top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“እኔ” ሲደመር “እኔ” (በሚስጥረ አደራው)


ሁሉም ነገር ከራስ ይጀምራል። አንተ እና እኔ “ከእኔነታችን” ጀርባ “እኛነታችን” እንዳለ እንዘነጋዋለን። እያንዳንዳችን ከሃገር ደመራ ውስጥ የተሰገሰግን ችቦዎች ነን። አንዱ ሲጎድል ደመራው ቀጥ ብሎ ለመቆም ይቸግረዋል። ሃገርም እንደዛ ናት ብዬ አምናለው። “ሃገር” የሚለው ትልቅ ማንነት የሚፈጠረው “እኔ” በሚባሉ ጥቃቅን ማንነቶች ነው። እኛ ማንነታችንን መቅረፅ ሲሳነን ከእኛ አልፈን ቤተሰብን፤ ከቤተሰብ አልፈን፤ ማህበረሰብን፤ ከማህበረሰብ አልፈን ሃገርን እንጎዳለን።

ሃገር የሚፈጠረው ከምንድን ነው? ከግለሰብ አይደለምን? ታዲያ ስለምን የግለሰብ አስተዋጽዎ እንደ ኢምንት ይቆጠራል? “እኔ ብቻ እንዲህ ባደርግ፤ ምን ዋጋ አለው?” የሚለው አስተሳሰብ የሚመጣው፤ “እኛን” ከ “እኔ” ስንነጥለው ነው። ተቀበልነውም አልተቀበልነውም ሁላችንም ሃገር ነን። የአንዳችን ቀጥ ብሎ አለመቆም የሃገርን ደመራ ያንገዳግደዋል።ሰዎች እራሳቸውን መለወጥ ሲችሉ፤ ያለምንም ድካም ቤተሰብ ይለወጣል፤ ማህበረሰብ ይለወጣል፤ ሃገር ትለወጣለች። ሃገር የብዙ “እኔዎች” ድምር ናት። ታዲያ ለምን ለውጣችን ከእኛ አይጀምርም?

በተተራመሰው አሰራር ውስጥ የእኔ አስተካክሎ መስራት ምን ለውጥ ያመጣል? የምንለው ብዙዎቻችን ነን። ግን አስቡት ሁላችንም እንደዛ ባንል እና ብንለወጥ፤ ትርምስምሱ አይሰተካከልም ትላላችሁ? እኔ በግሌ የሁሉም ነገር መሰረት ከገዛ እራሳችን ይጀምራል ብዬ አምናለው። ሃላፊነት የጎደለው ትውልድ፤ ታሪክ ለመስራት እንዴት ይችላል?

ሁላችንም መልካም ቤተሰብ፤ መልካም ማህበረሰብ፤ ድንቅ ሃገር፤ እንዲኖረን እንመኛለን ብዬ አምናለው። ነገር ግን ሃገር የ”እኔ” ድምር መሆኑን ዘነጋንና፤ እራሳችንን ከለውጥ ሰልፈኛነት አወጣን። አስቡት፤ ሁሉም ሃላፊነቱን ወስዶ፤ እራሱን መለወጥ ቢችል፤ ስለ ትልቁ ለውጥ እንጨነቅ ነበር? ሃገርን እንደ አንድ ንፁህ ባህር አስቧት፤ ሁሉም ያሻውን ቆሻሻ የሚደፋባት፤ ግን ያን ባህር ለማፅዳት ቢታሰብ መፍትሄው ምንድን ነው? ሁሉም የራሱን ሃላፊነት መውሰድ !!! “እኔ ቆሻሻ መድፋት ብተው፤ ሌላው ይደፋ የለ?” የሚል አስተሳሰብ ባይኖር፤ ሁሉም ባይሆን አብዛኛዎቹ ቆሻሻ መድፋታቸውን ያቆማሉ። መቼም ከብዙ ቆሻሻ ትንሽ ቆሻሻ ይሻላል።

እናም ሌላው ስለሚያደርገው ነገር ባንጨነቅ እና የራሳችንን ሃላፊነት ወስደን የገዛ እራሳችንን ብንለውጥ፤ ቢያንስ ካለብን ቆሻሻ፤ በእጅጉ የቀነሰ ቆሻሻ ነው የሚኖረን።

የኔ መልዕክት፤ እራስን ስለመለወጥ ነው፤ የእያንዳንዳችን መልካም ማሰብ፤ በጎ ማድረግ፤ ቀና መመልከት፤ ስራ መውደድ፤ ለውጡ ለገዛ እራሳችን ብቻ አይደለም። የሁሉም ነገር መሰረት “እኔ” ነው። “እኔ” ሲደመር ብዙ “እኔዎች” ናቸው ማህበረሰብን፤ ብሎም ሃገርን የሚፈጥሩት። እኔ እንደ ወጣት ትልቅ ምኞት አለኝ፤ ለአንዳንዶቻችሁ ላይዋጥላችሁ ይችላል፤ ግን መልካም እራዕይ ያለው ትውልድ ለመፍጠር፤ ሁላችንም የገዛ እራሳችንን መፈተሽ አለብን። “እኔ መልካም ባደርግ፤ ሌላው አያደርግም” ብለን የተሻለ ነገር ለማድረግ አንቆጠብ፤ እንደዛ ማለት ካቆምን ብዙ “እኔዎች” ይለወጣሉ፤ ብዙ “እኔዎች” ሲለወጡ፤ ማህበረሰብ ብሎም ሃገር ትለወጣለች። በመጨረሻ ሁላችንም ለማንኘውም ነገር ሃላፊነታችንን እንድንወጣ እለምናለው።


ሚስጥረ አደራው

42 views0 comments
bottom of page