የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ግጥሞች (ክፍል - 17)

145. ሐበሻ ስትደኸይ ስትቀጥን እንደ ድር
አዲስ መንግሥት ወጥቶ ይታደላል ምድር
ኸልቁ የዚያን ጊዜ ይለዋል ደንገርገር
ገንዘቡን ተወርሶ አታክልቱም ሳይቀር
እንኳን የተከለው የበረኻው ሳይቀር::
146. ይኸ ቻይና እሚሉት ዘራቸው ካልጠፋ
ችግር ይፈጠራል ይሆናል የከፋ
ማጥፋት ይሻል ነበር በአገር ሳይስፋፋ
ወልደን ሳንጥለው ልጃችን ሳይጠፋ
ጠብቀው ዘመኑን እስኪታይ በይፋ::
147. ሐበሻ ከገባ የቻይና ቁራሽ
ዲንን ያስፈራዋል እንዳይሆን ብላሽ
የዘመኑ ወጣት በሆኑት ቆስቋሽ
ስንቱን አደረጉት ደህይቶ እንዲሸሽ
እንዳይጣቀሙ ሀብታምና አራሽ::
148. ምን መላ ይገኛል ጦር ቢያከማቹት
አልገዛም ካለ ከወንድም ከሴት
ሸዋ ካልመከረ ይሆናል ወንፊት
እባብ መርዙን ከተፋ ይመጣል ፍጅት
ይህን እየሰማህ እንዳትገባ እሳት::
149. በድርቡሽ ሲገርመኝ የመተማ እልቂት
የማይጨው ሲገርመን የአድዋ ጦርነት
መቀሌን አየሁት አረሁ በልቶት
ሸዋ በገዛ እጁ በጫረው እሳት
ስንቱ ሰው ይነዳል ውቅሮ አዲግራት::
150. እንኳን የአንበሳ ልጅ እባብ ሲዞረው
ጀግና የሚወጣበት አገሩ የት ነው
ሥፍራውን ለይቼ እኔ ሳስታውቀው
ሽሬ ልጅ አንበራ ማይጨው ወያኔው
ምኒልክ ይመስክር ሲዋጋ ያየው::
151. የወልይ ልጅ ወልይ፣ የጀግና ጀግና ነው
እኛ እንኳን ባንቀምሰው በሌላው አየነው
በልተው እየጠጡ ጅስማቸው ቀጭን ነው
ወትሮም ደኅና ጎበዝ አካለ ቀጭን ነው
ተፈሪ የማይወፍር ሐሳብ በዝቶበት ነው::
152. ሸዋ አሥመራን ፈጅተህ አቃጥለህ በእሳት
ማምለጫም አታገኝ ሁሴን ፈረድኩት
ግን አሥመራ ያልቃል በራብ በጥማት::
153. ሐበሻ በሞላ በጦር ከተመራ
ወቅትቃቸው ያበቃል ፉቅራና ደብተራ
ለአገር ባይመቹ የሚሠሩት ሥራ
ምድር እያሳዩ ሲያስጥስ ደንቃራ
ጉዳቸው አያልቅም ቢወራ ቢወራ::
154. አሥመራ በጥጋብ ሲዘል ሲደነፋ
የልቡን ተናግሮ ገንዘቡን ሳያጠፋ
እስላም ከክርስቲያን ከሁሉም አይጠፋ
ሁሉም ሊከፋበት በረሃብ ሊያንቀላፋ
ወቅቱ ዘንበል ሲል ያለቅሳል በይፋ::
155. በርበሬ ቢጋገር እንጀራም አይሆን
አዟሪው ማን ይሆን አፍሳሹ ሊጡን?
አቡኪው ማን ይሆናል የሚሰድ እጁን
ሸዋ ግን አይፈራም ያውቀዋል ግዱን
በልቶ ሰው ያስባል እስኪገን አማን::
156. የከተማ ወንፊት በርበሬ እየነፋ
ንፋስ የመጣ እንደሁ ነፊው ዓይኑ ጠፋ
ዓይኑን እስከሚያሸው ነፊ አጥቶ ተደፋ
ንፋስ እያየ ነው በርበሬ የሚነፋ
ፍሬው ካልወደቀ ገለባ አይነፋ::