top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ትራምፕ ፍርጥርጥ ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ትወና (ሳዲቅ አህመድ ኡስማን)


የአባይ ውሃ ከግብጽም ባሻገር በሲናይ አርጎ እስራኤል ሊደርስ ይችላል የሚሉ ዘገባዎች መስተዋላቸው በግድቡ ዙሪያ ብዙ ተዋናዮች እንዳሉ ያሳያል።የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ባህሬን ከእስሬል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንዲጀምሩ የጫጉላ መሰናዶ ያደረገው የትራምፕ ልጅ ባል የሆነው ዴቪድ ኩሽነር እስራኤል የምትጠቀምበት ማንኛውንም ነገር ከማሳካት ወደ ኋላ አይልም።ለትራምፕም የቀረበ መሆኑ ይሰመርበት።

ቀደም ሲል የአባይን ግድብ አስመልክቶ በጻፍኳቸው ጽሁፎች ላይ ሱዳንን አትመኑ ከከንቱ «የሰበርታ» እንጉርጉሮ ዲፕሎማሲ ውጡ።ሱዳንን ጠርጥሩ ብዬ ነበር።ግብጾች በቅኝ አገዛዝ ወቅት ከሱዳን ጋር በአንድ ማእከላዊ አገዛዝ እንመራ ስለነበር ቢንሻንጉል ጉሙዝ ከሱዳን የተወሰደች በመሆኗ ግድቡ በሱዳንና በግብጽ ጥንታዊ የጋራ ይዞታ ላይ ነው የተገነባው ወደሚል ድፍረት እየመጡ ነው።ግብጽ በሱዳን በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በመሬት አትዋሰንም ብሎ የሚታስብ ካለ የዋህ ነው የሚል የማስጠንቀቂያ አናቅጽን በዚሁ መድረክ ላይ ለመክተብ ቢሞከርም ኢትዮጵያውያን አትክሮት አልሰጡትም።ድንበር ዘለል የሱዳን ትንኮሳዎች በተደጋጋሚ መስተዋላቸውን ልብ እንበል።


ቢንሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ በተደጋጋሚ ግጭቶች ይነሳሉ።የግድቡን ስኬት የማይሹ ተዋንያን አለመረጋጋቱ የረጅም ግዜ ጥቅማቸውን ማስከበሪያ በደስታ አይመለከቱትም ማለት ዘበት ነው።ጉዳዩ የትራምፕ ግድ የለሽነት አይደለም።ጉዳዩ የትራምፕ የአፍ ወለምታ አይደለም።ጉዳዩ የፖሊሲ ጉዳይ ነው።ትራምፕ የሚዘራጡና በግልጽ የሚናገሩ በመሆናቸው «ግድቡን መደብደብ» አሉ እንጂ ሌሎችም ፕሬዝዳንቶች የሚያራምዱት ፖሊሲ ተመሳሳይ ከሆነ በሌላ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ወይም በምስጢር ተመሳሳይ ይሁንታን አይሰጡም ማለት አይቻልም።ስለዚህ የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት ጠንክሮ መስራት ያሻል።

የምስራቅ አፍሪካን የሐይል ሚዛን በማደላደል ትታወቅ የነበረቸው ኢትዮጵያ ተቀናቃኞች ተከስተውባታል።ሱዳን ከተሸጎጠችበት ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ መውጣት ስለምትሻ ማንኛውንም ወዛደራዊ ስራ ትቀበላለች።ኤርትራ በአንድ አምባገነናዊ ግልሰብ አምሳል ለ30 አመታት በመቆየቷ እያጣፋት ካለው የምጣኔ ሀብት ችግር ለመውጣት ኢሳያስ በካይሮና በአዲስ አበባ መካከል «ጎምለል» ቢሉ አይገርምም።የአረብ አገራት በጣምራ አሰብን ተከራይተው የጦር ልምምድ እያደረጉ መሆኑ ከተዘገበ ቢቆይም አትኩሮትን አላገኘም።ስለዚህ ብዙ ተዋናዮች በበዙበት የተወሳሰበ ዲፕሎማሲ ውስጥ ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቀው እየወዘወዛቸው ያለውን አለመግባት በመፍታት ለውጭና ለባእዳን ወዝዋዦች እጅ የማይሰጥይ መሆን ነው።

በነገራችን ላይ የቤንሻንጉል ጉመዝ ግጭቶች አንቀጽ 39ን ወልውለው ከነግድቡ ህገመንግስታዊ መብታችን ይተገብር የሚሉ ድምጾች ለወደፊቱ «ሸብረቅ» ብለው ብቅ አይሉም ብሎ የሚገምት ካለ የሱዳን ደላላነት የግብጽ ያበቅየለሽ ሴራ ያልገባው የዋህ መሆን አለበት።

ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ትወና ባለበት ሒደት ውስጥ ኢትዮጵያውያን በሌሎች ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ የራሳቸውን ድክመት ሊፈትሹ ይገባል።ከስቼ ቢያዩኝ ጅማት ለመኑኝ እንደሚባለው የርስ በርስ መናቆሩ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ነው።ፍትህን አንግሶ መጠንከር ከተቻለ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፓምፔዮን ለማናገር ካርቱም መሔድ አይጠበቅብም።ቀጥ ብሎ በመጣ ነበር።

የጎረቤት አገራት በሰው ቁስል እንጨት ስደድ በሆኑበት አኳሗን ሐያላን አገራት ጨወታው ውስጥ ገብተዋል።የአረብ አገራት በሙሉ አሉበት።እስራኤል ተጨምራበታለች።እንደ ሶማሊ ላንድ ኮንፌደሬሽን መሳይ ነገር ወደ ቢንሻንጉል ጉምዝ ከመመዙ በፊት፣የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ተደምጦ ሱዳንና ግብጽ አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች ከመሆናቸው በፊት፣ ኢትዮጵያን በግለሰብ አምሳል ለመቅረጽ የሚደረገው የሞኝ ጉዞ ሰከን ብሎ በብሔራዊ ጥቅም ላይ መደማመጥ ያሻል።የውስጥ ችግሮች በውይይት፣በመመካከርና በድርድር በመፍታት የመጣውን ችግር በጋር መመከቱ ግድ ሆኗል።


ልብ ያለው ልብ ይበል!


ሳዲቅ አህመድ ኡስማን

150 views0 comments

Commentaires


bottom of page