የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የማይጠቅም ነገር አልሠማም! – (ከሶቅራጠስ እንማር)

አንድ ሠው መጥቶ ሶቅራጦስን፡- ‹‹እገሌ ስለተባለው ወዳጅህ የሠማሁት ደስ አይልም›› አለው፡፡
ሶቅራጦስ ግን ዝም አለ፡፡
ሠውየውም እንደገና፡- ‹‹ይገርማል ከእርሱ አይጠበቅም፤ በጣም ገርሞኛል›› አለው፡፡
ሶቅራጦስም እንደማይለቀው ስለተረዳ፡- ‹‹ ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የፈለግከውን ልሠማው የምችለው ሶስት ጥያቄዎች አሉኝ፤ እነርሱን ስትመልስልኝ ብቻ ነው›› አለው፡፡ ሠውየውም ተስማማ፡፡
‹‹የመጀመሪያው ጥያቄዬ የእውነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለወዳጄ የሠማኸው መቶ በመቶ እውነት ነው ወይ?›› አለ፡፡
ሠውየውም፡- ‹‹መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አልችልም›› አለው፡፡
ሶቅራጦስም፡- ‹‹ልትነግረኝ የፈለግከው እርግጠኛ ያልሆነ ነገር ነው፤ ሁለተኛው ጥያቄዬ የመልካምነት ነው፡፡ የምትነግረኝ መልካም ነገር ነው ወይ?›› አለው፡፡
ሠውየውም፡- ‹‹እርሱማ መልካም አይደለም›› አለው፡፡
ሶቅራጦስም፡- ‹‹አንደኛ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፤ ሁለተኛ መልካም ያልሆነ ነገር ልትነግረኝ ፈልገሃል፡፡ ሶስተኛ ጥያቄ አለኝ?›› አለው፡፡
ሠውየውም፡- ‹‹እሺ›› አለ፡፡ ሶቅራጦስም፡- ‹‹ለእኔ የሚጠቅመኝ ነገር አለው ወይ?›› አለው፡፡
ሠውየውም፡- ‹‹የለም›› ብሎ መለሠ፡፡
ሶቅራጦስም በመጨረሻ፡- ‹‹እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፤ መልካም ያልሆነ፤ ለእኔ የማይጠቅም ነገር አልሠማም›› አለው