• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የጉራጌ የክልላዊ መንግስት ምስረታ ያለምስራቅ ጉራጌ ተሳትፎ እውን ሊሆን ይችላልን? ክፍል - 02 (በአወል አህመዲን ሳሊሃ)ምስራቅ ጉራጌ እንደ አንድ የጉራጌ አካል ያደረጋቸው ልማታዊ ተሳትፎች እና ጅምር ላይ የከሸፉ የመሰረተ ልማት ስራዎች


 • በምስራቁ ጉራጌ የመስቃን ወረዳ እንደ አንድ የጉራጌ አካል ያደረጋቸው የልማት ተሳትፎች

ከዚህ ቀደም ጉራጌን መሰረት ያደረገ ትግል ያለምስራቅ ጉራጌ ህዝብ ተሳትፎ እንዳልተሳካ እሙን ነው። የጉራጌ ህዝብ ሀገራዊ አጀንዳ መሰረት ያደረገ ልማት የህብረተሰብ ተሳትፎ ሲጣልበት የምስራቅ ጉራጌ ህዝብ በተለይም የቡታጅራ ህዝብ ተሳትፎ እንደ ጉራጌ ድርሻው ከፍ ያለ እንደሆነ በተደጋጋሚ ዞኑም የሰጠው እውቅና እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። ምስራቅ ጉራጌ በርካታ የመልማት ጥያቄ ቢኖርበትም የመልማት ጥያቄው ምላሽ ባያገኝም እንኳን በጉራጌያዊ የልማት መዋጮዎችንና በጉራጌያዊ ልዩልዩ የህብረተሰብ ተሳትፎዎች የምስራቅ ጉራጌ ህዝብ ግንባር ቀደም እውቅና እንዳለው ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።

ለአብነት ያህል በከፊል

 1. የ1984 ዓም የጉራጌ ቴሌቶን አሰባሰብ እና ተሳትፎን መመልከት ይቻላል። የምስራቅ ጉራጌ ተሳትፎ በእጅጉ የላቀ የነበረ ሲሆን ተገኝቶ የነበረው በርከት ያለው ገንዘብ በሰባቱ ምዕራብ ጉራጌ ንጉሳዊያን ተጠርንፎ የት እንደደረሰ አይታወቅም።

 2. በአሁኑ ወቅት ያለው የኮሮና ቫይረስ መከላከል የህብረተሰብ ተሳትፎ ስራዎች ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ብቻ የዞኑ አንድ አራተኛ የሀብት የአሰባሰብ ስራ መመልከት ይቻላል። ይህም የዞኑ አፈፃፀም የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲሆን ድርሻው የጎላ ነው።

 3. በተለያዩ የህብረተሰብ ተሳትፎና በመንግስት ሰራተኛው ደሞዝ ለጉራጌ ዞን ልማት ማህበር (ጉዞልማ) በምስራቅ ጉራጌ ወረዳዎች በርካታ እና ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ገቢ እያገኘ እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

 • የጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ላይ ባደረጋቸው አስተዳደራዊ ጫናዎች ጅምር ላይ እንዲከሽፉ የተደረጉ መሰረተ ልማቶች

 1. በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጎርጊስ የመሰረት ድንጋይ የተጣለው የቡታጅራ ስታዲየም ግንባታን ብንመለከት የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረ ጉዳይ ነው።

 2. በጉራጌ ዞን ልማት ማህበር (ጉዞልማ) የምስራቅ ጉራጌ ህዝብ ለዘመናት በርካታ ቅሬታ ሲያቀርብ እንደቆየ ይታወቃል። ከብዙ እልህ አስጨራሽ ጥያቄዎች በኋላ የልማት ማህበሩ ፅ/ቤት አዳራሽ በሚል ስያሜ የግንባታው የስራ ሂደት ወጥ ባልሆነ መልኩ ለአመታት እየተካሄደ ይገኛል።

 3. የቡታጅራ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለዞናችን ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ዞኖችም አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ብቸኛ የቴክኒክና ሙያ ተቋም ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ተቋም ሆኖ ሳለ "የበሬውን ጉልበት ወሰደው ፈረሱ ከኋላ ተነስቶ ቀድሞ በመድረሱ" እንደሚባለው ሆነና በዞናችን ወልቂጤ አዲስ ቴክኒክና ሙያ ተቋም ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ የቡታጅራው እየወረደ የወልቂጤው እያደገ የመጣ ሲሆን በመቀጠል በርካታ የሙያ ዲፓርትመንቶች ከቡታጅራ ቴክኒክና ሙያ ወደ ወልቂጤ በማዘዋወር የወልቂጤ ቴክኒክና ሙያ ወደ ፖሊ ቴክኒክነት ኮሌጅ የማሳደግ ስራ ተሰርቷል።

 4. በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል በጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው ሆስፒታል የመልካም አስተዳደር ችግር የግበዓት እጥረትና አለመሟላት ህዝብ ቢጮህም ሰሚ አጥቶ ሆስፒታሉ ከተወዳዳሪነት ውጪ ከመሆንም አልፎ መደበኛ አገልግሎትም በተገቢ ሳይሰጥ እንደቆየ ይታወቃል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ለሚለው ጥያቄ በምዕራቡ ጉራጌ በንጉሳዊ አስተሳሰብ በምስራቁ ጉራጌ ውስጥ በሚገኙት የመሰረተ ልማቶች አንዱ የማቀጨጭ ዘዴና ምስራቁ ጉራጌ በእራሱ እንዳይብቃቃ በማድረግ ተመን ለሌለው ለምዕተ አመታት ቅኝ ግዛት ለመግዛት የታለመ አላማ መሆኑ አንዱ ምስክር ነው።

 5. የምስራቅ ጉራጌ ህዝብ የረጅም ጊዜ የዪንቨርሲቲ ጥያቄ ሲጠይቅ ቆይቷል አሁንም እየጠየቀ ነው የሚገኘው። ቢያንስ… ቢያንስ የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ አንድ ካምፖስ ማግኘት አልቻለም። በዞናችን ካሉ ወረዳዎች መስቃን ወረዳና ቡታጅራ ከተማ እንዲሁም ሶዶ ወረዳ ባማከለ በመስቃን ወረዳ የተቦን ማርታ ሆስፒታል ቡታጅራ ከተማ ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልና ግራር ቤት ለድኩማን 3 ሆስፒታሎች አሉ። እነዚህ ሆስፒታሎች በዞናችን ካሉ ወረዳዎች ምስራቅ ጉራጌን ቀዳሚ የሆስፒታል ብዛቶች እያሉ ወልቂጤ ዩንቨርስቲ የጤና ካምፖስ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም። ይሄም አንዱ አፈናና በአካባቢው በሙያና በእውቀት የተገነባ ትውልድ እንዳይኖር የሚደረግ ዘዴ መሆኑ ግልፅ ነው።

 6. በተጨማሪም በዞናችን ከሚገኙ ወረዳዎች መስቃን ወረዳና ሶዶ ወረዳ በመስኖ የግብርና ስራ ለክልሉ ሞዴል የሆኑና ለአገር አቀፍም ተሞክሮ መሆኑ የቻሉ የምስራቅ ጉራጌ ወረዳዎች የወልቂጤ ዩንቨርስቲ የግብርና ካምፖስ መስጠት ሲችል ጠቅልሎ ይዞ ዝምታ የመረጠ ዩንቨርስቲ ነው። በአገሪቱ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተለያዩ ካምፖሶቻቸው በዙሪያው ላሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንደየ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የሚመስል ካምፖስ በማከፋፈል ይታወቃሉ። የኛው ግን ሰብስቦ ይዞ ዝም ነው። ይሄንም አንዱ በጉራጌ ንጉሳዊያን ዘንድ የረጅም ጊዜ ምስራቅ ጉራጌን ለማቀጭጭና የቅኝ አገዛዙን ለማራዘም የታለመ ኢላማ መሆኑ ነው። የቡታጅራ ህዝብ በየስብሰባ መድረኩ የካምፖስ ጥያቄ ሲያነሳ የራስን ድካም ያልቆጠረ ህዝብ ግን ደግሞ መድረክ ያሰለቸ ሆኖ የበርካታ ጊዜ ምላሽ ቡታጅራ ከተማ ላይ ለኮንዶሚኒየም ታስቦ እየተገነቡ ግንባታቸው የተቋረጡ ኮንዶሚኒየሞች ወልቂጤ ዩንቨርስቲ ገዝቷቸዋል እየተባለ ትርክት ሆኖ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ሲሆን የህዝቡ ጩኸት ሲበረታ አሁን ግንባታ ላይ ነው። እውን ይሆን ይሁን ? ወይስ ማታለያ በእርግጥ በጉራጌ ንጉሳዊያን ዘንድ የሚደረጉና የሚሸረቡ ሴራዎች ላስተዋለው አላማው ሌላ እንደሆነ ምንም ምስክር ሳያሻ ነገሮችን በዝግታ ማየቱ በቂ ነው::

 7. ሌላው ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የሴራሚክ ፋብሪካ እንዲከፈት ቦታ ተረክቦ የአጥር ግንባታ ጀምሮ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የደረሰበት አይታወቅም በዚህ ጉዳይ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ምን ያህል ተንቀሳቅሷል? ወይስ የምስራቁ ጉራጌ አጀንዳ ማስቀየሪያ ንድፈ ሃሳብ ነበር ?

ቡታጅራ ከተማና አካባቢዋ ለኢንቨስትመንት ምቹነታቸው በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ሲሆን የዞንና የክልል ጫና እጅ ከማይሰጡት ኢንዲስትሪዎች መካከል የቡታጅራ ከተማ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው። በቅርቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ልዑክ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ቡታጅራ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና ቡኢ ከተማ አስተዳደር የችቡድ ፋብሪካ ለአካባቢው የልማትና የገበያ እንቅስቃሴ የአካባቢውና ዙሪያ ወረዳዎች ህዝብ የስራ እድል በማመቻቸት ከአካባቢያዊም ወጥተው ሀገራዊ ፋይዳ ማሳየት የቻሉ ናቸው። አካባቢው ሌሎች የተለያዩ መሰል ፋብሪካዎች ቢኖሩት ኖር ለአገሪቱ በርካታ አቅም መሆን በሚችልበት ደረጃ ላይ በሆነ ነበር ይህ ሁሉ ሆኖም ምስራቅ ጉራጌ ጉራጌነቱን አይደለሁም ወይም አልፈልግም ብሎ የሚጥለው ጉዳይ አይደለም። ምንም ስለ ጉራጌነት የሚነገረው በአፈ ታሪክ ደረጃ ቢሆንም የጉራጌነት ሰሜትና ፍላጎት ለምስራቁ ጉራጌ ከደሙ ጋር የተዋሃደ ነው። አሁንም ቢሆን የምስራቅ ጉራጌ ህዝብ ለጉራጌ አንድነትና ልማት እንደቀደሞው ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለኝ።

ውድ አንባብያን የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ያለምስራቅ ጉራጌ ህዝብ ተሳትፎ እውን አይሆንም የምለው በመረጃና በማስረጃ መሆኑ ታውቆ ንጉሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው የምዕራብ ጉራጌ ሰባት ቤታውያን የተነሱበት አላማ ግቡን የሚመታው በትግሉ ሂደት የምስራቁ ጉራጌ ሙሉ በሙሉ አምኖበት እና አብሮ በእኩል ሲሳተፍ መሆኑን ታውቆ የጉራጌ ህዝብ የጠየቀው ህገ መንግስታዊ መብቱን ወይም የክልላዊ መንግስት ምስረታ ጥያቄ እውን እንዲሆን ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ ማቀጣጠል እንዳለበት ጥሪዬን በድጋሚ አስተላልፋለሁ።

አወል አህመዲን ሳሊሃ

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

115 views0 comments