top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ከጉራጌ ክልል ምስረታ በፊት የጉራጌውያን አንድነት አይቀድም ነበርን? (በኢዱና አህመድ ኡስማን)

Updated: Jan 9, 2021


ከጉራጌ ክልል ምስረታ በፊት የጉራጌውያን አንድነት አይቀድም ነበርን? (በኢዱና አህመድ ኡስማን)

ዛሬ ላይ ሃገራችን በተለያዩ ጉዳዮች እየተናወጠች የምትገኝ ሲሆን በርካታዎች እንደፍላጎታቸው በየሶሻል ሚድያው የራሳቸው የሆነ ሃሳብን ብቻ ሲያራምዱ ገሚሱ ደግሞ ሃገራዊ በሆኑ ጉዳዮችና ሁሉ አቀፍ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲርመሰመስ ተስተውሏል። ነገሩ ለሃገር ብሎ ሁሉንም አቅፎና ሌላውን ሳይጎዱ ለሁሉም ደህና በሆነ ጉዳይ ብቻ መንቀሳቀስን ያህል ደህና አይኖርም። አንዳንዴ በግሌ እንደ ሃገር ሲታሰብ የሃገርና ህዝብን ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ሲባል የሚዋሽ ውሸት ቢኖር እንኳን ለመቀበል ዝግጁ የሆንኩ ያህል ይሰማኝል። ለምን ቢባል? ሃገር በሚል በተካለለው ዙሪያ ሰላም ሲሰፍን በሃገሩ ውስጥ የሚኖረው የሰው ፍጡር ሁሉ ደህና ስለሚሆን ነው። በእርግጥ በሃገራችን በሰሜኑ ክፍል ይሁን በሌሎች አካባቢ የሚደርሱ የሰላም መደፍረስና ክቡር የሆነው የሰው ህይወት መጥፋት በእጅጉ ያማል። በተጨማሪም ህዝብን ሲበድል እና ሲገድል በነበረው ላይ የሚወሰደውን እርምጃ የሚቃውሙት አቋም ደግሞ እጅጉን ያማል። መደግፍና መቃወም የግለሰቡ መብት እና መብት ቢሆንም በዚህ ደረጃ ለበዳይ፣ ገዳይ እና ዘራፊ ደጋፊና ጠበቃ ሆኖ መገኘቱ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ነበር። ትላንት የተሰማው በነጃሺ መስጂድ ላይ ደረሰ የተባለው ጉዳትና ዘረፋ ደግሞ የገዘፈ ጥርጣሬ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያስቀምጥ ሲሆን ማን አደረገው ለሚለው ሁሉም ላለመውደቅ የሚውተረተረው የፖለቲካ አራማጅ ተጠርጣሪ ያደርገዋል። በሰከነ መንፈስ አጣርቶና አረጋግጦ መጠየቁ የግድ ይላል። ነገር ግን የሙስሊሙን የእምነት ተቋም በማውደም እስልምናን እና ሙስሊሞች ከመንገዳቸው ማስተጓጎል እንደ ማይቻል መታወቅ እንዳለበት ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ “መስፍን ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ” የአለም አቀፍ የጉራጌ አንድነት ድርጅት አመራር በፌስ ቡክ ገጽ ላይ “የተሻለ አማራጭ ስላላየሁ የኢዜማን መስመር መርጫለሁ” በሚል ያስቀመጠው የመግቢያ ሃሳቡን በተመለከተ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቼው ነበር :-

የራስህ ብቻ የሆነ አማራጮች ማበጀት ካልተቻለህ አንዱ ላይ መውደቅ የግድ ይልሃል። ነገር ግን የትኛው ጉራጌ እማን ላይ መውደቅ የሚለው እራሱ በጣም አሳሳቢ ነው። ሶዶ፣ መስቃንና ሰባት ቤት ጉራጌ ምርጫቸው ሊለያይ ይችላል። ጉራጌ እንደ ብሔር እና እንደ ሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦች አማራጭ የፖለቲካ መነገዶቹን ማበጀት ተስኖታል። ለምን ብሎ የሚጠይቅ ከተገኘ? አዎን… በታሪክ ጉራጌ አንድ ሆኖ ስለማያውቅ ይሆናል ምላሹ። በጉራጌውያን ግራ አስተሳሰብ ምክንያት የጉራጌ እጣ ፈንታ "እናቴ ያገባ ሁሉ አባቴ ነው አይነት ሆኗል"። ብዙውን ግዜ ስለ ጉራጌ አንድ አለመሆን ከወደ ሶሳል ሚድያው ሲፃፍ ምኑም ያልገባቸው እምቦቅቅላዎችና የፖለቲካ ቆማሪዎች ወደ ስድብ እና ስም ማጥፋቱ ሲሮጡ ይስተዋላል። እውነታው ግን ይህ ነው “አዎን እኛ ጉራጌዎች በታሪክ አንድ ካለመሆናችን ባሻገር አንድ ለመሆን በሚያበቁ መስፈርቶች ዙርያ ተወያይተንም ሆነ ተስማምተን አናውቅም”። ሰባት ቤቱ ጉራጌ ልክ እንደ ትግራዩ የአድዋ ተወላጅ እኛ በላጭና ለእኛ ይገባናል በሚል የዘገየ አስተሳሰብ ተጠፍኖጎ ብቻውን ወይም በምስራቅ የሚገኙትን ሶዶና መስቃንን አግልሎ ለሶስት አስርት አመታት ስልጣንና ጥቅሙን ሲቀራመት ቆይቷል። የሚገርመው ክልል የሚባለውም ጉዳይ ሲነሳ ጭምር ከምእራብ ጉራጌዎች የይገባናል ጩኸት በርክቶ መክረሙ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ሰባት ጉራጌ ብቻ ፈላጭ እና ቆራጭ በሆነበት የጉራጌ ዞን የክልል ምስረታው ለሰባት ቤት ጉራጌ ወይም ለሁሉም ጉራጌዎች የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ነው ያለፈው። ታዲያ ወዳጄ ጉራጌን አንድ ሳታደርግና ሌላው ወንድምህን አንድ አላማው ውስጥ ለማካተት እራስህን ሳትገራ (የእኔ እና ለእኔ ብቻ የሚለውን የላይ ጉራጌን ፍላጎት ሳታቀጭጭና ሳታስወግድ) በምን መስፈርት ስለ ክልል በጉራጌ ስም ይደሰኮራል?


የሚከተለው ሃሳብ ለመስፍን ሙሉጌታ ከሰጠሁት ምላሽ ጋር በማያያዝ ጉራጌን አሳንሰው ለሚያስቡት የሰጠሁት ምላሽ ተደርጎ ይወሰድ!

የጉራጌ ማህበረሰብበጣም ሰላማዊና ለስራ ብቻ የተፈጠረ በሚያስብል ደረጃ የሚኖር ማህበረሰብ ነው። አንዳንድ ምስኪንና የሰላም ፍልስፍናው ያልገባቸው ኢትዮጵያውያን ጉራጌን ፊሪ እና አቅመ ቢስ በሚል ሲሰይሙት ይስተዋላል። እንደ ሌሎቹ በወረደና ደደብ ቋንቋ ይወራና ጉራጌ ሰፍሮ በሚገኝበት ዙሪያ የሚገኙ ከጉራጌ ውጪ የሆኑ ማህበረሰቦች ይጠየቁ! ልክ እንደ ማንኛውም አጎራባች ብሔረሰቦች መካካል እንደሚከሰተው ግጭት በጉራጌ ዙሪያ ከሚገኙት ጋር ተከስቶ ከሆነ ጉራጌ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣቸው ወይም አስፈላጊውን የመከላለል እርምጃ እየወሰደባቸው ቢሆን እንጂ በታሪክ ከአጉራባቾች ማህበረሰቦች ጫና ደርሶበት እና መብቱን ማስከበር ተስኖት አያውቅም ወይም በጫና ስር ብቻ ኖሮ አያውቅም። በአጼዎቹ ዘመን ጫና ይደርስ ነበር የሚል ከተነሳ አጼዎቹ የወጡበትን ማህበረሰብ ጭምር ጭሰኛ አድርገው ነበር የሚያስተዳድሩት ክስተት ነበር። ጉራጌ ሰላም ወዳድ እንጂ ፈሪ አልነበረም! አይደለምም!


ውድ ጉራጌዎች ስለጉራጌ ሲታሰብ እና ሲሰራ ሁሉም ማንነቱን ይዞ እንደ ጉራጌ ያስብ ይሰራል እንጂ ሁሉም ሰባት ቤት ጉራጌ ብቻ፣ ሁሉም መስቃን ብቻ ወይም ሶዶ ብቻ ሊሆን አይችልም ። የሶዶ፣ የመስቃንና የሰባት ጉራጌ ጥምረት የትልቁን ጉራጌ ጥምረት ይፈጥራል። ነገር ግን አንዱ ብቻውን ትልቁን ጉራጌ ሊሆን ወይም ሊሰራ አይችልም። የጉራጌ አንድነት የሚያሳስበን ከሆነ የምስራቁን አቅፈንና የሚገባውን ወደ እራሱ መልሰን እና ሰጥተን ለመስራት ቢጣር የተሻለ እንደሆነ እስከዛሬ የተጓዝንበት መንገድ ያስተምራናል ብዬ አስባለሁ። ካልተሳሳትኩ በሰባት ቤት ጉራጌ ተወላጆች መስራችንነት የጉራጌ ህዝብ ንቅናቄ (ጉህን) የሚሰኝ ድርጅት መሰረትን ተብሎ በሶሻል ሚድያ ወሬው ተረጨ። የዚሁ ድርጅት መሪ ነን የሚሉት በአዲስ አባባ የተለያዩ ስብሰባዎችን እና ወሊቂጤ ከተማ አንድ ስብሰባ ከማድረጋቸው ባሻገር ቡታጅራ ከተማ ሴራና አዳራሽ ውስጥ ወጣቶችን ቲሸርት በማስለበስ እና ከውስን የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎችና ለፕሮፓጋንዳው ስራ ከወልቂጤ ከተማ የመጡ የሰባት ቤት ጉራጌ ተወላጆችን በማካተት ስብሰባ አደርገው ነበር። ታዲያ ያ…“ጉህን” የተባለው ድርጅት መካከለኛ ምስራቅ የሚገኙት እህቶቻችን በመደለል ከገንዘብ መሰብሰቢያነት የዘለለ ስራ ሲሰራ ካለመታየቱ ባሻገር ከምስረታው ጠፍቷል። በቅርቡም እንደዚሁ የጉራጌ አለም አቀፍ ድርጅት ተብሎ ተመስርቶ የነበረ ሲሆን ይኸኛውም እንደ ከዚህ በፊቱ “ጉህን” እየደበዘዘ መጥቷል።

ውድ አንባቢያን ሰባት ቤት ጉራጌዎች በሚል የወቀሳ ሃሳቦች በእዚህ ጽሁፍ ይሁን ከዚህ ቀደም ጉራጌን በተመለከተ እንደ አንድ የጉራጌ ተወላጅ ሃሳቦቼን የማሰፍር ሲሆን ድርጊቴ ከእኛ በቀር የሚለውን የላይ ጉራጌን አመለካከት መቃወም እንጂ ለህዝቡ የተለየ ጥላቻ ኖሮኝ አይደለም። የሰባት ጉራጌ ህዝብ በስራ እና ሰላም ወዳድነቱ የሚታወቅ ነው። ወደድንም ጠላንም ወንድማማቾች ነን። ነገር ግን ጉራጌን አንድ አላደርግ ያለው አመለካከትን የሰባት ጉራጌ ተወላጆች በተለየ መልኩ የአመለካከቱ ደጋፊ ሆነው መገኘታቸው ከአመራሮቹ በደል በተጨማሪ እና በላቀ ሁኔታ ድርጊቱ ጎጂ እና የሚያሳምም ነው የሚሆነው።

በእርግጥ ለጉራጌ አንድነት ያሻዋል! የጉራጌን አንድነት በምን መልኩ እናምጣው ብሎ የሚጠይቅ ጨዋ ከተገኘ? አዎን በጉራጌዎች መካከል አንድነትን ለመመስረት ከፖለቲከኞቹ ባሻገር የሁሉም ጉራጌዎች (መስቃን፣ ሶዶ እና ሰባት ቤት ጉራጌ) የሃገር ሽማግሎዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሑራን፣ ወጣቶችን በእኩል ያካተተ ስራ ከተሰራ የአንድነቱ እቅድ ይሰምራል ብዬ አስባለሁ። ሌላው... ወደጆቼ የጉራጌዎች ጉዳይ ከሚሰራው ፕሮፐጋንዳ በላይ ስለሆነ የውሸትና የተጋነኑ የሰርተናል ወሬዎቹ ረገብ ቢሉ መልካም ነው። ጉዳዩ ሶሻል ሚድያ ላይ በሚለጠፍ የዘርማ እና አርዴዎች ጥምር ፎቶ ወይም የጉራጌ አንድነት ድርጅት በሚያደርጋቸው የቀጥታ ውይይቶች ብቻ የሚገመት መሆን የለበትም። መሬት ላይ የወረደ፣ ሁሉንም ያቀፈ እና ሁሉም ዘንድ የደረሰ ስራ ከተሰራ አላማው የሚሰምርበትና መልካም ፍሬውን የምናይበት ጊዜ ቅርብ ነው የሚሆነው። ሌላው መሬት ላይ የወረደ ስራ ሳይሰራ በሶሻል ሚድያ ውስን ጩኸት ብቻ የክልል እናሰመልሳለን የነበረው ጩኸት አሳዘኝና አሳፋሪ ነበር። ወዳጄ ሆይ... በሶሻል ሚድያ የተመለሰም ሆነ የተሰራ ክልል የለም! ሁሉንም ወይም የሚመለከተውን ያቀፈ እና መሬት በወረደ ስራ ቢሆን እንጂ! ብዙ ወንድምና እህቶች በሶሻል ሚድያው ጩከት የጉራጌ ክልል የሚመለስ ወይም ለጉራጌ ክልል የሚሰጥ የሚመስላቸው የነበሩ እንደነበር ታውቁ ኖሯል? ጉዳዩን ወደ ሶሻል ሚድያ ከማምጣታችሁ በፊት ትክክለኛ የሆነ እቅድ ነድፎ ፣ በርካታ ደጋፊዎችን አካትቶና አሰባስቦ የድምጽ ማሰማቱ ጥቅም ግንዘቤን መፍጠሩ የግድ ይላቹሃል። ሶሻል ሚድያ ጉዳይን ታደርስብትና ትቀሰቅስብት ቢሆን እንጂ በራሱ ብቻ ጉዳይ አያሰፈጽምልህም። የማድረሱና የመቀስቀሱ ጉዳይ እንኳን የተሳካ የሚሆነው በሚኖረህ ተከታታይ ብዛት ብቻ ነው የሚሆነው።


"በመልካም ለመልካም የሚደረግ አንድነትን የሚጠላ እና የሚቃወም ቢገኝ እርሱ... ሰይጣን ቢሆን እንጂ ሌላ አይሆንም!"


ቸር እንሰንበት!


ኢዱና አህመድ ኡስማን

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

ታህሳስ 24 2013

99 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page