• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ባለከዘራው ኮለኔል (በጌትነት ተስፋማርያም)


ፊታቸው ላይ የአልበገርም ባይነት ስሜት ጎልቶ ይነበባል፤ እያነከሱም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። መገናኛ ራዲዮናቸውን እና የምርኩዝ ከዘራቸውን ይዘው የጁንታው ቡድን አመራር ያለበት ቆላ ተንቤን አቅራቢያ በምትገኝ ሰዋራማ ስፍራ ላይ ጦሩን እየመሩ ይገኛል።

ኮሎኔል ሻምበል በየነ ይባላሉ። በቆሙበት የውጊያ ትዕዛዝ እየሰጡ ኮስታራ ፊታቸውን ወደእኛ ዘወር አደረጉ። ቆስለው አልታከምም በማለት በወኔ እየመሩ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራር መሆናቸውን ሰማንና ታሪካቸውን እንዲያካፍሉን ጠየቅናቸው።

ድንገተኛ ፈገግታ እያሳዩ ቀድሞም የጁንታው አባላት ውጊያ ሰራዊቱ ላይ ሊከፍቱ እንደሆነ ጥርጣሬ ነበረኝ በማለት በተረጋጋ ስሜት ትውስታቸውን ማጋራት ጀመሩ። እኔ የ31ኛ ክፍለጦር ምክትል የኦፕሬሽን አዛዥ ነበርኩ ዋና አዛዡ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ቀደም ብሎ የተወሰኑ አባላትን ሽሬ ድረስ ወስዶ ሲሰበስብ የሆነ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል አስበው እንደነበር።

ማታውኑ ችግር ሊኖር እንደሚችል በማመን በግሌ ዝግጅት አደረግኩ። ስዘጋጅ በባንክ አካውንቴ የነበረውን ጥቂት ገንዘብ በቤተሰብ አዞርኩ። ከዚያም ጥቃት ለማድረስ ከበባ ሲፈጽሙብኝ ተከብቤያለሁ በሚል ለበላይ አካላት ሪፖርት አደረኩ

በመከላከያ ላይ ጥቃት ሲፈጸምም የክፍለጦሩ አዛዡ ከድቶ የጁንታውን ቡድን ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ የክፍለጦር ኮሚቴ ወይም ከበታች አዛዦች አባላት ጋር በመሆን ግብግብ ፈጸምን። እኔም ከፊቴ ያለውን በጥይት መትቼ ጣልኩ። እኔ ጋር የተጀመረች የመከላከል ተኩስ እስከታችኛው የሻለቃ አመራር ድረስ እየተደማመጠ የመከላከል እርምጃውን ወሰደ። በኋላም የካምፑን ከበባ አጠናቅቄ ስወጣ ደግሞ የልዩ ኃይል ከውጭ ጠበቀኝ የሚሉት ኮሎኔል፤ እነሱንም ጥሼ በመውጣት ከስምንተኛ ሜካናይዝድ ጦር ጋር ተቀላቀልኩ ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሱታል።

በወቅቱ እግራቸው ላይ በጥይት መመታታቸው እምብዛም ቁብ አልሰጡትም። በዚያ ሁኔታ ላይ እያሉ ወደኤርትራ በማፈግፈግ በዚያ ከሚገኘው እና በጁንታው ታጣቂ ጥቃት ደርሶበት ከሚገኘው ጦራቸው ጋር ተገናኙ። ጦሩን አደራጅተው በመመለስ ሽራሮ ፣ሽሬ፣ አዲ አደራይ፣ አዲነብሪ እና በርካታ ቦታዎች በማስለቀቅ የህግ ማስከበር እርምጃቸውን በብቃት መወጣትም ቻሉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከታፋቸው የሚፈስ ደም እንደ ነበር በቅርበት የሚያውቋቸው ወታደሮች ይናገራሉ። ቁስሉን በየሶስት ቀኑ በጦር ሜዳ አካባቢ እየታከምኩ አንዷ ጥይት ወጣች የሚሉት ኮሎኔል ሻምበል፤ ምርኩዝ ይዘው ግዳጃቸውን መወጣታቸውን ነግረውናል። ዋና አዛዡ ግን የጁንታውን ቡድን በመቀላቀል ለጁንታው አመራር ሽፋን ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

አሁን ላይ ቆላ ተንቤን ላይ ወንጀለኛ ለማስመለጥ እና ወንጀለኛ ለመያዝ ዋናው እና ምክትል አዛዡ ፊት ለፊት ተፋጠዋል። ምክትል አዛዥ ዋናውን ከነጀሌዎቹ እያባረረ እርምጃ እየወሰደበት ይገኛል። ከሚመሩት ጦር ጋር በርካታ ሀገር የከዱ ጄኔራሎችን እያባረሩ ቆላ ተምቤን ላይ ያደረሱት ኮሎኔል ሻምበል፤ እዚህ በመድረሴ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ሲሉ በኩራት ይናገራሉ።

ቆላ ተምቤን ላይ የመሸገውን የከሃዲው ቡድን አመራር አባላት ለህግ ሲቀርቡ በተሻለ ህክምና በጥይት የተመታውን እግራቸውን ሊታከሙት እንደሚችሉ እንደተወርዋሪ ኮኮብ መሳይ ብልጭታ ባለው ፈገግታቸው ታጅበው በለሆሳስ ነገረውናል። ቦታው ላይ ቆስለውም ቢሆን ጦሩን እየመሩ መገኘታቸው ለሰራዊቱም ብርታት መሆኑን አልሸሸጉንም።

በእጃቸው ከዘራቸውን ጨብጠው የሚንቀሳቀሱት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ በጉዳት እያሉም ቢሆን በህግ ማስከበር እርምጃ የጁንታውን አመራሮችን ለመያዝ ፀሐይ ውርጭ ሳይሉ በመታገል ላይ ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን በየጊዜው አታጣም የሚባለው ብሂል እውነት መሆኑን ያረጋገጠ ነው።


አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013 ዓ.ም

27 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean