top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሚያንጠባጥበው ቀረጢት


የሚያንጠባጥበው ቀረጢት

ይህችንን ተረት ድንገት ሰማኋትና የሳምንቱ መነቃቂያ ትሆነን ዘንድ መረጥኳት። በአንድ መንደር የሚኖር አንድ ልጅ ነበር ። ይህ ልጅ በጣም ውድ የሆኑና ከባህር ውስጥ የሚገኙ ብዙ ድንጋዮኝ ነበሩት። ታዲያ እኒህን ውድ ድንጋዮች በቀረጢቱ አድርጎ በየሄደበት ቀረጢቱን ይዞ ይጓዝ ነበር። ልጁ ስለነዚህ ድንጋዮች ብዙ ያስባል፤ ነገር ግን ከማሰቡ እና ከመንሰፍሰፉ በቀር ከቀረጢቱ አውጥቶ አይጫወትባቸውም ወይም ምንም ነገር አያደርግባቸውም። ለራሱም ሆነ ለጓደኞቹ እያወጣ አያሳይም፤ አልያም በድንጋዮቹ ምንም ነገር ለመስራት አያስብም። ብቻ ዝም ብሎ በቀረጢቱ ይዟቸው በየሄደበት ይዞራል። እኒህ የተከበሩ ድንጋዮች እንዳሉት በማሰብ ብቻ፤ ለሰው እንኳን ከፍቶ ሳያያቸው ይዟቸው በመዞር ብቻ እረጅም ጊዜ አሳላፈ።

በሌላ በኩል እዛው መንደር ውስጥ ደግሞ ሌላ አንድ ልጅ ይኖር ነበር። ይህ ልጅ ደግሞ በህይወቱ ከሚመኛቸው ነገሮች ሁሉ አብልጦ የሚመኘው እኒህን የተከበሩ ድንጋዪችን መሰብሰብ ነበር። ሁሌም አብዝቶ ከመመኘቱ የተነሳ ምንም እንኳን ድንጋዮቹን ባያገኛቸውም፤ ቀረጢቱን ገዝቶ አኖረ። በየቀኑም ቀረጢቱን እያየ፤ እኒያን የሚመኛቸውን የተከበሩ ድንጋዮችን አንድ ቀን እንደሚያገኛቸው እያሰበ በአይምሮው ይስል ጀመር፤ በተስፋ ልቡን እያስደሰተ። የድንጋዮቹ ባለቤት የሆነው ልጅ ግን እንዲሁ በየሄደበት ድንጋዮቹን በቀረጢቱ ሲጎት፤ የቀረጢቱን ሁኔታ አላስተውለውም ነበር። ከጊዜ በዛት ቀረጢቱ እየሳሳ መጣ፤ ቀጥሎም ቀዳዳ አበጀ። እኒያ ውብ ድንጋዮችን ልጁ በሄደበት ስፍራ አንድ በአንድ መንጠባጠብ ጀመሩ።

ሁለቱም ልጆች በአንድ መንድር ይኖሩ ነበርና፤ ያ ድንጋዮቹን በየሄደበት በቀረጢት ይዞ ይዞር የነበረው ልጅ የሚያንጠበጥባቸውን እኒያን ውብ ድንጋዮችን ሁለተኛው ልጅ እየለቀመ አስቀድሞ ከገዛው ቀረጢት ውስጥ ይጨምራቸው ጀመር። የድንጋዩ ባለቤት የሆነው ልጅ ቀረጢቱን እያንጠለጠለ ከመሄድ በቀር ከፍቶ ስለማያያቸው ቀረጢቱ መቀደዱን እንኳን አላስተዋለም ነበር። እናም ቀስ በቀስ እኒያ ውብ ድንጋዮች ከቀረጡቱ እየተንጠባጠቡ ጠፉ። በሌላ በኩል እኒያ ውብ ድንጋዮች እንዲኖሩት ይመኝ የነበረው ልጅ በየሄደበት የተንጣባጠቡትን እየለቀመ ቀረጢቱን ከጊዜ ብዛት መሙላት ቻለ። ያ ምስኪን ግን በድንጋዮቹ ሳይጫወት፤ ለሰውም ሳያሳይ ፤ “አለኝ” በማለት ብቻ በተቀደደው ቀረጢት ይዞዋቸው ሲዞር አንጠባጥቦ ጨረሳቸው።

የብዙዎችችን የሃሳብ ቀረጢት ልክ የኒያ ውብ ድንጋዮች ባሌበት ይዞት እንደሚዞረው ቀረጢት ነው። ሃሳቦቻችንም ልክ እንደተከበሩ ድንጋዮች ይቆጠራሉ። ነገር ግን ልክ እንደዛ ሞኝ ልጅ ፤ ሃሳቦች አሉን ከማለት በቀር አውጥተ አናያቸውም፤ አንሰራባቸውም ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙባቸው አናደርግም። ዝም ብለን ብቻ በየሄድንበት የሃሳብ ቀረጢታችንን ይዘን ከመዞር በቀር ምንም አናደርግባቸው። ልክ እንደዛ ምስኪን ልጅ የሃሳብ ቀረጢታችን ዞር ብለን ስለማናየውም፤ ከጊዜ ብዛት እድሜያችን ሲገፋ አይምሮዋችን ሃሳቦቻችን፤ ምኞቶቻችን፤ እራዕዮቻችን፤ እያንጠባጠበ ባዶ ያስቀረናል። ሸክሞ የማይቃለልለት ቀረጢት መቀደዱ አይቀርምና።

በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ብዙ ሃሳቦች አሉ። ምናልባት አንድ ቀን እንሰራቸዋለን እያልን አምቀን ያቆየናቸው ብዙ ልዪ ልዩ ሃሳቦች። በቀጠሮ የምናቆያቸው ህልሞቻችንን፤ ትክክለኛ ቦታ እና ጊዜ በመጠበቅ ወደጎን የምናደርጋቸው እራዕዎቻችንን ሁሉ በምኞት ቀረጢት ውስጥ ይዘናቸው ከመሄድ በቀር ምንም እያደርግንባቸው አይደለም። ያ ልጅ እኒያ ውብ ድንጋዮችን አሉኝ ከማለት አልፎ ከቀረጢቱ ቢያወጣቸው እና ቢመለከታቸው ለሱም ሆነ ለሌሎች ሊያስገኙ ይችሉ የነበረውን ጥቅምና ፋይዳ ይገነዘብ ነበር። እሱ ግን እንደዛ ባለማስተዋሉ ፤ በግዴለሽነት በየቦታው ሲያንጠበጥባቸው ሌላው እያነሳ ሰራባቸው።

ቀረጢታችንን አስተውለነው እናውቅ ይሆን? ምን ይሆን ከተንበት እየዞርን ያለነው? አንጠልጥለነው ከመዞር በቀር በውስጡ የታመቁትን ምኞት እና ህልሞቻችንን፤ ልዩ ልዩ ሃሳቦቻችን ቀረጢቱን ከፍተን አይተናቸው እናውቅ ይሆን? “ቆይ አንድ ቀን አደርገዋለው” እያልን በቀጠሮ የምንኖር ስንቶቻችን ነን? እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችን። ፈረንጆች ” Someday is not on the calendar” ይላሉ። “አንድ ቀን የሚባል ቀን የቀን መቁጠሪያ ላይ የለም” እንደማለት ነው። ምኞታችንን “አንድ ቀን አደረገዋለው” እያልን ባቆየን ቁጥር፤ የምኞት እና የሃሳብ ቀረጢታችን ውስጥ ታስረው እንዲቆዩ እያደረግናቸው ነው። ታዲያ ይህ ቀረጢት የማናስተውለው ቀዳዳ ማበጀቱ አይቀርም ፤ በየመንገዱ የሚያፈስ…..በየሄድንበት ሁሉ ህይወታችንን ሊለውጡ የሚችሉ ሃሳቦችን እያንጠባጠብን የምንሄደው ቀረጢታችን ቀዳዳ ስላለው ነው። ይህ ቀረጢት የሚቀደደው በውስጡ የሚገቡት ነገሮች ተመልሰው ስለማይወጡ ነው።

ወደተግባር የማይለወጡ ሃሳቦችን ይዞ መኖር ማለት፤ ልክ እንደመጀመሪያው ልጅ የከበሩ ድንጋዮችን በቀረጢት አዝሎ እንደመኖር ነው። በጊዜ ብዛት ቀረጢቱ መቀደዱ አይቀርም፤ በየእድሜ እርከናችን ብዙ ሃሳቦችንን እያፈሰስን እንጓዛለን።እሲት ቀረጢታችንን እንፈትሸው፤ ምን ያህል ድንቅ ሃሳቦችን ቋጥረን ይዘንበታል? ስንትስ አፈሰስን? እውን ሳናደርጋቸው በየቦታው ያንጠባጠብናቸው ህልሞችስ ምን ያህል ናቸው? እንደው ሃሳቦቻችን እና ምኞቶቻችንን በቀጠሮ ቀረጢታችን ይዘን ስንኖር፤ ቀረጢታችን መቀደዱንስ አስተውለነው ይሆን? በእርግጠኝነት እስካሁን ወደተግባር ሳንለውጣቸው በየመንገዱ ያፈሰስናቸው ህልሞች አሉን፤ አሁን በቀረጢታችን ውስጥ የቀሩትንስ እንዴት እናድናቸው? መፍትሄው “ይህንን አስባለው፤ አንድ ቀን አደርገዋለው” ከሚል አስተሳሰብ መውጣትና ወደተግባር መሮጥ ነው። እውነትም እኮ ስናስበው “አንድ ቀን” የሚባል ቀን በቀን መቁጠሪያችን ላይ በየትኛውም ሳምንት ሆነ ወር ውስጥ የለም። እህንን እያወቅን “አንድ ቀን” ብለን ዳግመኛ ቀጠሮ እንይዝ ይሆን?


በሚስጥረ አደራው

23 views0 comments

Comentários


bottom of page