top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የራስን ሕይወት መቆጣጠር እና መምራትን የሚያዳብሩ 10 ነጥቦች


ሰዎች እቅዳቸውን በሚገባ ለማሳካት ራሳቸውን መቆጣጠር እና መምራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ፍላጎትን እና እቅድን ባለማጣጣም እንዲሁም መመሪያቸውን በአግባቡ ባለመተግበራቸው የቀን ውሏቸው እና የሕይወት ስኬታቸው ወጣ ገባ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ራስን የመቆጣጠር እና የመምራት አቅምን ለማሳደግ የሚጠቅሙ 10 ምክሮችን አቅርበናል፡፡

1. በተግባር የሚገለፅ አመለካከት

ራስን ማየት በነጻነት የምንሰራቸውን ስራዎች ሃላፊነት እንድንወስድባቸው ያደርገናል፡፡ በመሆኑም ሊተገበር የሚችል አስተሳሰብን ማስፈን እና አስቀድሞ አቅዶ የዕለት ውሎን መምራት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ይህም ራስን በራስ ለማረም ይረዳል፤ ያልተፈለገ ጭንቀት እንዳያጋጥም ያደርጋል፡፡

2. ግብ ማስቀመጥ

አንድ ሰው ሲኖር የሕይወት ግብ ሊኖረው ይገባል፤ ግቦች ደግሞ ምርጫን ይወስናሉ፤ ግብን በውል ለይቶ ያስቀመጠ ሰው ያሳካዋል፡፡የተዘበራረቀ ግብ ያለው ሰው ደግሞ ለቀውስ ይጋለጣል፤ ይህ ደግሞ ለጭንቀት እና ለሌላ ህመም ይዳርጋል፡፡ በመሆኑም በጊዜ የተገደበ፣ የተመጠነ፣ ሊለካ እና ሊሳካ የሚችል ግብን ማስቀመጥ ራስን ለመቆጣጠር እና ሕይወትንም በዚሁ መልክ ለመመራት አቅም ይፈጥራል፡፡

3. ራስን መገምገም

ራስን መገምገም ከተወሰነ ጊዜ በፊት የተከናወኑ ድርጊቶችን ወይም ስራዎችን መልሶ በማየት ምላሽን ለአዕምሮ መመገብ ነው፡፡ የተቀመጠውን የሕይወት ግብ ለማሳካት ቀድሞ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማረም በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን ለማካተትም ይረዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተግባር ሰዎች ባህሪያቸውን ራሳቸው እንዲያርሙ ያግዛቸዋል፡፡

4. መነቃቃት

ሰዎች አንድ ዓላማ ባስቀመጡ ቁጥር ያንን ለማሳካት የራስ ተነሳሽነት እና ትጋት ያድርባቸዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የተቀመጠው የሕይወት ስኬት ግብ እና የእለት ውሎ አቅጣጫ ለስራ የሚያነሳሳ እና ቁርጠኝነትን የሚጨምር ጥቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ ሰዎች የግቡ ስኬት ተደምሮ ውጤት እንደማይኖረው ካወቁ የስራ መነቃቃታቸው ይቀዘቅዛል፤ ስለሆነም የሚቀመጠው ግብ መነቃቀትን የሚፈጥር መሆን አለበት፡፡

5. በራስ መተማመን

መነቃቃትን ወደ አዕምሮ ለማምጣት በራስ መተማመን መኖር አለበት፤ በራስ መተማመን ለዓላማ ስኬት ዓቢይ መንገድ ነው፡፡ ሰዎች በራሳቸው ካልተማመኑ የሕይወት ስኬት ግቡን አይመታም፤ ይህ ደግሞ ራስን መቆጣጠር እና መምራትን ማጎልበት አልተቻለም ማለት ነው፤ በእጃቸው ያለውን ቀሪ ስራ ለማሳካት ይከብዳቸዋል በተጨማሪም ጭንቀትን ያመጣባቸዋል፡፡ በመሆኑም በርካታ ችግሮች ሊያጋጥሙ ቢችሉም እንኳ በራስ የመተማመን መንፈስ እቅድን ማሳካት ተገቢ ነው፤ ጥቅሙም ራስን የመምራት ጥበብን እስከ ማጎልበት ይደርሳል፡፡

6. ተስፋን መሰነቅ

ተስፋ ሰዎች ልቦናዊ አቅም በመፍጠር የሕይወት ጉዟቸው የተሳካ እንዲሆን የማስቻል አቅም አላት፡፡ በሂደት የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን በመጋፈጥ ለግባቸው ስኬት ወደ ፊት እንዲራመዱም መሪውን ታስጨብጣለች፡፡ የግሪኩ ፈላስፋ ፕሌቶ “አንድ ነገር ብቻ ተስፋ አድርግ እሱንም በሚገባ አሳካው” ብሎ ነበር፡፡ ስለዚህ ሰዎች ራስን በመቆጣጠር ያስቀመጡትን አንድ ዓላማ በልኩ ለመፈፀም ተስፋ የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡

7. ጫናዎችን ማስወገድ

አንዳንድ ጊዜ ያልተፈለጉ ፍላጎቶች ሕይወትን ለመምራት በሚደረገው ጥረት ላይ ያልተፈለገ ጫና ይፈጥራሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን የፍላጎት ቅጥ ማጣት ጫናዎችን በመቅረፍ የሕይወት ስኬት ጉዞን ወደፊት ማስቀጠል ይገባል፡፡

8. ለምን እና እንዴት የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ

በሕይወት ውስጥ ለምን የሚለው ጥያቄ በአጠይቆቱ ሩቅ ለማሰብ እና ስራን የሚከናወንበትን ዓላማ አውቆ ለማከናወን ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል እንዴት የሚለው ጥያቄ ደግሞ ሩቅ የታሰበውን ግብ የማሳኪያ መንገዶችን ለማፈላለግ ፋይዳ አለው፡፡ ጀርመናዊው ኒቼ በአንድ ወቅት “በለምን ጥያቄ ላይ የተመሰረተ ህይወት ያለው ሰው እንዴት የሚለውን ጥያቄ በተግባር እየመለሰ ለህይወቱ ትርጉም ያለውን ስራ ይሰራል” ብሎ ነበር፡፡ በመሆኑም ሕይወትን የመምራት አቅምን ለማጎልበት ለተቀመጡት ግቦች ለምን የሚለውን ጥያቄ አስቀድሞ እንዴት እንደሚሳኩ ሁልጊዜም በመጠየቅ እና ምላሹን በተግባር በማከናወን መኖር ያስፈልጋል፡፡

9. ራስን መቆጣጠር እንደ ባህርይ መገለጫ

ዛሬ የሚሰራ ሥራ ለነገው እቅድ አስተዋጽኦ አስቀምጦ ያልፋል፡፡ ፕሮፌሰር ራችሊን እንደሚሉት ራስን መቆጣጠር የሰው ልጅ የባሕርይ አንድ መገለጫ ነው፤ አንድን ስራ ለማቆም ወይም ለማስቀጠል በራስ መወሰን መቻል የሚያሳየው የግለሰቡን ባህርይ ነው፡፡ በመሆኑም ለአወንታዊም ሆነ ለአሉታዊ የሕይወት ውጣ ውረዶች ራስን መቆጣጠርና የባሕርይ መገለጫ በማድረግ መጓዝ መልካም ነው ተብሏል፡፡

10. ራሱን የሚተካ ወይም የሚያስቀጥል ግብ

በሕይወት ኡደት ውስጥ አንድ ግብ ከተሳካ በኋላ ወይ መተካት ወይም ደግሞ ተሻሽሎ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም አንድ የህይወት ግብ እንደተሳካ መደበላለቆች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ ራሱን የሚተካ ወይም የሚያስቀጥል ግብ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን የመምራት እና የመቆጣጠር ስኬታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ለመምጣቱ ማሳያ ነው፡፡

ምንጭ፡- ሳይኮሎጂ ቱደይ

37 views0 comments

留言


bottom of page