top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ተሳዳጅ ወሎየዎች! (አብዱልጀሊል አሊ ካሣ)

             ራሴን ወገቤን…. ብሎ ሳይናገር

             እንዲህ ሆኖ ቀረ …የወሎማ ነገር! (1)

በኢትዮጵያ ታሪክ ድርቅ ርኅብ፣ ተስቦ የመንግሥት ጉዳይ ሲሆኑ አይታዩም(2) ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ጥሎ ለአቢዮቱ ፍንዳታ ነዳጅ የነበረው የወሎ አጀንዳ ነው፤ የ1964ቱ ርሃብ በወሎ ብቻ ከሁለት መቶ ሺህ ሰው በላይ ጨርሷል፡፡  ይህ ርሃብ ለ1966ቱ አብዮት ፍንዳታ ከፈተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የወሎ ድርቅና ርሃብ ያስከተለው ዕልቂት በ1967 የመርማሪ ኮሚሺን እንዲቋቋም ረድቶ አንዳንድ ባለሥልጣናትን በሃላፊነት አሰጠይቋል (3)፡፡ በወቅቱ የነበረውን የፓለቲካ ትኩሳት ለማብረድ በ1966 መጋቢት 16 ቀን ንጉሡ ሹማምንቶቻቸው በህግ አግባብ እንዲመረመሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በልጅ እንዳልካቸው መኮነን በኩል ቀርቦ በፓርላማ ማሻሻያ ተደርጎበት በወቅቱ ስልጣን ላይ ያሉና ቀድሞ ባለስልጣን የነበሩ  የመንግሥት ሹማምንትን እንዲመረምር የተቋቋመው የምርመራ ኮሚሲዮን በራሱ አነሳሽነት ከጀመረው የምርመራ አጀንዳ ተቀዳሚው ከወሎ ርሃብና ዕልቂት ጋር ጉዳያቸው የተያያዘውን ባለሥልጣኖች ላይ ነበር፡፡ በዚህም ጉዳይ ጋር በተያያዘ 138 ፋይሎችን ፣ 87 ባለሥልጣኖችን አስቀርቦ መርምሯል፡፡ በዚህ እልቂት ምክንያት  በኃላፊነት ሊጠየቁ ይገባል ያላቸው 35 የቀድሞ ባለሥልጣኖች ናቸው፡፡ ከእነሱም ውሥጥ ሁለቱ ጠ/ሚኒስትሮች፣ ሃያ ስድስቱ ሚኒስትሮች፣ አንድ የክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ፣ ሶስት ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ ሁለት ምክትል ሚኒትሮች እና አንድ ሥራ አስኪያጅ ናቸው(4) ፡፡ እንደ መርማሪው ኮሚሲዮን የምርመራ ውጤት በወቅቱ የነበሩ ከላይ የተጠቀሱ ሹማምንቶች በወሎ ህዝብ ላይ ለደረሰው ርሃብና እልቂት ተጠያቂ አድርጓቸዋል፡፡ ርሃቡና እልቂቱን ቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ አደጋውን እስከመቀነስና አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ዳተኝነት እና ግዴለሽነት እንደነበር ያሳያል፡፡


በ1958 ዓ.ል በወሎ የተከሰተውን ርሐብ ምክንያት በማድረግ የክፍለ ሐገሩ አስተዳዳሪ በክፍለ ሐገሩ የእህል ጎተራ እንዲሰራና ህዝቡ በፈቃዱ እህሉን አጠራቅሞ በችግር ቀን እራሱን እንዲረዳ ሃሳብ ያቀረቡ ቢሆንም ምክርቤቱ ሁለት አመት ሙሉ ሲያንከባልለው ቆይቶ በመጨረሻም ከአጀንዳ እንዲሰረዝ መወሰኑ አንዱ ማሳያ ነበር፡፡ ሌላኛው ማሳያ በ1964 ዓ.ል በራያና ቆቦ አውራጃ ላይ በደረሰው ድርቅ ምክንያት አደጋውን ለመቀነስ ለተራበው ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ሰው ባስቸኳይ የሚያስፈለግ ስድሳ ሺህ ኩንታል አህል ለወቅቱ ምክርቤት ተጠይቆ ሁለት ሺ ኩንታል ብቻ በግዴለሽነት መላኩን ምርመራው ይገልጣል(5) ፡፡በወሎ ርሐብ መግባቱን ጭምር ዓለም እንዳያውቀው ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡መንገድ ላይ የረገፈው ረግፎ ሬሳውን መንገድ ላይ እየጣለ አጽም ተሸክሞ ለእርዳታ ፍላጋ ወደ አዲስ አበባ የመጣውን የወሎ ህዝብ ኮተቤ ላይ ጠብቀው አስቁመውታል (6)፡፡ ይህንን በማጋለጥ ረገድ እንግሊዛዊ Jonathan Dimbleby እና -መርማሪ ኮሚሲዮኑ ዋና ሰው የነበሩትና በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “የኢትዮጵያ ዮሴፍ!” ያሏቸው  ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ይጠቀሳሉ፡፡በወሎ ህዝብ ላይ ሹማምንቱ እና ንጉሱ ያራመዱት ዳተኝነት በወቅቱ ለነበረው የለውጥ ፍላጎት እርሾና ቁርሾ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም Drooght and its consquenses በሚል ያሳዩት የጂኦግራፊ ትርኢትና ዲምብልቢ ባወጡት ቪዲዮ አቢዮቱ ተጋግሞ የንጉሡ ሥርዓት አከተመ፡፡ በምርመራ ተካተው የነበሩ ባለስልጣኖችም በተለምዶ ስልሳዎቹ የሚባሉት ያገሪቱ ልሂቃን ያለ ፍርድ ተረሽነው በጅምላ ተቀበሩ፡፡

ለዚህ ሁሉ ግብአት የዋለው የወሎ ርሃብ አጀንዳ ለወሎ ህዝብ ምን ፋይዳ አስገኘ? በዚህ የወሎ ህዝቦች የርሃብ ዘገባ ያተረፈው የፓለቲካው ማህበረሰብ እንጅ የወሎ ህዝብ ፈጽሞ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለወሎ ህዝብ ውድቀት ትልቅ መነሻ ነጥብ ሆነ፡፡ በርሃብ ሜዳ ላይ የወደቁና በጠኔ ከሞት አፋፍ ላይ ሆነው ከጣዕረ ሞት ጋር የተናነቁ ወሎየዎችን በቴሌቪዥን አሳይቶ ቤተ መንግሥት የገባው የደርግ መንግሥት የትላንቱን የሚያስመሰግን በደል በወሎ ህዝብ ላይ አደረሰ፡፡ በአንድ በኩል ወሎየነትን ከድርቅና ከርሃብ ማንነት ጋር አቆራኝቶ በኢትዮጵያውያን ህዝቦች ህሌና ላይ አደላደለ፡፡ በሌላ በኩል በስሙ ነግዶ ቤተ መንግሥት የገባበትን ህዝብ በጦርነትና ግርግር ለተደጋጋሚ ርሃብ ዳርጎት አለፈ፡፡


ደርግ ከወሰዳቸው መፍትሄዎች አንዱ የሠፈራ ፕሮግራም ነው፤ ደርግ ከአቢዮቱ ማግስት በወሰደው የመሬት ሥሪት ማሻሻያ ለውጥ ተሞርክዞ እኢአ በ1975 በወጣው የመሬት ለውጥ አዋጅ “መንግሥት መሬት አልባ ጭሰኛ ገበሬዎችን ለማቋቋም በተመረጡ ቦታዎች ላይ የማስፈር ስልጣን እንዳለው በ አንቀጽ 18 ላይ በተደነገገው መሰረት በ1975/76 (እኢአ) 38818(ሰላሳ ስምንት ሺ ስምንት መቶ አስራ ስምንት) ሰዎችን በሰማኒያ ስምንት የሠፈራ ጣቢያዎች አሰፈረ፡፡ የመጀመሪያው የሰፈራ ፕሮግራም ወሎየዎችን ትግሬዎችንና ጎንደሬዎችን መአከል ያደረገ ነበር(7) ፡፡


በ1982 አንድ መቶ ሃያ ሺ ሰዎችን ማስፈር የሚችሉ መቶ አስራ ሁለት የሠፈራ ጣቢያዎች ተለዩ፡፡ እነዚህ ጣቢያዎች በአገሪቱ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ቀጠናዎች ላይ ያተኮረ ነበር፣ ይህም ቀጠናው ሰፊ  ጥቅም ላይ ያልዋለ ለም የእርሻ መሬት አለው በሚል ነበር፡፡በ1984 (እ.ኤአ) በድርቁ ከተጎዱ የሰሜኑ ክፍል አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎችን በዚሁ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ቀጠና ለማስፈር እቅድ ተይዞ ነበር፡፡ እንደ ሙላቱ ውብነህ ጥናት በ1986 መንግሥት ከስድሰት መቶ ሺ (600,000 ) ሰዎች በላይ አስፍሯል፡፡ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺዎቹ በወለጋ፣ መቶ ሃምሳ ሺዎቹ በጋምቤላ እና ከመቶ ሺ የሚልቁት ደግሞ ወደ ፓዊ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ሰባ ስምንት ሺ ያክሉ ወደ ከፋ ተወስደው እንዲሰፍሩ ተደርገዋል(8) ፡፡

ይህ በግዳጅ የተደረገ የሰፈራ ፕሮግራምን በመቃወም ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ ደጋግሞ ተቃውሞ ስላሰማ በሂደት ተገትቷል፡፡ሠፈራ ፐሮግራሙን በተመለከተ ከሰፋሪውም ሆነ ሰፈራው ከሚደረግባቸው ቀጠናዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡ አንዳንዶቹ የሂትለር ካምፕ ጋር አወዳድረው ተችተዋል፡፡ ይሁን እንጅ የደርጉ አቋም ሠፈራ በሰሜኑ አካባቢም ሆነ በሌላው ህዝብ ተጠቅጥቆ ከሚገኝባቸው ቀጠናዎች የሚያጋጥምን ርሃብና ድርቅ በዘላቂነት ለመፍታት የሳሳ ህዝብ የሰፈረባቸው፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መልማት የሚችሉ ቀጠናዎችን ለይቶ ወደተለዩት የሰፈራ ቀጠናዎች ህዝቡን ማሰራጨት መተኪያ የሌለው መፍትሄ ነው በሚል በ1986 በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ገትቶት የነበረውን የአስገዳጅ የሰፈራ ፕሮግራም እንደገና በ1987/88 ሰባት ሚሊዮን ህዝቦቸን ለማስፈር አቅዶ ከመቶ እስከ ሁለት መቶ ሺ ሰዎችን ከተወለዱበት ቀየ አፈናቅሎ ወደ ሌላኛው የአገሪቱ ቀጠና አሰፈረ፡፡ 

የሰፈራ ፕሮግራሙ ከላይ ሲመለከቱት መልካም ቢመስልም ከአፈጻጸም፣ ከሰፋሪዎቹም ሆነ ሰፈራው ጣቢያዎቹ ከሚገኙት ህዝቦች ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ተጨባጭ አንጻር ከፍተኛ ቀውስን በወቅቱም ሆነ ዛሬው ድረስ አስከትሏል፡፡ በሰፈራ ፐሮግራሙ አፈጻጸም ሂደት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተከስቷል፡፡ የተወለደበትን መንደርና ቀጠና “አገሬ” እያለ ለኖረ ማህበረሰብ፣ ሰውነት እና ማንነት የሚለካው በቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ማንነት ላይ በሆነበት ተጨባጭ አስገድዶ ከቀየው በማፈናቀል ወደ ሰፈራ መውሰድ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ የሞራል፣ የማህበረሰባዊ እሴት ኪሳራን እና ጉዳትን አስከትሏል፡፡ 

“የመጀመሪያው አስገዳጅ የሰፈራ ፕሮግራም በ1969 ተካሄደ፣ ከዚያ ቀጥሎም በ1974 እና 1977 እንዲሁ፡፡ ወደ የት እንደሚሄዱ እና ለምን እንደተፈለጉ ሳይነገራቸው ወጣትና ጎልማሳ ወንዶች ከሰሜን ኢትዮጵያ ታፈሱ፡፡ በጉዞ ላይ የጠፉ፣ ተይዘው ተመልሰው የገቡም፣ ለመጥፋት ሲሞክሩ የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ ከዚያም በተለያዩ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል አካባቢወች ሠፈሩ። እትብታቸው የተቀበረበትን የቀድሞ ቀያቸውን ረሱ፤ አካባቢውን መስለው ኖሩ፣ ወለዱ፣ የልጅ ልጅም አዩ። ጥሻ መንጥረው፣ አገር አቅንተው በአካባቢው ሕይወት ዘርተው ቢኖሩም ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ዘመን ጀምሮ ኑሯቸው ሁልጊዜም በስጋት ነው። ነገር ግን ይኼ ሁሉ የሥጋትና ኑሮ በአቶ ለማ መገርሳ የአስተዳደር ዘመን ከሚወስዱት እርምጃና ከሚያደርጉት ንግግር ተነስተን ይኼ የስጋት ኑሮ ያበቃል የሚል ተስፋ አሳድረን ነበር፤ አሁንም ተስፋችን ያልተሟጠጠ ቢሆንም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢወች እነዚህ ወገኖቻችን እየተፈናቀሉ ወደማያውቁት አያቶቻቸው መንደር እየተመለሱ ነው። ሕዝቡ የለውጥ ነጥብራቅ ታዬ ብሎ በሚፈነጥዝበት በዚህ ሠዓት በርካታ ወገኖች ችግር ላይ ናቸው። የትኛውም የመንግስት ተቋምም ሆነ የመገናኛ ብዙሀን ችግራቸውን አቤት ብሎ ሊያዳምጥ አልቻለም” ይላል አክቲቪስትና የታሪክ ባለሙያው ብሩክ አበጋዝ።


በወሎ አስተዳደር ወደ ሰፈራው መሄድ ያለባቸው ገበሬዎች ቁጥር በመንግሥት ከተወሰነ በኋላ ለየአውራጃዎቹና ቀበሌዎቹ ኮታ ተከፋፈለ፤ ገበሬዎቹ ስለ ሰፈራው ምርሃ ግብር በቂ የሚባል መረጃ ሳይጣቸው ትቂት የሚያጓጓ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ተነግሯቸው በቂ የዝግጅት ጊዜ ሳይሰጣቸው በውድም በግድም ወደ ሰፈራው ተወስደዋል፡፡ በመሆኑም ከወሎ ጠቅላይ ግዛት ውሥጥ ከደሴ ዙሪያ፣ከዋግ፣ ከወረሂመኖ፣ ከላስታ፣ ከቦረና፣ ከወረኢሉ፣ከራያ እና ቆቦ፣ ከቃሉ፣ ከየጁ፣ ከዋድላ ደላንታ እና አምባሰል ለሰፈራው ከቀያቸው ማፈናቀሉም ሆነ ለሰፈራ መሄድ አለባቸው ተብለው የተለዩት የወሎ ቀጠናዎች በትክክል ጥናት ሳይደረግባቸው በግብር ይውጣና በግዳጅ የሆኑ ነበሩ፡፡የደርግ ሹማምንቶቹ ከከተማ በቅርበት ያገኙትን ህዝብ ለሰፈራ ፕሮግራሙ አፍሰው ወርውረዋል፡፡ ለምሳሌ በወሎ ደሴ ዙሪያ፣ ቃሉ፣ አምባሰል፣ የጁ፣ ዋድላና ደላንታ የተሻለ የኑሮ ደረጃ  ቢኖራቸውም ለሰፈራ ከተወሰዱት ውሥጥ ብዙዘዎቹ ከዚህ አካባቢ የተወሰዱ ናቸው፡፡ በተቃራኒው ራያ አዘቦ፣ ቆቦ እና ዋግ ለድርቁ በተደጋጋሚ የተጋለጡ ቢሆንም ለሰፈራ ከወሎ ከተወሰደው ዝቅተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ቦረና አራት መቶ ሰባ ሺ ስድስት መቶ( 470600 ) ሰው ተርቦ ከወሎ ለሰፈራ ከተወሰደው 3 በመቶውን ብቻ ሲይዝ ደሴ ዙሪያ የተራበው ሁለት መቶ ሰላሳ ዘጠን ሺ ዘጠና ሰው (239090) ሰው ተርቦ ከወሎ ለሰፈራ ከተወሰደው 29 በመቶውን ይዟል(9) ፡፡ይህና ሌሎች ማስረጃዎች እንደሚሳዩት ከወሎ ለሰፈራ ፕሮግራሙ ሰዎች የተመረጡት ለመራጮቹ ሹማምንቶች በሚመች አቅራቢያ ካለው ህዝብ በይድረስ ይድረስና ለሪፓርት ዓላማ መሆኑን ነው፡፡ 

 ሰፋሪዎቹ እንዲለዩ የተደረጉት ካምፕ ውሥጥ ህዝቡ ከገባ በኋላ በመሆኑ የካምፕ የምግብ እጥረቱና ርሃቡ ህዝቡን በካምፕ ከምናልቅ እንዳሉን ወደ ሰፋራው እንሂድ ወደሚል ምርጫ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ በመጨረሻም ሰፈራው በወሎ ሰፋሪዎች ላይ በፈጠረው አደጋ ምክንያት የፈለገውን አይነት ርሃብና ችግር ቢመጣ እንኳን ሰፈራ ፕሮግራሙን ፈጽሞ የማይፈልገው ህዝብ ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ሰፈራ ፕሮግራሙን ህዝቡ ቢጠላውም ከወሎ የገጠራማው ክፍል ከአሰራ አንድ በመቶ በላይ ህዝብ በተለያዩ ቀጠናዎች በወለጋ፣ በከፋ፣ በኢሊባቦር፣ በመተከል እንዲሰፈር ተደርጓል፡፡ በጠቅላላው በሰፈራ ፕሮግራሙ ከሰፈሩት ህዝቦች መካከል ወሎ 63 በመቶውን በመያዝ ቀዳሚ ሲሆን 18 በመቶ ከሰሜንና ደቡብ ሽዋ፣ 15 በመቶ ከትግራይ የመጣ ነበር፡፡ በሰፈራው ከቀያቸው ከተነሱት ሦስት መቶ ሰባ ስድት ሺ ሁለት መቶ ዘጠና (376290) ወሎየዎች፣  86460 ትግራዋዮች፣ 108244 ሸዬ(ዌ)ዎች፣ 16425 ጎጃሜዎች እና 19687  ጎንደሬዎች ለሰፈራ ሲላኩ ከነዚህ ውሥጥ ሁለት መቶ ሰባ አራት ሺ ሰማኒያ አምስቱ (274085) በወለጋ፣150939ቱ በኢሊባቦር፣ 101123 በጎጃም/ቤኒሻንጉል፣ 64660ቱ በከፋ እና  6387 በጎንደር/መተማ እንዲሰፍሩ ተደርጓል(10) ፡፡

ህዝብን አሳምኖ በምርጫው ለሰፈራው እንዲነሳ ከማድረግ ይልቅ ‹እምቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው› በሚለው የደርግ አሰራር  ማህበረሰቡ  "እትብቴ ተቆርጦ ከተቀበረበት፣ ተድሬ ተኩየ ወግ ማረግ ካየሁበት፣ ልጅና ጥሪት ካፈራሁበት ቀየዬና ርስቴ አፈናቀሎ ከዱር ከጫካ ጣለኝ በሚል ከፍተኛ የሥነልቦናና ማህበራዊ እሴት መናጋት ደርሶበታል፡፡ ያጋጠመውን ቀውስም ብሶት እሮሮውን በሚገልጥበት ስነቃሉ ተቀኝቶታል፦

              የኮምሽን ስንዴ….. ጣዕሙ ጥሩ ነበር፣

              ውለው እያደሩ…. ስፈሩ ባልነበር።

በአገሪቱ የመንግሥት ሥርዓት ግዴለሽነት ርሃብ-ጠኔ ወለድ ሞት ለተራው ህዝብ የአርባ ቀን እድል የተተወ ነው፡፡ የፓሊሲና የተፈጥሮ ድርቅ የወለደው ርሃብና ጠኔ ደጋግሞ ቅስሙን የሰበረው ህዝብ ከፊቱ የተደቀነበትን የርሃብ ሞት ለማስታገስ በመንግሥት የቀረበለትን ስንዴ ቢወደውም በሌላ በኩል ከእትብቱ መቀበሪያ ቀየው መፍለሱ የሚያስከትልበትን አደጋ እያሰበ  የተቃኘው ነው፡፡

በወቅቱ የደርግ ሥርዓት በእናት አገር ጥሪና በአቢዮታዊ ዘመቻ ለአቅመ ጠመንጃ የደረሰ ያልደረሰውንም እያነቀ ወደ ጦር ሜዳ ሲያዳፋ በህዝቡ ላይ የደረሰው ዋይታና መከራ እጅግ ሰቅጣጭ ሆኖ ዛሬው ድረስ መጥፎ ትዝታ ሆኖ ለሁለት ትውልድ ተሻግሯል፡፡ ጦርነትና ሰፈራ ለሞት ያላቸው ተጋላጭነት በደፈናው ስንመለከተው እኩል አይመስልም፡፡ ግና በወቅቱ በሰፈራ ቀጠናዎች የነበረው ሁኔታ በተስቦ በሽታ፣ በመድሃኒት አቅርቦት እጥረት፣ በሰፈራ ቀጠናው አካባቢ በነባር ህዝቦች ጥቃት ወዘተ የመሞት እድሉ ከፍተኛ ስለነበር ለሞት ለሞትማ ከሚቀብረኝ ህዝብ ተነጥየ ሰፈራ ሄጄ  ከምሞት ባምንበትም ባላምንበትም ላገሬ ሄጄ ተዋግቼ ብሞት ይሻላል ለማለት እንዲህ ሲል ተቃኝቷል፡-

              ምንድነው ሠፈራ… ዶሮ ይመስል፣

              ላኩኝ ከጦር ሜዳ …ከወንዶቹ ሰፈር።

እንደ ግሪጎርያኑ አቆጣጠር ከ1984 እስከ 1986 ባለው ጊዜ ውሥጥ ሶስት መቶ ሰባ አራት ሚሊዮ (374,000,000) የአሜሪካን ዶላር ገደማ በጀት ተይዞ  አምስት መቶ ዘጠና አራት ሺ አንድ መቶ ዘጠና (594,190 ) ሰዎች ክብራቸው ተዋርዶና ሞገሳቸው ተገፎ በግዳጅ ከደጋማውና ቀዝቃዘው የሽዋ፣ የወሎና የትግራይ ቀጠናዎች ወደ ሀሩረ ቆላማ የጎጃም፣ ኢሊባቦር፣ ከፋና ወለጋ ቀጠናዎች እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡ ከነዚህ ውሥጥ ስልሳ ሁለት በመቶዎቹ ወይም ሶስት መቶ ስድሳ ሰባት ሺ አስራ ስድስት (367,016 ) ሆነው ከፍተኛ ቁጥር የያዙት ወሎየዎቹ ናቸው(11) ፡፡ የገብሩ ታረቀ ጥናት የሚያሳየው በሠፈራ ፕሮግራሙ ላይ አንድም የአንትሮፓሎጂ፣ የሥነ-ምህዳር፣ የምጣኔ ሃብትና የግብርና ባለሙያዎች ሳይሳተፉበትና አስተያየት ሳይጡበት ከሰፈራ ጣቢያዎቹ መካከል ሰባቱ በደመነፍስ የተመረጡት በራሳቸው በመንግሥቱ ኃይለማርያም እና በለገሰ አስፋው ነው፡፡ የሠፈራ ፕሮግራሙ በአግባቡ ሳይጠናና ለፓለቲካ ፍጆታ ብቻ እንዲውል የግብር ይውጣ ሆኖ አስፈላጊው ግብአት ሳይሟላለት የተፈጸመ በመሆኑም ከሰፋሪዎቹ መካከል ሰላሳ ሶስት ሺዎቹ ወይም ለሰፈራ ከተወሰዱ 5.5 በመቶ የሚሆኑት በአፋጣኝ ወረርሽኝና በምግብ እጥረት ሞተዋል፡፡ ቢያንስ 84,000 ወይም 14% የሚሆኑት ሰፋሪዎች ከሰፈራ መንደሮቹ ጠፍተዋል(12) ፡፡ ከሰፈራ ጣቢያዎቹ በአሳቻ ወቅትና ቦታ በቀጠናው ቀድመው ከነበሩ ጎሳዎች በሚደርስባቸው ጥቃት ታፍነው የተወሰዱት፣ ወደ ትውልድ መንደራቸው ለመሸሽ መንገድ ላይ ሲሸሹ በሽፍታና በአውሬ ያለቁት፣ በውርማ በገደል ያለቁት ብዙ ናቸው የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ሄልሙት እና አይናለም አዱኛ ጥናት ከሆነ ከሰፈራ ጣቢያ የጠፉት ወሎየ ሰፋሪዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ይላሉ፡፡


በ1976 እና በ1982 ከሰፈሩት ውስጥ 40319 የሠፈራ ጣቢያውን ለቀው መጥፋታቸውን የሚያስረዳው የደሳለኝ ራህማቶ ጥናት ሰፋሪዎቹ ከሠፈራ ጣቢያው አምልጠው ከሚጠፉት መካከል በግፍ ወደ ሰፈራ ጣቢያው በግዳጅ የተወሰዱ እና ከቤተሰቦቻቸው ከቀያቸው መለየት ያልሆነላቸው፣ ሰፈራው ከጠበቁት በላይ አስከፊ ሆኖ ያጋጠማቸው መከራ የገዘፈባቸው ይገኙበታል (13) ፡፡በተደጋጋሚ በድርቅ የተጎዳው የወሎ ቀጠና የድርቁ መሰረታዊ መነሻ በአገሪቱ በሰሜኑ ያለው ጦርነት እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ (14) ፡፡ በወሎ ውሥጥ በተደጋጋሚ ለተነሳው ድርቅ የመንግሥት ፓሊሲና የፓለቲካ አተያይ ዋና ምክንያት ናቸው የሚሉት ክሌይና ሆልኮምብ በ1984 እኢአ መንግሥት ህዝቡ ለችግሩ ቀን ያስቀመጠውን እህል የደርግ መንግሥት በነፍጥና በወታደር ወደ መጋዘን በማጋዙና ህዝቡ ለተደራራቢ ግብር በመዳረጉ ምክንያት ህዝቡን ለርሃብ ዳርጎታል፡፡ ቀድመው አርሰው ራሳቸውን ይችሉ የነበሩ ገበሬዎችን በተሳሳተ ፓሊሲ ለርሃብና ድርቅ አጋልጧል፤ ይላሉ፡፡ ቃል በቃል ለማስፈር ያክልም “We concluded that government policies had brought formerly self-sufficient farmers to the brink of starvation - that is, caused the famine.” (15). ፡፡

                 ምን ዓይነት ዘመን ነው… የዘመን ቁረንጮ

                 ወልዶ ለጦርነት …ሰርቶ ለመዋጮ

ከወሎ ወደ ተለያዩ ቀጠናዎች በሰፈራ ፕሮግራም የተወሰዱ ሰዎች ቀድመው ተወልደው ባደጉበት ቀየ ያፈሯቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ወደ ሰፈራ ጣቢያው እንዲወስዱ አልተፈቀደላቸውም፡፡ የደሳለኝ ራህማቶ ጥናት እንደሚያስረዳው ወሎየዎቹ ለሰፈራ ሲወሰዱ በአካባቢው ለተደራጁ ኮሚቴዎች ንብረታቸውን እንዲያስረክቡና ንብረታቸው በተሸጠ ጊዜ ወደ አሉበት የሰፈራ ጣቢያ ጥሬ ገንዘቡ ይላክላችኋል በሚል በተቻኮለና በግዳጅ ሁኔታ ለኮሚቴዎቹ ንብረታቸውን ሜዳ ላይ ጥለው እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ ግና ሰፋሪዎቹ ገንዘባቸውን ማግኘት አልቻሉም፤ የቀጠናው ሹመኛና ኮሚቴዎቹ መዝብረውት ተዳፍኖ ቀርቷል (16) ፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ ለሰፈራ ከተጋዙት ውሥጥ ወሎየዎችና ትግራዮች ለከፋ በደል ተዳርገዋል፡፡


ብሔርተኝነትና ሰፋሪዎቹ

ታሪካዊና ባህላዊ ልዩነት መር ክፍተቶች‼

በሰፈራ ጣቢያዎቹ አካባቢ ከአዲስ ሠፋሪዎቹ በአኗኗርም፣ በታሪክም፣ በቋንቋም፣ በሃይማኖትም ሆነ በባህል ፈጽሞ የተለዩ ማህበረሰቦች ቀድመው ይኖራሉ፡፡ በመተማ ዙሪያ የቤጃ ህዝቦች፣ በመተከል ዙሪያ የሺናሻና የቤጃ ህዝቦች፣ በአሶሳ የበርታ ህዝቦች፣ የኮሞ እና ኳዋማ ነገዶች ይኖራሉ፤ በአንገርና ዴዴሳ ሰፈራ ቀጠና የቤጃና ማዎ ህዝቦች፣ በደቡብ ምዕራቡ ወለጋ የሰፈራ ቀጠና የመዠንግርና የማዎ ህዝቦች፣ በጋምቤላ ሰፈራ ጣቢያ የአኟክ፣ ኒዬ(ዌ)ር ህዝቦች እና በባሮ ወንዝ አቅራቢያ የሺታ ህዝቦች አሉ፡፡ በደቡብ አና መአከላዊ ኤሊባቦር ዙሪያ ሞቻ አካባቢ መዠንግሮች አሉ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ከፋ አካባቢ ሸኮዎችና ማዒን ህዝቦች አሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ነገዶች እርስ በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከሰፋሪዎቹ የሰሜን ህዝቦች ፈጽሞ የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ መጤዎቹ ከነባሮቹ ህዝቦች ጋር በማህበራዊ፣ ባህላዊ እሴት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ መስክ ስምሪትም የተለያዩ ናቸው፡፡ ይህ ልዩነት በወጉ ፓሊሲ ተቀርጾለት ካልተያዘ ወደ አላስፈላጊ ጥላቻና ግጭት ማደጉ የማይቀር ነው፡፡


ሰፋሪዎቹ ይብዛም ይነስም በመንግሥት የሚደጎሙና ልዩ ትኩረት ያላቸው ሲሆን ነባሮቹ ደግሞ ለጫካ የተተዉ ናቸው፡፡ ግና ቀድሞ የኛ ምድር በሚሉት ላይ መጤው ሰፍሮ ሀብት (resource) የሚጋራ በመሆኑ የግጭት በሩ ሰፋ ያለ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ነባር ህዝቦች ሰፈራውን በወረራ መልኩ ይረዱትም ነበር፡፡ የሰፈራ ፕሮግራሙ ለመሰል የብሔርና የነገድ እልቂት የተጋለጠ መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ እንኳንስ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ኋላ ቀርና የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ ያላት አገር በሌሎችም ዘንድ መሰል ፕሮጀክቶች እጅግ አደገኛ ናቸው፡፡ የሰፈራ ፕሮግራሙ ሰፋሪዎቹን ብቻ ሳይሆን በሰፈራ ጣቢያው አዋሳኝ ወይም ከባቢ ያሉ ነባር ህዝቦችን ያማከለና ያሳተፈ እንዲሁም አመካክሮ የተፈጸመ ባለመሆኑ መጤዎቹንና አስፋሪውን መንግሥት በጥላቻ የመመልከቱ ሂደት የሚጠበቅ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ህዝቦች መካከል ብዙዎቹ ከሱዳንና ኬኒያ ጋር ድንበር በመሆናቸው ኢትዮጵያዊነት በሚለው የደርጉ  መሬት ያልወረደ ጽንሰ ሃሳብ ደርግን እንደ አገር አስቦ ሰፈራ ፕሮግራሙን እንዲቀርጽ ቢያደርገውም ለነዚያ ነገዶች ግን ገና በተግባር ያልተፈተነ ባዕድ ጽንሰ ሃሳብ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከፕሮፓጋንዳ ተሻግሮ ከጫካ እንዲወጡና ለስልጣኔ እንዲበቁ አልተጋምና፡፡ በመሆኑም ከሰሜን ከመጣው መጤ ይልቅ በቋንቋም ሆነ በአኗኗር የሚመስላቸው የሱዳንና የኬኒያ ድንበር ህዝብ እጅጉን ቅርባቸው መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ የጋራ ብሔራዊ ማንነቱ ባልዳበረበትና ባላደገበት ሁናቴ የሰፈራ ፕሮግራሙ በመጤውና በነባሩ መካከል ጥርጣሬንና ስጋትን ማስከተሉ አልቀረም፡፡

ከሰፈራ ፕሮግሙ ቀድሞ መሰራት የነበረበት የቤት ሥራ አልተሰራም፣ በድህረ ሰፈራውም መጤውና ነባሩ የሚዋሃድበት መላ አልተፈላለገም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰሜኑን እና የማዕከላዊውን መንግሥት በወራሪነት አውቆ ላደገ ማህበረሰብ ሰፈራ ፕሮግራሙን ባልተተረጎመ ኢትዮጵያዊነት ለመቀበል እጅጉን አዳጋች ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውሥጥ ነባሮቹንና መጤዎቹን የሚያስተሳስር የጋራ ማንነት አፈላልጎ ማሳደግ፣ ከሌለም ፈጥሮ ማሳደግ ይገባ ነበር፡፡ ታሪካዊ አረዳድንም በማህበራዊ ትስስርና ቁርኝት መጀመሪያ መፍታት ይገባ ነበር፡፡ ግና ይህ ሁሉ ከሠፈራው ጋር በተጓዳኝ ባለመሰራቱ የተፈራው አልቀረም፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሰፈራ የሄዱ ወሎየዎችን ከነባሩ ማህበረሰብ ጋር የሚያስተናስል ማንነት ፈልጎ እንዲዋሃዱ ለማድረግ እጅግ አስቸጋሪ አይሆንም  እስልምናንና ኦሮሞነትን ለጊዜው ሁለቱን ወገኖች ለመስፋት በክርነት የማገልገል አቅም ነበራቸው፡፡ በሂደት ኢትዮጵያዊነትን እንዲያጎለብቱ ርብርብር በማድረግ በኢትዮጵያዊነታቸው የተጋመዱ አንድ ህዝቦች የሚሆኑበትን እድል መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በአሶሳ ሰፈራ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም በከፋ ሰፈራ አካባቢዎች እንዲሁ እስልምናን መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ ይሕ ሙስሊም ለሆኑትና በዘራቸው ኦሮሞ ለሆኑት ከፊል ወሎየዎቸ ከነባሩ ህብረተሰብ ጋር ለመጋመድ የጋራ ማንነት ሆኖ ለጊዜው ማገልገል ሲችል ነገዳቸው ኦሮሞ ላልሆነውና ክርስቲያን ለሆኑት መጤዎችም ከነባሩ ህዝብ ጋር የጋራ ማንነት እንዲፈጥሩ ሁኔታውን በማመቻቸት በዚያ ላይ መስራትና በሂደት ኢትዮጵያዊነት የተሰኘ የጋራ ማንነት እንዲፈጥሩ ሰፊ ርብርብ ሊደረግ ይገባ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከተካሄዱት የሰፈራ ዓይነቶች “ስግሰጋ” የተባለው የሰፈራ ሂደት እጅግ ውጤታማ እንደሆነ ፓንክረስትም አጽነኦት ሰጥተውበታል፡፡ ስግሰጋ ሰፈራ ማለት ሳሳ ብሎ ዘርዘር በሎ በሚኖር ህዝብ መካከል ከሌላ ቀጠና ሰዎችን አምጥቶ መካከል ላይ እንደ ቀድሞው ነዋሪ የመሬት ይዞታ ሰጥቶ ማሰባጠር ማለት ነው፡፡ 

ከተለያዩ ክልሎች በፌደራል መንግሥቱ ከባቢ በተፈጠሩ የፓለቲካ ትኩሳቶች ሳቢያ የቁጭት ማስተንፈሻ ሆነው ተጋላጭ የሆኑት ሰፋሪዎች የአሰፋፈር ሁኔታቸው ለጥቃት ተጋላጭ ያደረገና ከነባሩ ህብረተሰብ ጋር ለአራትና ሦስት አስርት አመታት ሁሉ እንዳይዋሃድ ማነቆ በሆነ ሒደት የሠፈሩ ናቸው፡፡ ከነባሩ ማህበረሰብ በተለዩ የሰፈራ መንደሮች እንዲኖሩ በመደረጋቸው ከነባሩ ህዝብ የሚያጋምድ የወል ማንነት ከመፍጠር ይልቅ “እኛ” እና “እነሱ” ወይም “ሰፋሪ/መጤ” እና “ነባር” በሚሉ ማንነቶች ላይ የተገነባ ለባላንጣነት የቀረበ የማንነት ስሪት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ በዘመነ ኢህአዴግ በአደገኛ ፍጥነት ከጡዘቱ የደረሰው ጎሰኝነት ወትሮም በሚጨበጡና መሬት በቆነጠጡ የብሔራዊነት ካስማዎች ላይ ያልተገነባውን ኢትዮጵያዊነት ውጦ በቅጡ ያልተተገበረውን የጎሳ ፌደራሊዝም አሉታዊ ውጤቶች እየተመገበ በሰከረ ጊዜ ከትውልድ ቀያቸው በመንግሥት ፓሊሲ ምክንያት የሰፈሩ መጤዎችን የጥገኛነት ስነልቦና አላበሳቸው፡፡ በስጋት የተወጣጠረው ግንኙነት በነባሩና በመጤው መካከል በአኗኗርም ሆነ በማህበራዊ ትድድር መወራረስና መቀላቀል ሳይኖር ለአስር አመታት በአንድ ጠርሙስ ውሥጥ እንደተሞላ ውሃና ዘይት ሳይቀላቀሉ ኖሩ፡፡

ሰብአዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት የተሰኙ ዋስትና የሚሆኑ መጋመጃዎች ባልዳበሩበት በተለይም ብሄራዊ ማንነቱ ገና ተጠየቅ ውሥጥ ገብቶ አንዱ ሌላውን ጠላት አድርጎ በሚመለከትበት ሁኔታ፣ የሰሜኑን መንግሥት በክርስቲያን መንግሥትነት ለሚያውቅና በጅምላ “የአማራ መንግሥት” በሚል ለሚረዳ ህዝብ ያለበቂ ዝግጅትና መተማመን ከሰሜኗ ኢትዮጵያ ሰፋሪ ማምጣት አብሮት የተቆራኘ አደጋ መኖሩ የማናስተባብለው ሃቅ ነው፡፡ ሁሉም ባይሆኑም ከፊል ወሎየዎቹ በኦሮሞነትና በሙስሊምነት ከነባሩ ማህበረሰብ ጋር ትስስር እንዳይፈጥሩም በጅምላ “አማራ” ብሎ መሰየም ስህተት ነበር፡፡ ይህም “አማራ” የሚለው አረዳድ በነባሩ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በመጤውም ጭምር ከነገዳዊ አረዳድ ይልቅ ሃይማኖታዊ አረዳዱ የጎላ ስለነበር ነው፡፡ በነባሩ ህዝብ ዘንደ ቀደሞ “አማራ” ተብሎ የተለየው ህዝብ ክርስቲያኑና በቀድሞው የአጼዎቹ ሥርዓት በተፈጠሩ ክስተቶች ታጅቦ ለአሉታዊ ትርጓሜ የተጋለጠ በመሆኑ በጅምላው ‹አማራ› ብሎ ሰይሞ ማስፈሩም ችግሩን እንዳባባሰው አንዳንድ ምሁራኖች ይጠቅሳሉ፡፡ በአጼ ሚኒሊክ እና በመንግስቱ ኃይለማርያም ፓሊሲዎች ሳቢያ ወደሌላው ቀጠና የሄዱት ህዝቦች ከሰሜኗ ኢትዮጵያ ከመገኘታቸው ውጭ ፈጽሞ አንድ ዓይነት ማንነት የላቸውም፤ የአጼ ሚኒሊክና የአጼ ኃይለሥላሴ ሰፋሪዎቸ ሹመኞች፣ ገዥዎችና ወታደሮች ናቸው፡፡ የደርጎቹ ደግሞ ድሆች፣ በድርቅ የተቀጡ ምንዱባኖች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ነባሩ ማህበረሰብ ለቀድሞዎቹ የአጼው ሥርዓት ሰፋሪዎች በወል ስምነት ያገለግል ዘንድ የሰጠውን ስያሜ ለነዚህኞ በድርቅ ምክንያት በመንግሥት ተገደው ለሰፈሩት በወል ማስረከቡ በተለይም ወሎየዎቹን ሰፋሪዎች ዛሬው ድረስ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል፡፡ 

በእርግጥ ይህ አተያየት ተጠየቅ ውሥጥ የሚገባው ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከትግራይ እንዲሁም ከወሎ የተወሰዱት ነገዳቸው ኦሮሞ ያልሆነና ክርስቲያን ሰፋሪዎችን ያገናዘበ አለመሆኑ ነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል የሰፈራ ጣቢያዎች እየተፈናቀሉ ያሉ ወሎየዎችም በወሎና በኦሮሚያ መካከል ያለውን ከፊል የማንነት መስመር ተጠየቅ ውሥጥ ጨመሮታል፡፡ ወሎየ መሆናቸው የጥቃቱ ሰለባ ከመሆን አላዳናቸውም፡፡ ከዚህ አንጻር ከፍ ያለ የቁርኝት ገመድ ሆኖ የሚያጋምድ የወል ማንነት መፍጠርና እሱን ማሳደግ ግድ ይላል፡፡ ጥምር ማንነት ያላቸው ሰፋሪዎችን ከጥምር ማንነታቸው ውሥጥ ከነባሩ ጋር የሚያመሳስላቸው ካለ ያንን አሳድጎ መሄዱ ለጊዜው መፍትሄ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄው ሰብአዊነትንና ኢትዮጵያዊነትን በወል ማንነት አሳድጎና አጋምዶ ማስቀጠል ለትስስሩ የራሱ ማንነት ቢኖረውም ከሰፈራው ጎን ለጎን ሰፋሪውንና ነባሩን የሚያዋህድ አንድ ወጥ የጋራ ማንነት ፈጥሮ ማሳደግና መንከባከብ ያስፈልጋል የሚለው ገዥው መፍትሄ ነው፡፡ 

ታቼ እና ኦባ በመንግሥት ፓሊሲ አቀጣጣይነት ስለሚፈጠሩ የጎሳ ግጭቶች ባጠኑበት ጥናታቸው ላይ “በሰፋሪዎቹ እና በነባሮቹ መካከል የሚፈጠረው ውዝግብ በመሬት ሆኖ ታሪካዊ ትርክት ካለው ችግሩ በከፋ መልኩ ይባባሳል፡፡” (17) ይላሉ፡፡ ለምሳሌ በንጉሱ ዘመን የመንግስት ሹመኞች፣ ሰራተኞችና ወታደሮችን ለመቅጣት ሲታሰብ በወቅቱ በቤልሃርዚያ፣ በወባ በተስቦ በሽታ ደጋግሞ ይጠቃ ወደ ነበረው መተከል ይላኩ ነበር (18) ፡፡ ይህን መቅጫ ተደርጎ በንጉሡ ሥርዓት ይወሰድ የነበረን ቀጠና ንጉሱ በወረዱ በትቂት አመታት ውሥጥ ከአማራ ክልል በዋናነት ከወሎ አካበቢ ለመጡ ሰፋሪዎች የሰፈራ ጣቢያ ማድረግ በመጤውም ሆነ በነባሮቹ የቤጃ ጎሳ ጉምዝ ማህበረሰቦች ላይ የሚፈጥረው ስሜት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡


ሰው ሌላውን ቀጠናየ መጥተሃልና ውጣልኝ የሚል የሞራል ውደቀት ላይ እንዳይደርስ ሰብአዊነትን ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎች መሰራት ነበረባቸው፣ ይኖርባቸዋልም፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ‹‹ከሰፈሬ ውጣ፣ ከጎጤ ልቀቅ፣ ከክልሌ ጥፋ!›› እንዳይለው የጋራ ኢትዮጵያዊነትን ፈጥሮ ወይም ያለውን ከልሶ ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬው ድረስ ለቱሪስት ፎቶ ግራፍ እንዲሆኑ እርቃናቸውን ጫካ የተውናቸውን ወገኖቻችንን  እና ተምሮ፣ ለስልጣኔ አየር ተጋልጦ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ እሴትን ካካበተው ህዝብ ጋር እኩል መዳኘት ፍትሃዊ አይሆንምና ለቀስት መስሪያ የሚቆርጠውን ዛፍ እንኳን ቢሆን ለትምህርት ቤት ግንባታ አውሎ ማስተማር ማሰልጠን እንዲሁም እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ዘላቂው መፍትሄ ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ክፈተቶች

ከሰፈራ መርሃ ግብሩ ጋር ተያይዞ በሰፈራ ጣቢያዎቹ ቀጠናዎች ውድመቶችና ልማቶች መኖራቸው አይቀርም፤ የጫካ  ምንጠራ፣ የመሬት መራቆት፣ የዱር አራዊቶች መሰደድና መመናመን እንዲሁም የመሬት መሸርሸር ተጠቃሽ አሉታዊ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሰፋሪዎቹ ለመጠለያ፣ ለትራንስፓርት፣ ለእርሻ ምርት ግብአት የሚያራቁቱት የተፈጥሮ ሃብት በአደንና በለቀማ ላይ እንዲሁም በአርብቶ አደርነት ላይ ህይዎቱን አካባቢው በሰጠችው ተፈጥሮ ላይ ለመሰረተው ነባሩ ህዝብ ህልውና አደጋ መሆኑ አይቀርም፤ ወይም ለነባሩ ህዝብ ስጋት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም የሰፈራ ፕሮጀክቱ ለነባሩ ህዝብ በምላሽነት ሊያስገኝላቸው የሚገባው ጥቅም መኖር አለበት፡፡ ይሕ ጥቅም በነባሩና በመጤው ህብረተሰብ ማከክል በልውውጥ የሚደረግ የግብይት የጋራ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ያረጋገጠ መሆን ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዙሪያ ተገቢው ሥራ ባለመሰራቱ በመጤውና በነባሩ መካከል የሀብት ቅርምት ምክንያት አገሪቱ ካጣችው የሐብት በክነት በላይ በመጤውና በነባሩ መካከል ባላንጣኝነት አዝማሚያ እንዲፈጠር አድርጓል (19) ፡፡ አንዳንዶቹ የሠፈራ ጣቢያዎች አካባቢ ያለው ለግብርና በተለይም መታረስ የሚችለው መሬት ተጨማሪ ሰፋሪን የሚያስተናግድ አቅም ሳይኖረው የሠፈራ ጣቢያ በመከለሉ የተፈጠሩ የኢኮኖሚ ግጭቶች ፓለቲካዊ ቅርጽ ይዘው ወደ ብሄር መተላለቅ ከፍ የማለት እድላቸው ሰፍቶ ተስተውሏል፡፡

ፓለቲካ


የወሎ ህዝብ ከጥንት እስከዛሬ ለፓለቲካው ትኩሳት እርሾና ቅመም እየተደረገ እንደያስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ሲውል በራሱ ፈጽሞ ተጠቃሚ ሳይሆን ዛሬው ድረስ ዘልቋል፡፡ በንጉሡ አስተዳደር የወሎ ህዝብ በተለየ መልኩ ወሎ ጠል በሆኑ ቢሮክራቶችና የሥርዓቱ መዘውሮች ሳቢያ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማንነት ደፈቃን አስተናግዷል፡፡ ፊት አውራሪ ለማ እንደገለጹት የንጉሡ ሥርዓት ወሎን ተበቅሏል ማለት ይቻላል፡፡ በ1966/67 የተቋቋመው መርማሪ ኮሚሲዮንም ሆነ በድርቅ ፓለቲካ ዙሪያ ያጠኑ ምሁራን ወሎ በተደጋጋሚ በድርቅ የመመታቱ ምስጢር የሥርዓቱ ዳተኝነት ውጤት ነው ይላሉ፡፡ ይህ የወሎ መከራ ከዓለም ጆሮ እንዳይበቃም ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይሁን እንጅ ከወሎ በርሃብ መንገድ ላይ የረገፉት ረግፈው የገረጡ በአጽማቸው የሚራመዱ ዞምቢ መሳይ ሰዎች የተረፉ አዲስ አበባ መግባት በመቻላቸው ጉዳዩ ለህዝብ ጆሮ ደርሶ የአቢዮቱ ቤንዚን ሆኖ የንጉሡን ሥርዓት ሞት አፋጠነ፡፡ ደርግም የወሎን ርሃብ በቴሌቪዥን አሳይቶ ከፍተኛ የፓለቲካ ጥቅም አጋበሰበት፡፡

የደርጉ ሥርዓት በወሎ የተፈጠረውን ድርቅና ርሃብ ባልተጠና ፓሊሲ ለመፍታት በችግር ላይ ሌላ ችግር ደርቶ አለፈ፡፡ ቀጠናው ከሚችለው በላይ የግብርና ምርትን በመሰብሰብ በተኮላሸ የማህበረሰባዊነት ፍልስፍና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አደረገው፡፡ በሰፈራ ፕሮግራም ወደማያውቀው ምድር በግድና በችኮላ የተወሰደው የወሎ ማህበረሰብ በሰፈራ ጣቢያዎቸ ወረርሽኝ፣ ርሃብና የሠላም መናጋት ክፉኛ ተጎዳ፡፡ የት እንደ ደረሰ በውል የማይታወቅ ሰፋሪ ከቁጥርም ጎደለ፡፡ ይሕ የት እንደ ደረሰ የማይታወቅ ሰፋሪ ወደ እትብት ቦታው ከተመለሰው አንጻር በአሃዝ ቢያንስም ቁጥሩ ግን የሚናቅ አይደለም፡፡ ከቀየው በግዳጅ ሰፈራ የተወሰደው ማህበረሰብ ወሎየነትን አውቆ ቢኖርም በሰፈራ ጣቢያው የማያውቀውን ማንነት እንዲጎናጸፍ ተደርጓል፡፡ ነባሩ ቀጠናም በዚህ ማንነቱ እንዲለየው በመደረጉ የወል ማንነት ፈጥሮ ወይም አዳብሮ መስተጋብሩን እና ትስስሩን እንዲያሳልጥ ሁኔታው ባልተመቻቸለት እና በስጋት በተወጠረበት ሁኔታ የኢህአዴግ መንግሥት ወደ ስልጣን መጥቷል፡፡


በድህረ 1983 ለኢትዮጵያ የተሰበከው ፓለቲካ ብሄራዊ ስሜትን እጅጉን ጎድቶ ጎሰኝነትን በከረረ መልኩ ያሰመረ መሆኑ ወትሮም በቋፍ ላሉት እና በጅምላ ከሌላው ማህበረሰብ ተለይተው በሰፈራ ጣቢያ ለተቀመጡት ሰፋሪዎች የቆቅ ስጋ አላበሰ፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ይበረግጉ ዘንድ ፓለቲካው ያልተሰላ ቁማር ጋለበ፡፡ በቅጡ ያልተተነተኑ የታሪክ አረዳዶች ማወረረጃ ይሆኑ ዘንድ ከሰፈራ ጣቢያ ጀልመው የተቀመጡ ወሎየዎች ተቀዳሚ ዒላማዎች ሆኑ፡፡ በዚህም ሳቢያ በተከታታይ ባልበሰለ የፓለቲካ ስግረት፣ ፓለቲካው እና በቅጡ ያልተነተነው የታሪክ ትርክት ችኩሎችን እያሰገረ ወስዶ ሰፋሪዎቹን የጥቃት ሠለባ አደረጋቸው፡፡ ለሰፈራ ነዋሪዎቹ ወደ አትበት ቀያቸው ይመለሱበት ተስፋ ተሟጧልና የቆቅ ስጋ ተላብሶ መኖርን ተላመዱት፡፡ የአትብት መቀበሪያ ምድራቸው ወሎ- ትናንት ጥለዋት ከሄዷት ወሎ በከፋ ሁኔታ ልጆቿን ለስደት ስትቁት ታዘቡና ቆርጦ ለመመለስ አንገራገሩ፡፡ ይሁን እንጅ አቢዮታዊ ዴሞክራሲያዊነትን በተካረረ የብሔር ውጥረት ላይ ለመገንባት የተፍገመገመው አዲሱ ስርዓት በጎሳዎች መካከል የጥላቻን እሳት ወናፍ ሆነው የሚያቀጣጥሉ ትርክቶችን ማብዛቱ በአማራነት ለተለየው ማህበረሰብ እንደ ህዝብ አደገኛ ውጤትን አስከተለ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ የኢህአዴግ መድረኮች ኦሮሞና አማራ በሚሉ ጎራዎች በህዝቦች መካከል ጸብ አጫሪ አጀንዳዎች ሲንሸረሸሩ ደጋግሞ ተመልክቷል፡፡ ‹ትምክህተኛ እና ጠባብነትን› ለሁለቱ ብሔሮች ቅጽልነት አድለው ‹የማን አባት ገደል ገባ!› የሚያጫውቱ የገዥው መንግሥት መድረኮችና ትርክቶች የህብረተሰቡን አሰፋፈርና ታሪካዊ ወቅረት ሳያገናዝቡ ህዝቡን ላደጋ ያጋለጡ እንደ ነበር ታዝቧል፡፡

በዘመናችን የፓለቲካ ጡዘት እና ፓለቲካውን ተከትሎ በተፈጠረ የአንድ አገር ህዝቦች የትስስር ውል መላላት ሳቢያ ከአማራ ክልል በተለይም ከወሎ ቀጠና ተወስደው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እንዲሰፍሩ የተደረጉ ማህበረሰቦች ለተከታታይ ጥቃት ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ በብዙሃን ቀጠና ውሥጥ የሚኖሩ አናሳዎች በተለይም አናሳዎቹ ጅምራቸው በዚያ ቀጠና ሳይሆን ቀርቶ በዘመን ሂደት በፓለቲካዊ ውሳኔ የመጡ ከሆነ ለጥቃት እንደሚጋለጡ የተለያዩ አገራት ተሞክሮ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ከገምት ውሥጥ አስገብቶ የባላንጣነት ክሩን አላልቶ የመስተጋብር ሸማ በጊዜ መሸመኑ የሚበጅ ቢሆንም የፌደራል መንግሥቱም ሆነ፣ የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታቶች ጉዳዩን እኔ ምን ተዳዬ በሚል አለፍ ሲልም ለፓለቲካ ፍጆታ ይውል ዘንድ በመጤውና በነባሩ መካከል ቁርቁሱ እንዲፈጠር የማድረግ ወይም ልዩ ፍላጎት ያላቸው አካላት መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው በገለልተኝነት የመመልከት አሰራር ተግባራዊ በመሆኑ ኢትዮጵያን የሚያሣፍር ታሪክ ተፈጽሟል፡፡ ከመጤዎቹም ሆነ ከነባሮቹ መካከል የተለየ ፍላጎት ባላቸው አካላት በሚነሳ ጥቃት “ከክልሌ ውጡልኝ” የሚል ነውር በኛው ዘመን እውን ሆኖ መመልከታችን አንገታችንን ማስደፋቱ አልቀረም፡፡ በዚህ አሳፋሪ ክሰተት ውሥጥ የ19ኛውና የ20ኛው ክፈለ ዘመን የፓለቲካ አዙሪት አማካይ የሆነችው የወሎ ፍሬዎች ደግሞ የከፋውን ዋጋ ከፍለዋል፣ በመክፈል ላይም ይገኛሉ፡፡ ከኤሊባቦር፣ ከከፋ፣ ከመተከል የሠፈራ ጣቢያዎች ቤት ንብረታቸውን ተቀምተው፣ ወይም በአሰቸኳይ በሃራጅ እንዲሸጡ ገዳጅና ማስፈራሪያ ደርሶባቸው ለሶስትና አራት አሰርት አመታት ያፈሩትን ጥለው ህይዎታቸውን ለማትረፍ ከየሰፈራ ጣቢያዎቹ እየተሰደዱ ያሉትን ወሎየዎች ቤት ይቁጠራቸው፡፡

በእርግጥ በወሎ ምድር ከሰፈራ የተረፉትስ ምን አገኙ? ስደቱ ከጋር ውሥጥ ወደ አረብ አገር ከመዞሩ በስተቀር ለወሎ ጠብ ያለለት ነገር የለም፡፡ ገና ከኩበት ማገዶ ያልወጣው ህዝብ፣ መኪና አይቶ የማያውቀው ህዝብ የትየለሌ ነው፡፡ የወሎ ከተሞች ገና የኤሌክትሪክ አምሮታቸውን፣ የውሃ ጥማታቸውን አልቆረጡም፡፡ በከፍተኛ ቆሞ ቀር በሆነና በዘመድ አዝማድ በተተበተበ አስተዳደር ተጠርንፋ የምትንገላታው ወሎ የመዳን ዘመኗ በቅርብ የምታገኝ አትመስልም፡፡ በድህረ 1985 በተለይም በዘጠናዎቹ እና በሚሊየሙ የመጀመሪያ አመታት የወሎ ኮበሎችና ኮረዶች ወሎ ላይ ተስፋ ነጥፎ ባየር በባህሩ ወደ ስደት ባገኙት አጋጣሚ ተመሙ፡፡ ሴት የወለደ አባት “የዱባይ ወለድኩ” የሚል ዘየ ፈጥሮ ተስራራበት፡፡ ወሎየ ተስፋውን በሴት ልጁ ላይ ጥሎ ከጎጆ ቤት ወደ ቆርቆሮ ማዝገሙን የእድገቱ ጣሪያ አድርጎ ሴት ልጁን ለአረብ አገር በርሃ ገበረ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ በአካል እንዳረጋገጠው ወጣት ጠፍቶ ቀበር ቆፋሪ እሰኪታጣ ድረስ ወጣቱ አስኮላ ቀየውን ትቶ ስደትን መረጠ፡፡ ሚስት የምትሆን ልጃገረድ በቀየው እስኪጠፋ ድረስ ወሎ ቆነጃጅቷን አነጠፈች፡፡ ከአገሯ መንግሥት ይልቅ ተስፋዋን ቀይ ባህር ማዶ ተከለች፡፡  ወሎ በዚህ የተሳቀቀ ሁነት ውሥጥ ላይ ሆና በግዳጅ በሰፈራ የተነጠቁ ተወላጆቿን መከራና ስቃይ እህህ እያለች ሆድ ይፍጀውን ቆዝማ ዝም ማለቷ አግባብ አይደለም፡፡


ምን ይሻላል?

ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመተማመንና በኩራት አገሬ የሚሏት አገርን በማንነትም ሆነ በተጠቃሚነት መፍጠር ግድ ይላል፡፡ አንዱ ብሄር የጎደለባት ኢትዮጵያ ምሉዕ ልትሆን ከቶ አይቻላትም፡፡ የእርስ በእርስ ቁርቁስ ቅስሟን የሰበራትና በጎሳ ፓለቲካ አዙሪት የሰከረች ኢትዮጵያ ለማናችንም ልትመች አትችልም፡፡ ዜጎች በሃይማኖታቸው፣ በብሄራቸው፣ በፓለቲካዊ አረዳዳቸው እንዲሁም በሃሳባቸው ከየትኛውም ስጋትና ጥቃት አርነት ሊወጡ ይገባል፡፡ ዜጋ ሆነው በዜግነት የሚያጣጥሟት ኢትዮጵያን መፍጠር አማራጭ የሌለው ክትባት ነው፡፡ አማራ ጠል ሆኖ የበቀለ ፓለቲካ ነቀርሳ እንጅ ቤዛ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ ትግሬ ጠል ሆኖ የፈላ ፍል የሞት ዛፍን እንጅ ጥላ አይሆንም፡፡ ኦሮሞ ጠል ሆኖ የበቀለ ቆሞ ቀርነት አገሪቱን ወደ ውድመት እንጅ ወደ ልማት ፈጽሞ አያመራትም፡፡ በመሆኑም ሁላችንም የሌለንባት ኢትዮጵያ ለሁችንም አትሆንምና አግላይዋን ኢትዮጵያ ተጸይፈን የመሬቷን ኢትዮጵያ እውን ለማመድረግ የተባበረ ተስፋና ጥረት ማድረጋችን የችግራችን መፍቻ ነው፡፡

የፌደራል መንግሥቱና የሚመለከታቸው ክልላዊ መስተዳድሮች እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላት ይህንን አሳፋሪ ጠንቅ ለመፍታት በቁርጠኝነት ለመስራት ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡  የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ አቅዶችን በመንደፍ የችግር ስሪት በማጥናት ዘላቂ መፍትሄ መተለም ይኖርባቸዋል፡፡የማን አባት ገደል ገባ ፓለቲካን ተጸይፎ የፍቅርና የአብርሆት ትርክትን ማብዛቱ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡

የአማራ ክልል መስተዳደር እንደ ጤፍ በየክልሉ የተዘሩ ተወላጆቹን ደህንነት ለማስጠበቅ ነዋሪዎቹ ከሚገኙባቸው አቻ ክልሎች ጋር የጋራ ምክክርና የህዝብ ለህዝብ ሥራ በመሥራት በህዝቦች መካከል ሁነኛ መቋጠሪያ የሚሆነውን ሰብአዊነትና አገራዊነት እንዲመጣ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ በተወሳሰበ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ጥቃት ደርሶባቸው የሚፈናቀሉ ተወላጆቹን በስነልቦናም ሆነ በቁሳዊ ተክለ ቁመና መልሰው የሚቋቋሙበትንና እንባቸውን የሚጠርጉበት ፕሮጀክት ቀርጾ መንቀሳቀስ ይኖርበተል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል ለሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጅ ወገኖቹ የተሻለ አያያዝ ማድረግም ይኖርበታል፡፡

የሰፈራ ጣቢያዎቹ የሚገኙባቸው ክልሎች በዋናነት የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ አና የቤኒሻንጉል ክልሎችም በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ናት በሚል መሪ ሃሳብ ወደ ክልሎቻቸው የመጡ ሰፋሪዎች በጎሳ ደረጃ ባይመስሏቸውም በአገር ልጅነትና  በዜግነት እንዲሁም ክልሉ የሚፈልግባቸውን ግዴታዎች እስከተወጡ ድረስ አንድ ዜጋ ከመንግሥቱ፣ ካገሩ የሚጠብቀውንና ዜጋ በመሆኑ ማግኘት ያለበትን ሁሉ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ለደህንነታቸውም ዋስትና እና ከለላ ሊሰጧቸው ይገባል፡፡ ከቀጠናየ ውጣልኝ፣ ከክልሌ ውጡልኝ የሚለው አስተሳሰብ በየትኛውም ስሌት አፍራሽ እንጂ ገንቢ ሊሆን አይችልምና ለመሰል የጅምላ ፓለቲካ ውጤቶች ጽዩፍ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብር ከፍለው፣ ቤት ንብረት አፍርተው ቀየውን መስለው በሚኖሩ መጤዎች ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በዝምታ ማለፍ በህዝቦች መካከል መተማመንና አጥፍቶ ስጋትን የሚተክል ተውሳክ በመሆኑ በቁርጠኝነት ያለ አድልኦ ለክልል ነዋሪዎቻቸው ሁሉ ጥላ ሊሆኑ ይገባል፡፡

 ማጣቀሻዎች

🏽🏽🏽🏽

1. ሸህ ሙሀመድ ወሌ

2. ጌታቸው ኃይሌ፣ ሰምና ወርቅ፣ ገጽ 33

3. ገብርኤል ዳንኤል፣ ርሃብ ድርቅና መንስኤዎቻቸው፣ሰምና ወርቅ፣ ገጽ 46

4. ውብሸት አየለ ጌጤ፣ መርማሪ ኮሚሲዮን፣ 2010

5. ውብሸት አየለ ጌጤ፣ መርማሪ ኮሚሲዮን፣ 2010፣ ገጽ 9

6. ጌታቸው ኃይሌ (ፕ/ር)፣ሰምና ወርቅ፣ ገጽ 35

7. Desalegn Rahmato, Resettlement in Ethiopia the tragedy of population relocation in the 1980s 33

8. Mulatu Wubne. "Resettlement and villagization".

9. Helmut Kloos and Aynalem Adugna,Settler Migration during the 1984/85 Resettlement Programme in Ethiopia,1989

10. Desalegn Rahmato, Resettlement in Ethiopia the tragedy of population relocation in the 1980s

11. Gebru Tereke, The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa (New Haven: Yale University, 2009), p. 149 

12. Gebru Tereke, The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa (New Haven: Yale University, 2009), p. 150 

13. Desalegn Rahmato, Resettlement in Ethiopia the tragedy of population relocation in the 1980s

14. Theodore M. Vestal ፣Famine in Ethiopia: Crisis of Many Dimensions

15. Bonnie K. Holcomb and Jason W. Clay The Politics of a Famine Report: Rejoinder to Richard Pankhurst፣1987

16. Desalegn Rahmato, Resettlement in Ethiopia the tragedy of population relocation in the 1980s

17. Boku Tache and Gufu Oba, policy –Driven Inter –Ethinic Conflicts in Southern Ethiopia

18. Getachew Woldemeskel The Consequences of Resettlement in Ethiopia : 1989

19. See Desalegn Rahmato, Resettlement in Ethiopia the tragedy of population relocation in the 1980s

43 views0 comments
bottom of page