top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የተፈናቃዮች የሰቆቃ ጩኸት በምስራቅ መስቃን ወረዳ (በሻኪር አህመድ)


በ2011 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ የነበሩ ሰፋፊ ወረዳዎች በተወካዮች ምክር ቤት ለሁለት እንዲከፈሉ ውሳኔ ባስተላለፈው መሰረት የመስቃን ወረዳ አንዱ ተጠቃሽ እንደነበር ያቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑ ሁሉም ያውቀዋል ። በውሳኔው መሠረት በምስራቅ መስቃን እንሴኖን ማእከል በማድረግ በሁለት ማዘጋጃ ቤት አወቃቅሮ ማለትም እንሴኖ 01 ቀበሌና 02 ቀበሌ ከእንሴኖ ከቅርብ ርቀት የምትገኝ ከተማ ሀሙስገበያ በ01ቀበሌ በማካተት ምስራቅ መስቃን 17 ቀበሌን የሚይዝ ሲሆን ከእዚሁ ውስጥ 14ቱ የገጠር ቀበሌዎች ናቸው ። በመሆኑም በመስቃን ማረቆ በነበረው ግጭት በከፍተኛ ደረጃ ብዙ ንብረት የወደመበት የሰው ህይወት ጭምር የጠፋበት ቀበሌ ዲዳ ሚዶሬ ፣ ዲዳ አሊቦ ፣ ምስራቅ ዲዳ እና በቼ ቀበሌዎች ናቸው። ዲዳ ሚዶሬ ከቅርብ አመታት በፊት በመስቃን ወረዳ መስተዳደር ስር እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን አቶ ዲላ እያሱ የተወለድኩበት ቀበሌ ነው በሚል እና ባገኘው ልዩ አጋጣሚ ህብረተሰቡን በማስተባበር እና በማስወሰን በማረቆ ወረዳ መስተዳደር ስር እንዲሆን አስደርጓል። በመስቃን እና ማረቆ መካከል በተፈጠረው ግጭት በከፍተኛ ደረጃ ጥቃት ደርሶባቸው የነበሩት በዚሁ ቀበሌ ውስጥ በሚኖሩ የመስቃን ማህበረሰብ አካል ላይ ነበር።


ህዳር 11 - 2012 ዓ.ም የመስቃን ሚዲያ ኔትዎርክ አባላት በምስራቅ መስቃን ወረዳ ከተለያዩ የመስቃን ማህበረሰብ ጋር የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽ እንዲሰጥ አድርገዋል ። ከብዙዎቹ በጥቂቱ ለአንባቢ በሚመች መልኩ አቅርበነዋል።

ከመስቃን ወረዳ ከተለያየ ከተፈናቀሉ ማህበረሰብ ጋር ጥያቄ አንሰተን የሰጡን ምላሽ

ስሜ አማን የሱፍ ይባላል። የምኖርበት ቀበሌ ዲዳ ሚዶሬ ሲሆን እድሜዬ ስልሳ አመቴ (60) ነው። ከውልደት አሁን እስከ አለሁበት የእድሜ ደረጃ ድረስ እንደዚህ አይነት የሰው መጨካከን አይቼ አላውቅም። ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሞብኛል። እዚህ ያለውም ኮሚቴው ዘመዱን መርጦ ከመርዳት ውጪ ዞር ብለው አያዩንም። መፍትሄ የምለው መንግስት የህግ የበላይነት አስከብሮልን ወደነበርንበት ተመልሰን መልካም እና ሰላማዊ ኑሮ መኖር እንፈልጋለን ።

አያይዘውም ሌላኛው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ግለሰብ እንዲህ ይሉናል ።

ስሜ ሰባውዲን አማን ይባላል። የምኖርበት ቀበሌ ሚዶሬ ነው የሁለት ልጆች አባት ነኝ። እርዳታ ይሰጠናል ግን በቂ አይደለም ። ለአንድ ሰው በነፍስ ወከፍ 15 ኪ.ግ በወር አንድ ጊዜ ስንዴ ይሰጠናል፣ ዘይት በወር 0.45 ሌትር ይሰጣል። ይህ 15 ኪሎ እህል የት እናድርሰው? ፈጽሞውን አይበቃም። መንግስትን የምንማፀነው የህግ የበላይነት ተከብሮ ወደ ቀያችንና ቤታችን ተመልሰን እርሻችንን አርሰን እራሳችን እንድንችል ያመቻችልን ።

ሌላኛውም ተጎጂ እንዲህ ይላሉ ።

ስሜ አብደላ ሙክታር ይባላል። ነዋሪነቴ ዲዳ ሚዶሬ ቀበሌ ነበር ። የደረሰብኝ ከባድ አደጋ ነው ።ንብረቴ በሙሉ ወድሟል ምንም የለኝም። አሁን የምኖረው እንሴኖ 01 ቀበሌ በኪራይ ቤት ውስጥ ነው። በወር ለኪራይ የምከፍለው ካልሰራሁ ከየትም አላመጣም። ወደ ነበርኩበት ተመልሼ የመንግስት የህግ ማስከበር ተጠናክሮ መሬታችንን አርሰን ዘርተንና አምርተን ልጆቻችንን ተንከባክበን በሰላም መኖር ነው የምንፈልገው። በመቀጠል መስቃንን ክፉ አይንካው አልብሶናል አብልቶናል አጠጥቶናል። ከዚህ በኋላ ሰውን ማስቸገር ይብቃን ።

ታዲያ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት በምስራቋ ወረዳ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። አስከትለውም ሌላኛው ተጎጂ እንዲህ በማለት ይማፀናሉ ።

ስሜ ከድር ሀሰን ይባላል። የምኖረው ዲዳ ሚዶሮ ቀበሌ ነው። እድሜዬ (76) አመቴ ነው ።በምኖርበት ቀበሌ ብዙ ልጆች አፍርቻለሁ። የልጅ ልጆችም አሉኝ የደረሰብኝ በደልና አሰቃቂ ጉዳት ከፍተኛ ነበር። ዛሬ ኑሬዬ ወደ አልነበረ ነገር ተቀይሮ ጨልሞብኛል ። የነበረኝ የመሬት ስፋት ሁለት ሄክታር ከግማሽ ነበር ። በነጊዜያዊነት ቡታጅራ መጠለያ በነበርኩበት ወቅት የተሰጠኝ 14,000 ብር የት ላድርሰው ? ተራሩጬ አልሰራ ነገር እድሜዬ የገፋ ነው። ተከራይቼ እየኖርኩኝ ቢሆንም እጄ ላይ የነበውን በመጨረሴ የምከፍለው ብር የለኝም ። ከእኛ ውስጥ ተወጣጥተው በኮሚቴነት የተመረጡት ለቤተ ዘመዳቸው እያዳሉብን ይገኛሉ። ሰሚ አጥተናል ለቅሶችንም የህፃን ሆነ ምን ያደርጋል? እስከዛሬ እንደናንተ መጥቶ የጠየቀን የለም ! ብሶቴን ለእናንተ ስለተነፈስኩኝ ዛሬ ደስ ብሎኛል። ክፉ አይንካችሁ። እንደ እኔ ረጅሜ እድሜ ከጤንነት ጋር ከክብር ጋር ይስጣችሁ። ደስ ብሎኛል ጠያቂ በማግኘታችን አሉ ሃዘን እና ድካም በተጫጫነው ድምጽ…

ሌላኛው ተጎጂ በበኩላቸው ፦ ስሜ ፈቱዲን አህመድ ይባላል። የምኖርበት ቀበሌ ሚዶሬ ነበር። ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ደርሶብኛል። ቤቴ በሚዶሬ ቀበሌ በሞዴልነት የተሰራ ቤት ነው። ቤቴ በ116 የቤት ክዳን ቆርቆሮ የታነጸ ትልቅ ይዞታ ነበር ። ቢወድምም ከሀገር የመጣብኝ ስለሆነ ቅር አይለኝም። ንብረቴ ቢወድምም ቤተ መስቃኑ ከወደቅንበት አንስቶ አልብሶናል ። ቤት ውስጥ አኑሮናል። እኔ ጤናዬም ደህና አይደለም። በግጭቱ ምክንያት በደረሰብኝ አደጋ ሆዴ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ደርሶብኝ የቀዶጥገና ህክምና ተደርጎልኛል። መስራት አልችልም ቤተሰቤን የማኖርበት የእርሻ መሬት የነበረኝ ቢሆንም ወደ ቀያችን ባለመመለሳችን ለበለጠ ችግር ተዳርገናል። የእርሻ መሬቱ ተጠቅልሎ የሚሄድ ቢሆን ኖሮ ሰላም የሰፈነበት እና ህግ የሚከበርበት አካባቢ ወስደነው ለልጆቻቻን ህይወት ማቆያ የሚሆን እህል እናመርትበት ነበር ። እኔ አሁን ለማለት የምፈልገው መንግስት የራሱ ድርሻ በመውሰድ ህግን አስከብሮ ወንጀለኛን ተጠያቂ በማድረግ እኛንም ወደ ቀዬችን መመለስ አለበት ። እስከዛሬ ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግስት ሚዲያ የት አላችሁ ብሎ የጠየቀን የለም ። ለMMN ታላቅ አክብሮትና ምስጋና አለን ። ሌላ ማስታወስ የምፈለገው ቀደም ሲል ሚዶሮ ቀበሌ ስር መሰረቱ የመስቃን ነበር ። አቶ ዲላ እያሱ የትውልድ ቀበሌዬ ነው በማለት ዞንና ክልልን በማታለል ለማረቆ ወረዳ የተሰጠበት ሁኔታ ነው ያለው ይታሰብበት አደራ ። በማለት አስረድተውናል።

የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት የበቼ ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው ስለጉዳቱ እንዲህ ይዘረዝራሉ ።

ስሜ አሰፋ ከድር ይባላል የምኖርበት ቀበሌ በቼ ነው። የስድስት ልጆች አባት ስሆን ልጆቼን ያሳደኩት የቀን ስራ ላይ በመሰማራት ነበር። ይህ ችግር ከተፈጠረ በኋላ ልጆቼን ለዘመድ አዝማድ ከፋፍዬ የትም በመዞር ላይ እገኛለሁ። መኖሪያ ቤቴ ወድሟል ። ባለኝ ትንሽዬ መሬት ነበር የማኖራቸው። አሁን ግን ለራሴ መኖር አቅቶኛል። እኔ የምናገረው መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ቢችል መሬታችን አርሰን ልጆቻችን መመገብ እንደምንችል ይሰማኛል። ጠያቂ አልነበረንም እናንተ መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን በጣም ነው ደስ ያለኝ። ብሶቴን ተነፈስኩኝ ። ውስጤ ላይ ያለውን በመናገሬ ብሶቴ ይቀንሳል ።ጠያቂ አያሳጣችሁ ሀገሬን ብላችሁ የሀሳባችን ተካፋይ ሆናችኋል ።

በድሩ ጀማል እባላለሁ። ነዋሪነቴ በቼ ነው። እኔ ወንድ ልጆቼ ዘመድ በማስቸገር እያኖርኳቸው እገኛለሁ። ባለቤቴ ከሁለት ሴት ልጆቼ ጋር ቤቴ ውስጥ ትኖራለች። ቅሬታ የማቀርበው በተዋቀረው የእርዳታ ኮሚቴ ላይ ነው ። ተፈናቃይ አይደለህም ተብያለሁ ። ቤቴን ለቅቄ ከወጣሁ እንኳን ከ1 አመት በላይ ሆኖኛል ።የእርዳታ አሰጣጡ ሁሉንም ተፈናቃይ ያገናዘበ አይደለም ። አስተያየት አላበዛም በዚሁ ይብቃኝ ጨርሻለሁ ።

የተከበራችሁ የመስቃን ሚድያ ኔትወርክ ተከታታዮች ከላይ አስተያየትና ቅሬታ ያቀረቡት ሰዎች አብዛኛው በሚባል መልኩ የአንድ ቀበሌ ናቸው ።ግን አሰፋፈራቸው ይለያያል። ተፈናቃዮቹ ያቀረቡትን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ወደ ምግብ ዋስትና ቢሮ( የአደጋ ስጋት መከላከል ) በመሄድ ለተነሱ ሀሳቦች ምላሽ እንዲሆን በጠየቅነው መሰረት የሰጡት ምላሽ እንደሚከተው ነው።

እንደ መንግስት የተለያዩ አቅጣጫ ይዘናል ። የተፈናቀሉ ሰዎች የእርዳታው ሁኔታ በመከፋፈል የንብረቱ ውድመት የደረሰባቸው። ቤት ንብረታቸው የተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ከሰላምና ከደህንነት አንጻር ወደ ቀያቸው መመለስ ስጋት ያደረባቸው በማለት ከፍለን ይዘን ነው የምናደርሰው ። ባለፉት ወራቶች ወደ ሶስት ወር በቅርብ ቀን ነው ። ለአንድ ሰው የ3ት ወር 45 ኪ.ግ እህል የሰጠነው ። በህመም ምክንያት ቤት የቀሩትን በቋሚ እየተረዱ መሆኑን መታወቅ አለበት። ቤት ኪራይ ተከራይተው ለመኖር ለአባወራ በነፍስ ወከፍ እስከ 20,000 ብር ተከፍሏል ። ያም ቢሆን ሊያልቅ ይችላል ። ከመንግስት የተቀመጠ አቅጣጫ አለ ። በእርቀ ሰላም ሁለቱም ማህበረሰብ ሰላም እንዲፈጥሩ ተደረጎ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሙሉ አቅማችን እየጣርን መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን። የሚል ነበር።

ውድና የተከበራችሁ የመስቃን ሚድያ ኔትወርክ ተከታዮች በምስራቅ መስቃን ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቅሬታ በአጭሩ የቀረበ ነው። የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመለስሰው በሰላም ይኖራሉ የሚል ተስፋ ብንሰንቅም መቼ ይፈጸማል የሚለው ከስጋት ውስጥ ይዶለናል። ወደ ቀያቸው ተመልሰው በልፋታቸው መኖር እስኪጀምሩ ለመጠለያና ለቀለብ የሚሆን ከመንገስት እና ከማህበረሰብ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል።

“የረሃብን ምንነት የተራበው ብቻ ነው የሚያውቀው”


በሻኪር አህመድ

መስቃን ሚድያ ኔትዎርክ ቡታጅራ

161 views0 comments

Комментарии


bottom of page