የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ታማኝነት
Updated: Jan 18, 2020
ታማኝ የት አለ ?
ታማኝ ማን ነው ?

ታማኘነት የሥነ ምግባር ጉዳይ ነው፡፡ ታማኝነት በሥራ ላይ፤ በሰዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ የሚጠበቅ ትልቅ ፋይዳ ያለው እሳቤ ነው፡፡ ታማኝነት በመጀመሪያ ለራስ ሕሊና ሲሆን ተያይዞም ለበርካታ ሌሎች ጉዳዮች እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ዛሬ በዚህ ርዕስ ላይ ለመፃፍ ስነሳ በታማኝነት መኖር ምክንያት አያሌ ድንቅ ሥራዎች ሲሰሩ ታማኝነት ሲጎድል ደግሞ የሚደርሰው ችግር እና የሚፈጠረው አሉታዊ ሁኔታ ጉዳቱ የትየለሌ ይሆን ብዬ ጠየቅሁ፤ እናም ስለታማኝነት መገለጫም አሰብኩ፡፡
የታማኝነት መገለጫው ብዙ ነው ፡፡ በሥራ ላይ ታማኝነት፤ በወዳጅነት መሀል ታማኝነት፤ በባልና ሚስት መሀል ታማኝነት፤ በአበዳሪና ተበዳሪ፤ በወካይና ተወካይ፤ በማህበራዊው፤ በኢኮኖሚያዊውና በፖለቲካው ወዘተ ዘርፍ ታማኝነት ለአገር፤ በመሆኑም ታማኝነት ዐብይ ጉዳይ ነው ፡፡
ዱሮ ዱሮ የእኛ ቅድመ አያቶች፤ እና አያቶች፤ በማህበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ በሚፈጥሩት ግንኙነት፤ በርካታ ነገሮችን በመተማመንና በታማኝነት መንፈስ ቃላቸውን ሰጥተው፤ ቃል ተቀብለው፤ የሚያስሩት ውል በርካታ ነበር ይባላል፡፡ እንዲያውም ስለ ታማኝነትና ቃልን ስለመጠበቅ ያላቸው እሳቤ ክቡርና ትልቅ ነገር መሆኑን ሲያመለክቱ ከወለዱት ልጅ በላይ ነበር የሚያዩት እናም እንዲህ ይሉ ነበር ‹‹ የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ይህም አባባል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቶ እኛ ዘመን ላይ ደርሷል፡፡
ቃል እና ታማኝነትን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ አድርገው በመውሰድ በቃል የተዋዋሉትን ውል በታማኝነት በመተግበር ይጠብቁት ነበር፡፡ ለምሳሌ በቃል ጥያቄ እና ‹‹ ልሙትልህ፤ ልሙትልሽ ›› በሚል የመሀላ ማስተማመኛ የተበደሩትን ገንዘብ ይሁን፤ ሊያደርጉት ቃል የገቡበትን ነገር በታማኝነት ቃላቸውን ጠብቀው ያደርጉት እንደነበር አሁን የዕድሜ ባለፀጋ ሆነው ዛሬም ያሉ አባቶችና እናቶች ይናገራሉ፡፡
እውነት ነው የቀድሞ ዘመን አባቶቻችንና እናቶቻችን በታማኝነት እና በሥነ ምግባር ጉዳይ የላቀ ደረጃ ነበራቸው ማለት እንችላለን፡፡ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ በአብዛኛው ማለት በሚቻል ደረጃ ታማኞች ነበሩ፡፡ ለአገራቸው፤ ለመንግሥታቸው፤ ወዘተ ታማኝ በመሆን ከእነርሱ የሚፈለገውን ማንኛውንም ነገር በታማኝነት ያከናውኑ እና መስዋዕትነት ከፍለውም እንኳን ቢሆን ይተገብሩት ነበር ፡፡
በግለሰባዊ ሕይወታቸውና ኑሮአቸው፤ በታማኝነት ሰንሰለት ከሌላው ጋር ተያይዘው እና ተቆራኝተው ኑሮን ሲመሩ ድንገት አንዱ የማህበረሰቡ አባል ታማኝነት እሳቤ ላይ የላላ አቋም ኖሮት ወይም ኖሯት ታማኝነት ቢጎድል ከፍተኛ የሆነ ወቀሳ እና የማግለል እርምጃም እስከመውሰድ ይደርሱ ነበር፡፡
ይህ የታማኝነት ጉዳይ ትልቅ አገራዊ እና ማህበራዊ እሴት ነው ፡፡ ታማኝነት ባለ አደራነትን ያሳስባል፡፡ ታማኝ ነው የተባለ ሰው የሚሰጠው ኃላፊነት በርካታ ሆኖ በደረጃም ላቅ ያለ ሥፍራ ሊኖረው ይችላል፡፡ አገርን የሚመሩ ወይም የሚያስተዳድሩ ሰዎች ታማኝና አደራንም የሚጠብቁ መሆናቸው በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ታማኝ መሪዎች ወይም አስተዳዳሪዎች ታማኝነታቸው የሚገለጠው በአስተዳደራቸው ወይም በአመራራቸው ሥር ያሉ ሰዎችንም ይሁን ንብረቶችን በሁለንተናዊ ማንነታቸው ታማኝ ሆነው ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታና መንገድ ሲመሩና ሲያስተዳድሩ፤ክትትል ሲያደርጉና ሲንከባከቡ መታየታቸው ነው፡፡ ባላቸው ሥልጣንና የስልጣን አቅም ሁሉንም በእኩል ደረጃ ሲያገለግሉትና ሊያገለግሉም ፍቃደኛ ሆነው በመገኘታ ቸው ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ያሉ ሠራተኞችም በሚሰሩበት መሥሪያ ቤት ውስጥ በተመደቡበት የሥራ ኃላፊነት ላይ በሐቅና በእውነት ታማኝ ሆነው የቀጠራቸውን አካልና የሚያገለግሉትንም ሕብረተሰብ በማገልገል ሂደት ውስጥ ታማኝነታቸው ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ የአሰሪዎችን የሥራ መመሪያና ደንብ በመጠበቅ ሥራዎቻቸውን መሥራት ፤ ለርካሽ፤ የግል ጥቅምና ፍላጎት ሳይንበረከኩ በሐቀኝነት ‹‹ ደመወዜ ይበቃኛል ›› ብለው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ፤ ይህም አካሄድ ለታማኝነታቸው መገለጫም ይሆናል፡፡
ለምሳሌ በባንክ ሥራ ፤ በሕክምና ሙያ ፤ምህንድስና ፤ በአገር ሰላምና ደህንነት ጥበቃ ወዘተ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በሙያቸው አማካይነት ያወቁትን አገራዊም ይሁን የደንበኛን ምስጢር በታማኝነት ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ምስጢሩን መጠቀሚያ ሊያደርጉት ወይም ልዩ የሆነ ትርፍ ሊያተርፉበት መሞከር አይኖርባቸውም ፡፡
የባንክ ባለሙያ በያዘው የኮምፒዩተር ዕውቀት እና ችሎታ በፈለገው ጊዜ የደንበኛውን አካውንት ሰብሮ ዘው ቢልበት፤ ሐኪሙ ሊያክመው አልጋው ላይ ያስተኛውን ታካሚ ደንበኛውን ኩላሊቱን ቢመነትፈው፤ የአገር ደህንነት ጠባቂው ያወቀውን አገራዊ ምስጢር ለጠላት አሳልፎ ቢሰጥ ፤ ነገ ትልቅ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ግንባታን መሐንዲሱ ቢገነባና እንዲገነባም ቢያፀድቅ፤ ታማኝነትን መሬት ላይ ጥሎ በጭቃ መረምረም ሆኖ ይቆጠራል፡፡
የባንክ ባለሙያ ፤ ሐኪሙ፤የአገር ሰላምና ደህንነት ጠባቂው፤ መሀንዲሱ ወዘተ ካልታመነ ማን ሊታመን ነው? የሚል ጥያቄ እንዳይነሳ ዘወትር በተሰማሩበት ሙያ እና የሥራ ኃላፊነት ላይ ታማኝነትን አጥብቆ መያዝና ሙጥኝ ማለት የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡
ከታማኝነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በአደራ የተቀበሉትን ገንዘብ፤ እንደራሴ ሁንልኝ ተብሎ የፈረሙበትንና የተወከሉበትን ሕጋዊ ውክልና፤ ከመንግሥትም ሆነ ከግል መሥሪያ ቤት ሥራን ሰርተህ አሰራ ወይም አሰሪ ተብሎ የተሰጠን የስራ ኃላፊነትና ሹመት፤ ለራስ ፍላጎትና እቅድ ሲባል ችላ ብሎ ታማኝነትን ገዝግዞ በመጣል ተቃራኒ አቅጣጫ መያዝ እናም በጠራራ ፀሐይ የክህደትን ባንዲራ ሰቅሎ ማውለብለብ፤ የታማኝነትን ሕልውና አጥፍቶ ጉድጓድ ቆፍሮ መቅበር በፍፁም ሊሆን የሚገባ ድርጊት አይደለም የሚል አቋም አለኝ፡፡
ይሁንና አንዳንዶች በዚህ አቅጣጫ ተሰልፈው የታማኝነትን መርህና መልኩን በማጥፋት አሳዛኝ ድርጊት ሲፈፅሙ ይታያሉ፡፡ በእንደራሴነት የተሰጠን ውክልና መሰረት አድርጎ ወካይን አውላላ ሜዳ ላይ የሚጥል ተግባር መፈፀም፤የመንግሥትንና የሕዝብን ኃላፊነት ወደ ጎን ብሎ የራስን ሕልውና ሰማይ የሚያደርስ የራስ ወዳድነትና ፀረ- ታማኝነት የሆነን ሥራ መሥራት ፍፁም የሚወገዝ ድርጊት ነው፡፡ ድርጊቱ ቢፈፀምም ውሎ አድሮ መገለጡ አይቀርም ፤ ያን ጊዜ ደግሞ ትልቅ እፍረት ነው- የሚሆነው፡፡
ታማኝነት በቢሮ ሥራ ላይም አንድ እውነታ ሆኖ መገለጥ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የቢሮ የሥራ መገልገያ ቁሳቁሶችን ለግል ጉዳይ እንደፈለጉ ማዋል አልፎም ሌሎች እንዲገለገሉበት ማድረግ ይህ ሌላው ታማኝነት እንዲሰለስል ማድረግና የሥነ ምግባር ጉድለትም ነው፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለፀው ታማኝነት በብዙ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ሊገለጥ ይችላል፡፡ ዋናው እና አብይ ጉዳይ ግን ‹‹ቃል አክባሪነትና ሌሎች በራሳቸው ሚዛን መዝነው አውጥተውና አውርደው በሰጡት ኃላፊነት ፤ ባስቀመጡት ቦታ ታማኝ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የታማኝነት ጉዳይ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአ ብሔር›› ማለት እንጂ፤ በሰበብ አስባብ ታማኝነትን ለማጉደል ዳር ዳር ማለት አይደለም፡፡
ታማኝነት ለአገር፤ ለመንግሥትና ለግለሰብ፤ ታማኝነት ለትዳር፤ ወካይ ለተወካይ ወዘተ አስፈላጊ ነው፤ ለምሳሌ፡- ተወካይ ለወካይ ካልታመነ ሀብትና ንብረቱን ሕጋዊና ጠቃሚ ሰነዶቹን አይሆኑ ሁኔታ እንዲደርስባቸው ካደረገ፤ ንብረቱን ከሸጠ፤ ወዘተ ታማኝነት መሬት ላይ እንደ ፈሰሰ ውሃ፤ እሳት ውስጥ ወድቆ እንደቀለጠ ቅቤ ሆነ ማለት ነው፡፡ ድርጊቱ በታማኝነት ፅንሰ ሀሳብና በመልካም ሥነ ምግባር ላይ የተነቀነቀ ዘገር፤ እና የተወረወረ ጦር ፤በታማኝነት ላይ ተጎንጉኖ የተሰራ ጠልፎ የሚጥል ገመድ ሆነ ማለት ነው፡፡
መታመን ትልቅ ዕድል ነው፤ በየትኛውም ሁኔታ እና አጋጣሚ ውስጥ ታምነን ኃላፊነትና አደራ ሲሰጠን ታማኝነታችንን ለማረጋገጥ መሥራት ነው ፤ እያልኩ የዛሬውን ነገሬን በዚሁ ቋጨሁ በሌላ ነገረ- ትዝብት እስከምንገናኝ ብዙ ሰላም ተመኘሁላችሁ፤ ሰላም!!
ከፀሐፊው ሳምናስ
አዲስ ዘመን ጋዜጣ መዝናኛ አምድ።