የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ቢኖር …(ሚስጥረ አደራው)

ቀን ቀን ከሰው ጋራ፤ የረሳሽው ጭንቀት፤ ሃሳብ ከነበረ
ሌሊቱን ጠብቆ፤ ሲጋፋሽ ካደረ
በቅዠት አለም ውስጥ፤ ላነባሽውን ለቅሶ
ፊትሽን የሚያደርቅ፤ በመዳፍ እጆቹ እንባሽን አብሶ
ቢኖር
ከጠበበ ጊዜ፤ ከተጣበበ ሰዓት፤ ከጠፋ ደቂቃ፤ መናፈቅሽን አውቆ
ጊዜ ዘግኖ ‘ሚሰጥ፤ እልፍ አእላፍ ዘመን ከሰው ሁላ ነጥቆ
ቢኖር
የአለም ኦናነንት፤ የፍቅር መመነን፤ እንደሳት ሲፈጅሽ
አውሎ ነፋስ ሆኖ፤ ፍቅር እንደአሸዋ፤ የሚያዘንብ ከደጅሽ
እንደ መቅደላዊት፤ ግድቡን የጣሰ ፤ እንባ እንኳን ቢፈስሽ
እያንዳንዷን እንባ፤ በጣቱ ገድቦ የሚያባብስልሽ
ወይም
ሀዘን በቀደደው፤ በግዜያዊ ክፍተት፤ ስሜትሽን ሳይሰርቅ
ስታለቅሺ ካየ፤ የእንባሽን ዘላላ፤ በትንፋሹ ‘ሚይያደርቅ
ቢኖር
ተራራ ላይ ቆሞ፤ ጊዜን እያሳተ
ልብሽን የሚያሞቅ፤ የንጋቷን ጀንበር በእጁ እየጎተተ
ነይ ብሎሽ ስተመጪ
በደበተ እለት፤ ከጸሃይዋ ቀድመሽ ከቤትሽ ብትወጪ
ደመናውን ገፍቶ
ጊዜዋ ባይደርስም ፤ ጸሃይዋን ወትውቶ
ጠዋትሽን ‘ሚያበራ
ገላሽን የሚያጥብ፤ በንጋትዋ ጮራ
ቢኖር
ቀን ቀን ሲጎድለው፤ ፊቱን ባንቺ ሲያዞር
አለኝ ያልሽው ሁሉ፤ እንደ እፉዬ ገላ ከመዳፍሽ ቢበር
ክንዶቹን ዘርግቶ
በእቅፉ አስገብቶ
ሌላ አለም ‘ሚወስድሽ
ያጣሽውን ሁሉ፤ በጥፍ ‘ሚያሳይሽ
ቢኖር
ከውጥንሽ ቀድሞ፤ መሳካቱን ‘ሚያይ
ህልምሽን ‘ሚፈታ፤ ባንቺ አይምሮ ውስጥ ጨርሶ ሳይታይ
ባለም ጥርጣሬ፤ በ’አይሆንም ፍራቻ፤ መንፈስሽ ከራደ
እንደ ጥምቀት ታቦት ፤መንገድሽን ‘ሚያጥን ቀድሞ እየወረደ
ምላሽ ሳይጠይቅሽ፤ የልብሽን ጓዳ በፍቅር ‘ሚሞላ
የፍቅር ተመኑን ዋጋ ሳያሰላ
ቢኖር
ብርድ ብርድ ያለሽ ቀን፤ ከለኮሽው እሳት ቀድሞ የሚያሞቅሽ
ከዝናብ ተማክሮ፤ ሳቅ እያዘነበ፤ ከልብ ‘ሚያስቅሽ
በመብረቁ ጩኸት፤ ቢደነግጥ ልብሽ
በመዳበስ ብቻ፤ ድፍረት የሚሰጥችሽ
ቢኖር
ይህን ሁሉ ሰጥቶ በቃኝ የማይልሽ
ቁልፍ የሌለው መግቢያ፤ ስታንኳኪ አይቶ በር ‘ሚከፍትልሽ
በተከፈተው በር፤ አንቺን የሚመጥን ሌላ አለም ፈጥሮ
ያለውቅቱ ዘርቶ ፤ያለግዜው አጭዶ፤ የማያልቅ አዝመራ ከምሮ ከምሮ
‘እፎይ’ በይ የሚልሽ ፤ ዘላለም እረፊ
በብቻሽ አለም ውስጥ፤ ሺህ ጭሰኛ ሆኖ ከቶ እንዳትለፊ
ቢኖር አንድ አፍቃሪ
እኔ ነኝ ተጣሪ
ከለየን ወንዝ ወዲያ፤ ወንዝ ወንዙን እያየው
በውሃው ነጸብራቅ፤ ውብ ፊትሽን ስዬ እጠብቅሻለው
እስከዛ
ፍቅሬን ከግጥም ጋር በሀብል አስሬ፤
ወንዙ እንዲያቀብልሽ ወርውሬልሻለው!
(የዚህ ግጥም መነሻ ሀሳብ የለምን ሲሳይ “Invisible Kisses” ሲሆን፤ እኔ በተረዳሁት መጠን የተወረሰ ሀሳብ መሆኑ ይታወቅልኝ። Inspired by Lemn Sisay’s “Invisible Kisses” poem.)