top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ባእድ አምልኮንና ፖለቲካዊ ሴራን ማን በመስቃን ማህበረሰብ ላይ ዘራ?"ልጄ ከአህመድ ኡስማን ጋር እንዳትውል"


ከእንሴኖ መልስ የሐሙስ ገበያ መዞሪያን አልፎ ኢሌ ከመድረሱ በፊት የሚገኘውን ዳገት ወጥቶ ጨረሰ። ከመንገዱ በስተቀኝ በኩል ባለው ጠርዝ አንድ ሽማግሌ በእግራቸው ያዛግማሉ። ጠራራ ጸሃይ ቢሆንም ነጭ ጋቢ ደርበዋል። ጋቢው አድፏል። አህመድ ኡስማን የመኪናውን ፍጥነት እንደመቀነስ አለና አለፋቸው። ሽማግሌው እጃቸውን አውለብልበው እርዳታ ባይጠይቁም «ያዘነ ይጫነኝ» በሚል ስሜት የመንገዱን ጠርዝ ይዘው የሚያዘግሙ ይመስላል። የተቸገርን መርዳት የማይታክተው አህመድ ኡስማን ለሽማግሌው እርዳታ ለመስጠት አመናታ። «ግችም» የሚል አግላይ ስምን በመስቃን ህዝብ ጫንቃ ላይ የተቀመጡ በዝባዞች ጭነዋል። ተከታዮቻቸው (ሙሪዶች) የአግላይነቱን ሴራ ያባብሳሉ። አህመድ ኡስማን ደግሞግችምነው። እኔነቴን አውቀው የነጻ ግልጋሎቴን እንደ መቅሰፍት ያዩታል በሚል ፍራቻ ነበር ያመናታው። በድንገት መኪናውን "ሲጥጥጥ..." አርጎ አቆመ። የሗላ ማርሽ አስገባና ወደ ሗላ መንዳቱን ቀጠለ። በተሳፋሪ በኩል ያለውን መስታወት ክፈት ብሎ አዘዘኝ። መስኮትን በፍጥነት ወደ ታች ዝቅ አደረጉት። "ዋጆ የት ነው የሚሔዱት" ሲል ጠየቃቸው። እንደ ማመንታት እያሉ ቦታውን ነገሩት። ሸርሸራን አልፎ እሬሻ ወንዝ ከመደረሱ በፊት ያለ መንደር መሆኑን አስታውሳለሁ።


"ይግቡ አላቸው" እኔን ወደርሱ ጠጋ እንድል እጁ ምልክት እየሰጠኝ።

"ፈረንካ እ እ" አሉ ፈራ ተባ በማለት።

"በብላሽ ነው" አላቸው።


መኪና ውስጥ ገቡ። ጉዝ በመጀመራቸው ብቻ ሳይሆን በመቀመጣቸው እፎይታቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል። ተጫዋቹ አህመድ ኡስማን ስለ አዝመራ፣ ስለ ከብቶች፣ ስለ ድሮ ህይወትና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማንሳት መኪና ውስጥ ዘና እንዲሉ አደራጋቸው። በመረጋጋት ውስጥ የነበሩት አዛውንት ጎሮሮ አቸውን ጠረግ ረግ አድርገው «ልጄ» በማለት አትኩሮቱን ሳብ አደረጉ። "አንተ ጥሩ ሰው ነህ፣ የአንተን አይነት መኪና የሚነዳ አህመድ ኡስማን የሚባል ሰው አለ እርሱ እንዳያበላሽህ" አሉት። ፈገግ አለና ጨወታውን ቀጠለ።

*** አንድ ታጋይ ለውጥን ለማምጣት ሲንቀሳቀስ የመጀመሪያ ፈተናው ለውጥን ከሚያመጣላቸው የራሱ ወገን ከሆኑ ሰዎች እንደሆነ ታሪካዊ ሰነዶች ያሳያሉ። አህመድ ኡስማን የመስቃን ህዝብ የራሱ ባልሆኑ ጸጉረ ልውጦች በሐይማኖት ስም እየተበዘበዘ ነው። ልጆቹ በባእድ አምልኮና በጫት እየተኮላሹ ነው። ትውልድ እየመከነ ነው። ቀጣዩን ትውልድ መታደግ ያስፈልጋል በሚል እሳቤ የሚታገል ነበር። ከፈጣሪ ይልቅ ግለሰብን አማልክት አድርገው የያዙ ሰዎች «አቡል ጀበል» የሚባል ምድራዊ ተመላኪያቸውን መተው አልቻሉም። የመስቃን ህዝብ « የአቡል ጀበል ኢንዱስትሪ መሆኑ ማብቃት አለበት» የሚል መከራከሪያን ያነሳ ነበር አህመድ ኡስማን። እንደ ማፍያ የሚንቀሳቀሰው «አቡል- ጀበላዊ» እሳቤ ከአርሶ አደሩ አዝመራን በገፍ ይመነትፋል፣ ምርጥ ወይፈንን ነጥቆያርዳል፣ የሰባሙክትን በአይኑ ካየ አርዶ ያጣትማል፣ ምድራዊና ሰማያዊ ተዓምር አለኝ በማለት ሐዲያ (ስጦታን) በገፍ ይቀበላል፣ ሌላው ቀርቶ በውበት ፈካ ብለው ለጋብቻ የደረሱ የመስቃን ልጃገረዶች ክብር በመድፈር ህይወትን ያበላሻል፣ ለበረካ ብሎ የቤት እመቤቶችን ያማግጣል። ይህ የታፈነ የመስቃን ልጆች በድል ነው። የፊውዳል ስርዓት ቢገረሰስም መስቃን ዛሬም ቢሆን በሐይማኖት ፊውዳሎች ምድራዊና ሰማያዊ ህይወቱ እየተበዘበዘ ነው። በሐይማኖት ስም በመስቃን ጫንቃ ላይ የተጫኑትን «አቡል-ጀበላዊ» አምባገነኖችን አውርዶ ለውጥን ለማምጣት ውጣ ውረዱ ቀላል አልነበረም። ብቃት ያላቸው ኡለሞች፣ ባለሐብቶች፣ የማህበረሰብ መሪዎችና የነቁ የመስቃን ተወላጆች «ግችም» የሚል መጠሪያ እየተሰጣቸው ይገለላሉ። በመገለላቸው የሚገጥማቸው ማህበራዊ ውጣ ውረድና ቀውስ «ከራማ» ወይም (ተዓምር) የሚልመጠሪያ ይሰጠውና ህዝብ የበለጠ እንዲሳሳት ይደረጋል። አህመድ ኡስማን ይህንን ቤተሰባዊ የማፍያ ሰንሰለት አሳምሮ ያውቃል። ከ1950ቹ መጨረሻ ጀምሮ የለውጥ ንቅናቄ ውስጥ በመሳተፉ ግችም ለሚለው አማጺያን ቡድን ያልተሾመ መሪ (de facto leader) ሆኗል። እኚህም ሚስኪን አባት በዚያ "አቡል ጀበላዊ" የስም ማጥፋት ዘመቻ ተጠልፈዋል። አህመድ ኡስማን የሚባል ጭራቅ በሐሳባቸው ስለዋል። በተቆርቋሪነት፣ በአዛኝነት መኪናው ውስጥ አስገብቶ ወደሚፈልጉበት ቦታ የሚያደርሳቸው ግለሰብ አህመድ ኡስማን መሆኑን አልተረዱም። «ከራማ አለን» በማለት ከመስቃን ህዝብ ገንዘብ ሰብስበው የተንፈላሰሰ ኑሮ የሚኖሩት «አቡል ጀበላውያን» እኚህን የእድሜ ባለጸጋ መንገድ ላይ ቢያዩ ገቢና ላይ አስገብተው ግልጋሎት አይሰጧቸውም። ምን አልባትም «የአቡል ጀበላውያን» ቤተሰቦች መኪና እየነዱ በመንገድ ሲያልፉ ንፋሱ ስለነካቸው «በረካ አገኛለሁ» ብለው ቢኖሩ አይገርምም።


ኢማሞ ሸሊላ

ኢማሞ ሸሊላ

የቃጥባሬ ንፋስ ወደ እኛ ንፈሺ

አባ ፋሪስ ይዘሽ ቶሎ ተመለሺ


ተብሎ በሚዘፈንበት አካባቢ የነርሱ መኪና የተቸገረን ባይረዳም የሚያነሳው ንፋስ እራሱ በረካን ያመጣል ብሎ ጭው ባለ የመሳሳት ሜዳ ላይ የሚሮጠው ብዙ ነው። *** አህመድ ኡስማን ሽማግሌውን እያጫወተ ሸርሸራን አለፈ። ሾፌሩ እራሱን አህመድ ኡስማን ከሚባል አሳሳች እንዲጠብቅ የሚመክሩት አዛውንት ምክራቸውን አላቆሙም። መኪናውግን ቆመ። ገቢና ውስጥ የነበሩት አዛውነት በሩን ከፍተው ውረዱ። እግሮቻቸው መሬቱን እንደነኩበቀኝ እጃቸውበሩንይዘው አንገታቸውን ወደ ገቢና ውስጥ አስገቡ። ለምርቃት መዘጋጀታቸው ያስታውቃል። አህመድኡስማን ከመናገራቸው በፊት ቀደም ብሎ ድምጹን አሰማ። «በነገራችን ላይ አህመድ ኡስማን ማለት እኔ ነኝ» አላቸው። ሽማግሌውደነገጡ።የ«አቡል-ጀበላውያን» ከራማ መሬት ውስጥ ሰንጥቆ የሚያስገባቸው ይመስል ተርበተበቱ። ወዲያውኑ «ገብቶኛል› አይነትምልክት ሰጡት። ቃላትን ለማውጣት ታገሉ። የጌቶቹ ከራማ የሚሰማቸውይመስል ግራቀኝ አማተሩ። እንደምንም ተሟምተው በሹክሹክታ «በረካ ሁን» አሉት። ምላሳቸውና ጎሮሮአቸው በመተባበር ያላወጡት ድምጽ አለ። የታፈነ ድምጽ። ዛሬም የመስቃን ልጆች የታፈኑበት ድምጽ። ሽማግሌው በአዘኔታና «ነገርሩ ገብቶኛል» የሚሉ መልእክትን የሚረጩ ብርህናማ አይኖች ነበሯቸው። አዎ የድሮ ሰዎች ብዙ የሚያውቁት ነገር አለ። ብዙ የመስቃን ክዋክብት «በአቡል ጀበላውያን» ሴራ ደብዝዘዋል። መስቃን አውራ እንዳይኖረው «አቡል ጀበላውያን» ቡዳ ሆነውበልተዋል። የአቡል ጀበላውያን የሐማኖት ሴራ ዛሬም ወደ ፖለቲካው ተሸጋግሮ ካጎራባች ወረዳ ተራራውን ወርደው የመጡ የፖለቲካ አሳነባሪዎች የመስቃንን የወደፊት እጣ-ፈንታ ለመብላት እየተዘጋጁ ነው ሲሉ ዛሬም «የፖለቲካ ግችሞች» ቅሬታን ያሰማሉ። ሽማግሌው ጋቢያቸውን እያስተካከሉ ወደ ፊት አመሩ። መንገዱን እንዲያቋርጡ አህመድ ኡስማን ቆሞ ጠበቃቸው። መንገዱን አቋርጠው ከሌላኛው ጠርዝ ደረሱ። አንገታቸውን ቀስ አርገውአዞሩ። እጃቸውን እንደምንም እስከ እምብርታቸው አነሱና እንደ መሰናበት አሉ። አህመድ ኡስማን መኪናውን አስነስቶ ወደ ቡታጅራ ማምራቱን ቀጠለ። ሌላ የትግል የትግል ተልእኮ እና ሌላ የለውጥ ጉዞ ከፊትለፊቱ ይጠብቀዋልና።

156 views0 comments

Comments


bottom of page