የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የመልካም ስነ ምግባር ጽንሰ ሐሳብ

1) የስነ ምግባር ቋንቋዊ ትርጉም
የስነ ምግባር ቋንቋዊ ትርጉሙ ባህሪ ማለት ነው፡፡ እነዲህ ልንገልጸው እንችላለን፡- ‹‹ ሰውየው አንድን ድርጊት ለመፈጸም ወይም ለመታቀብ ይወስን ዘንድ ድርጊቱ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን የሚመዝንባቸው ከሕሊና ውስጥ የጸኑ መስፈርቶች ስብስብ ስነ ምግባር ይባላል፡፡
2) በእስልምና የስነ ምግባር ትርጉም
ኢማም አቡ ሐሚድ አልገዛሊ ስለ ስነ ምግባር ባሰፈሩት ድንቅ ጽሑፍ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ስነ ምግባር ማለት በሕሊና ላይ የጸናና ስራዎች ማሰብ ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ የሚመነጩበት ነገር ነው፡፡›› በአእምሮ ሚዛንም በሸሪዓውም እይታ መልካም የሚሰኙ ተግባራት ከመነጩበት መልካም ስነ ምግባር ይባላል፡፡ መጥፎ ተግባራትን ከመነጨ ደግሞ መጥፎ ስነ ምግባር ይባላል፡፡
‹‹በሕሊና ላይ የጸና›› ያልንበት ምክንያት ለስለት ወይም አንዳች ጉዳይ ገጥሞት ገንዘብ የሰጠ ሰው ይህ ድርጊቱ የስብእናው ጥልቅ አካል እና ልምዱ እስካልሆነ ድረስ ቸርነት ባህሪው ነው ሊባል አይችልም፡፡
‹‹ ስራዎች ማሰብና መገደድ ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ የሚመነጩበት›› ያልነውም ለምሳሌ በቀላሉ ሳይሆን ከራሱ ጋር ብዙ ታግሎ ገንዘብ የመጸወተ ቸር ሊሰኝ አይችልም፡፡ በጎ ተግባራትን ማወቅ ብቻም መልካም ስነ ምግባር አይሰኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እውቀቱ ይኖርና የመፈጸም ጉልበት ሊያንስ ይችላል፡፡ በጎ ስራ መስራት ብቻም ስነ ምግባር አይደለም፡፡ ቸርነት ባህሪው ሆኖ ገንዘብ ስለሌለው የማይሰጥ፣ ንፉግ ሆኖም ለይዩልኝ ሲል ወይም ተገዶ የሚሰጥ በርካታ ሰው አለ፡፡ ስነ ምግባር ማለት መልካም ስራ ለመስራት ውስጣዊ ዝግጁነት፣ የነፍስ ውስጣዊ ውበትና ባህሪ ነው፡፡
አንድ ሙስሊም ዓሊም፡- ‹‹የአርስቶትልን የሞራል ፍልስፍና አንብበውታልን?›› ተብለው ተጠየቁ፡፡ ‹‹ከርሱ ተጨማሪ የነቢዩ ሙሐመድ ቢን አብደላህን የሞራል ትምህርት አንብቢያለሁ፡፡ የአርስቶትልን እና የመሰሎቹን ፈላስፎች የሞራል ፍልስፍና አነበብን፡፡ የነቢዩ ሙሐመድንም አነበብን፡፡፡ ፈላሰፎች ከብዙ ጥረትና ልፋት በኋላ ከፊል ገጽታው የተሟላ፣ ከፊል ገጽታው ደግሞ ጎደሎ የሆነ ተምሳሌታዊ ስብእና በምናባቸው ሳሉ፡፡ ይህ ስብእና እጅግ በተሟላና በደመቀ መልኩ ስጋ ለብሶና ነፍስ ዘርቶ በተጨባጩ ዓለም ውስጥ የግሰለቦች ሕይወት፣ የሕብረተሰብ የኑሮ ስርዓት፣ የግዙፍ ሐይማኖት አስኳል ሆኖ አገኘነው፡፡ ይህም የሙሐመድ ቢን አብደላህ የሞራል ትምህርት ነው፡፡››
የአላህ መልእክተኛ (ሶ.ዐ.ወ) ለሚያስተምሩት የሞራል ትምህርት ለባልንጀሮቻቸው መካከል ዋነኛ አርአያ ሆነው ኖረዋል፡፡ ይህን የመጠቀ ስነ ምግባር በሶሐቦች ስብእና ውስጥ ከቃል በፊት በተግባር አስርጸዋል፡፡
3) የመልካም ስነ ምግባር መሠረቶች
1) የእውቀት ሐይል፡- በርሱ አማካይነት ትክክለኛውን ከተሳሳተው ይለያል፡፡ ጥበብ የሚባለውም ይህ ነው፡፡ ለክፉ አላማ በመዋል ሲባክን ‹‹ኹብስ›› ይባላል፡፡ ሲያንስ ደግሞ ቂልነት ነው፡፡ መካከለኛው ጥበብ ይሰኛል፡፡ እውቀት ክፉውን ከደጉ፣ መልካሙን ከመጥፎ ለመለየት ያስችላል፡፡
2) ጀግንነት፡- በአእምሮ ልጓም የተያዘ የቁጣ ሐይል ጀግንነት ይባላል፡፡ የቁጣ ጉልበት ከልክ ሲያልፍ ወደ አደጋ መማገድ (ተሐውር)፣ ከልክ ሲያንስ ደግሞ ፍርሃት ይሆናል፡፡ ጀግንነት የክብር ሸማ ያላብሳል፡፡ ከተግባር መልካሙን ለመምረጥ፣ ቁጣን ለመቆጣጠርና ለታጋሽነት ይረዳል፡፡
3) ቁጥብነት፡- የስጋዊ ስሜትን (ሻህዋን) ጉልበት በአእምሮና በሸሪዓ ልጓም መቆጣጠር ቁጥብነት (ዒፍፋህ) ይባላል፡፡ የሻህዋ ጉልበት ከልክ ሲያልፍ ስግብግብነት፣ ከልክ ሲያንስ ደግሞ ስንፈት ይሆናል፡፡ ቁጥብነት እኩይ ቃልና ተግባር ከመፈጸም ያቅባል፡፡ የበጎ ነገሮች ሁሉ ዓይነታ የሆነውን የይሉኝታ (ሐያእ) ባህሪ ያላብሳል፡፡ ሐያእ ከብልግና፣ ከውሸት፣ ከሐሜትና ነገር ከማሳበቅ የሚታደግ ስነ ምግባር ነው፡፡
4) ፍትህ፡- የቁጣንና የሻህዋን ጉልበት ተቋቁሞ ነፍስን በጥበብ ጎዳና የሚያስኬድ ባህሪ ፍትህ ይባላል፡፡ ፍትህ ከልክ ሊያልፍ ወይም ሊያንስ የሚችል ባህሪ አይደለም፡፡ በራሱ ሚዛናዊ ነው፡፡ የርሱ ተቃራኒ ባህሪ በደል ይባላል፡፡ ፍትህ ባህሪን ሚዛናዊ፣ ስነ ምግባርን ልከኛ ያደርጋል፡፡