• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የጎሳ መሪዎች ምስረታ በቢዳራ ተካሄደ ( በአብድረሂም አደም)


በመስቃን ወረዳ በቢዳራ ቀበሌ የሁሉም የመስቃን ጎሳ መሪዎች በተገኙበት በታሪክ መጀመሪያ የሆነው የጎሳ መሪዎች የምስረታ ጉ

ባኤ ተካሄደ። በመስቃን ቤተ-ጉራጌ የመስቃን ጎሳ መሪዎች የምስረታ ጉባኤ በመስቃን ታሪካዊ ቦታ በቢዳራ ተካሄደ።

ጉባኤው የተመራው በአስተባባሪ ኮሚቴዎች ፦

1. በአቶ መሀመድ ስርዋጃ

2. በአቶ አህመድ መሀመድ

3. በአቶ ጀማል ማንሰቦ የተመራ ሲሆን


የውይይቱ መክፈቻም በተመረጡ የሀይማኖት አባቶች ዱዓ/ጸሎት በማድረግ ውይይቱ ተከፍቷል።


የጉባኤው ታዳሚዎች ፦

▶46 የጎሳ መሪዎች እና በእያንዳንዱ የጎሳ መሪ ስር 5 የጎሳው ተወካይ ግለሰቦች 5 * 46 = 230 ከእነ በህሮቻቸው 276 አባላት

▶የሀይማኖት አባቶች

▶ተፅዕኖ ፈጣሪና ታዋቂ ግለሰቦች

▶የቀድሞው የመስቃን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታ ሸምሱ

▶የመስቃን በጎ አድራጎት ድርጅት ቡታጅራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች

▶የማህበረሰቡ ተወላጅ የሆኑ አርቲስቶች

አቶ ጀማል ሱለንጎ ፣ አቶ ሁሴን ሱለይማን የመ/በጎ አ/ድ ቡ/ቅ/ ጽ/ቤት ስራስካያጅ አቶ ሰመሩ ስርዋጃ እና ከስነ-ጽሁፍ ሰዎች አቶ አወል ረዲ እና አቶ አሸናፊ ጀማል

▶ወጣቶች ተገኝተዋል።


የጉባኤው ዋና አላማ የመስቃን ማህበረሰብ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲሞክራሲያዊ ተግዳሮቶቹ አስወግዶ በትላንት አባት እናቶቻችን የማህበራዊ ግኑኝነት እሴት በማጎልበት ቤተሰባዊ አንድነቱ ይበልጥ በማጠናከር በአንድ ቋት የሚመራ ተቋማዊ አሰራር መገንባት ነው።


በመቀጠልም የመስቃን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን በማጎልበት በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲኖር ለማስቻል ማህበራዊ ግኑኝነቱን ማጠናከር እንዳለበት ይታመናል። በመሆኑም የመስቃን ማህበረሰብ በግብርና እና በንግድ

ረገድም ከኋላ ቀር አሰራሩ ተላቆ ለዘመኑ በሚመጥን ዘመናዊ አሰራርን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እንዲያጎለብት ማስቻል ነው።


በትምህርት ረገድም የቀጣይ ትውልድ በተሻለ ት/ቤት በተሻለ መምህር በማስተማር ለአካባቢው ብሎም ለሀገር ችግር ፈች ምሁራን ለማፍራት ዛሬ የዚህ ማህበረሰብ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም ታምኖበታል።


በጤናው መስክም የመስቃን ማህበረሰብ የጤና ተደራሽነቱን በማሟላት እናቶች ብዙ ርቀት ሳይሄዱ የወሊድ አገልግሎትም ይሁን የጤና ክትትል እንዲያገኙ እድል በማመቻቸት መላ ማህበረሰቡ ጤናው የተጠበቀ እንዲሆን የጤና ተቋም በቅርብ እንዲኖር ማስቻልና እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታልን እንደሚያስፈልገው ያምናል።


የመስቃን ባህላዊ ቦታዎችን እና ታሪካዊ ስፍራዎች እጅግ በዘመነና የትላንት ማንነታችን በሚገልጽና የአባቶቻችን ታሪክ አንፀባራቂ በሆነ መልኩ እንዲዋብ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው።


በአንድም በሌላ የዚህ የጎሳ መሪዎች ፍላጎት በትላንት ጀግኖች አባቶች ልጆች በዛሬው ጀግኖች የመስቃን የቁርጥ ቀን ልጆች የተቋቋመው የመስቃን በጎ አድራጎት ድርጅት ዕቅድ አካል በመሆኑ የጎሳ መሪዎቹ በበጎ አድራጎት ድርጅቱ ስር በመሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ዕቅድ እንዲሳካ የበኩላቸው እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል በአቋም መግለጫቸውም አረጋግጠዋል።


የጎሳ መሪዎቹ በስራቸው ከሚገኙት 5፣5 አባላት ጋር በመሆን በየጎሳቸው ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የቤተሰቡ አባላት ፆታን ሳይለይ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አባል እንዲሆኑም ስራ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።


አደረጃጀቱ የመስቃን ማህበረሰብ ሰላም እና አንድነት በመጠበቅ ከመንግስት ጎን በመቆም የመንግስት መመሪያና ህገመንግስታዊ ስረዓቱን በመከተል የድርሻውን እንደሚወጣም አምኖ ወጣቱ ክፍልም በልማቱ ፊት መሪ በመሆን ለማህበረሰቡ ብሎም ለሀገር ሰላምና አንድነት ዘብ በቆመ በአመክንዮ የሚያምን ትውልድ ለማፍራትም የሚጠቅም አደረጃጀት ሆኖ ታይቷል።


በውይይቱ የመስቃን በጎ አድራጎት ድርጅት አመሰራረትንና የቦርድ ምስረታውም አስመልክቶ በሪፖርት የድርጅቱ የቡታጅራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራስኪያጅ አቶ ሰመሩ ስርዋጃ አቅርበዋል። ሪፖርቱ በጎ አድራጎት ድርጅቱ የሰራቸው ስራዎች ፣ የድርጅቱ ስኬቶች ፣ ያጋጠሙ ችግሮች ፣ የተወሰዱ መፍትሄ እርምጃዎች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንም በዝርዝር ዳሷል።


የዛሬው መድረክ የመስቃን ማህበረሰብ የኅላ ታሪክ በመዳሰስ የማህበረሰቡ ተወላጅ በሆኑ አርቲስቶችና የስነ-ጽሁፍ ልጆች በውብ ቃላትንና አቀራረብ በማቅረብ በታዳሚዎች ቁጭትና የቀጣይ ቀስቃሽ ስሜት በመጫር የጀግኖች አባቶቻችን የሀገር ፍቅርና የጀግንነት ወኔ ለመላበስም በር ከፋች ነበር።


ከዚህ የስነ-ጽሁፍ አካላት ከተዳሰሱት አንዱ የጀግኖች አባቶቻችን ፦ የፊት አውራሪ ፍሰሃ ውልግቾ የትውልድ ብርሃን መሆን ፣ የራስ ደስታ ዳምጠው ጀግንነት ፣ የቀኝ አዝማች ፍሬሰንበት የአካባቢ ልማት ጉጉት ፣ የመሀመድ ጁሀር የጀግንነት ወኔ ፣ የሼ ኢሳ አልቃጥባሪ የአንድነት አስተምህሮትንና የሌሎች ጀግኖች አባቶቻችን ስም በመጥቀስ ታሪካቸውን ዳሰው ለታዳሚው ታሪክ ያስተማሩበት እለት እንደሆነም ማህበረሰቡ በደስታ የተደመመበት እለት ነበር።


ከዚህ በተጨማሪም በስነጽሁፍ ሰዎች ከቀረቡት ግጥሞች እጅግ ስሜት ቀስቃሽ የሆነው በፋሺስት ኢጣሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተነሳው ጦርነት የኢትዮጵያ የጦር መሪ የመስቃን ተወላጅ የሆኑት ራስ ደስታ ዳምጠው እንደነበሩም በማውሳት በጀግናው አባታችን ራስ ደስታ ዳምጠው ስም ዘመናዊ ሆስፒታል እና ት/ቤት በአዲስ አበባ መኖሩን በመጥቀስ በመስቃን ምድር ግን ስማቸው የምንጠራበት አንድም ድርጅት አለመኖሩ ሲጠቀስ በታዳሚው ቁጭት ፈጥሯል።


በመቀጠልም ይህ የጎሳ መሪዎች በማያቋርጥ ግኑኝነት የማህበረሰቡ የበላይ ጠባቂ ሆነው እንዲቀጥሉ እራሳቸው የሚመሩበት የኮሚቴ አባል እንዲኖራቸው አስፈላጊ ሆኖ በመታየቱ የራሳቸው ኮሚቴ እንዲመርጡም እድል ተሰጥቶ የዚህ መሪዎች ኮሚቴ ሰብሳቢም ከጥንት ታሪክም እንደምናውቀውና በነበረው ተዋረድ መሰረት የሁሉም በህሮች ሰብሳቢ የአዝማች ቦንጂ በህር መሆኑን በማመን የዚህ ጎሳ በህር የሆኑት አቶ አህመድ ሼ/መሀመድ ሰብሳቢ በማድረግ መርጠው በስሩ የዘጠኝ የጎሳ በህሮች የኮሚቴው አባል አድርገው መርጠዋል።


ከዚህ በመቀጠል የመስቃን በጎ አድራጎት ድርጅት እንዲመሰረትና ዛሬ እንዲህ ባማረ ቦታ ላይ የተጠፋፋን ቤተሰብ እንድገናኝ እድል ላበረከቱልን ጀግኖች ልጆቻችን ዱዓ እናድርግ በማለት ሦስት ሽማግሌዎች ተመርጠው ፦

አምባሳደር ድንበሩ አለሙ ፣ አቶ ኸይሩ ስርጋጋ ፣ ወ/ሮ ገነት አዝማች ፍሬሰንበት ፣ ዶ/ር ባህሩ ሽኩር ፣ ኢንጅነር ሁሴን መሀመድ ሀጂ ሸምሱ ሀጂ ከድር እና ሌሎችም የመስቃን የቁርጥ ቀን ልጆች በመጥቀስ የቀድሞው አባቶቻችን ስም በመጥቀስ ዱዓ/ፀሎት አድርገዋል።


በመቀጠልም የመስቃን ማህበረሰብ ከፍታ ለማረጋገጥ በማያቋርጥ ግኑኝነትና ትጋት ለመስራት የውይይቱ ታዳሚ በፅኑ እምነት የተቀበለው የቀጣይ አቅጣጫ በማይነጥፍ ሂደት ለማስቀጠል በተመረጡ ሽማግሌዎች የአቋም መግለጫው ቀርቦ አባላቱ በሙሉ ድምፅ በእልልታና በጭብጨባ ተቀብሎታል።

በመጨረሻም የእለቱ ውይይት በሶስት አባቶች ዱዓ ተደርጎ የእለቱ ጉባኤ አብቅቷል።


አብድረሂም አደም

ቡታጅራ

ነሀሴ 19/2012 ዓ/ም

216 views0 comments