• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እንስሳ መሆን አማረኝ!

(በሎሬት የትነበርሽ ንጉሤ)

ያለ ወትሮው ዘር ሳልቋጥር እንዲሁ ሌጣዬን ሆኜ ሠው የመሆን አባዜ አውርጄ አውጥቼ አጢኜ ግብሩ ከምክሩ ሲጣረስ ሲጎድል ከሰውነቱ አንድ ቀን እራሱን ሳይሆን... እንደነ እንትና እየኖረ እገሌን መስሎ መሞቱ። ውሃ ቅዳ ውኃ መልስ ሰው መሆን አቦ ደበረኝ ሲያምርሽ ይቅር እንዳትሉኝ # እንሰሳ መሆን አማረኝ በቃ አማረኝ እንስስነት የት ይገኛል እባካችሁ መች መች ውል እንደሚለኝ ልንገራችሁ። የኑሮን መሻት ተቆጥሮ በተሰጠኝ ዕድሜ ወድያ ወዲህ በምልበት ታክሲ ጥበቃ ቆሜ መፈክር ሳያነግቡ ከቆሙ ሰልፈኞች መሃል አንድ ሱፍ ለባሽ ተነጥሎ ፊቱን ወደ ግንብ ያዞራል ሁላችንም በመገረም ይህን መሳይ ሙሁር ዜንጦ ምን የሚነበብ ቢያይ ይሆን የወጣው ሰልፍ አቋርጦ ክፍት የስራቦታ ይሆን? ነፃ የትምህርት ዕድል? የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ? ኮንዶሚኒየም ድልድል? እያለ ሁሉም በሆዱ ዝም ብሎ አጉቶምትሞ ይታደም ጀመረ አዳሜ ከረጅም የታክሲ ሰልፍ ቆሞ። ሱፍ ለባሹ ከመቅፅበት የሱሪዉን አዝራር ፈቶ እናንተ የምታዩኝ እኔ ማላያችሁ እያለ ጨረሰ ውኃ ሽንቱን ሸንቶ። እንዲህ የሰው ልጅ ነውሩን መሸፈን አቅቶት ሲገኝ እስኪ አሁን ምን ክፋት አለው እኔ # ድመት መሆን ቢያምረኝ? ሠው በሚለው የወል ስሙ ከዚህ ፍጡር ከመደመር በቃ አማረኝ ውሮ ሆኜ ነውሬን ቆፍሬ መቅበር። ጉድ ብለን ሳንጨርስ የቆየው ታክሲያችን መጣ የሚያምር አቋቋማችን በድንገት ደርሶ ቅጥ አጣ አቅመ ደካማው ሲማረር ጉልበተኛው ተጫነ መገፋፋት ነገሰና ተራ ማክበር ተራ ሆነ ተ…ራ ሆነ። ብዙ ተገፋሁኝና እኔም ገፍቼ ስሳፈር # ጉንዳን መሆን አማረኝ ሰልፍ አክብሮ መከበር አማረኝ አማረኝ ጉንዳን መሆን ውይ ሲያስቀና ሁሉም እኩል ለፍቶ አዳሪ ኪስ ጡንቻ ሳያፋልሰው ሁሉ ወረፋ አክባሪ በክፉ ቀን አብሮ ዘማች በደጉ ቀን አብሮ ነዋሪ በቃ አማረኝ ጉንዳን መሆን ያለዘብ ፍትህ አስፋሪ። ይህን አምሮት ሳሰላስል ከመውረጃዬ ደረስኩኝ አራስ ጓዴን መጠየቅያ ገፀ በረከት ሸከፍኩኝ ቤቷ ስገባ ... ባልየው ቁጭ ብሎ ከሶፋ ቃና እያየ ይዝናናል ይስቃል ልቡ እስኪጠፋ ሞቅ አድርጌ ሰላም ብዬ ወደ ጓዳ ስገባ የአንድ ወር አራስ ጓደኛዬ ልጇን አዝላ ከጀርባ ለባሏ መክሰስ ልትሰራ ድስት ጥዳ ታቁላላለች ልጁን ለማይወድ አባት ለምን ትመግባለች? # ፒንጊዊን መሆን አማረኝ ውይ ሠው መሆን ሲያስጠላ ወንድ ፒንግዊን ተሳክቶለት ፍሬ ልትሰጥ ሴቲቱ እንቁላል በጣለች ጊዜ እሲኪፈለፈል ጫጩቱ እንቁላሉን ይጠብቃል ከሴቷ ጋ ተራ ገብቶ እንጂ እንደ ሰው ተኮፍሶ ስራሽ ያውጣሽ አይል ከቶ። ሆቴል ገብቶ ሳይሰለጥን ለወርክ ሾፕ ሳንጋብዘው የዘመቻ ቲሸርት ሳይለብስ አበል ሳንከፍለው የአባትነት ድርሻውን ፒንግዩን በአግባብ ከተወጣ እንስስንት በስንት ጣዕሙ ሰው መሆን ትርጉም አጣ። ሰዉ መሆን ክብር መሆኑን በቃ እንግዲህ ድሮ ቀረ የሃምሳ አመት ጎልማሳ የአመት ህጻን ከደፈረ ሰርቶ አደሩ ደህይቶ ሰርቆ አደሩ ከከበረ የፈረቃ ትምህርት ሲቀር በፈረቃ ከተቃመ ልጅ ከአባቱ ቤት ዘርፎ ጥሪት ካጠራቀመ ይህ ሁሉ ስመለከት ሰው መሆን እጅግ ደበረኝ እያሰቡ ከማሳበብ ሳያስቡ ለመሰብሰብ እ…ን…ሰ…ሳ መ…ሆ…ን አማረኝ አማረኝ አማረኝ

101 views0 comments