የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ግጥሞች (ክፍል - 15)

118. ተፈሪ ክፉ ነው ልቡም አይገኝ
ለሰው ይመስለዋል ይናገራል ቀኝ
ኋላ እንዲህ ሊዋረድ ፍዳውን ሊያገኝ
እሳት ሰደዱበት ዳግሚያ እንዳይገኝ
ዘላለም የማዝበርድ በደም የሚያዋኝ::
118. የተማረ ወድቆ ደንቆሮው ከገዛው
ማን አለብኝ ብሎ አገሩን ወረሰው
ጥሩ አርጎ ባለበት በገዛ እጁ ናደው
ምድር ሊቆረቁር ኋላ እንዲህ ሊቆጨው::
119. አላህ ዝም ብሎ መንግሥት ሊያሳስት
ሰው እንደፍሪዳ ሲታረድበት
ምን ይችል ሐበሻ ጉድ አጃኢበት
በጦሩ ጨፍጭፎ ላይረጋ መሬት
እንኳንም አልደረስን ስትነድ መሬት::
120. አሥመራ ልትጠፋ ገመዱ ሲላላ
በሸዋ ከተማ ይኸለቃል በላ
በሦስት ቀን ይያዛል ጎንደር ላሊበላ
አክሱም የዚያን ጊዜ ትሆናለች ሌላ
ማርያም ትጠፋለች አያዋጣም ብላ::
121. ምን ኑሮ ይገኛል መንግሥት ከከፋ
ሰውን ለመግደል ጦሩን ከአስፋፋ
ውሸት እንዳይመስልህ ይሆናል በይፋ
ጠብቀው ዘመኑን እንዳታንቀላፋ
ወቅታቸው እስኪቀርብ እስኪዘልቅ በይፋ::
122. አይጥ ጠብመንጃ ይዞ ከገባ ከዋሻ
ሳትታይ አትቀርም አሥመራ አላህ ቢሻ
በደም ተጨማልቋል ትሆናለች እርሻ
ብዙ ሰው ይጠፋል ሳይገኝ ወጌሻ
ክፉ ነፋስ ነፍሶ አልብሶት ቆሻሻ::
123. የአሥመራ ወያኔ ከያዘ ጠመንጃ
ደንግጦ ይሞታል የአሥመራ ስልቻ፣
የኋላ የኋላ ከቲማውን እንጃ
ምን አስለፈለፈኝ ላይገኝ ፈረጃ
ነስሩም አይታወቅ ዘላለም ጦር ብቻ::
124. የአሥመራ ጦርነት ታኅሣሥ ሲጀምር
ብዙ ሰው ይጠፋል ነገሩ ሳያምር
አይሰድም መስሏቸው ሸዋ ብዙ ጦር
ወዲያው ሰደዳቸው በሰማይ በምድር
ወያኔው ይሞታል አያገኝም ነስር::
125. ቀልባቸው ነጃሳ ስማቸው እስላም
ንጉሣቸው ሰወው ይበላል ጅም ላም
በስሙ የሚመራ ዓለም ለዓለም
ለዲን ተቆርቋሪ ለሁሉ የሚጠቅም
በኋላ ያልቃሉ ቀኑ ሲጨልም::
126. ባሕር ወዲያ ማዶ አራት ሰዎች አሉ
ከእነዚህ ሁለቱ በቀንድ ይበልጣሉ
የጌታችን መቃም አየነው ባይሉ
ለአዳም ፍጥረቶች በላዕ ይሆናሉ
በአመጡት በላዕ እነሱ ያልቃሉ::
127. ሐበሻ ሁለት ነጭ ሳይገቡም አይቀር
አንደኛው በፍቅር አንደኛው በጦር
አስበው ነበረ ሊያረጓት አገር
አምስት ዓመት ገዟት ሲል ደንገር ደንገር
እኩሉን በሥራ እኩሉን በጦር::