top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"የንጹኻን ጥቃትና የለቅሶ ፖለቲካ መዘዝ" (አህመዲን ጀበል)

በመላሀገራችን የተለያዩ ምክንያቶች፣ ስያሜዎች፣ ሽፋኖች እየተሰጣቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሓን ዜጎች በግለሰቦች፣በታጠቁ ኃይሎች፣በቡድኖችና በመንግስት ጭምር ተገድለዋል፡፡ አሁንም ግድያው እንደቀጠለ ነው፡፡ በሚሊዮን ሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳወገዝነው ማንም ይፈጽመው ማን ሁሌም መወገዝ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ችግር ሲፈጠር የኃይማኖት አባቶች፣ታዋቂ ግለሰቦች፣የመንግስት ሹመኞት ድርጊቱን በሚዲያ ቀርበውና በየመግለጫቸው ሁሉም ያወግዛሉ፡፡ የግርጊቱን ፈጻሚዎችን አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን ይባላል፡፡ ሕዝቡም ‹‹መንግስት የህግ የበላይነትን ያስከብር›› ይላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሌላ ተመሳሳይ ጥቃት በሌላ ስፍራ ይፈጠራል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አሁንም የተለያዩ አካላት ተሰባስበውና በየፊናቸው በመግለጫቸው ጥቃቱን ያወግዛሉ፡፡ እንዲህ እየተደረገ ጥቃቱ ስፍራ እየቀያየረና እየተደጋገመ ዘለቀ፡፡ እኛም በተመሳሳይ መንገድ ስለምንጓዝ የንጹኃን ሞትና እልቂት ይኸው እንደ ሀገር ቀጥሏል፡፡ አሁንም ተረኛ ንጹሃን በተለያዩ አከባቢዎች እየተገደሉ ነው፡፡ የነገ ተረኞ ሟቾች እነማን እንደሆኑም አላህ ነው የሚያውቀው፡፡ለአንዳቸውም ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሺን ይቋቋምና እውነቱ ይውጣ ብሎ የጠየቀ ወይም የሰማ የለም፡፡


ለንጹሃን ሞትማብቂያ እና ሀገራችን ላለችበት ምስቅልቅል ከችግሩ መውጫ መንገድን በስሜት ተነድቶ ‹‹በለው፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው፣እሰረው›› አይነት ጩኸት ከማስተጋባት ቆም ተብሎ በስክነትና በመደማመጥ መፍትሄ ማምጣት ያልቻልነው ለምንድነው? ምንስ ጎሎን ነው? መፍትሄው እኔ የምለው ብቻ ነው ከሚል ወጥተን ቆም ብለን በመነጋገር ዘላቂ መፍትሄ እንፈልግ፡፡›› ስትል ለንጹኻን ሞትና ለሀገር እንዳለመጨነቅ የሚቆጥረው ብዙ ነው፡፡


አንድችግር ተፈጠረ ሲባል የተፈጠረው ችግር እንኳንስ በማን እንደተፈጠረ ለማወቅ ቀርቶ ምን እንደተፈጠረ እንኳ በዉል ማወቅ በማይቻልበት ፍጥነት የክስተቱ ዜና በተሰማ ቅጽበት ‹‹የሞትነው እኛ ነን፡፡ ገዳዮቹ እነ እገሌ ናቸው›› በሚል የሞቾችን ማንነት እየለዩና እያጋነኑ ጭምር በንጹሃን ሞት ዱንካን ጥለው ከለቅሶው ፖለቲካዊ ትርፍ ማካበትን እንደፖለቲካዊ የትግል መንገድ ስለሚያዩና ያ ስለሚቀርባቸው ‹‹ንጹኃን ዜጎች መገደላቸው አግባብ ነው›› ያልክ ያክል አንዱን ከሌላው እያምታቱ ዉዥንብር ሊፈጥሩና በሴራ ትንተና በመጠመድ ተቀናቃኝን የማስመታት ሌላ ዙር ሴራ ሲሮጡ ታያለህ፡፡


በተነገረውሁኔታ ስሜቱ የተነካው ወገን ደግሞ በስሜት ተሞልቶ ያለማመዛዘን በማህራዊ ሚዲያ ስሜቱን በተለያየ መንገድ ይገልጻል፡፡ የተገለጸው ስሜት ደግሞ በሌሎች ዘንድ ደርሶ በነርሱ ላይ ሌላ አሉታዊ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ እነኛም በአሉታዊ ስሜት ተሞልተው ስሜታቸውን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች በስሜት ባለፈ በማህበራዊ ሚዲያ ወደተግባር ይጣራሉ፡፡ በስሜት የተነዱትና የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ ያዩ ሌሎች ኃይሎች ደግሞ ከተፈጠረው ሁኔታ ለማትረፍ ሲሉ ከስሜት ባለፈ በተግባር ወደ ጥፋት ጎዳና ይሰማራሉ፡፡ ይህም ክስተት በተራው ሌላ ሰቆቃ ይፈጥራል፡፡እንዲሁም የለቅሶ ፖለቲካ ይካሄድበታል፡፡ይህም ከፍ ባለሁኔታ ሌላ በስሜት የመነዳት አዙሪት ይፈጥራል፡፡ ይኸው በዚህ መልኩ በስሜት አዙሪትና ዉጤቶቹ እየተላጋን እዚህ ደረስን፡፡ ሌሎች ደግሞ የሆነ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ሀገር እንድታስተዳድር ኃላፊነት የሰጡህ ወይም ሀገር ለመምራት ‹‹ብቸኛው መፍትሄ እኔ ነኝና ምረጡኝ›› ብለህ የጠየቅኃቸው ይመስል አንተን ምላሽ ይጠይቁኻል፡፡


በሀገራችን እየተንሰራፋ ያለው ንጹሃንን የማጥቃት፣ የለቅሶ ፖለቲካ እና የስሜት አዙሪትን መግታት እስካልቻልን፣ዜጎችን በእኩል ዓይን የማየትና እውነተኛ የህግ የበላይነትን ማስፈን እስካልቻልን ድረስ ገና በየተራ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ እጅግ የሚያሳዝኑት በዚህ ባልሰለጠነ ሂደት ምክንያት ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ዜጎቻችን ናቸው፡፡

የሀገራችንኋላቀሩ ፖለቲካ ሰልጥኖ ንጹሃንን ብሄር፣ ሃይማኖትንና አመለካከትን ሳይለይና ሳያሰላ በማንኛውም መንገድ ሰላማዊ ሰዎች ኢላማ ከማድረግ እስካልተላቀቀና ከዚህ እንዲላቀቅ በጋራ መቆም እስካልተቻለ ድረስ ሁሉም በየፊናው አገኛለሁ ብሎ ትግል እየደረገባቸው ያሉት ነጻነቶች፣መብቶች፣እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት፣ ዲሞክራሲና ልማት እንኳንስ በዘላቂነት ሊረጋገጡ ይቅርና በዚህ አካሄዳችንን የሀገራችን ሕልዉና ራሱ ጥያቄ ዉስጥ ሊገባ ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ የንጹኃን ጥቃትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስቆም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ከንጹኻን ጥቃት ጋር ተያይዞ እየተለመደ የመጣውን የለቅሶ ፖለቲካን ማስቆም ያሻል፡፡ምክንያቱም ለማልቀስ ብቻ የተዘጋጀ እስካለ ድረስ ለቅሶ ፈጣሪዎቹ ዓላማቸው ማስለቀስ በመሆኑ በተግባራቸው ይቀጥላሉ።


የለቅሶፖለቲካ ሌላኛው ለሀገራችን ሰላም በዘላቂነት መረጋገጥ አደገኛ እየሆነ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የለቅሶ ፖለቲካ ‹‹የተፈጠረው ችግር ዳግም እንዳይደገም ምን እናድርግ?›› ከሚል ይልቅ እንዴት ቶሎና በደንብ እናልቅስ? ለሚለው ቅድሚያ የሚሰጥ ነው፡፡ ተፈጠረ ስለተባለው ችግርና የችግር ፈጣሪዎቹን ዓላማና ፍላጎት በጥሞና ለማሰብ እንኳ ፋታ እንዳታገኝ በማድረግ በስሜት ተነሳስተው ሁሉም ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጫና መፍጠርን ያለመ ነው፡፡ ይህን አካሄዳቸውን ካልተረዳህና ባመንክበት በራስህ መንገድ እስካላስተናገድከው በቀር ‹‹ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና የመናገር ነጻነት ይከበር›› ተብሎ ትግል እንደተደረገው ሁሉ በተቃራኒው ደግሞ ሌላው ቢቀር በጥሞና ለማሰብ ፋታ እስክታገኝ እንኳ ‹‹ያለመናገር ነጻነቴ ይከበርልኝ›› ብዬ ልታገል ብለህ እስክትመኝ ይገፋፉኻል፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አንዱ ጉዳይ የተጠቃ ወይም የተበደለ አካል ማልቀሱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ የሚወቀስ ነገር የለውም፡፡መብትህን ጥሶ የሚያስለቅስ እያለ አልቃሽ ሊወቀስ የሚችልበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡


ስትበደል፣በእኩልነት መንፈስ ሳትታይስትቀር በደልን ማሰማትና ለመብትህ መቆም በደልና አድሎ እስካለ ድረስ ይቀጥላሉ፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ለሀገራችን የሚያሻት ለለቅሶ ፖለቲካ መሯሯጥ ሳይሆን የመፍትሄ ፖለቲካ እንዴት ይምጣ ብሎ በመነጋገር ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ዝግጁነት እምብዛም አይታይም፡፡ መንግስትም በራሴ መንገድ ብቻ ብሎ መጓዝን ሲመርጥ የለቅሶ ፖለቲከኞችም ሰፊ የሀገራችንን ህዝብ ታች ድረስ የሚያሳምን መፍትሄ ከማመንጨት ይልቅ በለቅሶ ፖለቲካ ላይ መጠመድን መርጠዋል፡፡


የለቅሶፖለቲካን የለመዱና ያጣጣሙ አካላት ሁሉ የነርሱን ለቅሶ አድምቀው የሚቀናቀኗቸውን ወይም ጠላቴ ብለው የፈረጇቸውን አካላት ለቅሶን ማደብዘዝን ሥራዬ ብለው መያያዛቸው ነው፡፡ እንደነርሱ እሳቤ የነርሱ ለቀሶ እንዲጎላና በዙሪያቸው የሚሰለፍ በርካታ አልቃሽና አስለቃሽ ለማግኘት እንዲመች የሌሎች ለቅሶ ሊደበዝዝ ወይም ከነአካቴው ሊታፈን ይገባል፡፡


ከዚህየተነሳ የእነኝህን አካላት የአንዳቸውን ‹‹የኔን ለቅሶ ለምን አብረኀኝ አላለቀስክልኝም?›› ብለው የሚከሱህ አካላት፣ በጣሉት የፖለቲካ ድንኳን ለቅሶዋቸውን አብረሃቸው ብታለቅስ እንኳ በዚህ አያቆሙም፡፡ ቀጥለው ደግሞ ‹‹እኔ እንደማለቅሰው ለምን አላለቀስህም?›› ብለው ይከሱሃል። ፍላጎታቸው ስለራሳቸው ችግር ማሰማት ብቻ ሳይሆን ‹‹ዋና ጠላቴ›› ወይም ‹‹ተቀናቃኜ›› የሚሉትን አካል ለቅሶን ማፈን፣ጥቃትን ማደብዘዝና የክስተቶችን ተረክ ቅኝት እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ መቆጣጠር ጭምር በመሆኑ አስከትለው ደግሞ የማንን ለቅሶ ማልቀስ እንዳለብህና እንደሌለብህ በተለያዩ መንገዶች ሊነግሩህና ሊያስገድዱህ ሲጣጣሩ ታያለህ። ፊት ከሰጠኻቸውና ከተንበረከክላቸው ሁሉም ቀጥለውም ያንተኑ ለቅሶ የራሳቸው ማድረግ ካልቻሉ የራስህን ወይንም የወገንህ ለቅሶ እንኳ ‹‹እኔ ዝም እንዳልኩት ለምን ዝም አላልክም? ለምን አለቀስክ?››፣ወይም እኔ ህመሙና ስሜቱ በተሰማኝ ደረጃ ልምን አልተሰማህም? ስለምንስ እንደኔ ከመሆን አልፈህ ስሜትህን ከፍ ባለ ለቅሶ ገለጽክ? ከሚል መነሻ ‹‹ለቅሶው ከፍየሏ በላይ ነው›› እያሉ ሊዘባበቱብህን ሲጣጣሩና በተለያዩ መንገዶች ሲተቹህ ታያለህ።


ንጹኻንንያጠቃና ምክንያት የሆነ አካል ማንም ይሁን ማን፣ከየትኛውም ብሄርና ሃይማኖት፣ በየትኛውም ክልል ወይም ሰፈር ይሁን በትክክል ተጣርቶ ተጨባጭና የማይስተባበል ማስረጃ የቀረበበት አካል ተገቢውን ቅጣት ያግኝ›› ስትል ለንጹኻን ተቆርቋሪ መስሎ ‹‹የህግ የበላይነት›› ሲል ታየው የነበረው አካል ከፊሉ ከእንደገና በየወገኑ ተቧድኖ ‹‹የኔ ወገን ንጹሕ ነው›› ብሎ ሌላዙር የሴራ ትንተናና የለቅሶ ፖለቲካ ይቀጥላል፡፡ ‹‹የኔ ወገን ንጹህ ስለሆነ በአስቸኳይ ይፈታ! የነርሱ ወገን ግን ወንጀለኛ ስለሆኑ የህግ የበላይነት ይከበር!›› እያሉ በየተራና በየሰፈራቸው ተባድነው ሲጮሁ ታያለህ፡፡ ብዙዎች መፍትሄው የህግ የበላይነት ነው ሲሉም ይደመጣል፡፡ ግና የህግ የበላይነት ትርጉምና አገባብ ራሱ ቆም ተብሎ መፈተሽ የሚሻበት ሁኔታ ላይ ወድቋል፡፡


ለመንግስት የህግ የበላይነት ራሱ ህግን ማክበርና ማስከበር፣የዜጎችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ በህግ አግባብ ብቻ ሕግ ማርቀቅና ማስጸደቅ የሚለው በህግ የተጣለበት ዋናው ሚናው ተረስቶ የህግ የበላይነት የሚፈልጋቸውን አካላት ማሰር በመቻል ብቻ የሚለካ ከሆነ፣ለዳኛ የህግ የበላይነት ግራ ቀኙን በህግ አግባብ ብቻ በፍትህ መዳኘት የሚለው ቀርቶ የህግ የበላይነት ‹‹ትዕዛዜ አልተከበረም›› በሚል ብቻ የሚለካ ከሆነ፣ለፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊና ሕጋዊ መብቶችን ጠብቆ መያዝና መመርመር የሚለው ቀርቶ ስለህግ የበላይነት ትዝ የሚለው የማሰር ጊዜ ብቻ ከሆነ፣ ለአቃቢ ህግ በሀሰት ከመክሰስ ርቆ ለእውነት ጥብቅና መቆም የሚለው ዓላማው ተዘንግቶ የህግ የበላይነት በተከሳሾች ላይ በማስፈረድ አቅም የሚመዘን ከሆነ፣


ለተከሳሽ በነጻናገለልተኛ የፍትህ ስርዓት የመዳኘት ጉዳይ ተዘንግቶ የህግ የበላይነት መፈታት በመቻል ብቻ የሚመዘን ከሆነ፣ ለጠበቃ ለህሊናና ማስረጃ መቆም ተዘንግቶ ደምበኛን ነጻ በማስባል የህግ የበላይነት የሚለካ ከሆነ፣ለአክቲቪስቶች ፍትህ በእውነተኛ ማስረጃ ለእውነት ብቻ ድምጽ መሆንና መቆም የሚለው ተዘንግቶ እኔ ያወገዝኩትና ያስወገዝኩት አካል በ‹‹የሕግ የበላይነት ይከበር›› ስም ማስመታት በመቻል አቅም የሚለካ ከሆነ፣ ለተበዳይ ተከሳሽ ፍርድ እስኪያገኝ ድረስ እንደ ንጹህ የመገመት መብቱ ተገፎ የህግ የበላይነት ሚዛኑ በተከሳሽ ላይ መፈረድ መቻል ብቻ ከሆነ፣ለዜጎች በህግ አግባብ የተጣለባቸውን ግዴታቸው መወጣት ተዘንግቶ የህግ የበላይነት መብታቸውን በማግኘት መቻል ብቻ የሚለካ ከሆነ የህግ የበላይነት ከምኞት አልፎ በሀገራችን በተግባር እዉን የመሆን እድሉ ገና ሩቅ ነው፡፡


በኡስታዝ አህመዲን ጀበል

68 views0 comments

Comments


bottom of page