• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አስተሳሰብ ክፍል 1 - መጥፎ ቃል ከወጣ አይመልስም!


መጥፎ ቃል ከወጣ አይመልስም

ከአፉ የሚወጣ መጥፎ ቃልን በቁጥጥር ስር ማድረግ ይቻላል? አዎ! በደንብ አሳምሮ መቆጣጠር ይቻላል!! ለዚህ ደግሞ ቀላል መፍትሄና ዘዴ አለኝ፡፡ ትክክለኛ ጣቢያ ላይ መጥተዋል፡፡ ከኔ ጋ ይቆዩ! የሚያዩትንና የሚሰሙትን ከወደዱት ደንበኛ ይሁኑ፡፡ ለጓደኞችዎም ያካፍሉ!

ከሁሉ በፊት ለማስታወስ ያህል ከአፍ የወጣ ቃል አይመለስም፡፡

ልክ እንደፈሰሰ ወተት አይመለስም፡፡ የዛሬው ዋና አላማየ፤ 1ኛ) መጥፎ ቃል ማለት ምን ማለት ነው? 2ኛ) መጥፎ ቃል መነሻው ከየት ነው? 3ኛ) መፍትሄው ምንድነው? የነዚህን ሶስት ጥያቄወች መልስ አብረን እናያለን፡፡

1) መጥፎ ቃል ማለት ምን ማለት ነው?

ባጭሩ መጥፎ ቃል ሲሰሙት የሚቀፍ፣ የሚያናድድ፣ የሚያሳዝን ወዘተ ነው፡፡ መጥፎ ቃል ወዳጅ ያሳንሳል፡፡ እራስን ዝቅ ያደርጋል፡፡ ጠብ ይጭራል፡፡ ሰወች ግን ለምን መጥፎ ነገር ይናገራሉ? ስለሚቸኩሉ ሁኔታው ከቁጥጥራቸው ውጭ ሲሆን ይመስለኛል፡፡

ችግሮች በመጥፎ ቃል አይፈቱም፡፡ መጥፎ ቃል ከሌሎች የተሻለ ሰው አያደርገንም፡፡ እንዳውም ደራ ውስጥ ያስገባናል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ሁሉ መጥፎ ቃል ከወጣ በኋላ አይመለስም፡፡ አይረሳም፡፡ ምክንያቱም የሰወችን ስሜት ስለሚጎዳ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ሁኔታውና ቦታው ቢለያይም በግለሰቦች መካከል ቂም ሊፈጥር ይችላል፡፡ ወዳጅና ጓደኛሞችን ሊያራርቅ ይችላል፡፡ ቤተሰብ ሊበትን ይችላል፡፡ በህብረተሰብ መካከል ግጭት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ህዝብ ሊለያይ ይችላል፡፡ ሃገር ሊያፈርስ ይችላል፡፡ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ በታሪክ ላይ ጠባሳ ሊጥል ይችላል፡፡

2ኛ) መጥፎ ቃል መነሻው ከየት ነው?

የመጥፎ ቃል መነሻው ችኮላ ይመስለኛል፡፡ ያስቆጣን ነገር ቢኖርም ለማሰብ ጊዜ ካልተጠቀምን መጥፎ ቃላት ይቀድማሉ፡፡ ሰወች ነንና መናደድና መቆጣት ስህተት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ህይወት ውስጥ ብዙ የሚያስቆጣ ነገር ሞልቷል፡፡ የሚያናድድ ሰውም አለ፡፡ ይኸ በራሱ ትልቅ ችግርና ፈተና ነው፡፡

3) መፍትሄው ምንድነው?

ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? መልካም! በመጀመሪያ ለመጥቀስ ያህል ያስቆጣን ነገር በቁጥጥራችን ስር እንዲሆን ማሰብ መቻል ነው፡፡ ችግሩ በቁጥጥራችን ስር ከሆነ መፍትሄው ሩቅ አይደለም፡፡ የሚጥም ወጥ እንኳን ሲሰራ በቁጥጥራችን ስራ ካልሆነ ይገነፍላል፡፡ ወጥ ሰሪው የሙቀቱን ሃይልና መጠን ካስተካከለው ድስቱ በሃይል አይግልም፡፡ የድስቱ ሙላትና ውስጡ ያለው አይነት በልክ ካስገባው ደግሞ ወጡ አይገነፍልም፡፡ መቆጣጠር ማለት ይሄ ነው፡፡ ሃሳብና ቃላትንም ለመቆጣጠር ተመሳሳይ ነው፡፡

አስተሳሰብ ክፍል 1 - መጥፎ ቃል ከወጣ አይመልሰስም!

አንዳንድ ሰወች ማንኛውንም ቃል የመጠቀም መብት አለኝ ሊሉ ይችላሉ፡፡ በምድር ላይ ያየሁት በሙሉ ለኔ ብቻ ይገባኛል ብለው ሊያምኑ ይችላሉ፡፡ ይኸ ጠብ መጫር ነው እንጂ መብት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ከተሳሳተ መብት በፊት ትክክለኛነት ይቀድማል፡፡ ትክክል ያልሆነ ነገር መብት ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክል ካልሆነ ነገር መራቅ ደግሞ መብትን መገደብ አይደለም፡፡

ለማንኛውም የሆነ ሰው ወይም ነገር ሲያናደን በችኮላ ንዴታችንን ለመወጣት መጥፎ ቃል ልንጠቀም እንችላለን፡፡ ችኮላን ለመቀነስ ቀሥሥሥ ብለው ጊዜ ይጠቀሙ፡፡ ጊዜ መጠቀም መሸነፍ ወይም መፍራት አይደለም፡፡ ቀስ ካሉ ለማሰብ ጊዜ ይኖረዎታል፡፡ ማሰብና ጊዜ መጠቀም ከጀመሩ ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡

ችግሩ አስቸኳይ ከሆነም ባስቸኳይ ያስቡበት፡፡ በንግግር ላይ እንኳን ከ 2 - 3 ሰኮንዶች አረፍ ካሉ ጭንቅላታችን ጥሩ ቃል ያፈልቃል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን፤ ካሰቡበት ቃላት መመረጥ ይችላሉ መለቴ ነው፡፡ ለጊዜው ተናደን ከቁጥጥር ውጭ ሆነን ሊሆን ይችላል፡፡ እየቆየ ሲመጣ ግን ሰወች ነንና ብዙ በጎ ቃላትን መጠቀም መጀመራችን አይቀርም፡፡ አስተያየት መስጠት የፈለጉበት ጉዳይ ያነበቡት ከሆነ እንደገና ደግመው ያንብቡት፡፡ ተቀድቶ የሚታይና የሚሰማ ከሆነ ደግመው ይዩት፡፡ ደግመው ይስሙት፡፡ በቃል ብቻ የሰሙት ከሆነ ደግሞ የሰሙትን ነገር ለማስታወስ ይሞክሩ፡፡ ያሰላስሉት፡፡ በግልጽ እንደሚያዩት ለዚህ ሁሉ ጊዜ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ዘዴወች ከተጠቀሙ መጥፎ ቃላትን ለመቀነስ ቀላል ነው፡፡ መጥፎ ቃላትን ከቀነሱ ቢያንስ ለሃገርዎ ኢትዮጵያ አንዲት የሰላም ጠጠር ያበረክታሉ፡፡ የግለዎም ክብርና ዝና ከፍ ይላል፡፡ ቋንቋም የተፈጠረው እንዲንግባባበትና ቃላት መምረጥ እንድንችል ነው፡፡ እውነት ለመናገር ከመጥፎ ቃላት ይልቅ በጎ ቃላት ብዙ ናቸው፡፡ መልካም እድል!

54 views0 comments