top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ያልተማረ ይግደለኝ"


የተማረ ይግደለኝ የሚለው አገርኛ አባባል ትልቅ መልዕክት አለው። ምክንያቱም ክፉም ሆነ ደግ በተማረ ያምራል። እዚህ ላይ ግን አንድ አከራካሪ ነገር አለ። የተማረ ማለት ምን ማለት ነው? በመደበኛ ትምህርት በሚገኘው ከሆነ አይገልፀውም። ብዙ ጊዜ ግን የተማረ የሚባለው መደበኛ ትምህርት ተምሮ ዲግሪ፣ ፕሮፌሰር ምናምን የሚሉ ነገሮችን የያዘ ነው። ወይም ደግሞ በተለያዩ ሙያዎች እውቅና ያገኘን ሰው ነው። ለምሳሌ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ዘፋኝ ወዘተ የተማሩ ከሚባሉት ተርታ ይሰለፋሉ። እንዲያውም የበለጠ ክብርና እውቅና ያገኛሉ።

እንግዲህ የተማረ ማለት ይህ ከሆነ ያልተማረ ማለት ደግሞ እነዚህ መጠሪያዎች የሌለው፣ በገጠር የሚኖር አርሶ አደር ወይም ነጋዴ ሊሆን ነው ማለት ነው። ይህ ሰው ግን በአስተሳሰብና አርቆ በማስተዋል ምን ያህል ጀግና እንደሆነ ያስተዋለው የለም። እንዲያው በደፈናው ብቻ ያልተማረ እየተባለ ይጠራል።

እንዲህ ከሆነ አባባሉን ቀይሬ ያልተማረ ይግደለኝ ብያለሁ። ይህን ስል ካጋጠሙኝ ነገሮች ተነስቼ ነው። እስኪ በጉዞ ወቅት ካጋጠመኝ ልጀምር። የጋዜጠኝነት ሥራ በፈጠረልኝ አጋጣሚ የተማሩ ከሚባሉም ያልተማሩ ከሚባሉም ሰዎች ጋር የመሄድ እድል ገጥሞኛል። የተማሩ ስል እንግዲህ አርቲስቶችን ጨምሬ ነው።

በተለይ የረጅም ርቀት ጉዞዎች ላይ ከረዳቶችና ከሾፌሮች በርካታ ትዕዛዞች ይተላለፋሉ። ከእነዚህም አንዱ ለመናፈስ፣ ለቁርስ፣ ለምሳ ወይም ለሌላ ጉዳይ መኪናው ሲቆም ይህን ያህል ደቂቃ ብቻ ተብሎ ይነገራል። ይህ የሾፌሮች መልዕክት ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለመንገደኞችም ሲባል ነው። የታሰበው ጉዳይ በታሰበው ቀን ይደረግ ዘንድ ሁሉም ሊያስብበት ይገባል። የተላለፈውን መልዕክት ማን ይጥሰዋል ቢባል እነዚህ የተማሩ የሚባሉ ሰዎች ናቸው።

ከተነገረው ሰዓት በእጥፍ ዘግይተው ይመጣሉ። ለምን ቆያችሁ የሚል ጥያቄ ቢነሳ የእነርሱ አስነዋሪ ስድብ ይከፋል። ያልተማረ የተባለው ሰው ቢሆን ግን ከተባለው ደቂቃ አንድም አያሳልፍም። የሚያሳዝነው ነገር እነዚህኞቹ ሰዎች ላይ የሾፌሩም የረዳቱም የቁጣ ጩኸት ነው። ልክ የተማሩ የሚባሉት እሱ ላይ የሚጮኹበትን ያህል እሱ ደግሞ እነዚያ ላይ ይጮሃል። የተማሩ የሚባሉት እፈለጉበት ቦታ ለቁርስም ይሁን ለምሳ ሲያስቆሙት ያልተማሩ ለሚባሉት ግን እርሱ እፈለገበት ቦታ ብቻ ያቆማል። በትልቅ ትህትና እባክህ እዚህ ቁርስ እንብላ ሲሉት ቁጣና ስድብ ያወርድባቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ የተማሩ የሚባሉት በግልምጫ እዚህ አቁም ሲሉት ተሽቆጥቁጦ ያቆማል። እንግዲህ እንዲያ ላከበሩት ሰዎች አክብሮታዊ ምላሽ ቢሰጥ ምን ክፋት ነበረው?

የሰዓት ማክበር ነገር ከተነሳ ደግሞ የተማሩ የሚባሉ ሰዎች የሚያደርጓቸውን ስብሰባዎችና ገጠር ያሉ ሰዎች የሚያደርጓቸውን የእድር ስብሰባዎች ማነፃፀር እንችላለን። በእድር ስብሰባ አንዲት ደቂቃ ማሳለፍ አይቻልም። ያሳለፈም በህግና ደንባቸው ተገቢውን ቅጣት ያገኛል። የተማሩ ሰዎች ስብሰባ ግን ማንም በፈለገው ሰዓት የሚገባበትና የሚወጣበት ነው። ከፈለገም ስልክ እያጮኸ ሌላውን የሚበጠብጥበት ነው። ከፈለጉም እስከነ ጭራሹ አለመድረስ ይችላሉ። እድር ላይ ግን ከእድሩ ይወጣል የሚል ደንብ ካለ ያለምንም መዝረክረክ የዚያኑ ዕለት ይወጣል። በህግም ይሁን በባህል የተከለከለን ነገር ማን ያከብራል ብለን ብናስተውል ልዩነቱ የትየለሌ ነው። ብዙ ጊዜ መደፋፈርና ጥፋት የሚመጣው ተምረዋል ከሚባሉ ሰዎች ነው።

ብዙ ጊዜ ስለ ብክነት ይሰበካል። አብዝቶ መደገስ፣ ያለ አስፈላጊ ወጪ ማውጣት፣ ለጤና ጎጂ የሆኑ ነገሮችን በገንዘብ እየገዙ መታመም ስለሚያስከትለው ጉዳት አልተማሩም ለተባሉ ወገኖች ትምህርት ይሰጣል። ይህን ትምህርት የወሰዱ ሰዎች ቤታቸው ገብተው ምን እንደተባሉ በማስታወስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያወሩ እስከዛሬ ባባከኑት ይቆጫሉ። የሰሙትንም ለመተግበር ይወስናሉ። ያ ሥልጠና የሰጣቸው ሰው ቢታይ ግን ግሮሰሪ ገብቶ ያን የከለከላቸውን ሁሉ ሲያደርግ ነው።

እስኪ ልብ እንበል ቅጥ ያጣ የሰርግ ወጪ ያለው ከተማ ነው ገጠር ነው? ልደት፣ ምርቃት፣ ቀለበት ምናምን እየተባለ የወጪ መዓት የሚዘረዘር ከተማ ነው ገጠር ? እንግዲህ ከተማና ገጠርን ለማነፃፀሪያነት የተጠቀምኩት ከተማ የተማረ ገጠር ደግሞ ያልተማረ ይበዛል ስለሚባል ነው። እንዲያውም የምግብን መዝረክረክ ካየን የተማርኩ ነኝ ባዩ ነው አባካኝ። እህል ተደፍቶ እንጀራ ወድቆ ቢያገኙ «የእህል ጡር(ግፍ) አለው» በማለት ያነሱታል። እህልም ከሆነ ይለቅሙታል። አንድ ገበሬ መንገድ እየሄደ እህል ፈሶ ቢያገኝ አጎንበሶ ይለቅምለታል። ይህም ለዚያ ለሚለቅመው እህል ጉጉት ሳይሆን «እህል ፈሶ አይታለፍም» የሚል ብሂል ስላለው ነው።

ሌላ ደግሞ እስኪ የሥራ ትጋትና ትህትናን እንይ። አንድ አልተማረም የተባለ የገጠር አርሶ አደር ለሌላኛው ባልንጀራው (አብሮ አደጉ) ሥራ ሊያግዘው ቢሄድ ያለምንም ልግመት የልቡን ይሠራል። ባለቤቱ በሌለበት እንኳን «እኔ መሥራት ያለብኝ ለህሊናየ ነው» በማለት ምንም ሳይቦዝን ይሠራል። እንዲያውም ገበሬዎች እንደሚሉት ባለቤቱ በሌለበት መሥራት በጣም ያደክማል። ምክንያቱም ምን ይለኛል በማለት(በይሉኝታ) ከአቅሙ በላይ ሁሉ ይሠራል። በሄዱበት አጋጣሚ የተበላሸ ሥራ እንኳን ቢያገኙ «ይህ እንጀራውን የቀበረ» በማለት ይወቅሱትና እንደገና አስተካክለው ይሠሩታል።

ይህን ነገር እስኪ የተማረ ነው ወደሚባለው እናምጣው። ስንቶች ናቸው የአለቃን ትዕዛዝ በመፍራትና አቴንዳንስ ለመፈረም ብቻ መሥሪያ ቤት የሚሄዱ። በመሥሪያ ቤት አካባቢ ያለ አንድ የተበላሸን ነገር እስኪ ማነው «እኔ በበጎ ፈቃድ ያለ ክፍያ ላስተካክለው ወይም ገዝቼ ልተካበት» የሚል? እንዲያውም ምንም እንከን የሌለበትን መገልገያ ዕቃ ለማበላሸት የሚሮጠው ይበዛል።

እንግዲህ ይህን ልዩነት ስናይ የተማረ ማለት ምን ማለት ነው? ዲግሪ የሚባል ቅፅል ብቻ መያዝ የተማረ ያስብላልን? እንዲህ ከሆነ ያልተማረ ይግደለኝ ብያለሁ።

ዋለልኝ አየለ - sewasew.

28 views0 comments
bottom of page