top of page
 • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የጉራጌ ክልላዊ መንግስት ምስረታ ያለ ምስራቅ ጉራጌ ተሳትፎ እውን ሊሆን ይችላልን ? - ክፍል 01 (በአወል አህመዲን ሳሊሃ)


የጉራጌው እንቅስቃሴ አሁን ካለው ድር የደራበት አካሄድ እስካልቀየረና ትግሉ የሁሉም ጉራጌ መሆኑን እስካልታመነበት ድረስ የክለላዊ መንግስት ምስረታው እውን የመሆኑ እድል የመነመነ ነው። በተጨማሪም የመላው ጉራጌ ተወካይና ፈላጭ ቆራጭ ነን የሚሉት እንዲሁም በእራሳቸውን ላይ የጉራጌ ንጉሳዊ አስተሳሰብ የጫኑት ቡድኖች ለዘመናት ያደፈው አመለካከታቸው ካልጸዳ የጉራጌ ክልላዊ ምስረታው እውን ሊሆን ይቅርና የጉራጌው አንድነት ከስጋት ላይ ይወድቃል።

ለዚህም ማሳያው ከዚህ ቀድም በተደረጉት ጉራጌያዊ እንቅስቃሴዎች “ከምስረታ ውይይት እስከ ምስረታ ፍፃሜ” የነበረው ብንመለከት የምስራቁ ጉራጌ በሰባት ቤታውያን ዘንድ ይህንን መሰረትኩልህ፣ ላንተ የማውቅልህ እኔ ብቻ ስለሆንኩ ያመጣሁልህን ጉዳይ ብቻ ተቀብለህ ደግፈኝ፣ በገንዘብ ይሁን በቁስ ድጋፍ አድርግ እንጂ ጉዳዩ የመላው ጉራጌ ነውና ከፅንሰ ሃሳብ እስከ ምስረታ አፈፃፀም የምዕራቡ ይሁን የምስራቁ ጉራጌ ጉዳይ ለሁሉም ይመለከተዋል የሚል አመለካከትና አስተሳሰብ ሲተገበር ፈፅሞ አይስተዋልም።

አድምጡኝማ… እናንተ እላይ ያላችሁት ጉራጌዎች ያለ ምስራቅ ጉራጌ ተሳትፎ የሚደረጉ ጉራጌያዊ እንቅስቃሴዎች ጅምር ላይ የመከኑ ስለ መሆናቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ። ድል እና ስኬት ከተፈለገ ጉራጌን በተመለከተ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ምስራቅ ጉራጌን ማካተቱ የግድ ነው። ምርጫ 97ትን ብንመለከት ሁሉም ጉራጌዎች ተሳትፎ አድርገውበት ስለበር ነው ገዢው ፓርቲ በዝረራ የተሸነፈው። በወቅቱ የምስራቁ ጉራጌ ህዝብ የምዕራቡ ጉራጌ አስተሳሰብ ነውና አልቀበልም የሚል ሃሳብ ሳይኖረው በአንድ ድምፅ በመቀበል የመላው የጉራጌ ህዝብ ድምፅ ወያኔን መቀመቅ አውርዶት ነበር።

ይሁንና ይሄ ስር የሰደደው የምዕራቡ ጉራጌ አፋኝነትና ንጉሳዊ አስተሳሰብ መላው ጉራጌ አንገቱ ቀና እንዳያደርግና የእርስ በርስ መተማመን እንዳይኖር ያድርግ እንጅ ምንም ሲጠቅም አልታየም ለዚህም ማሳያው ወያኔ የደርግ ስርአትን ገርስሶና በትረ ስልጣኑን ጨብጦ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ድሮ የነበረበት አስተዳደራዊ መዋቅር አፈራርሶ የራስ እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለው ወያኔያዊ አስተሳሰብን በመጫኑ የጉራጌ ህዝብ ከሌላው ብሔር በተለየ መልኩ አስተዳደራዊ በደል በግድ ተጭኖበት 27 የጨለማ አመታትን አሳልፏል።

ስለሆነም በደል እና ጭቆና መሸከም አቃተን ያለው የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ በማጣቱና ጭቆና የበዛበት ህዝብ በወያኔያዊ አስተዳደር ላይ ጣቱን በመቀሰሩ በተነሳው የህዝብ አመጽ ወያኔን አሽቀንጥሮ በመጣል አሁን ላለው የአብይ መንግስት ቢያስረክብም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ሁኔታ ለ27 አመታት የነበረው ብልሹ አሰራር ሊስተካከል ካለመቻሉ በተጨማሪ ወደ አዘቅት ወርዷል። የምዕራቡ ጉራጌ ቡድን ምስራቁን ጉራጌን በንጉሳዊ አስተሳሰብ እየጨፈለቀ ከፍተኛ የሆነ ልማታዊ በደል እየፈጸመ ይገኛል።

ይሁንና የጉራጌው አንድነትና የንግድ እንቅስቃሴው እጹብ ድንቅ ስለነበር እንዲሁም ከሌላው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር የሚያደርገው መልካም ትስስር ስር የሰደደ ስለነበር ይሄው ወያኔ በጠማማው እና በተንሸዋረረው አስተሳሰቡ የጉራጌው የአኗኗር ዘይቤው ስጋት ስለገባው የወያኔ ሹማምንቶች ዘዴ ዘይደው ጉራጌን በብቀላ አይቀጡ ቅጣት ቀጡት።

በጉራጌ ላይ ከተፈጸሙት በደሎች በጥቂቱ፡-

 • ጉራጌ በሃገሪቱ አለኝ የሚለው ሃብቱ ለወያኔያዊያን ቅጣት በሚስማማ መልኩ ህግ በማውጣት በኢኮኖሚው ማንኮታኮትና ጉራጌን ከንግድ አለም በሆነ ባልሆነ ውሃ በማይቋጥር ሰበብ የንግድ ፈቃዶችን መንጠቅና ያለምንም ማስጠንቀቂያ የመንግስት ያልተከፈለ እዳ በመጫን ወንጀለኛ በማድረግና ቋሚ ንብረቶችን በግዳጅ መውረስ።

 • በንግዱ አለም አንቱ የተባሉ የጉራጌ ባላሃብቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ግብር በመጣል ፣ በማጨናነቅ እና ከፍተኛ የሆነ ጫነ በመፍጠር ውሱን የሆኑት ነጋዴዎች ህይወታቸውን አጥፍተዋል።

 • ጉራጌው በአዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሃገሪቱ በያለበት አካባቢ ማህበረሰብ ተስማምቶና ተመቻችቶ የሚኖረው የንግዱ ማህበረሰብ ካለበት አካባቢ ቁርኝትና ስምምነት እንዳይኖረው ማድረግና በጉራጌው ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረግና በያለበት አካባቢ ፣አድማ በሚመስል መልኩ ለፍቶና ጥሮ ግሮ ያፈራውን ንብረቱ እንዲወድምና እንዲዘረፍ ማድረግ።

 • የጉራጌው ተወላጅ ሆነው በተባራሪ ንግድ የተሰማሩ የሀገር ኢኮኖሚ ሞተሮች ቋሚ ስራና ስፍራ ይስጣል በሚል ከጎረቤት ሀገር በሆነችውና በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በምትተዳደረው የንግድ ማዕከል በመባል በምትታወቀዋ ጅቢቲ ድረስ በመዝለቅ ጉራጌው እንዲፈናቀልና ከጉራጌው በተዘረፈ ዶላር ከጅቡቲ ሹማምንቶች በመደራደር ነጋዴው ጉራጌ ከጅቡቲ እንዲወጣና እንዲፈናቀል በማድረግ በባህር እንዲሰደድ ተደርጓል።

 • በንግዱ አለም በነበረው ጉራጌ ላይ ታጋይ የሚል ታፔላ የተለጠፈላቸው የትግራይ ወንበዴዎች በማሰማራት ነጋዴ በመምሰል እና የተለያዩ የንግድ ስልቶች ውስጥ በመግባት ጉራጌውን ከንግድ ስራው እንዲፈናቀል ተደርጓል።

 • በመላው ሃገሪቱ በወያኔዎች ዘንድ በጥቁር አይን የሚታየው ጉራጌ በጭፍለቃ ምክንያት በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ተበትኖ ስለሚኖር ያፈራኸውን ንብረት ለቀህ ውጣ በሚል ንብረቱ በእሳት ወድሟል ከሚኖርበት አካባቢ እንዲፈናቀል ተደርጓል።

እላይ የተጠቀሱት በደሎች ሲፈፀሙ የነበሩት በጅምላ ጉራጌ በሚል እንጂ የላይኛው ወይም የታችኛው ጉራጌ በሚል ላይ ተመስርቶ አልነበረም። አብሮ የተፈናቀለ አብሮ በጉራጌነቱና አብሮ የወደመው ጉራጌ በንጉሳዊው ጉራጌ ለምስራቁ ጉራጌ ምን አደረሰበት የሚለው በጥቂቱ ለማየት እንሞክራለን።


 • በአንድ ዞንና በአንድ መዋቅር የሚኖረው የምስራቁ ጉራጌ ከላይኛ እራሱን ንጉሳዊ አስተሳሰብ ባላቸው ጉራጌዎች በተለያዩ በልማት ተኮር በሆኑ ጉዳዮች መበደልና ማቀጨጭ

 • በተለያዩ ጊዜያት ተመን የሌለው አመታት ታስቦ ቅኝ ግዛት በሚመስል መልኩ ረግጦ ለመግዛት እንዲያመች በአካባቢው የሚወጡ ወጣት ምሁራን አካባቢያቸውን እንዲያስተዳድሩና ህዝባቸውን ባላቸው እውቀት እንዳይጠቅሙ የተለያዩ አጀንዳ በመፍጠር ከስራ ማበረርና በእስር እንዲማቅቁ ማድረግ።

 • በምስራቁ ጉራጌ አካባቢ በተለይ በቤተ_መስቃን ላይ በልማት አርበኛ በሆነው መስቃን ህዝብ ላይ የማያባራ አጀንዳ በመፍጠር ቤተ መስቃኖችን የሌለ የመዋቅር ጥያቄ እንዲጠይቁ ማድረግና አካባቢው እንዳይረጋጋ ማድረግ።

 • በንጉሳዊ አስተሳሰብ በመስቃን ህዝቦች ላይ አሁን የበላይነቱን ለመቆናጠጥ ሲባል አሁን ላይ የሚታየው ምስራቅ ጉራጌ የስጋት ቀጠና እንዲሆን ማድረግ ነበረ ይሄም ለተንኮል ጠንሳሾቹ ተሳክቷል በሚባል ያክል ሆኗል።

 • አሁን ላይ የጉራጌ የክልል እንሁን ጥያቄ ያለ ምስራቁ ጉራጌና ምሁራን በማን አለብኝነት የሚደረገው የላይኛው ድንገት እንኩዋን ቢሳካ የትግሉ ባለቤት እኛው ነበርን ድሉም የኛ ነው ፈላጩም ቆራጩ እኛ ነን ለማለት በሚመስል መልኩ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ጉራጌ የተነሳበት አላማ የሚያቀጭጭ መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።

ውድ አንባብያን ይህ የግል ሃሳቤ እና አመለካከቴ ሲሆን ጉራጌ አንድነቱን እንዲያጠናክርና የምዕራቡ ጉራጌ እንቅስቃሴ ያለ ምስራቁ ጉራጌ ምንም እንደሆነ ታምኖበትና ትግሉአጠቃላይ የሁሉም ጉራጌ ምሁራንና ባለሃብት ከሊቅ እስከ ደቂቅ አላማውንና ንቅናቄውን በማቀጣጠል የክልልነት ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ እውን እንዲሆን እመኛለሁ። ነገር ግን ያለ ምሰራቅ ጉራጌ ተሳትፎ የሚደረጉ ጉራጌያዊ እንቅስቃሴዎች አላማቸው ግቡን ይመታል የሚል እምነት የለኝም።


አወል አህመዲን ሳሊሃ

ሪያድ ሳውዲ አረቢያ

267 views0 comments

Comentários


bottom of page