የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ግጥሞች (ክፍል - 18)

157. የአሥመራን ልቅሶ ሸዋ ካልሰማው
እንደ ጥቅምት ማር ይልሰዋል ሰው
የጠገበው ጎበዝ ቁንጣን የነፋው
ይጨፈጭፈዋል ዳግሚያ እንዳይለምደው
ቤቱን እስከሚያገኝ በግድ የቀማው::
158. ከቴዎድሮስ አንስቶ ተፈሪ ድረስ
የመኑ ያበቃል ዘውድና ንጉሥ
ንጉሥ አለ ብለህ አትወሳወስ
በምርጫ ካልሆነ የለም የሚነግሥ
ግን ሰውን አየሁት ብዙ ቀን ሲያለቅስ::
159. እያሱ ተረግሞ ሰክሮ ሲያንቀላፋ
ተፈሪ ይነግሣል ሳይደክም ሳይለፋ
ቀጥሎ ያውጃል እንዲያውቁት በይፋ
ፈረንጅን ድል አርጎ ተይዞ ሳይጠፋ
ዘለዓለም የእሱ ናት እስኪሆን አንጋፋ::
160. ሐበሻ ክፉ ነው ቆርጦ ከተነሣ
ፈረንጅን አረጉት ባንዴየ እንዲነሣ
ጦርነት አስቦ ዳግሚያ እንዳይነሣ
አገር መች ይቻላል ቆርቶ ከተነሣ
ሲያዩት ሞኝ ይመስላል ሲነሣ እንደ አንበሳ::
161. እንደ እንቁላል ገምቶ ሲፈርጥ እንደ አምቧይ
ምን ይበጀው ይሆን ባለዛር ጠንቋይ?
ሳትያዝ አትቀርም ዕዳህን ሳታይ
ምን ጠንቋይ ይባላል መጪውን የማያይ
እኛ ባንደርስበት ምንቅሩ ሊታይ::
162. አሥመራና ትግሬ ስትል ሰገደይ
እባብ ከተፍ ይላል ማምጫው ሳይታይ
ሸዋ የዚያን ጊዜ ይላል ዋይ! ዋይ!
ጀርባውን ምች መታው ወደ ትግሬ ሲያይ::
163. ሲተክሏቸው ጥሩ ሲበቅሉ ጠማማ
ታመጣው ይሆናል ወይንስ ከማማ
አላህ ያሳያችሁ የወሎ ኡለማ
ደረጃው ምንድን ነው? ቃልቻው ሰው ታማ
ግን ኋላ ላያቸው ይሆናሉ አሳማ::
164. እንግዲህ የእኔ ጠጅ ነገር ካመጣሽ
ቃልቻ ይጠጣሽ ይታጠብብሽ
ሌላ ሳትነኪ ሐሲድ እያየሽ
ሰው እስኪስቅበት እስኪሆን ብላሽ
በስተቀር ወላሂ ዳግሚያ ላልቀምስሽ::
165. እንግዲህ ቃልቻ አትጫወትብኝ
አንተ እቤቴ ቀርተህ ምንድን ጎደለብኝ?
ትዕቢትህ በስተቀር ሌላ ምን ቀረብኝ::
166. በላ አላህ ይሁንህ የመንደር ቃልቻ
ይኸው አድርገነሃል የቋንቋ ስልቻ
ከቤት እንዳትወጣ ሁን እንደ ጉልቻ
ሴት ወንዱ ያዋርድህ አታግኝ ፈረጃ
በልተህም አትጥገብ ሁን እንደ ስልቻ::
167. የሐበሻ አውሊያ ያሳያችሁ አላህ
እኔ እገሌ አላልሁም በድፍን ሺሊላህ
መቀመጫ አጣሁኝ በቃልቻ ታማሁ
ከፍርሐል በዟሂር አሉኝ ጠጅ ጠጣህ
ከስንቱ ልጣላ አረ የአላህ ያለህ::