top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ይቅርታ ቁስልን ካከመ እኔ ለህዝቤ ስል ይቅርታ እጠይቃለሁ! (አቶ ሸምሱ አማን የመስቃን ወረዳ አስተዳደር)በኮረና ወረርሽን ጭንቀት ውስጥ ሆነን ከማህበራዊ ሚድያው ዞርዞር ስንል ትኩረታችንን የሳበው ጉዳይ አገኘን። በርካቶች በጽሁፍ ያነብቡት ቢሆንም በድምጽ ማቅረቡ በተሻለ ሁኔታ መልእክቱ ለብዝሃኋኑ ይዳረሳል ብለን ስላሰብን በመከሸን ወደ እናንተ ለማቅረብ ወደድን። ጉዳዩ እንዲህ ነው በአለም ውስጥ የሚገኘው የሰው ዘር በኮረና ወረርሽን ናላው በዞረበት ወቅት ሹም ሽረት ከወደ ቦታጅራ ተሰማ የሚል ሲሆን ያንን ሹመት ተከትሎ አዲሱ ተሿሚ አቶ ሸምሱ አማን በግል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ይቅርታ የሚል ርእስ የተሰጠው ጽሁፍ በማግኘታችን እንደ ወረደ እናቀርብላቹአለን።

አቶ ሸምሱ እንዱህ ይላሉ...

ለሁሉም ይድረስልኝ በተለይም ባለፈው 2 ዓመት ቅር ለተሰኛቹ የህዝቤ አካሎች አንድ እንሁን መከፋፈል ይብቃን!! እኔ የመስቃን ብቻ ሳልሆን በወረዳው ውስጥ ለሚኖር የሁሉም ሰው ነኝ! ይቅርታ ቁስልን ካከመ እኔ ለህዝቤ ስል ይቅርታ እጠይቃለሁ!

እስካለሁ ድረስ በመስቃን ወረዳ ውስጥ ላለ ማንኛውም ሰው በፍትሃዊነት ማገልገልን እሻለሁ!! በየትኛውም ዘመንም ይሁን በማንኛውም ሁኔታ ፤አውቆም ሆነ ተሳስቶ ሰውን በጎሳውም ሆነ በብሄሩ የሰደበ፤የዘለፈ፤ያንቋሸሸ ግለሰብም ሆነ መሪ ከነበረ እኔ ዛሬ መሪ ስለሆንኩ በዛ ሰው ፈንታ #ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ!! ሁሉም ሰው የኔ ነው። እኔም ሁሉም የኔ ነው እዲለኝ አስቤ መስራትን እሻለሁ!!

የኮሮና ወረርሽኝ የሰው ልጆች በብሔራቸው ወይም በጎሳቸው ማንነት ሳይሆን በሰውነታቸው እንዲያስቡ ሊያስተምር የመጣ የፈጣሪ ቁጣ ውጤት ነው። በመሆኑም ሁላችንም ይቅር ተባብለን ትኩረታችን ይህንን በሽታ ላይ ልናደርግ ይገባናል!! ጎሳን ብሄርን በማይለይ በሽታ ተከበን ቂምን እና ጥላቻን አለመተው ሰውነት አይደለም። ባለስልጣኑም ሀብታሙም ፖለቲከኛውም ለጊዜውም ቢሆን ኮሮና ነው!! እሱን ከስልጣን ሳናወርድ ስልጣን የለንም፤ እሱን ሳናደኸይ ሀብት የለንም፤ እሱን ዝም ሳናሰኝ ፖለቲካ የለንም ስለዚህ የሁላችንም ጠላት ነው ማለት ነው። የጋራ ጠላትን ደግሞ በጋራ እንጂ በተናጥል አይረታም!!

ለብዙ ዘመናት አብሮ እየፀለየ ብዙ መቅሰፍትን የረታ ህዝብ በእኛ ዘመን የመጠላላት መንፈስ በበሽታ ሊረታ አይገባውም!!

እጅ ለእጅ ተያይዘን ይህንን በሽታ እንርታ፤ በፍቅር እናሸንፈዋለን! ለማንኛውም ውይይትም ሆነ ምክክር ቢሮዬም ስልኬም ክፍት ነው። በአካል ያልገባሁባቸው ቀበሌያት ገብቼ ለህዝቤ ትምህርት እስክሰጥና ችግሩን አድምጬ እስክፈታ ጓጉቻለሁ!! በዚህም ወቅት ደርሼ ይህንን ማድረግ ባለመቻሌ ባዝንም በቅርቡ እንደማደርገው እርግጠኛ ነኝ። ምክኒያቱም ይቅርታ ተቀባይ ደግ ህዝብ ነውና!! ስትመራ የሰው ብቻ ሳይሆን የእንሰሳቱም ያራዊቱም መሪ ነህ፤ እኔም ህዝቤ እየመራኝ ጥሩ መሪ እንድሆን እጥራለሁ!! የጀመርነው የግንዛቤና የደግነት ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን በወረዳዬ እስካለ ወይም እስከኖረ ድረስ ጉራጌው ብቻ ሳይሆን ሌላውም ብሔር የኔ ነው!!" በማለት አቶ ሸምሱ መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የወረዳው ህዝብ ለመልካም የሚያድረጉትን ጥረት በቅን ልቦና እንዲቀበል እያሳሰብን ምንም እንኳን ስራ በቃል መግባት ብቻ የሚለካ ባይሆንም የተግባር ስራቸውን በጉጉት እና በንቃት እንድንጠብቅ በድጋሚ ለማሳሳሰብ እንወዳለን።

22 views0 comments

Comments


bottom of page