top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ክብር ለሚገባቸው ክብር እንስጥ ! (በአብድረሂም አደም)



ቡታጅራ ያፈራቻቸው ቡታጅራዬ ውለታሽ አለብኝ ብለው ጊዜ፣ ድካም የአየር ንብረት፣ ሳይገድባቸው እንዲሁም የህዝቡ የአመለካከት ልዩነት ሳያሸንፋቸው እራስእስከመሰዋት ድረስ ቢሆን እንኳን ህዝብን የሚያገለግሉ የህዝብ ልጆች አሏት:: ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እና ፊት መሪው የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ስራአስኪያጅ ወጣት “መሀመድ ሁሴን ሽራጋ” ነው።

ወጣት መሀመድ ሁሴን በቅርቡ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ ሆነው ሲሰሩ የከተማው ህዝብ ያወዛገቡ በርካታ ውስብስብ ስራዎች ለህዝብ ግልጽ ሆነው እንዲታወቁና ተደራሽ እንዲሆኑ ህዝቡም በቀጣይ መብቱ ሆኖ አውቆት መጠየቅ እንዲችል ካደረጋቸው አንዱ የህዝብ ማከፋፈያ ዳቦ ቤት በከተማው ተደራሽ ሆኖ ህዝቡ ተጠቃሚ በሚያደርግ ርቀት እንዲገኝ ማድረግ ችሏል። ወጣት መሀመድ ሁሴን የሴክተሩ ውስብስብ ስራዎች በማጥራት ሴክተሩ መምራት ሲጀምሩ በከተማው ግዙፍና የበለጠ ውስብስብ ስራ ባለቤት የሆነው የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራአስኪያጅ በመሆን ተሾመ።

ወጣት መሀመድ ሁሴን ማዘጋጃ ቤቱ መምራት ሲጀምር የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገው ከሚመራው ሴክተር ሰራተኛ ከተበታተነ አመለካከት ወደ አንድ አይነትነት ማምጣት እንዳለበት በመረዳት ይህን ተግባራዊ አድርጓል። የባለሙያ መግባባትና መተባበር ካለ ምን የማይሳካ ተግባር አይኖርምና ማዘጋጃ ቤቱ ለበርካታ አመታት በወረቀት ላይ ያቆያቸው ተግባራት ወደ ተግባር በመቀየር ተግባራቶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፦

1. የከተማው ነዋሪ የሆኑ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት ችግሩ አሳሳቢና ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን በመረዳት 16 ክፍሎች ያሉት የቁጠባ ቤት low cost house 748,009.61 ብር ቡታጅራ ጨርቃጨቅ ፋብሪካ አካባቢ እያስገነባ ይገኛል። ለዚሁ አካላት የሚሆን የጋራ መፀዳጃ ቤት /Communal toilet 299,404.37 ብር በመገንባት ላይ ነው።

2. ከረድኤት ሆቴል በስተጀርባ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች አንድ ደረጃውን የጠበቀ የጋራ መጸዳጃ ቤት 197 991.82 ብር ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል።

3. ቡታጅራ ከተማ እድገትዋን ተከትሎ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ እንሚያስፈልጋት በማመን የሚሰሩት መንገዶች በመለየት መንገዶቹ ሁሉንም በአንድ በጀት አመት ማሰራት ስለማይቻል የሚሰሩት መንገዶች በጊዜ በመከፋፈል እንደሚገነቡ አቅጣጫ በማስቀመጥ በመጀመሪያ ዙር በከተማው በሶስት አቅጣጫ አንደኛው ከጉብሬ መንገድ በከተማ አስተዳደሩ አድርጉ በርሄ ዘይት መጭመቂያ መንገድ ያገናኘ ሀለተኛው ከሆስፒታል ዝቅ ብሎ ከአዲስ አበባ ዋናው መንገድ ያገናኘ ሦስተኛው በቆዳ ሌጦ ሆሳና ዋናው መንገድ እስከ ቡታጅራ ትልቁ መስጅድ የተሰሩ ሲሆን አጠቃላይ የመንገዶቹ ርዝመት 4.65 ኪ.ሜ ነው። እነዚህ መንገዶች ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የሁለተኛው የግንባታ ጊዜ በአቶ መሀመድ ሁሴን ስራአስኪያጅነት ወቅት ሆነና የመጀመሪያው የግንባታ ተግዳሮቶች በመለየት ለሁለተኛው መደገም እንደሌለባቸው ውሳኔ በማስቀመጥ ለዚሁም ችግር ፈቺ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እውቅና ያለው ዳምራ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የመንገዱ ስራው አማካሪ ሆኖ እንዲሰራ ውል ተገብቷል።

4. የሰው ልጅ በሚኖርበት አካባቢ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራ አንዱ ነው። ማዘጋጃ ቤቱ ይህንን ፍላጎት በመረዳት የአረንጓዴ ስፍራ/Green area ግንባታ በእሬሻ ክፍለ ከተማ 03 ቀበሌና በእሪንዛፍ ክፍለ ከተማ 05 ቀበሌ ግንባታ ላይ ይገኛል።

5. ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ቴሌ ፊት ለፊት ከዚህ በፊት ተተክሎ ለበርካታ ጊዜያት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ሰርቶ ማሳያ መስሎ የቆየውን የትራፊክ መቆጣጠር መብራት ቀሪ ስራውን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጓል።

ይህ የትራፊክ መብራት የከተማው እድገት ተከትሎ የተሽከርካሪዎች መብዛትና ከተማዋ የደቡብና የኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የምታገናኝ ከተማ በመሆንዋ በርካታ ተሽከርካሪዎች የምታስተናግድ ከተማ ናት ይህን ተከትሎ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋ ችግሮች ለመቅረፍ አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን በርካቶች አስተያየታቸው አስቀምጠዋል።

6. የቡታጅራ ከተማ ኤሌክትሪክ መስጫ ማዕከል ከ630 KVA ወደ 1250 KVA Compact ትራንስፎርመር እንዲያድግ በማድረግ በደቡብ ክልል ብቸኛ ሆኖ ቡታጅራ ፖስታ ቤት ፊት ለፊት ተተክሏል። ይህ የከተማው የኤሌክትሪክ መስጫ ማእከል በቀጣይ የከተማውና ዙሪያው አካባቢዎች የመብራት ችግር ሙሉ ለሙሉ ከመቅረፉም ባሻገር ከተማዋ የኤሌክትሪክ ሀይል ችግር ባለመኖሩ ትላልቅና ግዙፍ ኢንደስተሪዎችንና ኢንቨስትመንቶች የመቀበል አቅም ስለሚኖራት የበርካታ ኢንቬስተሩች ቀልብ በመሳብ በርካቶች በከተማው መዋለንዋያቸው በማፍሰስ ተጠቃሚ በመሆን በርካታ የአካባቢው ህብረተሰብ የስራ እድል በመፍጠር አካባቢው ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።

7. የመምህራን የጋራ ቤት ልማት ፕሮግራም መምህራን በማህበር የተደራጅተው ቁጠባቸው አጠናቀው ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ለአመታት ሲንከባለል የቆየውን ፈጥኖ ይዞታው ከይገባኛል ነፃ በማድረግ ለማህበራቱ ማስረከብ ችለዋል።

መምህራን የተከበረው ሙያቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት በሰው ልጅ ጭንቅላት ላይ በመሆኑ የቀጣይ ትውልድ ህይወት ከፈጣሪ በታች አስተካክሎና በአግባቡ አብቅቶ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚያፈራ ሙያ ባለቤት እንደመሆናቸው የመምህራኑ የይዞታ ባለቤት ማድረጉ ሙያው ያከበረ ለትውልድ መልካሙን ያሰበ ተግባር ነው።

በዚህ የማዘጋጃው መልካም ተግባር መምህራኖች በሙያቸው ፍቅር እንዲኖራቸውና ያላቸውን ጊዜ በትምህርት ስራና በአካባቢው ችግር ጥናትና ምርምር በመሳተፍ የአካባቢው ችግር ፈቺ አካል እንዲሆኑ የሚያነሳሳ ተግባር ነው።

8. የልማት አርበኛው ወጣት በ21565029.63 ብር የዲች ግንባታ 2.5 ኪ.ሜ , የመንገድ መብራት በአዲሱ አስፋልት ከዋርካ እስከ ጉብሬ መንገድ 2.26 ኪ.ሜ የኮንክሪት ግንባታና የፒቪሲ ዝርጋታ እንዲሁም የኮብል ንጣፍ ውል ተገብቶ እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ በፊት ተገንብተው ካልቨርት ያለበሱና የተለያዩ ተቋማት መውጫ መግቢያና የተለያዩ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የሚያገናኙ የአስፋልት መንገዶች ተገቢውን ካልፈርት ግንባታ ማድረግ ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ የከማው የውስጥለውስጥ መንገድ አስፈላጊ በሆነባቸው አካባቢዎች ከዚህ በፊት በተሻለ የኮብል ንጣፍ ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ወጣት መሀመድ ሁሴን የሁልጊዜ መፈክራቸው ከዚህ በፊት የለሙ ልማቶች ደህንነታቸውን ጠብቆ ማስቀጠልና አዳዲስ ልማቶችን እንደ አስፈላጊነታቸው ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየትና ህዝቡን በማሳተፍ እያለማን እንቀጥላለን ይላሉ። አቶ መሀመድ ሁሴን በድጋሚ "እኛ ህዝቡን ይዘን ለልማት፣ ልማት ደግሞ ለህዝቡ እና እኛ ደግሞ መሪም ሆነን ህዝብ ነን መጠቀማችንም ከህዝብ ጋር ነው" ይላል።

ክብር ለሚገባቸው ክብር እንስጥ !


አብድረሂም አደም

መስቃን ሚድያ ኔትዎርክ

ቡታጅራ

93 views0 comments
bottom of page