top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ተያይዘን እንዳንወድቅ” (በሰለሞን አበበ)የዘመን ክፉ


ዘመኑ ክፉ ነው። ዘመኑን ያከፋው በክፉ ሰዎች ስለ ተሞላ ይመስለኛል። በዓለማችን ልዩ ልዩ አቅጣጫዎች የምናየውና የምንሰማው ዜና እጅግ የሚያሠቅቅ ኾኗል። ጽንፈኝነት ተስፋፍቷል። የጥላቻና የምሬት ቅስቀሳዎች ሰላም እያደፈረሱና ዕልቂት እየወለዱ ነው። ግለ ሰባዊ “እንካ ቅመሶች” እና ዐምባጓሮዎች ተባብሰዋል። ማኅበረ ሰባዊ ብጥብጦች በብዛትም በስፋትም ጨምረዋል። ዐይነታቸው ብዙ መጠናቸውም አስፈሪ የኾኑ ፖለቲካዊና ባህላዊ ቀውሶች ተበራክተዋል። ግጭትና ፍጅት፥ ሰቆቃና ዋይታ፥ አድልዎና መፈራረጅ፥ ጥላቻና ነገረኛነት ተስፋፍቷል። ጥፋትን በጥፋት፥ ጥላቻን በጥላቻ፥ ስሕተትን በስሕተት ለማረም የሚኳትኑ ሰዎች በዝተዋል። በዝተዋል ብቻ ሳይኾን ሕዝቦችን ለሥጋትና ፍርኀት አጋልጠዋል።

ሰው ከራሱም ከሌላውም ጋር የተጣላ ይመስላል። ቂምና በቀል የተንሰራፋባቸውና ጥላቻ የነገሠባቸው ማኅበረ ሰቦች ሞልተዋል። ጥላቻ የጠብ፥ የቅራኔ፥ የሁከትና የመቈራቈስ መንሥኤ እንደ መኾኑ፥ የሰው ሕይወት እየቀጠፈ፥ አገራትን እያናቈረ፥ ሕዝቦችን እያፋጀና ማኀበራዊ ትስስሮችን እየበጣጠሰ ይገኛል። ውክቢያ፥ ዉካታ፥ ብጥብጥና ትርምስ የዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን ዕለታዊ አርእስተ ዜናዎች ናቸው። አርቆ አስተዋይነት የጐደላቸውና በዐመፅ መንፈስ ናላቸው የተበጠበጠ ግለ ሰቦችና ቡድኖች በግልጽም ኾነ በስውር የሚያሽከረክሩት ትውልድ የሚኖርበትን ዓለምና ሕዝብ እያወከ ይገኛል።

ሥጋት ያንጃበበበት ዓለም

ጀብደኝነት ጥበብ የጐደለው የትዕቢት እብደት ነውና፥ ጠብን እንደ ቋያ እሳት ያቀጣጥላል። አንዱ ለሌላው የማይተኛ እየኾነ መታየቱ የምር ያስጨንቃል። ጭቈና፥ ምዝበራ፥ ጭቅጭቅና ዐምባጓሮ እየተበራከተ መኼዱ አሳሳቢ ኾኗል። አንዳንዶች በደረሰባቸው ጥቃት አቂመው የበቀል ብድር ለመክፈል ጥቍር ደም በማነፍነፍ ላይ ናቸው። ጥላቻ፥ ክፋት፥ ግጭት፥ አለመደማመጥ፥ ብጥብጥ ወዘተ. በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት፥ በየቦታው በየኹኔታው ስለ መዛመቱ እናውቃለን። ሥጋት ያላንጃበበበት የዓለም ክፍል የለም፤ ቢኖርም ትንሽ ነው። የሰው ልጅ ደም በትንሽ በትልቁ ሰበብ እንደ ጅረት እየፈሰሰ በመኾኑ ጸጥታና ሰላም ከምድራችን ርቀዋል። ዓለማችን በጠና ታማለች፤ ታውካለችም። በሚያስጨንቅ ዘመን ውስጥ ገብተናል።

የምንለው ችግር በሩቅ በሚገኙ ወገኖች ላይ ብቻ የሚታይ ሳይኾን በእኛው ፊትም የተደቀነ ነው። ወደድነውም ጠላነው በተመሳሳይ ኹኔታ አገራችን ታማለች። ነገሩን ሸፋፍነን ልናልፈው በሞከርን ቍጥርም እየባሰበት መኼዱ አልቀረም። ከበደል አዙሪት መውጣት ተስኖናል፤ የክፋት ሰንሰለቶችም የሚበጣጥሳቸው አልተገኘም። ከሥጋትና ፍርኀት ነጻ አይደለንም። በእውነት እንነጋገር ከተባለ በጽኑ ታመናል። ችግር ላይ ነን። አልታመምንም ብሎ የሚሞግተኝና ጤና መኾናችንን በተጨባጭ ማስረጃ የሚያሳይ ሰው ቢገኝ ንስሓ ልገባ ዝግጁ ነኝ፤ አለመታመማችን እውነት ኾኖ እኔ ብሳሳት እመርጣለሁ።

ብዙዎች ተገንዝበውታል ብዬ እንደምረዳው፥ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ምኅዳሩ መታወክ ገጥሞታል። የፖለቲካ ተዋንያኑ የአጨዋወት መንገድ እንከን የሚታይበት እንደ መኾኑ ፍርኀት፥ ጥርጣሬ፥ አለመተማመንና ንትርክ በዝቶበታል። በ2006 ዓ. ም. በታተመው የትሩፋን ናፍቆት በተሰኘ መድበል ውስጥ “መንገዱም ቢጠብ፥ ጠብን እንጠብ” የምትል መጣጥፍ አለች። በመጣጥፏ ውስጥ ከተባሉት ነገሮች መካከል የሚከተለውን አንቀጽ እንዋስ፤ እንዲህ ይነበባል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡድኖች መካከል የሚታየው ፍጥጫ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙና ተመሳሳይ ዜግነት ያላቸው ወንድሞች መኾናቸውን እንድንጠረጥር የሚገፋፋ ነው። ከጥላቻና ከበቀል አዙሪት መውጣት ተስኗቸው ፖለቲካዊ ፉክክርን በጠላትነት በመተርጐም [እርስ በርስ] ተፋጠዋል። በየማኅበረ ሰቡ ውስጥ የተወተፉ የትውልድ እንግውላዮች በበኩላቸው፥ በዘመን ደመና ውስጥ ሰርጎ የተሰወረ ቍስል እየጐረጐሩ ሊያመግሉ ሥንጥራቸውን አሹለው ቆመዋል። እርስ በርስ [ለመተላለቅ] “ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡ” ቀላል ቍጥር የማይሰጣቸው የጠብ አባቶች ከብበውናልና የጠብ ምሳሌ ፍለጋ ሩቅ መዋተት አያስፈልገንም።

ችግርማ አለ። አፍንጫችን ሥር የተጐለተ ችግር አለ። ዐይናችንን ጨፍነን ምንም አይታየንም ካላልን በቀር በአስፈሪና አሳፋሪ መፋጠጥ ተከበናል። በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ያልቻሉ ልሒቃን፥ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ፥ ያገኙትን የጠብና የጥላቻ ትቢያ ባገኙት ኹሉ ላይ እየበተኑ ነው። ለአንዳንዶች የተጋነነ መስሎ ቢታያቸውም እንኳ በተወሳሰቡ ኹኔታዎች መካከል እየዳከርን ለመገኘታችን ምስክሮቹ እኛው ነን። አገራዊ ግጭትና ትርምስ ሊያስከትሉ የሚችሉ መሰናክሎች ተደቅነውብናል።

ማናችንም እጃችንን አጣጥፈን የሚኾነውን ኹሉ በትዝብት መመልከት አንችልም። ይህ የነብሩስ ሊ፥ የነሽዋዚንገር፥ የነብራድ ፒት … ተምኔታዊ ዓለምና ምናባዊ ቅጥቅጥ አይደለም። ፍጥጫው የሰው ልጆች ነው፤ እንደ እኛው ዐይነት ሕያዋን ፍጡራን ናቸው የተቀያየሙት። የአንድ እናት ልጆች ናቸው ቂም የቋጠሩት። ሰዎች ናቸው ደማቸው የሚፈስሰው። እየከፋ ከሔደም የጋራ አገር ነው የሚፈርሰው።

ወገኖች ሆይ፥ የጥላቻና ብጥብጥ እሳት እየተንበለበለ አይደልምን? ወደ አምላክ ለመጮኽም ኾነ እንደ ሰው የሚጠበቅብንን የመፍትሔ ፍለጋ ጥረቶች ለማድረግ ከዚህ በላይ የት ድረስ መበጣበጥ አለብን? ችግሩ በጊዜ መፍትሔ ካልተፈለገለትና እየተባባሰ ከኼደ ማናችንም ከቅራኔው ወላፈን ማምለጥ አይቻለንም።

የጠብ ጽልመት ዐብሮነታችንን በኀዘን ማቅ ሊከድነው እያደባ ባለበት በዚህ ወቅት፥ በፀጕር ስንጠቃ ዐይነት ንግግራችንን ለማሳመር መሞከር መፍትሔ አይኾንም። ችግሩ እንደ ኾነ በየሰፈራችን አድፍጧል። በየልቡናችን ጐድቧል። ጥላቻና ቂም ሥር እየሰደደ ነው። ከመወያየት ይልቅ መፈራረጅ ባህል ኾነ። ከመደማመጥ በላይ ጀብደኝነት ተወደሰ። ለችግሮቻችን ኹነኛ መላ ከመሻት ይልቅ የቂም በቀል አዙሪት ናላችንን በጠበጠው። ገጣሚ ነቢይ መኰንን፥ ይህን ማኅበረ ሰባዊ ደዌ ልንገላገለው ከምንችልበት ምኞት ጋር ግብ-ግብ ገጥሞ ይመስላል፥ እንዲህ ሲል ያምጣል፤

መች ይበጠስ ይኾን፥ ይህ የቂም ሰንሰለት? ይህ የቂም ጕማሬ፥ ይኼስ የቂም ዑደት መች ይኾን አገሬ፥ ልጅ የሚወጣላት? ቂም አርጅቶ ሞቶ፥ ሰው የሚኖርባት

በቀል ሬሳው ወጥቶ፥ ሰው የምንኾንባት።

በርግጥ መች ይኾን? ሕመማችንና መዘዙን መጠየቅ አስፈልጎናል። አዎን፥ ታመናል። ለመደማመጥ የማይችሉና የማይፈልጉ ታዳጊዎች በጠብ አባቶች እየተመሩ ጽንፍ ለጽንፍ በማሸብሸብ ላይ ናቸው። ቂመኞች ጨክነዋል፤ ስድብ፥ ዛቻና ማስፈራራት ነግሧል። የእምነት አባቶች “መንፍቀዋል”፤ ውሸት ባህል ወደ መኾን እየተለወጠ ይመስላል። መማር ለማኅበረ ሰባዊ ለውጥ፥ ፍትሕ፥ ነጻነትና አገራዊ መተባበር ወደ ፊት መራመድ ነው ወይስ እንጣጥ ብሎ ወደ ኋላ መዝለል አስብሏል። ተምህሯዊ ሴሰኝነት አገር ምድሩን በክሏል፤ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን እውነትን ከመናገር ጾመዋል፤ አንድም አንደበታቸው ጐድፏል፤ አንድም ብርዓቸው ታጥፏል። ኹኔታው የእውነት ያስፈራል።

በጕዳዩ ላይ ጥናታቸውን አድርገው በቅርቡ በታተመው መጽሐፋቸው ያስነበቡት ዶ/ር ጠና ደዎ እንደሚያሳስቡት ሥጋቱ ጥልቅ ይመስለኛል፤

ዛሬም በፖለቲካው ረገድ በነበረው ክፋት ላይ ሌላ ዐዳዲስ ክፋቶች እየተጨመሩ ናቸው። ኹኔታዎች ኹሉ በነበረው መልካቸው የሚቀጥሉ ከኾነ ከዚህ በፊት ካደረግነው በላይ ዕጥፍ ድርብ ዋጋ ለመክፈል እንገደድ ይኾናል። በዚህ ምክንያት ዛሬም ዜጎች ይሠጋሉ። ሥጋታቸው ደግሞ ስለ ብዙ ነገር ነው። ለግል ሕይወታቸው ይሠጋሉ፤ ስለ አገራቸው ደኅንነትና ሰላም ይሠጋሉ፤ ዛሬ ስላለውና ወደፊት ስለሚኖረው ይሠጋሉ፤ ሥጋቱ ትክክለኛ ሥጋት ነው። ሥጋቱ እውነት ነው። የሥጋቱ ሰበብም ብዙ ነው። የበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውጤት መኾኑም አከራካሪ አይደለም።


ሽማግሌዎችን ዐሰሳ

በጸሎት ፈጣሪ ፊት ከመፈለግ ጐን ለጐን በምድር ላይ እንድናደርገው የተሰጠንን ኀላፊነት ለመወጣት መታዘዝ አለብን። የቍጣ ትረካዎች ይለዝቡ፤ “ልክ እናስገባዋለን” ፎካሪዎች አደብ ይግዙ፤ ሰይፍ ወደ ሰገባው ይመለስ፤ ሰደፍ ወደ ድኾች ሰርን አይጣደፍ፤ ምላስም ይሰብሰብ፤ ሰው የመኾን ክብርና አስተዋይነት ይታይብን፤ ንግግራችን ደርዝ ይኑረው። ሽማግሌዎች ይነሡ።

ከቤት እስከ ጎረቤት፥ ከሰፈር እስከ አገር ጠብ አብራጅ ድምፅ አስፈልጎናል፤ “አንተም ተው፥ አንተም ርጋ” ሲል የሚደመጥ አባት አልናፈቃችሁም? በዛሬ ጊዜ ዕርቀ ሰላም በትኛውም ቦታ የሚያስፈልግ ነው። ጠብ ኅብረትን ያናጋል፤ ሰላምን ያደፈርሳል፤ ሕይወትንም ያሳጣል። ወንድሜ ሰላም ዐጥቶ እኔ ሰላም ሊኖረኝ አይችልም። ነገሩ ‘በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል?’ እንደ ተባለው ኾኗል። ሲናገር የሚደመጥ አባት ያስፈልጋል። የሚኾነውን ስናይና ስንሰማ፥ የኾነ የሚያስቈዝም ነገር አንጃቦብናልና፥ እንዲህ ስንል እንጠይቃለን፤ ሽማግሌ የለንም ወይ?

እንዲህም ብለን እንብሰለሰላለን። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያችን ምንድር ናት? ሽማግሌ የሌላት አገር? … ወይስ ሽማግሌዎቿን በልታ የጨረሰች አገር?... ወይስ ሽማግሌዎቿ የማይደመጡባት አገር? … ወይስ ሽማግሌዎቿ በአርምሞ ያደፈጡባት አገር? እነሆ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ይህ ሐሳብ መንፈሴን እያልመዘመዘው አለሁ። አገሬ ሽማግሌዎች የሌሉባት (ያጣች) ወይስ የሌሉላት (ኖረውም እንኳ በሽምግልና ክብርና ሞገስ ያልተገኙላት) ናት? ምነዋ፥ ሽማግሌዎቻችንን የበላ ጅብ አልጮኽ አለሳ!

በዘመናዊው ዓለም መንግሥታዊ መዋቅሮችና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ሊያከናውኑት የተገባውን ነገር “ሽማግሌ ምን ቤት ኾኖ ነው ጥልቅ የሚልበት?” የሚለኝ ሰው ይኖራል። ምላሹ እኒህ ተቋማት የአቅም ውሱንነት ከታየባቸው ሌላ ምን ይደረጋል? የሚል ነው። ወይም ኖረውም ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ካልቻሉስ? ወይም ተቋማቱ፥ እንደ እኛ ገና ድክ ድክ በማለት ላይ ባለ አገር እንደመኖራቸው፥ ድጋፍ ካስፈለጋቸውስ? ወይም እነርሱም በአስተዳደራዊ ጕድለት ከተጠቁስ? … ሽማግሌማ ያስፈልገናል።

በጥንታዊ ማኅበረ ሰቦች ዘንድ ሽማግሌዎች ይጫወቱት የነበረው ሚና ትልቅ ነበር። ዛሬም ቢኾን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት፥ በተለይ በገጠር ቀመስ አካባቢዎች፥ ኹለት ፀጕር ያወጡ አባቶች፥ የሃይማኖት መሪዎችና የየጐሣ አለቆች፥ እንደ ቀድሞው ዘመን ባይኾንም እንኳ፥ ይከበራሉ፤ ይደመጡማል። ስለዚህም በገጠመን ዙሪያ መለስ ምስቅልቅል ውስጥ እነዚህ አባቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ቀላል አለመኾኑን እያሰላሰልሁ “የሽማግሌ ያለህ!” ለማለት እገደዳለሁ።

ይኹን እንጂ እውነትን ጥሎ ሽበት ያበቀለ፥ ለኅሊናው ሳይገዛ ጺሙን ያንዠረገገ፥ ጽድቅን ሰባብሮ ከዘራውን የተመረኰዘ፥ ፈሪኀ እግዚአብሔርን አምዘግዝጎ ጥሎ የየሃይማኖቱን ካባ የለበሰ አዛውንት ይነሣልን ማለቴ አይደለም። ወገኑን የሚወድና ዕርቀ ሰላም የሚያወርድ ተክለ ሰብእና የተላበሰ ሽማግሌ ነው የናፈቀኝ። “የናፈቀን” እንዳልል፥ “ራስህን ቻል” የሚለኝ ቢኖርስ ብዬ ነው። ሐሳቡን የሚጋሩ ብዙዎች ስለ መኖራቸው ግን ጥርጥር የለኝም። ለማንኛውም፥ መንፈሳዊ ልዕልናው ከአካላዊና ሥልጣናዊ ግዝፈቱ የጐላ ጎምቱ የፍቅር ሰው በዚች ትልቅ አገር፥ ምናለ በነበር!

ርግጥ ነው፤ ችግር ፈጣሪው ሰው ራሱ መፍትሔ አፈላላጊ ለመኾን ሲንጠራራ የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች በሽማግሌዎች ተስፋ ቈርጠዋል። እኔም ከአገራዊም፥ ማኅበረ-ፖለቲካዊም ኾነ ሃይማኖታዊ ችግሮቻችን መካከል ጥቂት የማይባሉቱ የተፈጠሩት በአዛውንቶች መኾኑን አላጣሁትም። ትውልድ ለመመረቅ “እንትፍ እንትፍ” ሊሉ የተገባቸው የማኅበረ ሰብ አለቆች ትውልድ እንዲተራረድ ቂምና ጥላቻ ሲተፉ አይተናልና። ስለዚህም ነው ሽምግልናን የሚያሳብቁ ውጫዊ ገጽታዎች ባለቤት ከመኾን በላይ ልባዊ አዘንብሎት ላይ ማተኰር አለብን የምለው።

ሽማግሌ ይምጣልን ስል ያረጀ ያፈጀ አዛውንትን ብቻ በመከጀል አይደለም። የልብ ቅንነቱን በዘመን ክፋት ለውሶ ያላሳደፈ ሽማግሌ ነው የምመኘው። “ምራቃቸውን የዋጡ” ደጋግ ሽማግሌዎች ያስፈልጉናል፤ እኒህ ተፈላጊዎች ታዲያ “ምራቃቸውን በዋጡ” ጊዜ እውነትን ተጕመጥሙጠው በአደባባይ ያልተፏት መኾን አለባቸው። ከስሕተታችንና ስሕተታችን ከወለደው መዘዝ ጋር ፊት ለፊት እንድንጋፈጥ በፍቅር የሚያግዙን ልበ-ሰፊ የአገር ባላዎች ወደ የት ይገኛሉ? ሽማግሌ ይፈለግ!

የቅን መንፈስ ባለቤት የኾነ፥ ነገአችን እንዳይጨላልም አሻግሮ የሚያይ ባለ ብሩህ ልቡና ሰው አስፈልጎናል፤ በመንፈስ ልዕልና የገዘፈ፥ ምክረ ልቡናው በሆይ ሆይታ ያልተዛነፈ አባት፥… ኅሊናው ላይ በሆዱ ያልተኛና ለነፍሱ ያደረ አረጋዊ፥ … አገር ሚዛን እንዳይስት የምግባር ክብደቱ ሞገስ ያላሳጣው ሽማግሌ ተመኘሁ …። ያው ምኞት መኾኑ ነው እንግዲህ። ምኞት በሕግም በጕልበትም ስላልታገደ መመኘቴን እቀጥላለሁ። የሽማግሌ ያለህ!

ከትናንት ጋር በብሶት መንፈስ ያልተጣመደ፤ ከዛሬ ጋር በክፋት አፍላል ውስጥ ያልተጣደ፤ ከነገ ጋር “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ኪዳን ያልተጣበቀ፤ … ሽማግሌ፥ ክቡር አባት ፈለግሁ። “የእብድ ገላጋይ” ሰፈሩን እንዳይወር “ሽማግሌ” ያስፈልገናል። የጠብ ቡድን አባቶች በርክተው በመንደርቶ መጣለዝ እንዳይስፋፋ አስታራቂ ገላጋይ ይነሣ። አስታራቂ ያጡ የአንድ እናት ልጆች የጋራ ጎጇቸውን አጋይተው “ለትኋኔ በጀኝ” ብለው እንዳይጃጃሉ ሸምጋዮች ይገለጡ። ሸምጋዮች ይምጡ ስል የብቻዬ ሐሳብ ኾኖ አይደለም። የአስታራቂ ፍለጋው ጥረት የከረመ መሰለኝ። በዓሉ ግርማ፥ ያኔ ገና፥ በኦሮማይ፥ ይኸን የአስታራቂ መጥፋት እያሰበ እንዲህ እየቈዘመ ጽፏል፤ የአስመራ ጎዳና ዘንባባዎች ያረገዱበት መዝሙር አስመስሎ ነው በመጽሐፉ በኩል የሚነግረን። [4]

ያንድ እናት ልጆች በዓላማ ተለያይተው፥ በአመለካከት ተሳስተው፥ ተጣልተው፤ የሚያስታርቅ ጠፍቶ ፥

የዕብድ ገላጋይ በዝቶ። …

በዚያን ዘመን የሚያስታርቅ በመጥፋቱ ምን እንደ ተፈጠረ አሳምረን እናውቃለን። የአካልና የሕይወት ዋጋ ተከፍሎበታል፤ ማኅበራዊ ውጥንቅጥ አስከትሎብናል፤ የታሪክ መዛበር ወልዶ ኼዷል፤ ሥነ ልቡናዊ መዳሸቅ አስከትሎ ነጕዷል። መዘዙ ዛሬ ድረስ እንደ ጥላ ይከተለናል። ለመነጋገር፥ ለመወያየትና ቅሬታን በምሕረትና ይቅርታ ለማስወገድ የማይችል ማኅበረ ሰብ የሚገባበትን ውጥንቅጥ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ኹሉ እኛም አይተነዋል፤ ቀምሰነዋልም።

ምንም እንኳ ይቅርታ መቀባበልና የእርቀ ሰላም ተግባር በአገራችን የተከበረ ዕሴት የነበረ ቢኾንም የእርቅ አቅምና ሥራ ግን መዳበር የሚገባውን ያህል ባለመዳበሩ፥ “በየሠፈሩ የሚከሠቱ ችግሮች ከመፍታት ዐልፎ አገራዊና ብሔራዊ ጕዳዮችን የማየት አቅም አላገኘም፤ በተለይ ሁሌም የችግሮች ኹሉ ቋት ኾኖ የቈየው የአገራችን ፖለቲካ እስካኹን ድረስ በአገር-በቀል ማኅበራዊ ዕሴትና ተቋም የመዳኘት ፍላጎት አላሳየም። ይህ ለችግሮቻችን መግዘፍና መወሳሰብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።”

ሰለሞን አበበ

29 views0 comments

Comments


bottom of page