• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ዓድዋ (ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን)


ዋ! .... ያቺ ዓድዋ

ዋ!....

ዓድዋ ሩቅዋ

የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

ዓድዋ.....

ባንች ብቻ ሕልውና

በትዝታሽ ብጽዕና

በመስዋዕት ክንድሽ ዜና

አበው ታደሙ እንደገና.....

ዋ!

ዓድዋ የዘር ዐጽመ ርስትዋ

የደም ትቢያ መቀነትዋ

በሞት ከባርነት ሥርየት

በደም ለነጻነት ስለት

አበው የተሰውብሽ ለት፤

ዓድዋ

የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ

የኢትዮጵያነት ምስከርዋ

ዓድዋ

የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ

ታድማ በመዘንበልዋ

በጽምሽ በትንሣኤ ነፋስ

ደምሽ በነጻነት ሕዋስ

ሲቀሰቀስ ትንሣኤዋ

ተግ ሲል ሲንር ትቢያው

ብር ትር ሲል ጥሪዋ

ድው እልም ሲል ጋሻዋ

ሲያስተጋባ ከበሮዋ

ሲያስገመግም ዳኘዋ መድፍዋ

ያባ መቻል ያባ ዳኘው

ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው

ያባ በለውበለው በለው ሲለው

በለው-በለው-በለው-በለው!

ዋ!.....ዓድዋ ....

ያንችን ጽዋ ያንቺን አይጣል

ማስቻል ያለው አባ መቻል

በዳኘው ልብ በአባ መላው

በገበየሁ በአባ ጉራው

በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው

በለው ብሎ፥በለው-በለው!

ዋ!......ዓድዋ.......

ዓድዋ የትላንትናዋ....

ይኸው ባንቺ ሕልውና

በትዝታሽ ብፅዕና

በመስዋዕ ክንድሽ ዝና

አበው ተነሱ እንደገና።

......ዋ!....ያቺ ዓድዋ

ዓድዋ ሩቅዋ

የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

ዓድዋ.........

23 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean