top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ባሻ አሸብር በአሜሪካ”

መንግሥቱ ለማ

የዛሬ አሥር ዓመት፥ በታላቅ ሹመት

አሜሪካ ልኮኝ፥ ነበረ መንግሥት፤

ዋሽንግቶን ገብቼም፥ ዋልሁ አደርሁኝና

ሽር ሽር ስል ሳለ፥ ባንድ አውራ ጐዳና

አላፊ አግዳሚውን፥ ጥቁሩን ነጩን

ሳይ ስመለከተው፥ በኢትዮጵያዊ ዐይን

የውሀ ጥም ደርሶ፥ ስላረገኝ ቅጥል

ከመንገድ ዳር ካለች፥ ካንድ ትንሽ ውቴል

ጐራ አልኩና፥ ገና ከወምበር ላርፍ ስል

ተንደርድሮ መጣ፥ የውቴሉ ጌታ

አማረው ቋመጠ፥ ከጀለው ሊማታ፤

“አብዷል ሰክሯል እንዴ? ምንድን መሆኑ ነው?

በል ንካኝ በዱላ፥ ግንባርህን ላቡነው!”

ብዬ ስነጋገር፥ ሰምቶ ባማርኛ

አሳላፊው ሆነ፥ አስታራቂ ዳኛ፤

ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፥ እንዳገራችን ሕግ

አክብሮ ጠየቀኝ፥ ምን እንደምፈልግ፤

እኔም ጐራ ያልሁት፥ የሚጠጣ ነገር

ለመሻት መሆኑን፥ ነግሬ ከወንበር

“ይቅርታዎን ጌታ፥ አዝናለሁ በጣሙ

ምናምኒት የለም፥ በከንቱ አይድከሙ”

አለና እጅ ነሣኝ፥ ሳቁን እየቻለ

“ውሀም የለ?” ብለው፥ በሳቅ ገነፈለ፤

ቤቱን የሞላው ሰው፥ ሁሉም አጨብጭቦ

“ብራቮ!” ተባለ፥ “ብራቮ! ብራቮ!”

በጣም ተገርሜ፥ ደንቆኝ ‘ያየሁት

ከዘራየን ይዤ፥ ሄድሁኝ ወጣሁት፤

ሀሳብ ገብቶኝ እደጅ፥ ሳሰላስል ቁሜ

ያን ቂዛዛ መስኮት፥ ባስተውለው አግድሜ

አራዳ ግሪኮች፥ እንደሚሸጡት

ያለ በያይነቱ፥ አየሁኝ ብስኩት፤

ትዝ አለኝ “አራዳ አዲሳባ ሆይ

አገርም እንደ ሰው፥ ይናፍቃል ወይ?” …

አጐመዠኝ በሉ፥ ሳይርበኝ ጠግቤ

አስተውለው ጀመረ፥ መስኮቱን ቀርቤ፤

የምገዛውንም፥ በልቤ ቆጥሬ

ዳግም ልገባ ስል፥ በስተበሩ ዞሬ

ዘወር ብዬ አያለሁ፥ የውቴሉ ጌታ

ተኩሮ  ያየኛል፥ ወደኔም ተጠጋ

“ስንት ነው ሰውዬ፥ ያንዱ ብስኩት ዋጋ?”

የያዘው አባዜ፥ ብሎት አላናግር

ዐይኑ ደም ለበሰ፥ ይጉረጠረጥ ጀመር፤

“ዓለም ሁሉ ያውቃል፥ መሆኔን ታጋሽ …

ትግሥቴ አሁን አልቋል

ጥፋ ብረር ሽሽ! …

አገጭህን በቦክስ፥ ሳላፈራርሰው

ይህ ፈጠጤ ዐይንህን፥ እዚህ ሳላፈሰው

እሱቄ መግባትህ፥ አንሶህ አሁንስ

መስኮቴ ፊት ደሞ፥ ልትልከሰከስ?!

ገበያ አላገኝም! ደምበኛዎቼም

እዚህ አንተን ካዩ፥ ዳግመኛ አይመጡም

ሥራ ሥራ እኮ ነው፥ አይገባህም እንዴ?

ወግድ! አትገተር፥ ይቋረጣል ንግዴ!”

ይህንን እንዳለ፥ ቁጣው ጠና ጋለ

አገጨና ጉንጨም፥ በቡጢ ነገለ

በቦክስም አይለኝም፥ መልሶ መልሶ!

እስኪሸረፍ ድረስ፥ ጥርሴ በደም ርሶ!

ዠለጥ አደረግሁት፥ በያዝሁት ከዘራ

ግና አልጠቀመውም፥ ዘበኛ ተጣራ፤

ፖሊስ ቢሮ ሄድን

እሱ ተለቀቀ

አሸብር ከልካይ ግን፥ እወህኒ ማቀቀ፤

ማን ሊሰማኝ እዚያ፥ ዘሬን ብቆጥር

ብሸልል ባቅራራ፥ ወይስ ብፈክር

ደረቴ ላይ ያለው፥ ያገሬ ባንዲራ

ያምራል ተባለ እንጂ፥ ከብሮም አልተፈራ!

የሞጃው ተወላጅ፥ የጠራሁት መንዜ

ሸጐሌ ሻንቅላ፥ ተብዬ መያዜ

በግፍ እንደሆነ፥ ባሰት በውሸት

አቃተኝ ማነንም፥ ከቶ ማስረዳት፤

ሲቸግረኝ ጊዜ፥ አንዱን ተጠግቼ

‘ሻንቆን’ እንዲህ አልሁት፥ ነገሬን አስልቼ፤

“ሰማኸኝ ወንድሜ፥ አላሳዝንህም

በሰው ጠብ ገብቼ፥ በከንቱ ስደክም?

“አውቃለሁ ከጥንትም፥ ነጭና ሻንቅላ

በቂም እንደኖረ፥ ሲዋጋ ሲጣላ

እኔ ግን ሐበሻው፥ ምን ወገን ልለይ

በማይነካኝ ነገር፥ ለምን ልሰቃይ?

እንካ … ጠጉሬን እየው፥ … ሸጐሌ አይደለሁም

ፊቴን ተመልከተው … እንዳንት አልጠቆርኩም

ቀይ ዳማ ነኝ … እየኝ፥ ይሁን ጠይም ልባል …

እኔን መቁጠሪያ ራስ፥ የሚለኝ ሰው አብዷል!

“ዘራችንም ቢሆን፥ ከነገደ ሴም

ሲወርድ የመጣ ነው፥ ከዳዊት ካዳም

የንግሥተ ሳባን ታሪክ፥ ሰምተህ የለ?

ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ ተባለ …

ዛጔማ ከገረድ፥ ነው የተወለደ …

አያወጣው ወጥቶ፥ ከዙፋን ወረደ፤

የካም ልጆች ናችሁ፥ እናንተ ጥቁሮች

ፈንጆችም ናቸው፥ የያፌት ልጆች …”

ብዬ እንደጀመርኩኝ፥ ታሪክን ላስጠናው

ባጭሩ አቋረጠኝ፥ ትግሥት አጣ ሰሚው፤

“እንዲህ ያል ንግግር፥ ያሰኛል አላቲ!

ባሻ አሸብር ከልካይ፥ ልጠይቅህ እስቲ

ገና አንተ ነህና፥ ኢትዮጵያዊ

አይደለሁም ልትል፥ ጥቁር አፍሪካዊ?!

“ምን ይሆናል እንጂ፥ አንተን ላይዘልቅህ

ነበረኝ ባያሌው፥ ብዙ እምነግርህ …

“ቁጥርህ ከማን እንደሁ፥ ከነጭ ወይ ጥቁር

ማወቅ ቢፈልግህ፥ ወዳጄ አሸብር

እነጮች ቡና ቤት፥ ገብተህ ቡና ጠጣ

ወይ በባቡር ስትሄድ፥ አብረህ ተቀመጣ!

ይህም ባይቻልህ፥ ሞክር ባልደረባ

ነጮች እገቡበት፥ ሆቴል ልትገባ፤

“ባንተ አልተጀመረም፥ ያዳሜ ምኞት

ከተጠቃው ‘መራቅ’፥ አጥቂን ‘መጠጋት’

ኀይለኛውን ‘መውደድ’፥ ደካሙን ‘መጥላት’ …

ሰው ባያቱ ይምላል፥ አባቱ ሳይከብር

ማነው የድሀ ልጅ፥ ዘሩን የማይቆጥር?”

እስከ ዛሬ ድረስ፥ ይህ አነጋገር

ሲታወሰኝ አለ፥ ባሰብሁት ቁጥር፤

ይመስገነው ገባኝ፥ ከጊዜ በኋላ

‘አማራ’ ‘ጊሚራ’፥ ቢባልም ‘ሻንቅላ’

‘ሱማሌ’ ‘ኪኩዩ’፥ ‘ሡዋሂሊ’ ‘ባንቱ’

‘ኩኑኑሉሉ’ ‘ማሣይ’፥ ‘ኔግሮ’ ‘ባማንጓቱ’

ማለት እንደሆነ፥ ስልቻ ቀልቀሎ፤

ቀልቀሎ ስልቻ፥ ስልቻ ቀልቀሎ

ስልቻ ስልቻ፥ ቀልቀሎ ቀልቀሎ።

.

መንግሥቱ ለማ

(1950ዎቹ)


32 views0 comments

Recent Posts

See All

Comments


bottom of page