሳን
ሪያድ ሳኡዲ አረቢያ