top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ትልቅ ሃሳብ እና ትልቅ ሰው


ትልቅ ሃሳብ ከትልቅ ሰው ወይንስ ትልቅ ሰው ከትልቅ ሃሳብ ይወለዳል? ወይንስ ተመጋጋቢ ይሆኑ? ያለመነሻስ እንዴት ሊመጋገቡ ይችላሉ?

የሉል አቀፋዊውን ስርአተ-ዓለም ስንዳስስ ምን ግዜም የተሳቀሉና የተመሳቀሉ አያሌ ጉዳዮች ይገኛሉ። ከነዛም ውስጥ አንዱ የትልቅነት እሳቤ ነው። ተምረዋል፣ ልቀዋል፣ ርቀው ሄደዋል የተባሉት ምዕራባውያንም(ምን እንዳላቸው ባላውቅም) ትልቅነትን በአሳብ ደረጃ(Idology) ውጫዊ ከሆነው የሰው ልጅ ማንነት የሚመነጭ አይደለም ብለው ቢያምኑም በሃሳብና በሙግቶች፣ በባሕርይና በምግባሮች ማግኘት ሲያቅታቸው በዘረመል ጥናትና "ትልቅ" ከተሰኙ ቤተሰቦችና ከቤተ መንግስት ከሚወለዱ ልዑላኖች ሲፈልጉ ይስተዋላሉ። እንደውም በአንዳንድ የአውሮፓ ሃገሮች መሪነትንና ተጽዕኖ ፈጣሪነትን ከቁመና ጋር በማንሰላሰል ትከሻው የሰፋ፣ ቁመቱ የረዘመ፣ ድምጸቱ ያስገመገመና የአይኑ ብሌን ሰማያዊ የሆነውን Born leader (ውሉድ መሪ፣ በውልደት መሪነትን ያገኘ) እስከማለት ደርሰዋል። ከዚህም የተነሳ የትልቅነት እሳቤ "ትልቅ" ከሆኑ ሰዎች ብቻ በመጠበቅ ራሳቸውን የትልቅ ሰው እስረኛ አድርገውታል። በፊልሞቻቸውም የጥልቅ አሳቢያንን መገኛ ከBiomedical Enginering ምርምር ማዕከሎቻቸው ሲያወጡ ያሳዩናል።


በዚህ ጽሁፍ ስለ ሃሳብ መልስ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ስለሃሳብ የሚያስቡ አሳቢያን ይገኙ ዘንድ ሃሳብ መስጠት ዋናው ግቡ ነው። ብዙ የፍልስፍናና የስነ-ሰብዕ ተመራማሪዎች የሰው ማንነት የሚወሰነው በአጋጣሚና በአርባ ቀን እድሉ ሳይሆን በአዕምሮው በሚመላለሰው ሃሳብ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህም በፍልስፍናው አለም ያሉቱ ብቻም ሳይሆን በታላቁ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስም ይኸው ሃሳብ በተደጋጋሚ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል።


በጽሁፎቹና በአነቃቂ ንግግሮቹ እውቅናን ያተረፈው ዶ/ረ ምህረት ደበበ የተባለው ሳይኮሎጂስት በአንድ ወቅት በEBS በተባለው የቴሌቭዥን ስርጭት ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ይህንን ሃሳብ ሲደግፍ "በዚህ ሰዓት የአዲስ አበባን ህዝብ ወደ አንድ ያደገች ሃገር ብንወስደውና የዛችን ያደገች ሃገር ህዝብ ወደ አዲስ አበባ አምጥተን በዓመቱ ተመልሰን ብናያቸው አዲስ አበባ ያደገችውን ሃገር ስትመስል ያቺ ያደገች ሃገር አጺስ አበባን መምሰሏ አይቀርም" በማለት እንኳን ኑሮና እሴቶቻችን ይቅርና ሃገርና ገጽታችን 'ራሱ የሃሳባችን ውጤት መሆኑን ያስረዳናል።

ለአንድ ሃገር፣ ማኅብረሰብ፣ ቤተሰብ፣ ድርጅት . . . ሃሳብና አሳቢ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በሃገራችን የሚታዩ ምስቅልቅሎችና የትውልዱ ሞራል መላሸቅ የመጣው በዕድልና በአጋጣሚ ሳይሆን በጥልቀት የሚያስብ መሪና ግለሰብ ከመጥፋቱና ግልብ አሳቢዎችና በእንስሳዊ የደመነፍስ እሳቤ የሚነዱ ሰዎች መበራከት ሳቢያ ይመስለኛል። ለነገሩ ጥቂት በዝምታ ጠለቅ ወዳለ የአሳብ ባህር ስትገቡ ምን ያስተክዛችኋል ብሎ የሚያናጥባችሁ ቁጥሩ የትየለሌ ነው። እንደውም ይህንን በማድረጉ በክፉ ቀን የደረሰላችሁ ያክል ራሱን የሚቆጥርም አይጠፋም።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተባለው ጸሃፊ ስለ ሃሳብ ባነሳበት ጽሁፉ ላይ አንድ ስንኝ ቋጥሮልን ያልፋል።

ኢኮኖሚ ቢሞት በሃሳብ ይነሳል

ፖለቲካ ቢሞት በሃሳብ ይነሳል

ሃሳብ የሞተ ዕለት ወዴት ይደረሳል?


በማለት ስንኙን በጥያቄያዊና መልስ ሰጪ ደግሞም ሞጋች በሆነ አጨራረስ ያስቀምጥልናል። ሃሳብ የሁሉ ነገር መሰረት ነው። የሃገራት ዕድገት የተመሰረተው በአሳቢያን ትከሻ ላይ ነው። ያሰቡ የማያስቡትን ይመራሉ። ይመራሉ ብቻም ሳይሆን ይነዳሉ። አለማችን የምትጓዘው በእድል ሳይሆን በአሳቢዎች ምሪት መሆኑ የተፈታ ህልም ነው። የምድራችን ጥልቅ አሳቢዎች ከተጽዕኗቸው የተነሳ ሞተው እንኳን እየመሩን መሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለው ሃቅ ነው። ለአብነትም የነሶቅራጥስ፣ አፍላጦን፣ ፍሮይድ፣ አንስታይን ሌኒን ማርክስ እና የሌሎችም አያሌ አሳቢያን ስራዎችና ፍልስፍናዎች ዛሬም ድረስ እየገዛንና እየመራን መሆኑን ልብ ይሏል።

የምድርራችን የመፍትሔ ሰዎች የተባሉት በድንገት ሃሳብ የመጣላቸው ሳይሆኑ ጊዜ ወስደው ችግሮችን አይተውና አገናዝበው የመነሻ ችግሩን (Root couse) አጥንተውና ተንትነው ደግሞም ለ'ዛ ችግር መፍትሔ ከተለያየ አቅጣጫ በማየት በመመዘንና በማመዛዘን የሰጡን ሃሳብ በአንድም ሆነ በሌላ ለምድራችን መፍትሔ ሲሆን አይተነዋል።

እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነጥብ ደግሞ በሃሳብና በጭንቀት መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት መኖሩን ነው። ሃሳብ መፍትሔ ተኮር የሆነና በተረጋጋ አዕምሮ የምናውጠነጥነው ሲሆን ጭንቀት ግን ፍርሃትና ውጥረት የነገሰበት፣ መፍትሔ ሳይሆን ሽሽት የሚስተዋልበት፣ ለውሳኔ ያልሆነና በትላንት ቁጭትና በነገ ፍራቻ የተወጠረ ለአዕምሮ በሽታ የሆነ ጉዳይ ነው።

ስለዚህ አገራችን በጥልቅ አሳቢያን ድርቅ የተመታችበት ወቅት ላይ የምንገኝ ይመስለኛል። በአገራችን ሞራል ሲወድቅ፣ ጉርብትና ሲላላ፣ መተሳሰብ ሲሽመደመድ፣ ብሔራዊነት ሲጠፋ፣ ብሔርተኝነት ሲነግስ፣ መተማመን ሲላሽቅ ማኅበረሰቡን በትኩረት የሚያይና የሚገመግም ደግሞም የሚሞግትና የመፍትሔ ሃሳብ የሚያፈልቅ ብርቱ አሳቢ የሚያስፈልገን ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን።

ጥሪው ወደ አሳባውያን መንደር እንዲገቡና የመፍትሔ ሰው በመሆኑ ለዚህ ትውልድ በረከት ይሆኑ ዘንድ ነው።


ምንጭ - ሰዋሰው

75 views0 comments

Comentarios


bottom of page