የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ግጥሞች (ክፍል - 19)

169. አሽሙር ነው ነገሬ እንዳትሳሳት
አፈር በገባን በአርባ አምስት ዓመት
በሐበሻ መሬት ይመጣል ፍጅት
አውሊያ የተባልክ በደኅና ሰንብት
ዚያራው ያስፈራል መኮች ባወሩት::
170. ወልይ የለም ካሉ የኸልቁን መብራት
መኮች ባወሩት መንገድ እንዳትሳሳት
ሽሊላ በላቸው ከወንድም ሴት
በዟሂር ከሞቱት በዱኒያም ካሉት::
171. አለህም እንዳልል ሥፍራህን ማን ያውቃል?
የለህም እንዳልል ሥፍራህን ማን ያውቃል?
እንዴት የአንተን ሥፍራ ሸይጧን ይደፍረዋል?
ወትሮ ጭቡ ሱሪ ሰው ያስወነጅልሃል
ያልሆነውን ሆነ እያለ ያወራል::
172. ከአሜሪካ ወዲያ አለ ጥሩ ባሕር
ሃያ አምስት ያስኬዳል በግምት በእግር
ከዚያ አንድ ጎራ አለ ተተክሎ እንደ ጦር
ነጮች ከዚያች ሥፍራ ሳይደርሱም አይቀር
ላዩ ግን ሜዳ ነው የአንድ ጋሻ አገር::
173. ከአሜሪካ ወዲያ አለ ጥሩ አገር
ተራራውን ወጥቶ ከተገኘ ቀድ(ጽ)ር
ላዩ ግን ሜዳ ነው የሚያጭበረብር
ሥፍራው ከንዝ አያጣም ለሆነ ዘኪር
እዚህም አይደርሱ እንኳን ከቀመር::
174. ነጮች ሄዷል ካሉ ነጭን ከጨረቃ
መወሊድ የለም ካሉ ዚያራ ሰደቃ
ነቢን ከጠሏቸው የኸልቁን ጠበቃ
እንኳን ማውራት ቀርቶ መስማትም አይበቃ
ልባቸው እርኩስ ነው ሥራቸ ጨምላቃ::
175. አምስተኛው መዝሕብ ተሺጦ ሲለማ
ኋላ ጉድ ታያለህ የወሎ ኡለማ
የማታውቀው ነገር ቀርቧል ልትሰማ
ሰምተህ እንዳትከፍር ጆሮህ እየሰማ
አሟት እንዳይረግምህ አህያ ስትሰማ::
177. ምስክር የለኝ ተናግሬ አልሸሽ
አዋጁን ተከተል ሳትከፍር ብላሽ
በሁለት መንግሥት እንዳትቆሽሽ
ያሲን መስክሮታል ቁርዓንም አይዋሽ
ሌላ ካልፈሠሩት ሰው እንዲበላሽ::
178. በአምስትና በአራት በሦስት ሰጠር
ሲከትበው አየሁት ሼህ መሐመድ ኑር
ቆንጥሮ ያወራል መንደር ለመንደር
ጠቅላላ ሳይዘው ቀርቶ ሳይከርር
ሰውን እያየሁ ነው ጠልፎ ሲናገር::
179. ፈረስ ደኅና ሰንብት አላህ ይሁንህ
ነጭ ሐበሻ ገብቶ ጉድ አሸከመህ
የናታውቀው ነገር ጭኖ አስጎተተህ
ጉድክን ወደ ኋላ እንዳታይ ሆነህ
በአንዱ ስታለቅስ ሦስት ሰው ጫኑህ::